የሐመሩ ላሎምቤ

ከቡስካው በስተጀርባ፤ ከኢቫንጋዲው የምሽት ጨረቃ፤ ከጋልታምቤና ዋልታንቤ መንደር ውስጥ… ሰው ተወልዶ ሰው ተሠራ። ጥቋቁሮቹ ሐመሮች ቀይ ሸጋ የጥበብ ልጅ ወለዱ። ፍቅር ባረሰረሰው መታቀፊያ አቅፈው ጎረምሳውን ልጅ አዲስ ሕፃን አደረጉት። ስሙንም “ላሎምቤ” (ቀዩ ጥጃ) አሉት። የሐምሮቹ ቀይ ጥጃ፤ የዘይሴዎቹና ሱርማዎቹ ልጅ፤ ፍቅረማርቆስ ደስታ ሆኖ ተገኘ።

ፍቅር አገናኛቸው፤ ጥበብ አቆራኝቶ አስቀራቸው። ዛሬ ላሎምቤ ላሎምቤ እያሉ በፍቅር የሚዘምሩለት አንድያ ልጃቸው ነው። “ኢቫንጋዲ”፤ “ከቡስካ በስተጀርባ” እና “የዘይሴዎች ፍቅር” እኚህ ሁሉ ለእነርሱ ክብርና ፍቅር የሰዋባቸው መጻሕፍቶቹ ናቸው። በተፈጥሮ ውስጥ ተወልደው፤ ለተፈጥሮ ኖረው፤ ስለተፈጥሮ የሚሞቱ ነገር ግን ያልተመለከትናቸው የውበት አጸድ ነበሩ። የእነርሱ ወርቅ ማለትም የሚያብለጨልጨው ድንጋይ ሳይሆን የከብቶቻቸው ጥቁር አዛባ ነው። ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ግን ከዓይን አልፎ በልባችን ውስጥ አንዠረገጋቸው። እናት አባቱ፤ ወንድም እህቶቹ አድርገው፤ በፍቅር አቅልጠው ማንነቱን አስረሱት። ከቡስካው በስተጀርባ ብቅ ብሎ፤ በጥበብ ጋራ ውስጥ ያበቀሉት ብዕረኛ ዛሬ የሁሉም ኩራት ሆኗል። ከቀናት በፊትም፤ የራሱን ግለታሪክ የያዘች መርከብ ከሥነ ጽሑፍ ወደብ ላይ ደርሳ፤ ያመጣችውንም መጽሐፉን አስመርቆ ነበርና በአጋጣሚው ስለራሱ ጥቂት ከአንደበቱ ለመስማት ችለናል። ከመጽሐፉ ውጭ የሠፈሩት አንዳንድ ታሪኮቹም፤ ሲነግረን ከሰማነው የተቀነጨቡ ናቸው። በሁለቱም ግራ ቀኝ፤ የሕይወት አውድማውን እንዲህ እንቃኘው።

ልጅነቱን ስንል የእርሱ አሳዛኝ የሕይወት ምዕራፍ የሚጀምረው ከልጅነቱ ይሆንና ገና ከጅምሩ ፈተናው ፈተናችን ይሆንብናል። እናም በእንቦቅላው ዕድሜ ወላጆቹን በሞት ተነጥቆ፤ የፍቅር ጥም እያቃጠለና እየሞረሞረ ተናንቆታል። ገና በልጅነታቸው ወላጆቻቸውን ያጡት የአባቱ ታሪክ በእርሱ መደገሙ ደግሞ እጅግ አሳዛኙ ነገር ነው። መጥፎው ህመም፤ እርሱንም አመመው። ግን ከልጅነቱ ጀምሮ መውደቅን እንጂ ወድቆ መቅረትን አያውቅም። እናም እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ “የነበረውን ፍርሃት፤ ባይተዋርነቱን እኔ ወደ ፍቅር ቀየርኩት”። እውነት ነው፤ ይህን የፍቅር ጥሙን በሐመሮቹ መንደር እነርሱን መስሎ ሳይሆን ሆኖ አስታግሶታል። የእነርሱ ልብ ለፍቅር ሲከፈት፤ የእርሱም ልብ ለጥበብ ጭምር ተከፈተች። እነርሱ እሱን ወለዱት፤ ፍቅር ደግሞ ጥበብን ወለደ። ፍቅረ ማርቆስ የነበረውን ሰው ላሎምቤ ሲያደርጉት፤ በርግጥም ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍና ማንነት መጥቷል። እትብቱ የተቀበረው ከጎጃም አፈር ውስጥ ነበር። ልጅነቱን ቦርቆ የተንቦራጨቀውም በጣና ሀይቅ።

ታዲያ ከዚህ ልጅነት በኋላ በዳግም ውልደት የሐመሮቹ ልጅ መሆን ልዩ ኢትዮጵያዊነትን ያሻል። ከሰሜን ዋልታ ወስዶ በደቡብ ዋልታ ገጠመው። በጣና ሀይቅ የመንቦራጨቅን ያህል በሐመሮቹ እበት መለቅለቅን ነብሱን ደስ አሰኘው። ከሐመሮቹ ጋር እንዲገናኝ ያደረገው አንድ ጉዳይ ነበር። በጊዜው ፍቅረ ማርቆስ፤ በኬሚስትሪ መምህርነት ተመድቦ ወደ ደቡብ የሀገራችን ክፍል ማቅናቱ ነበር። ከሥራ መልስ ለዕረፍት፤ ሌሎች መምህራን ወደ ከተማ ሲመለሱ እርሱ ግን ልቡ አይፈቅድለትም። በአንድ አጋጣሚም ወደ ሐመሮቹ መንደር የመሄድ ዕድሉን አገኘና ልቡን ተከትሎ ሄደ። እየዋለ ሲያድርም ፍቅርና እንክብካቤያቸው ጠለፈውና ከዚያው ጭልጥ ብሎ ቀረ። ከዚህ በኋላም “ከቡስካ በስተጀርባ” ተጀመረ። መጽሐፉም አልቆ የሐመሮቹን የውበት ጓዳ ገልጦ አስመለከተን። እርሱም ከታላቅ ብዕሩ ጋር ከአንባቢው አልፎ በሕዝቡ ጋር ተዋወቀ። የመጀመሪያውን የወጣትነት እንቅስቃሴው በአስጎብኚነት ላይ የተደገፈ ነበር። የኋላ ኋላም የራሱን አስጎብኚ ድርጅት ከፍቶ፤ ውሎ አዳሩ ሁሉ ከቱሪስቶቹ ጋር አደረገ። በግል ሕይወቱም ቢሆን ጥሩ ሕይወትን እየመራ የነበረበት ጊዜ ነው።

እርሱ ማለት፤ የነካው ብዕር ሁሉ ሌላ ብዕር የሚወልድ የጥበብ በረከት ነው። ብዕሩን አንስቶ መጽሐፎቹን ባስነበበን ቁጥር፤ የርሱን መጽሐፎች ተከትሎ ደግሞ ሌላ ዓይነት ጥበብ ይወለዳል። “ኢቫንጋዲ” የሚለውን መጽሐፉን ገና አንብበን ሳንጠግብ፤ ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ተነስቶ፤ በሚስረቀረቅ ድምጹ “ኢቫንጋዲ” የተሰኘውን ጥዑም ዜማ አሰማን። ሙሉ ለሙሉ ከመጽሐፉ የተወሰደና በፍቅረ ማርቆስ እገዛ የተሠራ ሙዚቃ ነበር። በዚያን የ90ዎቹ ሰሞን ላይ፤ ዓይኖች ሁሉ ወደ ሐመሮቹና ሙርሲዎች ነጎደ። ፍቅረ ማርቆስ፤ የእነርሱን የውበት ልክ በማሳየት፤ ብዙኅኑን ያስከተለ መሪ ሆነ። ለዚህ ብቻም ሳይሆን፤ ጥቋቁሮቹ አበባዎች ሲወዱት መጠን የለውም። አብሯቸው በነበረበት ጊዜ ሁሉ፤ እንደ አንድ የጎሳው አባል እንጂ እንግዳ ሆኖ አልነበረም። እናት አባት፤ ወንድም እህት አድርጎ ቆጠራቸው፤ ልጃቸው አድርገውም ተቀበሉት። በባሕሉ መሠረት፤ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ ልጅ የሚከውነውን ሥርዓት ለመከወን፤ አዛባውን ተለቅልቆ እምነቱን በደስታ አሳይቷቸዋል። እርሱ ወደዚያ ባይሄድ ኖሮ፤ “ከቡስካው በስተጀርባ” ባልተጻፈ ነበር። “ኢቫንጋዲን” የመሰለ መጽሐፍ አንብበን፤ ያን ሙዚቃ ባልሰማን ነበር። እንዲያውም፤ “ከእነርሱ ጋር ባልገናኝ ኖሮ ፀሐፊም መሆኔን እንጃ…” ይላል፤ ፍቅረ ማርቆስ ያን ትዝታ ባነሳው ቁጥር። እናም፤ ጥበበኛውን የፈጠሩ የጥበብ መልዕክተኞች ናቸው። እርሱ እንዳሳየንም፤ የብዕር ማንጠቢያ ቀለም፤ የፍቅር መወደሪያ ገመድ ናቸው። እናም እኚህን ተመልክተን ወደድናቸው፤ ፍቅራችንን ከፍ አደረገው። ፍቅረ ማርቆስ ትህትናው እጅግ የበዛና ሠራሁ ብሎም የማይኮፈስ ነውና “ብዙ ሰዎች ሐመሮችን አስተዋወቅህ ብሎ ያስባል፤ ይላልም። ነገር ግን እኔ ሳልሆን እነርሱ ናቸው እኔን ያስተዋወቁኝ” ሲል ይናገራል።

ከ2009ዓ.ም ጀምሮ ኑሮው በአሜሪካ ሆነ። የሕይወትን ፊትና ጀርባ፤ ግራና ቀኝ ተመለከትኩ ቢል ሰው፤ የፍቅረ ማርቆስ ደስታን ያህል ለማለት ግን የሚከብድ ይመስላል። እርሱ፤ የሕይወትን ጣፋጭ የወይን ብርጭቆ ባነሳበት እጁ፤ እንዴትስ ሊቀመስ ይቻላል የሚባለውን መራራውን የኮሶና እሬት ጭማቂ ተግቶበታል። ስሙ በፍቅር እየተቆላመጠ፤ በአድናቂና ወዳጆቹ እንዳልተከበበ ሁሉ፤ በባዕድ ሀገር ወድቆ ለዓይን እንኳ የሚያየውን አጥቷል። ኪሱ በረብጣ ብር ታጭቆ፤ ከራሱ አልፎ ለሌላውም የተረፈው ሰው፤ ኪሱ ቀርቶ ሆዱ ባዶ ሆና በረሀብ ጠኔ ፍዳውን በልቷል። በተንጣለለ ቤቱ እየኖረ ቆንጆ መኪና እንዳልነዳ፤ ማደሪያ መጠለያ አጥቶ ጎዳና ላይ ወድቋል። ከመኪናው ውስጥና መኪና ማቆሚያ እያደረ፤ ያሳለፋቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም። የሚበላ የሚጠጣውን ቢያጣ ጊዜ በእንባ ታጅቦ የጋብቻ ቀለበቱን ከጣቱ አውልቆ፤ በ80 ዶላር የሸጠበትን መጥፎ አጋጣሚ ከዓይነ ህሊናው አይጠፋም። “ከዚያን በኋላ፤ ለተወሰኑ ጊዜያት ያህል እጄን በዓይኖቼ ለመመልከት እንኳን ያስጠላኝና ይከብደኝ ነበር” ይላል፤ ነብሱን ለማቆየት ሲል ቀለበቱን የሸጠበትን የሞት ሽረት አስታውሶ። በሐመሮቹ የፍቅር ዝናብ ሲታጠብ የኖረው ሰው፤ እዚያ ግን ለገላው መታጠቢያ ውሃ እንኳ ሲያጣ፤ ለሚያውቀው ቀርቶ ለሚሰማው እንኳን ለማመን ፈታኝ ነው። እውቁና ሁሉ ልሙትልህ ሲለው የነበረው ደራሲ፤ በሰው ሀገር ግን፤ ከክብር ክብር ከፍቅርም ፍቅር አጥቶ በባይተዋርነት ሰቀቀን ተዘፈቀ። ከሰው እርቆ ከሰው ተገሎ መኖር ጀመረ። ውዱ የአልማዝ ፈርጡ ላሎምቤ፤ እርካሽ መናኝ ሆነ። የጽናቱ ኃይል ግን ለማመን የሚከብድ ነው። እንዲያ ጉስቁል ብሎ፤ ተርቦና ተጠምቶ ሲወድቅ እንኳን፤ “እንዲህ ሆንኩ ብዬ አንዱንም ሰው ለማስቸገር አልፈለኩም” ይላል። የሆዱን በሆዱ፤ እንባውንም በዓይኑ ይዞ ለብቻው ሲታገለው ነበር። ከዚያ ሁሉ የከፍታ ማማ ላይ ተፈጥፍጦ የተሰበረ ሰው፤ ተሰብሮ አለመቅረቱን ስንመለከት እንዴትስ ያለ ምትሀተኛ ኖሯል ያስብላል። ላሎምቤ ዳግም ተነስቶ ቆመ፤ ተራመደ። መቼም የእነዚያ ጥቋቁር መልአክት አምላክ፤ እጁን ይዞ የሰሀራውን በረሀ የኤርትራውን ባህር አሻገረው፤ እንጂማ እንደሰውኛ ከሕይወት አሞራ ተርፎ ለመነሳት የሚበቃ የማይመስል ነበር። የተነሳው ከውድቀት ሳይሆን ከሞት ነው። ይግረማችሁ ሲል ደግሞ፤ እረመጡን አልፎ ብዕሩን አነሳ። የሐመሮቹ ልጅ፤ ሕይወቱን እንደ ንስር ክንፍ አድሶ፤ በአዲስ ብዕር አዲሱን የመጽሐፍ ሥራውን ይዞልን ሲከንፍ መጣ። “የሚሳም ተራራ” ከሰቆቃው ፍቅረ ማርቆስ መልስ… በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት በሙሉ፤ የእርሱና በእርሱ ዙሪያ የነበሩ ታሪኮች ናቸው። አሁን ሁሉም አልፏል። የወደቀው ተነሳ የሞተውም ሕይወት ዘራ።

ሰው በሰው ልብ ውስጥ ጥሩ ትዝታን ያኖራል፤ መጥፎ ትዝታንም ይቀብራል። አሜሪካን በነበረበት ወቅት፤ እርሱ ለፍቅር የኖረውን ያህል ፍቅርን አጥቶ ባዝኖ ነበር። በሀገሩ ውስጥ በሐመሮቹ ውስጥ የተመለከተውን ፍቅር ከዚያ ባሉት ሐበሾች ዘንድ ፈልጎ ለማግኘት የቻለ አይመስልም። ኢትዮጵያዊነትን ያጣበት ስለሆነ እዚያ ያለውን የሀገር ልጅ ስሜትና ማህበረሰባዊ መተሳሰቡ ሞቶ ትዝታውም ጥሩ አይደለም። ቅናትና ምቀኝነት የሰፈነበትም ጭምር ስለመሆኑ ሳይደብቅ ይናገረዋል። ከዚህ የተነሳም፤ በገዛ ጓደኞቹ ወሬ የነበረውን ትዳር ስለማጣቱም ይገልጻል። በዚህ ምክንያትም የሀገሩን ልጆች በተመለከተ ቁጥር ሲሸሽና ከእነርሱ ራቅ ብሎ እራሱን በማግለል ይኖር ነበር። በርግጥ በዚህ ሁሉ መሀል ደጋጎች ስለመኖራቸውም አይሸሽግም። እንዲያውም በግለ ታሪክ መጽሐፉ ውስጥ “ትንሿ መልአክ” በሚል ያስቀመጠው አንድ ታሪክ አለ። ላሎምቤ አሜሪካ ከገባ ከሆነ ጊዜ በኋላ፤ ሁሉን አጥቶ በሕይወት ጉስቁልና ውስጥ በወደቀበት ሰሞን ነበር። ለባቡር ቲኬት የምትሆን ገንዘብ እንኳን አጥቶ፤ በርዝራዥ ሳንቲሞች ከማሽኑ ጋር ሲታገል ያገኘችው የሐበሻ ሴት ነበረች፤ ትንሿ መልአክ። ትኬቱን ቆርጣለት አብረው በባቡሩ ተሳፈሩ።

“ገላዬን ከታጠብኩ ስለቆየሁ በገዛ ሰውነቴ ጠረን ተሳቅቄ ከተቀመጥንበት ወንበር ፈቀቅ በማለት ከእርሷ እራቅ ብዬ ሳወራት ሁሉም ነገር ገብቷት ተረድታኝ ነበር። ቤቷ ከባቡር ጣቢያው ቅርብ እንደሆነ በመናገር እቤቷ እንድንሄድም ጋበዘችኝ። ” ግብዣውንም ተቀበላትና ከቤቷ ሄዱ። የሀገሩን ሽሮ ሠርታም፤ ቡናውን ለማፍላት ስትጀምር፤ በሰቀቀን ሲቁነጠነጥ ቆይቶ፤ ፈራ ተባ እያለ ገላውን ለመታጠብ እንደሚፈልግ ገለጸላት። ጥያቄውን በደግነት ተቀብላም መታጠቢያ ፎጣውን ሰጥታ ወደ መታጠቢያው መራችው። “ከሰውነቴ ላይ ጎርፍ መስሎ የሚወርደውን ቆሻሻ፤ አምስት ጊዜ ያህል ደጋግሜ ከታጠብኩ ኋላ፤ ጨርሼ ስወጣ በውስጤ ልክ እንደ እናቴ እልል! አልኩኝ። ” በመጨረሻም ትንሿ መልአክ አብልታና አጠጥታ፤ ስሙን ሳትጠይቅ እርሱም ሳይጠይቃት ሸኘችው። “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለ እርሷ እየገረመኝና ሄጄ ልጠይቃት እያሰብኩ፤ ሳይሞላልኝ ቀርቶ ዓመት ሆነው። አንድ ቀን ግን እንደምንም ብዬ ባጠረቃቀምኳት ሳንቲም ስጦታ ገዝቼ ወደ ቤቷ ስሄድ በሯ ታሽጎ ነበር። ዞር ዞር ብዬ ጎረቤት ብጠይቅ፤ እራሷን አጥፍታ ሞተች አሉኝ…” እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስም፤ ይህ አሳዛኝ ትዝታ ከልቡ አይጠፋም። “ሞት የሚገባኝና መሞት ያለብኝ እኔ ሆኜ ሳለሁ፤ እርሷ እኔን አትርፋ ሞተች” ይላል በሀዘን ውስጡ እየደማ። ትንሿ መልአክ፤ በባዕድ ሀገር ሆኖ በብዙዎች የተሰበረውን ልቡን ያከመች ነበረች።

ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፤ እንዴት ያለ ሰው ይሆን? ብለን ስናጤነው፤ በምንም ነገር የማይለዋወጠና በመንፈስ የሰከነ አመለሸጋ ሆኖ ይታየናል። ኢትዮጵያዊነት በደም ስሩ የሚዘዋወርበት ቀናኢ ፍቅር ያለው ሰው ነው። ልቡ በስሙ ልክ የተሰፋ እውነተኛ ሰው። ከእሩቅ ፊቱን አይተው፤ ውስጥን የሚያከብድ መስሎ ቢታይም፤ ቀረብ ብለው ሲያወጉት ግን አንደበተ ርቱእነቱ ቀልብን ይሰርቃል። ዝም ብሎ መስማትን ያስመኛል። ለልብም መራቅን ይከብዳል። ኢትዮጵያዊ ብሔር አልባ ፍቅሩ፤ ከመጻሕፍቶቹ ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከልቡ ውስጥም በዓይን እስኪነበብ ድረስ የሚታይ ስለመሆኑም እናስተውላለን። እኚህን ሁለት ነገሮች ግን አብዝቶ የሚሸሻቸው ስለመሆኑ እንገነዘባለን። ኢትዮጵያዊነትን እንጂ፤ ብሔር፣ ቋንቋ፤ ጎሳ…የሚሉ ነገሮች ቁብ አይሰጡትም። እኔ አውቅ እያሉ ፖለቲካን መፈትፈትም ሆነ ለሚፈተፍቱትን ጊዜም ቦታም የለውም። ይህቺ ፖለቲካ ግን አሳር ፍዳውን አብልታው ነበር። አፍላ ወጣት ሳለ፤ በዘመነ ደርግ በኢሕአፓ ጦስ ለእስር ተዳርጎ፤ ጓደኛውን ከእቅፉ ተነጥቋል። በአንድ ክፍል ውስጥ እንደታሰሩ፤ መብረቅ የታቀፈው ሰዓት ደረሰና ውዱ ጓደኛው ከሚረሸኑት ስም ዝርዝሮች መሀከል አንደኛው ሆነ። ተረሽነውም፤ በእስረኛው በራሱ ጉልበት በተቆፈረው የሽንት ቤት ጉድጓድ ተወረወሩ። ፍቅረ ማርቆስን ትረፍ ሲለው፤ የሦስት ዓመት የእስር ፍርድ ተበየነበት። የማያልፍ የለም፤ ይህም አለፈ።

“ኤማን ቢካሚንግ ኢን አፍሪካ” እና “ብላክ ሳሞራይ” በተሰኙት ዘጋቢ ፊልሞቹ ውስጥ ስሙ ከፍ ብሎ ተነስቷል። ዓለም አቀፍ ዝናና አድናቆትም ያተረፈባቸው ጭምር ናቸው። ሽልማቶችንም ተጎናጽፎባቸዋል። “ላንድ ኦፍ ዘ የለው ቡል”ን በመጻፍ ደግሞ፤ የእንግሊዘኛውን አንባቢ አስደምሞበታል። ከሁሉም መጻሕፍቶቹና ሥራዎቹ መካከል፤ “ከቡስካ በስተጀርባ” የተሰኘው መጽሐፉ፤ የእርሱ መልክ በሕዝቡ ዘንድ የተቀረጸበት መታወሻ ምልክቱ ነው። “ኢቫንጋዲ”፤ “አቻሜ”፤ “የንስር ዓይን” የሚሉት የመጽሐፍ ሥራዎቹም፤ እጅግ ተወዳጅነትና አድናቆትን ያተረፈባቸው ናቸው። ሌላኛውና በዓይነቱ ከሌሎቹ ወጣ የሚለው “ጃገማ ኬሎ”(የበጋው መብረቅ) የተሰኘው የታሪክ መጽሐፉ ነው። የጀግናውን ታሪካዊ ሕይወት፤ ታሪክ በማይዘነጋው ድንቅ የብዕር ዐሻራ ውስጥ አኑሮበታል። ከብዙ የሕይወት ግትልትሎች በኋላ፤ ተራራውን ወጥቶ ቁልቁለቱን ወርዶ በቅርቡ ደግሞ “የሚሳም ተራራ”ን አበርክቶልናል። ሁል ጊዜም ቢሆን እራሱን ብቻ መስሎ መኖሩ፤ በራሱ ቀለም የተለየ ማንነት እንዲኖረው አድርጎታል። ሥራዎቹ ሁሉም፤ ከየትኛውም ጋር ያልተበረዙ ከመሆናቸውም በላይ የርሱ ብቻ የሆነ አዲስ የሥነ ጽሑፍ መንገድ የቀደዱ ናቸው፡

የሐመሩ ላሎምቤ፤ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፤ በደቡብ ኦሞ ውስጥ የተከለውን ብዕሩን እንኳንስ ሰውና ከእጽዋት እስከ እንስሳቱ ያለው ተፈጥሮም የማይረሳው ነው። በባህልና ተፈጥሮው መሀከል ሆኖ ለሠራቸው ዘመን ተሻጋሪ ታላቅ ሥራዎቹ፤ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋዜጠኞች ማህበር እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር፤ በባለፈው የመጽሐፍ ምረቃ ወቅት ዕውቅናና ሽልማት አበርክተውለታል። ከዚህ በኋላ ፍቅረ ማርቆስ፤ “እንዲህ ዓይነት ወግ ማዕረግ ካየሁ ቆይቷል” ሲል፤ ከውድቀት መልስ ያገኘውን አዲስ ፍቅርና ክብር እያሰላሰለ፤ ለሁሉም ስለሁሉም ታላቅ ምስጋናውን አቀረበ። የመጨረሻውን የደስታ ቃሉን ለመስማት ጓጓሁና… እርሱም በእነዚህ ቃላት ለክቶ አስቀመጠው፤ “እንኳንም ኢትዮጵያዊ ሆንኩ! አሁን ወንድም አለኝ። አሁን እህት አለኝ። እንኳንም…”

የእርሱ ታሪክ፤ ተነግሮ የሚያበቃ ተተርኮ የሚያልቅ አይደለምና ገና ጀመርነው እንጂ አልጨረስነውም። ላሎምቤውን፤ ፍቅረ ማርቆስ ደስታን፤ “የሚሳም ተራራ” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ታገኙታላችሁና ስማችሁ ተገላገሉት።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You