የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት

ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (በኋላ የአፍሪካ ሕብረት) የተመሰረተበትን ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተው ከ61 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ነው።

ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ነፃ ሀገር በመሆኗ፤ የተባበረች አፍሪካን ለመመስረት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረችው ከ1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነበር። በወቅቱ የነበሩትን 30 አካባቢ የሚሆኑ ነፃ የአፍሪካ ሀገራትን በማነሳሳትና የመሪነት ሚና በመጫወት ግንቦት 17 ቀን በ1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ።

ይህ ድርጅት ሲመሰረት፤ ከሃያ በላይ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን ነፃ ማውጣትና የጥቂት ነጮች የበላይነት ሥርዓት ያለባቸውን ሀገራትም ከዚህ የዘር መድልዎ ሥርዓት ማላቀቅ ዋነኛ ዓላማው ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይህን ዓላማውን አሳክቷል።

በመጨረሻ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተቀላቀለችው ሀገር ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ነበረች። ደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የዘረኝነት ሥርዓትን አስወግዳ በ1986 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ተቀላቀለች።

የአፍሪካ ሀገራትን ነፃነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የተመሰረተውና ዓላማውን ያሳካው አፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትና ተልዕኮውን እንዲወጣ በማደረግ ረገድ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ያደረጋቸው ደግሞ የነፃይቱ ሀገር ኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በዚህ ስሙ የቆየው ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ነው። ድርጅቱ በ1994 ዓ.ም ወደ ሕብረትነት በመለወጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የነበረው የአፍሪካ ሕብረት ተብሏል። የአፍሪካ ሕብረት የተባለው በ1993 ዓ.ም በዋና መቀመጫው አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ቢሆንም ይፋ የተደረገው ግን በ1994 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ነው።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ኢትዮጵያ በመሪዋ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተማ ይፍሩ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገችው ሁሉ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆንም የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በ1994 ዓ.ም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሴኔጋል መንግሥት ተወካይ የሕብረቱ ማቋቋሚያ ሰነድ ላይ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ይሁን የሚለውን አንቀጽ (አንቀጽ 24) ተቃወሙ። ወደ ሌላ ሀገር መሄድ እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ አቀረቡ። የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የሴኔጋላዊውን ሃሳብ በመቃወም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።

‹‹የሴኔጋሉ ተወካይ አንቀጽ 24ን በተመለከተ አሁን መወሰን በጣም እንደሚያስቸግር፤ በተቀሩት አንቀጾች ላይ ግን ምንም ችግር እንደሌለባቸው ተናግረዋል። ተወካዩ የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የት መሆን እንዳለበት ለመወሰን እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

በእኔ እምነት በጣም ቀላሉ አንቀጽ ይሄኛው አንቀጽ ይመስለኛል፡፡

ይህን ጉዳይ አሁን ለመወሰን እንደእኔ ከሁሉም በጣም የቀለለ ጉዳይ ይመስለኛል፤ ልክ ጁሊየስ ኔሬሬና ከዋሜ ንኩርማህ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንድትሆን እንደወሰኑት ማለት ነው፡፡

የያኔዋ ኢትዮጵያ በዘውድ ሥርዓት፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ነበር የምትተዳደረው። ኢትዮጵያን የትኛውም ዓይነት መንግሥት ያስተዳድራት ሁሌም ለአፍሪካ ነፃነት በፅናት መቆሟን ማንም ሰው ሊክደው የማይችለው ሃቅ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካውን የነፃነት ታጋይና አርበኛ ማንዴላን ማን አሰለጠናቸው?! … አጼ ኃይለ ሥላሴ አብዮተኛውን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ አሰልጥነዋቸዋል። የዚምባቡዌው ሙጋቤ ያደረገውን ፀረ ሮዴሽያ ትግል ማን ነው የደገፈው?! መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነው። መንግሥቱ በሀገር ውስጥ አምባገነንና ጨፍጫፊ ነበር። በአፍሪካ ጉዳይ ግን መንግሥቱም እንደ አጼ ኃይለ ሥላሴ ጠንካራ አቋም ነበረው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ያላት አቋም መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የማይቀያየር የፀና አቋም ነው …፡፡››

የአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ መሪዎች የሚሞገሱበት ነው ማለት ይቻላል። ሥርዓትና መሪዎች ቢቀያየሩም የአፍሪካ ሕብረት ግን የኢትዮጵያን የነፃነት ተምሳሌትነት ሲመሰክር ይኖራል።

በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሌላው ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ሰው ደግሞ የንጉሡ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ ናቸው። እኚህ ሰው የንጉሡ ዘመን የውጭ ጉዳይ ግንኙነት አድራጊ ፈጣሪ ነበሩ፤ የንጉሡም ዋና ልዩ አማካሪ ነበሩ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊመሰረት በነበረባቸው ጊዚያት ካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ጊዜ የአፍሪካ ሀገራት ተዋህደው አንድ መሆን አለባቸው የሚለው የካዛብላንካ እንቅስቃሴ እና መጀመሪያ መተባበር ይቀድማል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድን እሳቤዎች ነበሩ። በከተማ ይፍሩ የሚመራው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ግንኙነት እነዚህን ሃሳቦች የማስታረቅ ሥራ ነበር የሚሰራው።

ብልህና በሳል የነበሩት ከተማ ይፍሩ ነገሩን በዲፕሎማሲያዊ ዘዴ ሲያግባቡ ቆይተው የካዛብላንካንም ሆነ የሞኖሮቪያ ሰዎችን ከንጉሡ ጋር በማወያየት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንድመሰረት አስደርገዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ፤ በቆራጥና ጀግና አርበኞቿ ነፃነቷን አስጠበቀች፣ በብልህ ዲፕሎማቶቿና መሪዎቿ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረተች፣ መቀመጫውንም አዲስ አበባ አስደረገች።

ዋለልኝ አየለ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You