አዲስ አበባ:- የህዝብ ተወካዮች ምክር የኦዲት ግኝትን ተከትሎ ተጠያቂነት እንዲኖር የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ አፀደቀ። የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በበጀት ዓመቱ 1 ሺ 653 ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውቋል
አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አርባ ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ የመንግሥት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የኦዲት ግኝት ተከትሎ ተጠያቂነት እንዲኖር የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በድምጽ ብልጫ አጽድቋል።
የውሳኔ ሐሳቡ የጸደቀው በአብዛኞቹ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም መንግሥት ከዘረጋው አሠራርና ሥርዓት ያፈነገጡ በመሆናቸው ነው።
የመንግሥት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ የሱፍ የውሳኔ ሐሳቡን አስፈላጊነት አስመልክተው እንደተናገሩት፤ የዋና ኦዲተር ግኝትን ተከትሎ በባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ላይ የእርምት እርምጃና ማስተካከያ እንዲካሄድ ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ እየተደረጉ አይደለም። ከዚህም በኋላ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሚችል ምንም መተማመኛ የለም።
በመጋቢት ወር ባለበጀት መሥሪያ ቤቶቹ በተገኙበት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ችግሩን ለመቅረፍ አቅጣጫ ቢያስቀምጡም ተግባራዊ ባለመደረጉ ችግሩ እየገዘፈ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የማስተካከያ እርምጃ በማይወስዱ ሃላፊዎች ላይ የተጠያቂነት እርምጃ አለመወሰዱ ዋናው ምክንያት ነው። በመሆኑም እርምጃዎች በመንግሥት በኩል እንዲወሰዱ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ በምክር ቤቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የውሳኔ ሐሳቡ ቀርቦ ፀድቋል።
የውሳኔ ሐሳቡም ለሀብት ብክነት ምክንያት የሆኑ አሠራሮችንና ሕግን ያልተከተሉ የመንግሥት ወጪዎች ላይ መንግሥት አስቸካይ እርምጃ እንዲወስድ፤ ከዚህ ቀደም የተፈፀሙ የሀብት ብክነትና ምዝበራ እንዲሁም የአሠራርና የሕግ ጥሰት በተመለከተ በሕግ አግባብ እርምጃ ተወስዶ የህዝብና የመንግሥት ገንዘብ እንዲመለስ እንዲደረግ፤ ሕግና አሠራርን የጣሱ በየደረጃው የሚገኙ ሃላፊዎች ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤ ሕግና አሠራር ያልተዘረጋላቸው ጉዳዮች የኦዲት ግኝቶችን መነሻ በማድረግ በኦዲት የማሻሻያ አስተያየቶች መሰረት እርምጃ እንዲወሰድ ሲሆን፤ ለዚህም የሚያስችለውን ግልጽ መርሐ ግብር መንግሥት እንዲያዘጋጅና የተወሰደውን እርምጃና የተገኘውን ውጤት በየሦስት ወሩ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ የሚያስችል እንደሆነ ሰብሳቢው ተናግረዋል።
በዕለቱ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የበጀት ዓመቱን የአስራ አንድ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የተጠቃለለ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ ተቋሙ 1 ሺ 403 የአቤቱታ መዝገቦችን እና ከ2010 ዓ.ም የዞሩ 250 መዝገቦች ላይ ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን ዋና እንባ ጠባቂው ዶክተር እንዳለ ሃይሌ ተናግረዋል።
እንደ ዋና እንባ ጠባቂው ማብራሪያ፤ ምርመራ ከተካሄደባቸው 1 ሺ 653 መዝገቦች መካከል ለ1 ሺ 347ቱ እልባት መስጠት ተችሏል። ቀሪዎቹ 306 መዝገቦች ምርመራቸው በሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል። ይሄ እንዳለ ሆኖ የ 41 መዝገቦችን ውሳኔ በተመለከተ ተቋሙ የሰጠውን የመፍትሄ ሐሳብ ተግባራዊ ያላደረጉ አስፈፃሚ አካላት በመኖራቸው ጉዳዩን በምክር ቤቱ ለሕግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማስተላላፋቸውንም አስታውሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ በበኩላቸው ተፈፃሚ ባልሆኑት ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በሎጀስቲክና በጀት ረገድ ተቋሙ የገጠሙትን ችግሮች ለመቅረፍ ምክር ቤቱ እንደሚሠራ በመግለጽ፤ ስለ እንባ ጠባቂ ተቋም የሥራ ድርሻ በህዝቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት አመራር አካላትም በኩል ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል። በተጨማሪም ተቋሙ በክልል ያሉ ቅርንጫፎቹን ቁጥር መጨመርና አሁን ያሉትንም በሰው ሃይልና በግብአት በማጠናከር ያለውን ክፍተት ለመቀነስ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ