አፍሪካዊ ሚዲያ ለምን አልኖረም?

የአፍሪካ ሕብረት ከተሠረተ 60ኛ ዓመቱን ጨርሶ እነሆ ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም 61 ኛውን ጀመረ:: ‹‹ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ›› የሚል መሪ ሃሳብ ቢኖረውም አፍሪካ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሳይፈታ እነሆ ወደ 100ኛ ዓመት ሊንደረደር ነው::

በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የሕብረቱ መቀመጫ የሆነችው የኢትዮጵያው መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አፍሪካዊ ጉዳዮችን አጉልቶ የሚያሳይ የራሳችን ሚዲያ እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ይታወሳል::

አዎ! ምዕራባውያን ሀገራትን ኃያል ያደረጋቸው መገናኛ ብዙኃን ነው:: እነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሚገኙት በምዕራባውያን እጅ ነው:: ዓለም አቀፍ ያደረግንባቸው ምክንያት ግን በመላው ዓለም የሚገኙ ነገሮችን ስለሚዘግቡ ነው እንጂ በይዘት የምዕራባውያን ናቸው:: የአፍሪካን ጦርነት ሲዘግቡ ምናልባት አካታችነት ሊመስለን ይችላል:: በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የእርስበርስ ብሽሽቅ ስላለ እነዚህ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ደካማ ጎን እየፈለጉ ሲዘግቡልን እውነተኛነታቸውና የሕዝብ ድምጽነታቸው ይመስለናል::

ያም ሆነ ይህ አሁን ዋናው ጥያቄ ለምን የእነርሱ ሚዲያዎች ገናና ሆኑ ሳይሆን ለምን አፍሪካስ ገናና ሚዲያ አይኖራትም የሚለው ነው መሆን ያለበት::

አፍሪካ ውስጥ እንደነ ቢቢሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ ሮይተርስ፣ አልጀዚራ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒዮርክ ታይምስ፣ ዘ ጋርዲያን… የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸው መገናኛ ብዙኃን የሉም:: በህትመት መገናኛ ዘዴም ሆነ በብሮድካስት ያን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባል የለም:: እነዚህ የምዕራባውያን መገናኛ ዘዴዎች እና አልጀዚራ ናቸው በመላው አፍሪካ እየተዘዋወሩ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ የሚዘግቡልን:: ለዚያም ነው አፍሪካ ችግሮቿ ብቻ የሚዘገቡት::

የመላው አፍሪካን ሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ማወቅ ባይቻል እንኳን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን፤ በአፍሪካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ መፈጠር ያልተቻለበትን ምክንያት መገመት ቀላል ነው፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ የባሱ እንጂ የተሻሉ አልሆኑም::

ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ብሽሽቅና የመንግሥታት ፍርርቅ ነበር:: አፍሪካ ውስጥ ደግሞ መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር ነውጥ አለ:: ከገዥው መንግሥት ጎን ለተቃወሞ የተደራጁ አካላት ይኖራሉ:: ይህም ገዥው መንግሥት የተረጋጋ እንዳይሆን ያደርገዋል:: በዚያ ላይ የገዥዎቹ መንግሥታት ባህሪም ነፃነትን የሚፈቅድ አይደለም::

በእነዚህ ምክንያቶች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ልሳን ሲሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን ደግሞ (በተለይ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ) ጭፍን ተቃዋሚና ግጭት አቀጣጣይ ይሆናሉ:: ይባስ ብሎም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የእርስበርስ መወነጃጀል አለ:: ስለዚህ በሀገር ውስጥ ያሉትን መገናኛ ብዙኃን የሀገሬው ሕዝብ አያምናቸውም::

አንድ መገናኛ ብዙኃን ተፅዕኖ ፈጣሪና ተወዳጅ የሚሆነው ደግሞ መጀመሪያ በሀገሩ ሕዝብ ተወዳጅና ታማኝ ሲሆን ነው:: የሀገሩ ሕዝብ ካጣጣለውና ከናቀው ዓለም ለምን ብሎ ይቀበለዋል?

አፍሪካዊ ሚዲያ እንዲኖረን ከማን ምን ይጠበቃል ከተባለ ሁሉም ነገር ከሁላችንም ነው የሚጠበቀው:: ሁሉም ነገር ከሁላችንም ቢጠበቅም ከመንግሥትና ከሕዝብም ብለን ልንለየው እንችላለን:: ከመንግሥት ነፃነት መስጠት ከሕዝብ ደግሞ በራስ ሀገር ተቋም መኩራትና የራስን ማመን::

እያየነው ያለው ነገር ግን ብሽሽቅ ነው:: አንዳንዱ፤ መንግሥትን ምንም እንከን የማይወጣለት አድርጎ ይሠራል፤ አንዳንዱ ደግሞ መንግሥትን የሀገር ጠላት አድርጎ ይሠራል:: ይህ አይነት መካረር የሚያዳክመው የሚዲያ ተቋምን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር ነው፤ ራሱ ፖለቲካውንም ነው::

ሌላውና ትልቁ መሰናክል ደግሞ በተለይም የህትመት ሚዲያው ላይ የተጋረጠው የወረቀት ውድነት ነው:: የ2010 ዓ.ም ለውጥ እንደመጣ ብዙ የግል ጋዜጦች ተጀምረው ነበር:: ፖለቲካው ላይ ምንም ለውጥ ሳይመጣ እነዚህ ጋዜጦች ወዲያውኑ ከሰሙ:: በዚህ ጉዳይ ላይ እኔው ራሴ ዘገባ ሰርቼ ነበር:: የአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቤል ዋቤላ በወቅቱ የሰጡኝ መልስ፤ ጋዜጣዋ የወረቀት ዋጋውን መቋቋም አቅቷት እንደተዘጋች ነው:: ቀጥሎም ሌሎች ጋዜጦች እየተዘጉ ሄዱ:: የቀሩትም መጠናቸውን መቀነስ ጀመሩ፤ አንዳንዶችም በA4 ቅርጽ መታተም ጀመሩ::

ይህ የሆነው እንግዲህ በነፃነት ማጣት ብቻ ሳይሆን በወረቀት ውድነት ተዘጉ ማለት ነው፤ በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ባህል ብዙም ስላልዳበረ አጋር የማግኘት ዕድሉም ጠባብ ነው::

በወቅቱ የተዘጉት ጋዜጦች አዘጋጆች የሰጡት አስተያየት፤ ነፃነት ቢኖርም በተዘዋዋሪ አሁንም በመንግሥት ቸልተኝነት እንደተቀዛቀዘ ነው:: አንዳንድ ነገሮች ከቀረጥ ነፃ ቢገቡ መንግሥትንም እንደሚያስመሰግኑት ምክረ ሃሳብ አቅርበው ነበር::

እንግዲህ ከሕዝቡም ከመንግሥትም ብዙ ይጠበቃል ስንል መንግሥትም አስቦበት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ፣ ሕዝብም ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ማለት ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ከፈጠርን በአፍሪካ ብሎም በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናል ማለት ነው::

የ‹‹ሲ ጂ ቲ ኤን›› ጋዜጠኛ የሆነው ግሩም ጫላ በአንድ ወቅት በሰይፉ በኢ ቢ ኤስ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ አፍሪካዊ ሚዲያ የማቋቋም ዓላማ እንዳለው ገልጾ ነበር:: ይሄው ጋዜጠኛ ከአንድ ዓመት በፊት በፋና ቴሌቭዥን ቀርቦ ሲናገር ነበር:: የሚዲያው ዋና መቀመጫ የሚሆነው በአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እንደሆነ ተናግሯል:: ይህንኑ በተመለከተም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር:: ሆኖም ግን እስከ አሁን ድረስ ምንም የተጀመረ ነገር አልሰማንም::

ቀደም ሲል እንዳልኩት አፍሪካዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ለማቋቋም እኛ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ መሆን አለብን:: አባቶቻችን የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ ኢትዮጵያ እንድሆን ያደረጉትን ጥረት እኛም በዚህኛው መድገም አለብን:: ለዚህ ደግሞ አንዱና ዋናው ሥራ ብሽሽቅና ምቀኝነትን ማቆም ነው:: በፖለቲካው ውስጥ የሚታየውን መጠላለፍ እዚህ ውስጥ አለማስገባት ነው::

ይህን አፍሪካዊ ሚዲያ ለቋቋም በተለይም ጋዜጠኞች ከፍተኛ ሚና ሊወጡ ይገባል:: የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች እና የቅርቡን የጋዜጠኝነት ሳይንስ የተማሩ ወጣት ጋዜጠኞች በጋራ ሊሠሩ ይገባል:: አንጋፋ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት (እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የቅርቦቹ የግል መገናኛ ብዙኃን) ሙያዊና ቁሳቂ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል::

ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሲሆን ሀገር ውስጥ ካሉን ሚዲያዎች የተሻለ የመሣሪያ ጥራትና አይነት እንደሚያስፈልገው ቢታወቅም ዳሩ ግን ሙከራው እንኳን ሲጠናከር አላየንም:: ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን የሚችሉ ጋዜጠኞች፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ልምድ ያላቸው ሰዎች ድጋፍ ቢያደርጉ ታስቦ የነበረው ነገር እውን ይሆን ነበር:: የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ሃሳብ በአጭር ጊዜ ተሳካ ማለት ነው:: ይህ ቢሳካ ደግሞ ፉክክር ስለሚኖር የሀገር ውስጥ ሚዲያዎቻችንም ጠንካራ የመሆን ዕድል ይኖራቸዋል:: ሀገር ወዳድ ነን የሚሉ ሁሉ ልባዊ የሀገር ፍቅር ቢኖራቸው ይሳካ ነበር:: ‹‹የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ነን›› እያሉ ከመፎከር እንዲህ አይነት ነገሮችን ማጠናከር!

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You