የሀገር ሠላም ማሳያዎቹ

ጦርነትና ግጭት የተመላለሰበት ሕዝብና ሀገር የሠላምን ዋጋ በሚገባ ያውቃል:: በጦርነትና ግጭት አያሌ ዜጎቹን ያጣ፣ አያሌዎቹም የተፈናቀሉበት፤ ጥሪትና ሀብቱ የወደመበት ወደ ድህነት የተመለሰ፣ እድገቱ የቆመ ሕዝብና ሀገር የሠላምን ዋጋ በሚገባ ይገነዘባሉ:: እንኳንስ እነሱ በችግሩ ውስጥ ያለፉት፣ ስለችግሩ ያነቡበትና ያዳመጡትም ይህን በሚገባ ይገነዘባሉ::

ጦርነትና ግጭት ገጽታቸውን ክፉኛ አበላሽተውባቸው ነው የሚያልፉት፤ ገጽታው የተባለሸ ሕዝብና ሀገር በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በቱሪስቶችና በመሳሰሉት የመፈለግ ዕድሉ ዝቅተኛ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው:: ያን የተባለሸ ገጽታ ማስተካከል ብዙ ዓመታትን ሊወሰድም ይችላል::

ጦርነትና ግጭት ብቻም ሳይሆኑ ድርቅና የመሳሰሉትም የዜጎችንና የሀገርን ገጽታ በማበላሸት ይታወቃሉ:: ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት በተከሰተው አስከፊ ድርቅና ያንን ተከትሎ በዜጎች ላይ የደረሰውን እልቂትና ጉዳት መሠረት በማድረግ አንድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ረሀብ ለሚለው ቃል ኢትዮጵያን መገለጫ አድርጎ መጠቀሙና ይህም ሀገሪቱን ምን ያህል ሲጎዳ መኖሩ ይታወቃል::

በሀገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ጦርነቶችና ግጭቶች በዜጎችና በሀገሪቱ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል:: የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እነዚያን ጦርነቶችና ግጭቶች በብልሃት ተቆጣጥሯቸዋል፤ መቆጣጠር ብቻ አይደለም በምትካቸው ተስተጓጉለው የቆዩ የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉ ርብርብ ሲያደርግም ቆይቷል::

እነዚያን ግጭቶችና ጦርነቶች ለመቆጣጠር ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፤ በጦር ግንባር ብቻ አይደለም ዋጋ የተከፈለው:: በጦርነቱ የተገኘውን ድል ዘላቂ ለማድረግ ሲባል መሣሪያ አንስተው ሀገርና ሕዝብን ከወጉ ቡድኖች ጋር የተኩስ ማቆም ስምምነት በማድረግ ችግሩን በሠላማዊ አማራጭ ለመፍታት ተሠርቷል:: ለዚህም ከሕወሓት ጋር የተደረገውን ጦርነት በሠላማዊ አማራጭ ለመፍታት የተከናወነውና እየተከናወነ ያለውን ተግባር መጥቀስ ይቻላል::

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ብዙ ተሠርቷል:: በየአካባቢዎቹ መሣሪያ ካነሱ ኃይሎች ጋርም ጭምር በመነጋገር ችግሮቹን በሠላማዊ አማራጭ ለመፍታት ጥረት ተደርጓል:: በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ሠላምና መረጋጋትን ለመመለስ ተሠርቷል:: በዚህ ሁሉ የሀገር ሉዓላዊነትን አስጠብቆ በመቆየት ውጤታማ ተግባር ማከናወን ተችሏል::

በሀገሪቱ ጨርሶ ሠላም እንደሌለ ተደርጎ በማኅበራዊ ሚዲያና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በአሁኑ ወቅት የሚሰራጩ መረጃዎች ኢትዮጵያን በፍጹም አይገልጹም:: አሁን በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች የሀገርን ሉዓላዊነት ፈትነው ከነበሩት የሠላም ችግሮች ጋር ሲወዳደሩ “እግርና እግርም ይጋጫል” በሚል ሊታዩ የሚችሉ ናቸው::

እርግጥ ነው ግጭቶቹ ወይም አንዳንድ የፀጥታ ችግሮች የሕዝብን እንደ ልብ የመንቀሳቀስ ሂደት ሊያውኩ ይችላሉ፤ የፖለቲካ ወይም ሀገርና ሕዝብ የመጉዳት ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች እነዚህን ችግሮች አሳድገው በማቅረብ ሊሞግቱ ይችላሉ:: እነዚህ ኃይሎች በሀገሪቱ የትኛውም ልማት ስኬታማ ሆኖ ቢፈጸም ለእነሱ ስኬት አይደለም:: እሱን እግረ መንገድም ቢሆን ላይጠቅሱት ይችላሉ:: ምክንያቱም ጭር ሲል አይወዱም::

በሀገሪቱ አሁን እየሆነ ያለውም ይህ ነው:: በሀገሪቱ ምንም አይነት ሠላም የለም የሚሉ አካላት አሉ:: ብዙ የሠላም ማሳያዎች፣ ማረጋገጫዎች በፊታቸው እየተመላለሱም፣ ወሬያቸው የሠላም መደፍረስ፣ አፈና፣ ጨረስነው፣ ፈጀነው፣ ቆረጥነው ፈለጥነው የሚል ነው::

በዚህ እዚህም እዚያም ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ባሉበት ወቅት፣ በርካታ ፕሮጀክቶች ሌት ተቀን እየተሠሩ ባሉበት በዚህ ወቅት እነሱ የጦርነት፣ የግጭት አጀንዳ ማራመዳቸውን ቀጥለዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በወለጋ ነቀምት ስታዲየም የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ለለውጡ መንግሥት ያላቸውን ድጋፍ በገለጹበት መድረክ ላይ መገኘታቸው ለእነሱ ምንም አይነት የሠላም ጠረን የለውም:: ድፍን ወለጋን ቅኝ ይዘነዋል ብለው የሚያስቡ አይነቶች በመሆናቸውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ መገኘት እድሜያቸውን እንደሚያሳጥርባቸው አድርገው ያስባሉና የቱንም ያህል የሠላም አየር ቢነፍስ ሠላም አለ ብለው አይቀበሉም::

ባለፉት ዓመታት በዚያ አካባቢ የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት መቆም ለእነሱ መልካም ዜና አይደለም:: የእነሱ መልካም ዜና እውነታውን ትቶ ተቃራኒውን ይዞ አየሩን መበከል ነው::

የጠቅላይ ሚኒስትሩ በባሕር ዳርና ጎርጎራ መገኘትም እንዲሁ በስፍራው ለሚንቀሳቀሰው አክራሪ ኃይልና በሌላ አካባቢም ተመሳሳይ ዓላማ ላለው ቡድን ውርደት ተደርጎ ነው የሚወሰደው:: እነሱ መላ አማራ በቁጥጥራችን ስር ነው ያለው የሚሉ እንደመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባሕር ዳር መገኘታቸው፣ በባሕር ዳር ዓባይ ወንዝ ላይ የተሠራውን ግዙፍና ውብ ድልድይ ግንባታው ተጠናቆ መመረቁ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ተገኝተው ምረቃው መካሄዱ በአካባቢው ሠላም ስለመኖሩ መልእክት የሚያስተላለፍ ነው ብለው ለመቀበል ሕመም ይሆንባቸዋል::

እውነታው ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ መገኘት፣ የድልድዩ ግንባታ ተጠናቆ መመረቅ በክልሉ ሠላም መረጋጋት መኖሩን ያመለክታሉ:: በተለይ የድልድዩና የጎርጎራ ፕሮጀክት ግንባታ እዚህ ደረጃ መድረስ አክራሪው ኃይል ክልሉን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሬዋለሁ በሚልበት በዚያ ወቅት ግንባታው ሲካሄድ እንደነበርም ነው የሚያመለክተው::

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ሞጆ አካባቢም ተገኝተዋል:: በዚያም ለሚገነባው የገዳ ልዩ ኢንዱስትሪ ዞን የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ደግሞ በባሌ የበልግ ቡቃያ ጎብኝተዋል፤ በመደመር መጽሐፍ ሽያጭ በሶፍ ኡመር ዋሻ ግንባታው እየተካሄደ ያለውን ፕሮጀክት አፈጻጸምንም ጎብኝተዋል::

እነዚህ ትላልቅ ሥራዎች ያለ ሠላም ከቶውንም እይታሰቡም፤ ሥራዎቹ ሀገሪቱ ሠላም የሰፈነባት አይደለችም ለሚሉ ሁሉ ትልቅ መርዶ ናቸው:: እነሱም እንደለመዱት ይህን ዐቢይ ዜና ትተው ሌሎች የጭር ሲል አልወድም አጀንዳዎችን ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል፤ ልዩነቱም እዚህ ላይ ነው፤ መንግሥት ልማትና ሠላምን፤ እነሱ ደግሞ ሽብርን መንገዳቸው አድርገዋል::

በቅርቡም በአዲስ አበባ ከ210 በላይ አምራቾች ምርቶቻቸውን ይዘው የቀረቡበት፣ ከሦስት ቢሊየን ብር በላይ ግብይት የተፈጸመበት፣ ከ100 ሺ በላይ ጎብኚዎች የጎበኙት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተካሂዷል:: በሌላም በኩል በዚሁ ሰሞን የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ስብሰባ በመቀሌ ተካሂዷል:: በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ተመርቋል::

በቢሾፍቱ የመከላከያ ግዙፍ ሆስፒታል ተመርቋል፤ ይህ ዜጎችም ሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጪ የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያስቀር መሆኑ ተገልጿል:: ከ35 ዓመት በፊት ሊገነባ ታቅዶ የነበረ ሆስፒታል ነው ተገንብቶ የተመረቀው:: በአዲስ አበባ በአይነቱ ልዩ የሆነ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤትም ተገንብቶ ተመርቋል::

በግብርናው፣ በገቢዎች እና በሌሎችም የኢኮኖሚው ዘርፎች የተያዙ እቅዶች አፈጻጸሞች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የላቁ ናቸው፣ ማዳበሪያ ከአንዳንድ ዞኖች በስተቀር በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ መልኩ አስቀድሞ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው::

በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት በየዓመቱ ከፍተኛ እምርታ የታየበት የስንዴ ምርት እየተገኘ ነው:: በተለያየ ምክንያት የተወሰነ መንጠባጠብ ቢታይበትም፣ ማዳበሪያ ተጓጉዞ አርሶ አደሩ ዘንድ እንዳይደርስ ያደረገ ኃይል የለም:: ይህ ሁሉ የሠላም መገለጫ መሆኑ ነው::

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ከተማዋን እንደ ስሟ የማድረግ፣ የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗን ታሳቢ የሚያደርግ ግዙፍ የኮሪደር ልማት ለ24 ሰዓት ለሰባት ቀናት በከፍተኛ ርብርብ እየተካሄደ ይገኛል:: ይህ ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሽፍን የመንገድ ፕሮጀክትን ያካተተ ልማት በተለይ የመንገድ ፕሮጀክቱ ወደ መጠናቀቅ እየተቃረበ ይገኛል::

የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና የከተማዋን ከንቲባ ጨምሮ ከፍተኛ የከተማዋ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በዚህ ፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር ላይ ተጠምደዋል:: በዚህ ፕሮጀክት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዘዋወሩ ተደርጓል:: ነዋሪዎቹ የቀበሌ ቤት ውስጥ ከሆኑና ኮንደሚኒየም ምርጫቸው ከሆነ ኮንደሚኒየም ቤት፣ የቀበሌ ቤት ይሻለናል ላሉት ደግሞ የቀበሌ ቤት ተሰጥቷቸው ወደ አዲሱ መንደራቸው ገብተዋል:: ባለይዞታዎች ደግሞ ቦታና ካሣ ተሰጥቷቸው ተነስተዋል::

እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ለማከናወን ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት፣ ምትክ ቤትና ቦታ ያስፈልጋል፤ ይህን ሁሉ ይዞ ነው መንግሥት ወደ ኮሪደር ልማቱ የገባው:: ተነሺዎችን የማሳመን፣ አዲሱን አካባቢያቸውን በመሠረተ ልማት የማሟላት፣ የማጓጓዝና የመሳሰሉት ሥራዎች በስኬት ተጠናቀው ወደ ልማቱ መገባቱ የመንግሥትን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ያመለክታሉ::

እየተካሄደ ያለውን የመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማት እንዲሁም የመልሶ ልማት ሥራዎችን ለተመለከተም የመንግሥት ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ እንዲገነዘብ ያደርገዋል:: እነዚህ ሁሉ ግዙፍ ሥራዎች ሀገር በሠላማዊ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን እንጂ በጦርነት ቀጣና ውስጥ መሆኗን በጭራሸ አያመለክቱም::

አክራሪዎች ግን ሀገሪቱን የግጭት፣ የጦርነት አውድማ አድርገናታል ብለው በሚያስቡባቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት በኃይል ሊመጣ የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እያስገነዘበ፣ ወጣ ያለ ነገር ሲያጋጥምም እርምጃ እየወሰደ ልማቱን ቀጥሏል:: ልማቱን ለመቀጠሉ ደግሞ እዚህ ለአብነት የተጠቀሱት ልማቶች ብቻ አይደለም ማሳያዎቹ:: እጅግ በርካታ ማሳያዎችን በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች ከተካሄዱና እየተካሄዱ ከሚገኙ የልማት ሥራዎች መጥቀስ ይቻላል::

እዚህ የቅርብ የቅርቦቹን አነሳሁ እንጂ የዓባይ ግድብን ግንባታ ለማጠናቀቅ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት፣ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ፣ ግንባታው አሁን የደረሰበት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ፣ ወዘተ ሲታሰቡም ሀገሪቱ በጽንፈኛ ቡድኖች አጀንዳ ሳትናጥ ልማቷን አጠናክራ መቀጠሏን ያመለክታል::

መንግሥት በልማት ላይ ብቻ አይደለም ሙሉ ጊዜውን የሰጠው:: በሀገሪቱ ሠላምን ማስፈን ለልማትም ሆነ ለሌሎች ማኅበራዊ ሥራዎች ያለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሀገሪቱ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው ጦር ሰብቀው ብዙ ቢያደርጉም ሠላማዊ አማራጭን በመከተል የሰሜኑ ጦርነት ቆሞ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ነገሮች እንዲታዩ የወሰደው እርምጃና በዚሁ መሠረት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ስለሠላም እየተከናወነ ያለውን ተግባር ከማመልከት በተጨማሪ ሀገሪቱ ሠላም መሆኗንም ይጠቁማሉ::

ምክንያቱም፣ ሠላም የሌላት ሀገር አይደለም ግዙፍ የልማት ሥራን ልትሠራ ያሉትን መጠበቅም አትችልም:: በኢትዮጵያ ከዚህ በተቃራኒው ጠላቶቿ ሠላም የላትም በሚሏት ሀገር ልማቱ ተጠናክሮ የሄደበት ሁኔታ በሀገሪቱ ሠላም የለም የሚሉትን እነዚህን አካላትና ሠላም ስለመኖሩ የሚጠራጠሩ አካላትን ሁሉ የሚያሳፍር ትልቅ ክንውን ነው::

ይህን ሁሉ ማንሳት ውስጥ የተገባው ሀገሪቱ ከእነሠላሟ መሆኗን በማሳያ ለማስገንዘብ ነው:: ሀገሪቱን ሁሌም ግጭትና ጦርነት ውስጥ አርገው የሚስሉት የገዛ ልጆቿም ሆኑ እነሱን መሣሪያ ያደረጉ የውጭ ኃይሎች የሀገሪቱን የልማት ጉዞ ሊያስተጓጉሉት እንደማይችሉ በሚገባ ለማስገነዘብ ነው::

እነዚህ ኃይሎች የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታንም ፈተናውን ሊያበዙበት ይችላሉ እንጂ ከመስመሩ አያስወጡትም:: የሀገሪቱ ሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎች ለዘመናት ሲናፍቁት የኖሩት ሀገራዊ ምክክርም ሊጀመር ነው::

የሀገሪቱ ጠላቶች ባለፉት ዓመታት አንዴ አብረው፣ ሌላ ጊዜ በየተራ እየተነሱ ያደረሱት ጥፋት የትም እንዳላደረሳቸው አሁን እንኳ አውቀው ፊታቸውን ወደ ሠላማዊ አማራጭ ቢመልሱ መልካም ነው እላለሁ::

በዚህች ሀገር መሣሪያ አንስቶ ሊፈጸም የሚችል ተግባር ስላለመኖሩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መሣሪያ አንስተው ጫካ ከገቡም ሆነ መንግሥትን ፊት ለፊት ለመግጠም ከሞከሩ መማር የሚቻለውም ይህንን ነው:: ትርፍ አለው ከተባለ ትርፉ የጠፋው የአያሌ ዜጎች ሕይወት፣ የወደመው የሀገርና የዜጎች ሀብትና ጥሪት ነው:: ይሄ ደግሞ ትርፉ ለሀገርና ሕዝብ ሳይሆን፤ የሀገርን ሠላም በማወክ፣ ሕዝብን በመረበሽ ትርፍን ለሚናፍቁ ኃይሎች ነው::

እንደሚታወቀው ይህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲናፍቁት ወደ ኖሩት ሀገራዊ ምክክር የሚገባበት ነው:: ይህ ምክክር ሊጀመር ጥቂት ነው የቀረው:: እንደ ሀገር እና ሕዝብም ያለው ፍላጎት፤ ለጥፋት ኃይሎችም የሚሻለው ሠላማዊ አማራጭን ይዞ ወደዚህ ምክክር በመምጣት ለሀገር የሚበጀውን ሀሳብ ማመላከት ነው::

ዘካርያስ

 አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You