ጉዳፍ ጸጋይ በዩጂን ዳይመንድ ሊግ ከበርካታ ኬንያውያን ጋር ተፋጣለች

ከአህጉረ እስያ እና አፍሪካ ወደ አሜሪካ የተሻገረው ዳይመንድ ሊግ ዛሬ በኦሪጎን ዩጂን ይካሄዳል:: የኦሊምፒክን መዳረስ ተከትሎ አትሌቶች አቅማቸውን ለመፈተሽ በሚመርጡት በዚህ ውድድር ስመጥር እና የዓለም ክብረወሰንን መጨበጥ የቻሉ በርካታ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች እንዲሁም የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ይፎካከራሉ:: ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ተፎካካሪ ናቸው:: የጎረቤት ሀገር ኬንያ የኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ሰዓት ማሟያ ሩጫ በውድድሩ የተካተተ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ከዳይመንድ ሊግ በተሰረዘው በዚህ ርቀት የሚካፈሉ መሆኑ ተረጋግጧል::

የዳይመንድ ሊግ 5ኛ መዳረሻ በሆነው ዩጂን በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ በተለያዩ ርቀቶች ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል:: ዝነኞቹ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ከ800 ሜትር አንስቶ የተለመደ ብቃታቸውን ለማስመስከር ተዘጋጅተዋል:: በውድድሩ በይበልጥ ትኩረት የሳበው ግን የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮናና የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ተሳትፎ ነው:: ባለፈው ዓመት እዚሁ ዩጂን ዳይመንድ ሊግ ላይ ጉዳፍ ጸጋይ በ5 ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን በማሻሻል የርቀቱን ክብር መቀዳጀቷ ይታወሳል:: በተያዘው የውድድር ዓመት በቤት ውስጥ ውድድር ስኬት የጀመረችው አትሌቷ በዳይመንድ ሊጉ የቀጠለች ሲሆን፤ ክብረወሰን የመስበር እቅድ እንዳላትም ሲነገር ቆይቷል:: ይሁንና ከዩጂን በተገኘው መረጃ አትሌቷ በተጠበቀችበት የ1ሺ 500 ሜትር አሊያም 5ሺ ሜትር ሳይሆን በ10ሺ ሜትር ርቀት እንደምትካፈል ተረጋግጧል::

እንደሚታወቀው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዳመንድ ሊግ 10ሺ ሜትር ርቀት ተሰርዟል:: ይሁንና የኬንያ አትሌቲክስ በፓሪሱ ኦሊምፒክ ሀገሪቷን የሚወክለውን ብሄራዊ ቡድን ለመለየት የሚያስችለውን የሰዓት ማሟያ ውድድር ዛሬ በዩጂን ያካሂዳል:: ይህንንም ተከትሎ በዝርዝሩ ከተካተቱት ኬንያዊያን አትሌቶች መካከል ሁለት ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው ታውቋል:: በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አስደናቂ በሆነ ፉክክር አሸናፊ የሆነችው ጉዳፍ ከሁለት ወራት በኋላ በሚካሄደው ኦሊምፒክ በዚህ ርቀት የምትሮጥ ስለመሆኗም አመላካች ይሆናል:: በሰዓት ማሟያው ከሚሮጡ አትሌቶች መካከልም ፈጣኑ ሰዓት የጉዳፍ ሲሆን፤ ከተፎካካሪዎቿ ኬንያዊያን አትሌቶች ጋር መገናኘቷ በቀጣይ ለሚኖራት ተሳትፎ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይጠበቃል:: ከጉዳፍ ባለፈ አትሌት ቦሰና ሙለቴ በዚህ ርቀት ውድድሩ ላይ የምትካፈል አትሌት ናት::

ሌላኛው እጅግ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያስተናግድ የሚጠበቀው ርቀት ደግሞ 5ሺ ሜትር ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች እንዲሁም በዜግነት ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሃሰን ተካፋይ መሆናቸው ታውቋል:: በዚህ ርቀት ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወጣት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በበላይነት የማጠናቀቅ እድላቸው የሰፋ እንደሚሆንም ይጠበቃል:: 14:12.98 የሆነ ሰዓት ያላት እጅጋየሁ ታዬ የውድድሩ ፈጣን አትሌት ስትሆን ሲፈን ሃሰን እና ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ ለአሸናፊነት በብርቱ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው:: በ1ሺ 500 ሜትርም በተመሳሳይ ባለፈጣን ሰዓት አትሌት የሆነችው ድርቤ ወልተጂ የምትሳተፍ ይሆናል:: ከሳምንት በፊት እዚያው አሜሪካ በተካሄደ ውድድር ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው አትሌቷ ባለፈው ዓመት በዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው:: እጅግ ተስፈኛ ከሆኑ የርቀቱ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው ወጣቷ ድርቤ በዳይመንድ ሊጉ ብቻም ሳይሆን በፓሪስም አቅሟን ታስመሰክራለች በሚል ትጠበቃለች:: ሂሩት መሸሻ እና ወርቅነሽ መሰለም ጠንካራ ሊባሉ የሚችሉ የርቀቱ አትሌቶች ናቸው::

የአትሌቲክሱ ዓለም በቅርቡ ከተዋወቃቸው ወጣት ኮከብ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው ጽጌ ድጉማ በዚህ ውድድር የምትካፈል ሲሆን፤ በተለይ ከአሜሪካዊቷ አትሌት ጋር የሚኖራቸው ትንቅንቅ ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል:: ከሳምንት በፊት አሜሪካ ላይ በተካሄደው ውድድር በዚህ ርቀት እጅግ አስደናቂ የአሸናፊነት ተጋድሎ ያደረገችው አትሌቷ በኡጋንዳዊቷ ተፎካካሪዋ 0ነጥብ006 ሰከንድ በሆነ ልዩነት ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃን መያዟ የሚታወስ ነው:: ለዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አዲስ ብትሆንም የማይታመን ብቃት በማሳየት ላይ የምትገኘው አትሌቷ በተለይ ከአሜሪካዋ አቲንግ ሙ ጋር ሊኖራት የሚችለው ፉክክር ተጠባቂ ነው:: በርቀቱ የኦሊምፒክ እና የዓለም ቻምፒዮና ሜዳሊያዎችን ጠራርጋ በመውሰድ የምትታወቀው አትሌቷ ምናልባትም በአዲሲቷ ኢትዮጵያዊት ኮከብ ልትፈተን እንደምትችል ይገመታል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You