ትኩረት ያልተሰጠው መስማት የተሳናቸው ስፖርት

በኢትዮጵያ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚገኙ ይገመታል። እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደማንኛውም ዜጋ በስፖርቱ የመሳተፍ እና ተጠቃሚ የመሆን መብት ቢኖራቸውም የተሰጣቸው እድል ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ተሳትፏቸውን ለማስፋትና ለማሳደግም ከመንግሥት፣ ከህብረተሰቡ እንዲሁም ከተቋማት ልዩ ድጋፍ እና ተገቢ ትኩረት ሊሰጣቸውም አልቻለም።

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያካሂደውን መስማት የተሳናቸው የአትሌቲክስ ውድድር (ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ) እና የጠረጴዛ ቴኒስ(ለ2ኛ ጊዜ) በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አካሂዷል። ውድድሩ ከግንቦት 12 እስከ 14/2016 ዓ.ም በደማቅ ፉክክር ሲካሄድ፣ ሶስት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ተካፍለዋል። በጠረጴዛ ቴኒስ 13 ወንድ እና 16 ሴት ተወዳዳሪዎች እንዲሁም በአትሌቲክስ ስፖርት 61 ወንድ እና 17 ሴት በድምሩ 107 መስማት የተሳናቸው ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል ።

ቻምፒዮናው ሀገር አቀፍ ቢሆንም ክልሎች ለስፖርቱ የሰጡት ትኩረት አናሳ በመሆኑ የተሳታፊዎች ቁጥር በሚፈለገው ልክ መሆን አልቻለም። በዓመት አንድ ወይም ሁለት ውድድሮችን ብቻ በማካሄድ መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞችን ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደማይቻል ይታወቃል። በሀገር ውስጥ ውድድሮችን ለማዘጋጀት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ለመሳተፍ ደግሞ ፌዴሬሽኑ በበጀት እጥረት መፈተን ከጀመረ ውሎ አድሯል።

በስፖርቱ የሚሳተፉ መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ አነስተኛ ነው። ይህም ከሁለት ስፖርቶች ባለፈ በሌሎች ስፖርቶችም ተሳትፎ ሊያረጋግጥ ይቅርና እነዚህንም በአግባቡ እንዳይሳተፉ እንቅፋት ሆኗል። ስፖርቱን ለመደገፍ እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሌላው ፈተና የሆነው እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች በሚመለከት ያለው ግንዛቤ አለመቀየሩ ነው። በመቀጠል ተቋማት ስፖርቱን ለመደገፍ ፍቃደኛ አለመሆናቸው እና ለሚቀርብላቸው የድጋፍ እቅድ መልስ አለመስጠትም ሌላው የተስተዋለ ክፍተት ነው።

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ተክላይ፤ ክልሎች መስማት የተሳናቸውን እና ሌሎቹን የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል እየተመለከቱ እንዳልሆነ መታዘባቸውን ጠቁመዋል። በውድድሮች ላይ በጀት መከልከል የተለመደና በተደጋጋሚ የሚታይ ክፍተት መሆኑን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ስፖርት ያለ ምንም ልዩነት ለሁሉም የተሰጠ ጸጋ ቢሆንም አካታችነትን ተግባራዊ የማድረግና መስማት የተሳናቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በእኩል የማሳተፍና የመብቱ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ይቀራል ይላሉ።

ስፖርቱን ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙኃን ሚና የማይተካ ቢሆንም፤ ለዚህ ስፖርትና ለሌሎች ስፖርቶች የሚሰጡት ትኩረትና ሽፋን እኩል አለመሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ያመላክታሉ፡፡ መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች በስፖርተዊ ጨዋነት እና ከአበረታች ቅመሞች ነጻ በመሆን የሚታወቅ በመሆኑ ሊበረታቱና ሽፋን ሊሰጣቸው እንደሚገባም ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በፊት በአህጉር እና ዓለም አቀፍ (ኬንያ እና ቱርክ) በተካሄዱት ውድድሮች ተሳትፎ የተሻለ ውጤት ቢመዘገብም ከበጀት ችግር ጋር ተያይዞ ግን ማስቀጠል አልተቻለም። ይህንን ለማስቀጠል ጥረት ቢደረግም በዚሁ ምክንያት በአራት ዓመት ውስጥ ሶስት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን መሳተፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ፌዴሬሽኑ ማድረግ የሚገባውን ጥረት በማድረግ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በር ያንኳኳ ቢሆንም ምላሹ አርኪና አበረታች አልነበረም፡፡ ከዚህ ውድድር በኋላ በቻይና በሚካሄደው አህጉር አቀፍ ውድድር ለመሳተፍ ቢታሰብም በበጀት እጥረት መሰረዙን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። ስፖርቱ ከፓራሊምፒክ የተለየ ቢሆንም እንደ አንድ በመታየቱ ድጋፍ እንደማያገኝ ፕሬዚዳንቱ ያብራራሉ።

ህብረተሰቡ መስማት ለተሳናቸው ስፖርቶች ያለው ግንዛቤ ተቀይሮ ተሳትፎንና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር የመገናኘት እድል የሚፈጥር ከሆነ ስፖርቱን ማገዝ ይቻላል። አዲሱ የመንግሥት መዋቅር እያንዳንዱ ፌዴሬሽን ሀብት ማሰባሰብ እንዳለበት ቢገልጽም፤ ስፖርቱ ላይ ያለው አመለካከት ካልተቀየረ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ፌዴሬሽኑ በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ ለደጋፊ ተቋማት እቅዶችን ለማሳወቅ ግን ጥረቱን ቀጥሏል፡፡

ቻምፒዮናው በአትሌቲክስ(በአጭር፣ መካከለኛ ርቀት እና የሜዳ ተግባራት) ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ መስማት የተሳናቸው አትሌቶች ጥሩ ፉክክር በማድረግ በየደረጃቸው የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በአትሌቲክስ፣ ኦሮሚያ ክልል በወንድና ሴት የቡድን አሸናፊ በመሆን ሶስት ዋንጫዎችን መውሰድ ችሏል። በጠረጴዛ ቴኒስ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። በቴኒስ ድሬዳዋ የጸባይ ዋንጫውን ሲያነሳ በአትሌቲክስ ሲዳማ መውሰድ ችሏል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You