የለሚ ፋብሪካ ለአየር መንገድና ለሸራተን ሆቴል እንጀራ እያቀረበ ነው

አዲስ አበባ፡- የለሚ እንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለሸራተን አዲስ ሆቴልና ለተለያዩ ተቋማት እንጀራ በማቅረብ አቅሙን ማሳደጉን የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሰብለ ስማቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የለሚ ኩራ እንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ ለሸራተን አዲስ ሆቴል በወር ዘጠኝ ሺህ እንጀራ እያቀረበ ይገኛል፡፡

ሆቴሉ የራሱ የጥራት መርማሪ ባለሙያዎች ስላሉት የጤፉን ደረጃ መርምረው እንደሚወስዱ ወይዘሮ ሰብለ ጠቁመው፤ የሆቴሉን መስፈርት በሚያሟላ መልኩ የሚቀርበው የጤፍ እንጀራ ተቀባይነቱ ከፍ እያለ መሆኑን አንስተዋል።

ከሆቴሉ ጋር ከ325 እስከ 360 ግራም የሚመዝን እንጀራ ለማቅረብ ስምምነት መደረጉን አስታውቀው፤ለሆቴሉ በቀን ሦስት መቶ እንጀራ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሆቴሉም በኩል ጥሩ እንጀራ ሲቀርብ አበረታች አስተያየት እንደሚሰጥና መሻሻል ያሉባቸው ነገሮች ሲኖሩ ደግሞ እንዲስተካከል ሃሳብ በመስጠት በመግባባት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የእንጀራ መጋገሪያው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋናው የምገባ ክፍልና ለካፌው በቀን ስድስት ሺህ እንጀራ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።

የሚቀርበው እንጀራ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየጊዜው የደንበኞቹን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ከፋብሪካው እንጀራ የሚረከቡ ተቋማት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ወይዘሮ ሰብለ እንደገለጹት፤ የእንጀራ ፋብሪካው ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስምንቱም ካምፓሶች በቀን 20 ሺህ እንጀራ እያቀረበ ይገኛል።

የእንጀራ መጋገሪያው በቀጣይ ዋና ዓላማው በዓለም ገበያ የኢትዮጵያን እንጀራ ማቅረብ ነው ያሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ ለዓለም አቀፍ ሆቴሎች እንጀራ ማቅረብ ከወዲሁ መጀመሩ በጥራት በኩል በቂ ልምምድ ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።

የተለያዩ ተቋማት ከፋብሪካው እንጀራ ሲወስዱ ንጹህ እንጀራ ከማግኘታቸው በተጨማሪ ለእናቶች ሥራ በመፍጠር የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እድል እየፈጠሩ መሆኑንም መረዳት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ምክትል ኮሚሽነሯ እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት በፋብሪካው 570 እናቶች ተቀጥረው እየሠሩ ይገኛል።

ስልጠና ወስደው የተቀመጡ አራት ሺህ እናቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ፋብሪካው አቅሙን እያሳደገ ሲመጣ ስልጠና የወሰዱ እናቶች በሙሉ ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ፋብሪካው ድርቆሽ እንጀራ በማዘጋጀት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ እስካሁን ድረስ 56 ኩንታል የእንጀራ ድርቆሽ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ድርቆሹን ከሚወስዱ መጠነኛ ደንበኞች ባለፈ ከገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ ውስንነት መኖሩን አንስተው፤ የድርቆሽ እንጀራውን የገበያ ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

እንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካው በ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በአራት የማምረቻ ሼዶች ገቢ የሌላቸው እናቶች በማደራጀት ሚያዚያ 2015 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱን ይታወሳል።በቀን 288 ሺህ እንጀራ የሚጋገርበትና እንጀራን ኢንዱስትራላይዝ በማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መሆኑም ይታወቃል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You