ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ያለመው የትምህርት ቤቶች ውድድር

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት ለምታስመዘግባቸው አመርቂ ውጤቶች፣ የአትሌቶችና የአሰልጣኞች ጥረትና ልፋት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ይታወቃል፡፡ ትምህርት ቤት የሁሉም ሙያዎች መፍለቂያና ማሳደጊያ እንደመሆኑ፣ በስፖርቱ ዘርፍም አትሌቶችን በእውቀትና ስነ-ልቦና የዳበሩ እንዲሁም በተገቢው የእድሜ ደረጃ ተፎካካሪና ውጤታማ የሚሆኑበትን ስንቅ ያስይዛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በኢትዮጵያ በአግባቡ ተሰርቶበታል ለማለት ያዳግታል፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት ትምህርት ቤቶች ላይ መሰረት ተደርጎ ባለመሰራቱ በየወቅቱ ከእድሜ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

የተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ሲያግዝ የቆየው ሶፊ ማልት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሳይንሳዊ እውቀት የዳበሩ ታዳጊ አትሌቶችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ትምህርት ቤቶች ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ ተቀዛቅዞ የቆየው በትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በድጋሚ ማንሰራራት መጀመሩም ይታወቃል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች የተሳተፉበት የአትሌቲክስ ወድድር ግንቦት 10 እና 11/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም ተካሂዷል፡፡ ውድድሩን የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ሶፊ ማልት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፤ ለአሸናፊ ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡

የትምህርት ቤት ስፖርትን የማነቃቃትና ተተኪ ወጣት አትሌቶችን የማፍራት አንዱ እንቅስቃሴ የሆነው የሁለት ቀናት የ2ኛ ደረጃ የትምህርት ቤቶች የአትሌቲክስ ውድድር በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ተሳታፊ ትምህርት ቤቶችን ለመምረጥ ለሁሉም ክፍት የሆነ ምዝገባ የተደረገ ሲሆን፤ ለአራት ሳምንታት ልምምድ ኃላፊነት የወሰዱ ትምህርት ቤቶች ተመርጠው ወደ ውድድር መግባታቸው ተጠቅሷል። በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች አምና ከተወዳደሩ ተማሪዎች ውጪ፤ ተተኪና አዳዲስ መርጠው እንዲያመጡ በማድረግ መለየት ተችሏል። ከእያንዳንዱ ትምህርት ቤት 15 ወንድ እና 15 ሴት ተማሪዎች፣ በድምሩ 300 ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ተማሪዎቹ በአምስት የሩጫ ሁነቶች ማለትም በ100፣ 200፣ 400፣ 800 እና 1500 ሜትር ፉክክር በማድግ በየርቀቱ አሸናፊዎችን መለየት ተችሏል፡፡

ትምህርት ቤታቸውን በመወከል የተሳተፉት ተማሪዎች ቀጣይ አቅጣጫቸውን የሚያውቁበትና ተሰጥኦአቸውን የሚያወጡበትን መድረክም ማግኘት ችለዋል። ትምህርት ቤቶቹ ባካሄዱት ፉክክር ቦሌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። ምኒልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ደግሞ ቀጣዮቹን ደረጃዎች በመያዝ አጠናቀዋል።

አቶ ዳዊት ባዬ የሄኒከን ኢትዮጵያ የኮርፖሬት ጉዳዮች ሥራ አስኪያጅ፣ ሶፊ ማልት በኢትዮጵያ የሚደረጉ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴዎችን እየደገፈ መቆየቱን ጠቁመው፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሩጫ ውድድሮችን ለተከታታይ ሁለት ዓመት ሲያካሂድ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ ውድድሩ በትምህርት ቤት ለሶስተኛ ዓመት የተካሄደ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በባህርዳር፣ በጎንደር፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ እና በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተከናውኖ ለትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ሽልማት መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ በሀዋሳ እና ጅማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የአትሌቲክስ ውድድር በቀጣይ ይካሄዳልም ብለዋል፡፡

ድርጅቱ የተማሪዎችን ውድድር በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት በተጨማሪ ታዳጊና ሀገርን መወከል የሚችሉ አትሌቶችን ለማፍራት እየሰራ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችን እና ተማሪዎችን ለማበረታታትና ለማነቃቃት የሚያስችል ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፤ አንደኛ ለወጣ ትምህርት ቤት 50 ሺ ብር፣ ሁለተኛ 30 ሺ ብር እና ሶስተኛ 25 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ተማሪዎችን ለማበረታታት ከሜዳሊያና ገንዘብ በተጨማሪ የትጥቅ ሽልማትም ተበርክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራው ገብሬ፣ ሶፊ ማልት በራሱ ተነሳሽነት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ቤት ወርዶ አትሌቲክስ ላይ በመስራቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በአትሌቲክሱ እየተከናወነ ያለው ሥራ ለውጤታማነት እገዛ እያደረገም ነው፡፡ ተተኪዎች እና ማዘውተርያ ስፍራዎች የሚገኙበትን ትምህርት ቤት በመምረጥ እና የስፖርት ሳይንስ መምህራንን አሰልጥኖ ተማሪዎቹ የወሰዱትን ስልጠና በውድድር እንዲመዘኑም ያስችላል፡፡ የሚሰጠው የማበረታቻ ሽልማትም ተማሪዎች ወደ አትሌቲክስ ስፖርት እንዲሳቡ እንዳደረገና አትሌቲክሱን ለማሳደግ በቀጣይ ከሶፊ ማልት ጋር በመሆን ተተኪ አትሌቶችን ከትምህርት ቤት ለማውጣት፤ መሥራት የሚገባቸውን ጉዳዮች በመነጋገር እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

ሶፊ ማልት የስፖርትን ባህል በትምህርት ቤት ለማዳበርና ለተማሪዎች የውድድር እድልን ለመፍጠር ታስቦ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ተማሪዎቹ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ለአራት ሳምንታት ልምምድ በማድረግም ውድድራቸውን አካሂደዋል። ከዚህም በተጨማሪ የተማሪዎችን ጤናማ የአኗኗር ዘዴን ለመደገፍና እርስበርስ እንዲግባቡ፣ በራስ የመተማመን ብቃታቸውን እንዲገነቡና ጠንካራ አትሌት በመሆን እንዲያድጉ ያስችላል፡፡ ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ከታች የሚመጡት ታዳጊ አትሌቶች ላይ እንዴት መሠራት እንዳለበት የሚጠቁም አቅጣጫ ይዞ በመሥራት ላይ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You