ከሚሳመው ተራራ ስር

ተራራ ሲሳል እንጂ ሲሳም ተመልክተን ይሆን? አጃኢብ ነው! ድጉስ ልውስ የመጽሐፍ ጥበብ፤ ተራራ ሊያስመን ወዷል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጠፍቶ የከረመው እውቁ ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፤ እጅ ከምን ሲባል…”የሚሳም ተራራ” ከተሰኘ መጽሐፉ ጋር እጅ ነስቶ እጅ መንሻ ይዞ ቀርቧል። ደራሲው ከዚህ ቀደምም የሚጽፋቸው መጻሕፍት ርዕሶች ለየትና ጥፍጥ ያሉ ቢሆኑም የአሁኑ ተራራ የመሳም ጉዳይ ግን እረቀቅ ሰበቅ፤ ጠበቅ ያለ ይመስላል።

ውስጣቸውን ገልጠን ሳናገላብጥ ርዕሶች ብዙ ሊናገሩ ይችላሉ። ላዩን በመመልከት ብቻም የመጽሐፉን ይዘት ለመገመት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ቀለል ያደርጉልናል። ይህን ተራራ መገመት ግን ተራራ እንደ መውጣት ፈታኝ ነው። በትልቁ ገምተን በትንሹ ልክ ላንሆንም እንችላለን። ደራሲው ከ“ሚሳም ተራራ” ትዝታን በጭልፋ ብሎናል። ፍቅረማርቆስ ከተራራው አናት ላይ ተቀምጦ የራሱን ግለታሪክ ሊነግረን ሽቷል።

መጽሐፉን ለማንበብ ስናቀረቅር የምናውቀውን ይህን ሰው እንደማናውቀው እናውቃለን። እናም፤ “የሚሳም ተራራ” ከሰሞኑ ለ6ኛ ጊዜ ተመርቆ ነበር። ይሄም ሌላ አጃኢብ ነው። 6ኛ ዙር የመሆኑ ምክንያት ከዚህ ቀደም አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ አምስት የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ በመመረቁ ነው። የተራራው መጽሐፍ ገና ጉዞ ከመጀመሩ ብዙ ክብረ ወሰኖችን እየሰባበረ ከአማዞን የመጻሕፍት ዓለም ደርሷል። ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ መጽሐፍ መደብር በሆነው አማዞን ውስጥ፤ “የሚሳም ተራራ” ለአራት ተከታታይ ሳምንታት ያህል የአፍሪካን የሥነ- ጽሑፍ ሽያጭ በአንደኝነት ሲመራ ቆይቷል።

የምረቃው ዝግጅት ባህር ማዶ ዞሮ እስኪመጣ ድረስ ጥቂት ወራትን ቢፈጅም፤ የመጽሐፉ ሽያጭ ግን እዚህም ተጧጡፎ ነበር። ከተራራው ስር ወርቅ የተገኘበት ያህል፤ እጅግ በሚያስገርም መልኩ አንባቢው ሁሉ ይህን መጽሐፍ ከእጁ ለማስገባት ሲሽቀዳደም ነበር ለማለት ያስችላል። የአንዳንዶቹንም፤ የተቆለፈውን የንባብ ፍላጎት የከፈተም ጭምር ነው።

ተራራው ምንስ ቢኖረው ይሆን እንዲህ መፈለጉ፤ መወደድና መላመዱ? ርግጥ ነው ደስ የሚል፤ የተለየ ዓለምና መንገድ አለው። በዚህች የሰናፍጭ ቅንጣት በምታህለው ጽሑፍ ውስጥም፤ ይህን መንገድ ለመጠቆም ያህል እንጂ ለማሳየት እንኳን የማይሆን ነው። ፍቅረማርቆስ ደስታ ማለት…ተብሎ ለአንባቢያንም ሆነ ለሥነ ጽሑፍ ወዳጆች መናገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው። እርሱና ሥራዎቹ ከማንም ልብ ውስጥ የሚደበዝዙም፤ የሚበልዙም አይደሉም። እናም፤ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ስነሳ አንዲት ጥያቄ ከምናቤ ሽው አለችብኝ፤ “የሚሳም ተራራ” ገና ከመድረሱ የአንባቢውን ልብ መበጠሱ፤ ከመጽሐፉ ሳይሆን ከፀሐፊው ተራራነት የተነሳ ይሆን እንዴ? የሚል ነበረ። ከሌላው በበለጠ፤ ስለሚያውቁትና ስለሚያደንቁት ሰው ግለ ታሪክ ማንበብ፤ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር መሆኑ አይካድም። የዚህ መጽሐፍ ደራሲም፤ በቀደሙት ሥራዎቹ የምናደንቀውና አብዝተን የምንወደው ታላቅ ደራሲ እንደመሆኑ፤ እርሱ ግን ታይታን የሚፈልግም ሆነ የአደባባይ ሰው አልነበረም። ስለዚህም፤ ግለ ታሪኩን ለማንበብና ይበልጥ ስለእርሱ ለማወቅ የማንፈልግበት ምክንያት አይኖርም።

በጥያቄዬ ውስጥ ያገኘሁት ከፊል እውነታ ይህ ቢሆንም፤ ተራራውን የመሳም ሽሚያ የታየበት ትልቁ እውነታ ግን በዚህ ብቻ የመጣ አይደለም። ከምንም ነገር በላይ፤ ከተራራው አናት ላይ የተለኮሰው ሥነ ጽሑፋዊ ችቦ፤ በኃይለኛው የበራበት በመሆኑ ነው። ምናልባትም፤ እስከዛሬ ድረስ ከመጻሕፍት እርቆ የቆይበትን ጥርቅም የብዕር ጉልበት ያፈሰሰበትም ይመስላል። ውስጣዊ አየር ከሚማግበት ተራራ ላይ ቁጭ ብሎ ብዙ የተራቀቀበትና ለሥነ ጽሑፉ አንባቢ አዲስ ፍኖት ለመሆን ያሰበበትም ጭምር መስሎ ይታያል። በግለ ታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ሊደፈሩ የማይችሉ፤ ግዙፍ ተራሮችን ንዶ ያሳየበት ፈር ቀዳጅ መጽሐፍ ሆኖ ተገኝቷል።

“የሚሳም ተራራ” እንዴትስ ያለ ስንግ ነው? መጽሐፉ፤ የአንድ ሰው ግለ ታሪክን የያዘ ነው። ግለ ታሪኩም በልቦለዳዊ የአቀራረብና የትረካ ሚዛን ውስጥ የሚመዘን፤ በእውነተኛ የሕይወት ምላጭ የተከመከመ ግለ ታሪካዊ ልቦለድ ነው። ባለታሪኩም፤ እራሱ ደራሲው ነው። እስከዛሬ ድረስ ብዙ ግለ ታሪካዊ መጻሕፍትን ያነበብን ቢሆንም፤ ይህን መጽሐፍ ባነበብን ጊዜ ግን፤ ደራሲውን በተለየ እይታ ለመመልከት እንገደዳለን። የዚህ ምክንያት ደግሞ፤ ባለታሪኩ አስቀድሞ ታሪኩን ለማስቀመጥ የወሰነበት እይታና ያቀረበበት መንገድ ነው።

ከተለመደው ታሪክ አሰናሰን ወጣ ብሎ ራሱን በአዲስ የነፃነት ጎዳና ውስጥ አረማምዶበታል። የአንባቢው ስሜት፤ መጽሐፉን ገልጦ ከማንበብ በመጀመር፤ ጨርሶም እስከ መክደን ድረስ ብቻ የሚዘልቅ አይደለም። ከጨረሱ ወዲያ የሚጀመር ሌላ ምናባዊ ጥያቄና መልስ የያዘ፤ ከራስ ዓለም ጋር የሚታገሉት ሀሳባዊ መንገድ አይጠፋም። የባለታሪኩን እንቆቅልሾች፤ ምላሹን እንድንፈልግ ይገፋፋናል። የሚሰጠን እጅግ ብዙ ነው፤ ሥነ ልቦናዊ፣ ሥነ አዕምሯዊ፣ ማህበራዊና ሰብዓዊ ማንነታችንን የሚገነቡ ሙሌቶችን የያዘ ነው።

ደራሲውን በልዩነት እንድንመለከተው ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ፤ ታሪኩን ያቀረበው ለማያውቀው አንባቢ ሳይሆን ከጭንቅላቱ እያወጣ በልቡ የሚያመላልስና ለራሱ የሚናገር ዓይነት አድርጎ ማቅረቡ ነው። የሆነውን ነገር እንደሆነው ብቻ በማድረግ እውነትን አክብሮ ግልጸኝነትን አንግሶበታል። ብዙውን ጊዜ የግለ ታሪክ ፀሐፊያንን እያዳለጥ ከሚጥላቸው ነገር አንደኛው፤ ታሪኩ ውስጥ አንዳችም ባዕድ ነገር ሳይጨምሩና የነበረውንም ሳይቀንሱ እንደወረደ ማስቀመጡ ላይ ነው። አንባቢና ማህበረሰቡ ከሚያውቀው ማንነቱ ጋር የማይሄድ ሆኖ ያገኘውን ታሪክ መግደፍ ይኖራል። ባለታሪኩን ተወዳጅ በማድረግ በአንባቢው ልብ ውስጥ ስፍራ እንዲኖረው በማሰብ ደግሞ እውነት ያልሆኑ ተጨማሪ ቅመሞች ይጨማመሩበታል።

አርዕስቶች … “ስር የሌላት አድናቆት” በዚህ ስር በምናገኘው ታሪክና የባለታሪኮቹ ውስጥ ማንነት ከራስ አልፎ፤ ኩራትም ክብርም ከሆነው ኢትዮጵያዊው እኛነታችን ጋር የምንፋጠጥበትም ጭምር ነው። ደራሲው ከሀገር ወጥቶ በውጭ ይኖር በነበረበት ወቅት የገጡሙት ጉዳዮች ናቸው። አንደኛው ጉዳይም፤ ከቀድሞው የትዳር አጋሩ ጋር ድንገት የተገናኙበት አጋጣሚ ላይ “እውነት ትንፋሿ ቆሞ ሞተችብኝ። ” ሲል ይገልጸዋል።

እዚህ ተራራ ላይ፤ ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሊህቃን ወጥተው ወርደው ምልከታዊ ቅኝቶቻቸውን አኑረውበታል። በአምስቱ የአሜሪካ ግዛቶች የተካሄዱትን የምረቃ ሥነ ሥርዓቶችን ጨምሮ፤ በሁሉም መድረኮች ውዳሴን ችረውታል። በርካታ የጥበብ አፍቃሪያን እየተገኙም፤ አድናቆታቸውን ገልጸውለታል። መጽሐፉ ከአንባቢያን እጅ በገባ ቁጥር፤ ሁሉም ነገሮች የሙቀት መጠናቸው ከፍ እያለ መሄዱ አልቀረም። ከዚህ የተነሳም፤ ከፊተኛው የኋላኛው፤ ከመጀመሪያው ይልቅም የሁለተኛው እያለ መድረኩ ደማቅ እየሆነ ቀጥሏል። ምንም ይሁን ምን፤ የአዲስ አበባው ግን ከሁሉ የላቀው ስለመሆኑ ጥርጥር አይኖረውም። እዚያ መድረክ ላይስ ምን ተፈጠረ…

በምረቃው ዕለት፤ ስለ መጽሐፉ ጠለቅ ያለ ሙያዊ አስተያየታቸውን ካቀረቡ ሁለት ሰዎች መሀከል አንደኛው የቲያትር ጠበብቱ፤ ነብዩ ባዬ ነበር። የቲያትር ባለሙያ እንደመሆን የመጽሐፉን ግምገማ የጀመረበትን ነጥብ፤ ሙያዊ ዕውቀቱ ከሸለመው የገጸ ባህሪያትና የትረካው ቅጠል ላይ ነበር። “የመጀመሪያ የሪፍሌክሽን መንገድ፤ ከመጽሐፉ መግቢያ ጋር አያይዤ የሳበኝን ጉዳይ መፈለግ ነበር። የቲያትር ተማሪ እንደመሆኔ የመድረክ ትርኢት፤ ባለ አምስት ገቢር፤ ዓለም የቲያትር መድረክ ናት፤ ዊሊያም ሼክስፒር፤ ትወና…የሚሉት ቃላት፤ በመጽሐፉ መግቢያ አብይ የመተረኪያ ስፍራን ይዘው ተቀምጠዋል። ስለዚህ ይሄ ነገር አንድ ቲያትራዊ መስብ ነበረው።

በሁለተኛ ደረጃም ባለ አምስት ገቢር ነው ያለውም እውነት ነው፤ እውቂያ አለው። ውጤት የምንለው እንቅስቃሴ አለው። ጡዘትንም የያዘ ነው ሲሆን ዝቅጠትና መፍትሔ የምንላቸውን ጨምሮ አምስቱም ይገኙበታል። መጽሐፉ የሕይወት ታሪክ ነው ተብሏል፤ ታዲያ የሕይወት ታሪክ እውን አለው? አዎን አለው፤ አለው ለማለት እንዲቻል እውንና ክውንን፤ እውንና ምናብን ለማቆራኘት ብዙ ጥረት ተደርጎበታል። ይህ ጥረት ደራሲው፤ “ዓለም የቲያትር መድረክ ናት፤ እኔም ተዋናይ ነኝ” እንዳለውም ሊሆን ይችላል አልኩ። ከዚያ ደግሞ እንደገና ይህ ፀሐፊ፤ በእውነት የገጠመውን ነገር ተውኔት ነው ብሎ ያለው፤ ዲስክሌመር እየሰጠን ነው እንዴ? ብዬ አልኩኝ።

ከዚያ በኋላ ግን እኚህን ሁሉ የሚያስተው አንድ ነገር አገኘሁኝ። ይሄውም ምን ይላል፤ “ትወናዬንና መድረኬን ተመልከቱት” የሚል ነው። እዚህ ጋር ተለያየን፤ በመጽሐፉ የሚገኘው ተዋናይ አይደለም። በአሰሳዬም ተዋናይ ሳይሆን ገጸ ባህሪ ነው ያገኘሁት። …ልብ የሚሰብር አቀንቃኝ ገጸ ባህሪ… ስለዚህ ከቲያትር ቀመስ መግቢያው በመሸሽ፤ በአጠቃላይ መጽሐፉን በሦስት ነገሮች ከፋፍዬ ተመለከትኩት። የመጀመሪያው፤ ከሚሳመው ተራራ ወዲያ። ሁለተኛ በሚሳመው ተራራ ላይ። ሦስተኛው ከሚሳመው ተራራ ወዲህ፤ የሚሉ ናቸው…” በማለት የመጽሐፉን ግራ ቀኝ እያገላበጠና ከብዙ እይታዎች እያያዘ አስቀምጦታል።

ደራሲው፤ ከተራራው በስተጀርባ የተከለሉትን ዜጎች በማሳየት ደረጃ ወደር አልባም ነው፤ የሚል ሃሳቡን አጋርቷል። ይህን ሲል፤ የደራሲውን ሌሎች መጻሕፍቶችንም ያስታውሰናል። “ከቡስካ በስተጀርባ”፤ “ኢቫንጋዲ”፤ “የዘርሴዎች ፍቅር” ለዘመናት ያልተመለከትነውን ውበትና ፍቅር ያሳዩን መጻሕፍቶቹ ናቸው። እነዚህን መጻሕፍት ተከትሎም፤ የተለያዩ የፊልምና የሙዚቃ ሥራዎች ተሠርተዋል። ነብዩ ባዬ እንዳለውም፤ የዘር ዓይነ ጥላችንን የገፈፉም ጭምር ናቸው።

ሌላኛው ምልከታ፤ ከውጫዊ ፍራቻና ስጋቶች ነፃ ሆኖ በነፃነት ጎዳና ላይ መንፏለሉ ነው። ደራሲው ታሪኩን ለማስፈር ብዕሩን በጨበጠ ቁጥር፤ ቅድሚያ እራሱን በነፃ ዓለም ውስጥ አድርጓል። ልቡ ከምን ይሉኛል ስሜት ውስጥ ለመዘፈቅ አንዳንችም ሃሳብ የገባው አይመስልም። ምክንያቱም ደግሞ፤ ይህን ሰው ቢሰማው ለኔ ያለውን አመለካከት ይቀይረዋል በማለት ስጋት የሚያጭሩብን ግላዊ የሆኑ ነገሮችን እንኳን ያለ ምንም ሰቀቀን፤ ፊት ለፊት ግልጥልጥ አድርጎ ይነግረናል። እውነትና ግልጸኝነት፤ ማንም ተመልካች እንደሌለው ሰው እራቁታቸውን ቆመዋል። ገጾቹን እየገለጥን ባነበብን ቁጥር ይበልጥ ይህን እየተረዳንና እየተገረምን እንሄዳለን።

ከአንዳንዱ ቦታ ስንደርስ፤ ለብዙኃኑ አንባቢ የተጻፈ መጽሐፍ ሳይሆን፤ በሚስጥር የተሸፋፈነ የግል ማስታወሻ መስሎም ይሰማናል። አንድ ደራሲ፤ በፈጠራ ልቦልድ ውስጥ እንዳሻው እስከ ጥግ ድረስ ተጉዞ የገጸ ባህሪያቱን ማንነትና ሚስጥሮች በግልጽ ሊነግረን ይችላል። በግለ ታሪክ ውስጥ ግን ሚስጥራዊ እውነትና ነፃነት፤ እንደ ራስ ዳሽን ተራራ ተቆልለው የሚታዩ ከባድ ነገሮች ናቸው።

ደራሲው እውነትን መለመሏን ለማቆም ለምንስ ፈለገ? “ከተሰጠኝ ጥበብ ብዙ እርቄ ወደ ልቦናዬ ስመለስ፤ በብዙ ወዳጆቼ ጉትጎታ ግለ ታሪኬን ለመጻፍ ወሰንኩ። ይህንን ለመጻፍ ስነሳም፤ የመጽሐፎቼን ቁጥር ከፍ በማድረግ ዝናን ለማካበት አይደለም። የተለየ ጥቅማጥቅም አስቤም አይደለም። እናም ግለ ታሪኬን፤ ከሆነውና ከደረሰብኝ አንዳችም ሳልጨምርና ሳልቀንስ፤ ብዙዎች የሚፈሯትን እውነት ላቆማት ፈለኩኝ። ትልቁ ነገር በኔ ውድቀት ሌሎች እንዲማሩ ስለምፈልግ እንጂ ስለስኬቴ ስል አልጻፍኩትም” በማለት ነበር ያስረዳው።

እውነትን በዚህ ልክ ፈልጎ ማግኘት፤ ከእልፍ እጆች መሀከል የምትገኝ አንዲት ጣት ናት። በዚህ ልክ ከእውነት ጋር ለመቆም፤ የተለየ መባረክና መታደል ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል። ብዙ ግለ ታሪክ ፀሐፊያን የሚወድቁበትን ሜዳ፤ ፍቅር ማርቆስ ደስታ በዚህ መጽሐፉ በድል ከማለፉም፤ ቦርቆበታል ለማለት ይቻላል።

ብዙውን ጊዜ፤ የግለ ታሪክ ፀሐፊያኑ የሚወድቁት ስፍራም ይሄው ግለ ፈጠራዎችን ሸሽቶ ማምለጥና እውነትን በቁሟ ማቆሙ ላይ ነው። እውነትን ከውሸት ጋር ለማስታረቅ የሚሹበት፤ ምናልባትም በዋናነት ሁለት ጉዳዮችን ለመጥቀስ እንችላለን። የመጀመሪያው ነገር፤ ሚስጥር የምንላቸውን ግላዊ ጉዳዮችን ሌሎች እንዳያውቁትና በይሉኝታ ነፃነትን በማጣት ነው። በዚህ ስሜት የተሸበበ ደራሲ፤ ማወቅ የሚገባንን ብዙ እውነታዎች ይደብቅብናል። ከዚህም የከፋውና ሁለተኛው ደግሞ፤ መጽሐፉንንና ባለታሪኩን በሌላው የውሸት ማንነት ልዩና ተወዳጅ በማድረግ በግላዊ ምኞት አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ነው። ለምሳሌ፤ ታሪኩን እንደወረደ ከማቅረብ ይልቅ፤ እጅግ አስደናቂና አነጋጋሪ የሆኑ የፈጠራ ታሪኮችን በየመሀሉ በመሰግሰግ፤ አንባቢውን አጃኢብ ማስባል ነው። ይህ ደግሞ መጽሐፉን ተወዳጅና ተፈላጊ እንዲሆን፤ ፀሐፊውም ዝናን ከገንዘብ ለማጋበስ ይረዳዋል። ፀሐፊው የፈለገው ይህን ከሆነ፤ በፈጠራ ልቦለድ ሊያደርገው አይችልም ወይ? ካልን ምላሹ አንድና አንድ ነው፤ ይሄውም ከፈጠራ ታሪክ ይልቅ አንባቢውን ሊስበውና ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ሊያደርገው የሚችለው እውነተኛና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ነው።

“የሚሳም ተራራ”ን እንድንወደው የሚያደርግን ሌላኛው ቁመናው፤ በሥነ ጽሑፍ የስበት ሕግ ላይ መሠረቱን መጣሉ ነው። ተራራው በሌሎች ትናንሽ ተራራዎች ተከፋፍሎ፤ በስሩ በርካታ አርዕስቶችን አጭቆ የያዘ ቢሆንም፤ በታሪክ ፍሰቱ ምንም ዓይነት ድግግሞሽ አንመለከትበትም። እያንዳንዱ ታሪክ እጥር ምጥን ባለ መንገድ ተቀምጧል። ምንም ዓይነት አሰልቺነት እንዳይታይባቸው በጥንቃቄ ሰፍረዋል።

ከአንዱ ታሪክ ወደሌላው እያንደረደረ በፍጥነት ከማሸጋገሩም፤ ለንባብ የሚገፋፋ የአንባቢውን ቀልብ የሚስብ ማድረጉ ነው። በውስጡ የተካተቱት ታሪኮች፤ ውስጣችንን ሰቅዘው የሚይዙ ከመሆናቸውም፤ በስተመጨረሻ በጥያቄና በቁጭት በሀዘንና በመሰል ስሜቶች ጠፍሮ የሚይዙ፤ ገልጠው አንብበው ዘግተው የማይጨርሱት የራስ ጥላ የሆነ መጽሐፍ ነው። “ትንሿ መልአክ” ከሚለው ትንሽዬ ተራራ ስር ባለው ታሪክ ውስጥ ንጹህና ደጓ፤ መልከ መልካም ኢትዮጵያዊት… ወፊቷ ልብን የምትሰብር የልብ እንባ ናት። ከዚያ ስንሆን ብዙ እናያለን።

ከሰቆቃው ወዲያ፤ ከሀዘን ውስጥም ደስ የሚል ስቃይ አለ። ከእሾህ ላይ ጽጌረዳ፤ ከተራራው ማዶም መንገድ አለ። ከስሩም የጥበብ ምንጭ። ሁላችሁም ይህንን ተራራ ያዙ። ከስሩም ተቀምጣችሁ እዩት፤ ገልጣችሁም አንብቡት።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You