ለሰባት ሰዓታት ያህል (ከ2፡40 እስከ 9፡30) በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ግቢ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ብዙ ነገር ሳስተውል ውያለሁ፡፡ የሰልፉን ርዝመት፣ የሰዎችን ሕግና ደንብ ማክበር አለመላመድ…. በአጠቃላይ የነበረውን አሰልቺ የግቢው ውስጥ ወከባ ባለፈው ቅዳሜ ትዝብታችን አይተናል፡፡ ‹‹የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል›› እንዲሉ በእንዲህ አይነት ቦታዎች ላይ የማጭበርበር አይነቶች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው፡፡ በዚያን ዕለት ያስተዋልኩትን የማጭበርበር አይነት ለማጋራት ወደድኩ።
የፓስፖርት አሻራና ፎቶ ለመስጠት የነበረው ሰልፍ ቀጥ ያለ ሳይሆን የተወለካከፈ ነበር፡፡ ሕንጻዎችንና መንገዶችን ሁሉ እያቋረጠ የሚቀጣጠል ስለሆነ በየቦታው ስብራቶች አሉት፡፡ ስለዚህ በየመታጠፊያው ‹‹የፓስፖርት አሻራ ሰልፍ ነው?›› እያሉ መጠየቅ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም የሌላ ጉዳይ ሰልፍም ሊኖር ይችላል፡፡
ለማረጋገጥ በየመታጠፊያው ይህን እየጠየቅኩ መጨረሻው አካባቢ ደረስኩ፡፡ መጨረሻው አካባቢ ያሉትን ስጠይቅ፤ አንድ የባንክ ሠራተኞች የሚለብሱትን አይነት አለባበስ የለበሰ፣ ከወጣትነት ይልቅ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚሆን ሰው ‹‹አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ነው?›› አለኝ፡፡ ‹‹አዎ!›› አልኩት፡፡ መሰለፍ ያለብኝን ቦታ አሳየኝና ተሰለፍኩ፡፡ ‹‹ባለጉዳይ ነው ወይስ አስተባባሪ ነገር!›› እያልኩ በውስጤ ሳሰላስል፤ ሌላ ከፊት ካሉ ሰልፈኞች ጋር ሥራ የሚሰራ የሚመስል ተመሳሳይ አለባበስ የለበሰ ባልደረባውን ‹‹እነዚህን አስሞላኻቸው?›› አለው፡፡ ተጠያቂውም ልክ በሥራ የተወጠረ (ቢዚ የሆነ) በሚመስል ስሜት ‹‹አዎ! አዎ!›› አለው፡፡
ሰልፉ እጅግ በጣም ረጅምና አሰልቺ ከመሆኑ የተነሳ አሰራሩን ለማፋጠን ከአሻራ በፊት አንዳንድ መፈጸም ያለባቸውን ጉዳዮች (ምናልባት ካሉ) ለማስጨረስ በሚል የተቋሙ አሰራር አካል ነው ብዬ አሰብኩ፤ ወይም በየቦታው የምናየው የተለመደው የባንክ ሰራተኞች ‹‹አካውንት ክፈቱ፣ ይህን አገልግሎት ክፈቱ…›› ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡
እንዲሰለፍ የጠቆመኝ የባንክ ሰራተኛ መሳይ መጣና መጀመሪያ ስልኬን ጠየቀኝ፤ ነገርኩት፡፡ የምነግረውን የሚጽፈው ስልኩ ላይ ነው፡፡ የሚጽፍበት ቦታ (ስፔስ) የሆነ ነገር በኦንላይን ስንሞላ ያለውን አይነት ቅጽ ያለው ነው፤ ምን እንደሚል ግን ማንበብ አልቻልኩም። ቀጥሎ የኔን ስም፣ የአባቴንና አያቴን እየጠየቀኝ ሞላ፡፡ እስከዚህ ድረስ ‹‹ተገላገልኩ!›› በሚል የደስታ ስሜት ነበር እየነገርኩት የነበረው፡፡ ምክንያቱም አሰራሩን ለማፋጠን የሚደረግ ነው የመሰለኝ፡፡
ቀጥሎ የእናቴን ስም ጠየቀኝ፡፡ አሁን ነገሩ አላማረኝም፡፡ የተቋሙ የአሰራር አካል አልመስልህ አለኝ። አሞላሉንም እየተጠራጠርኩት መጣሁ፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ሲሞላ የፊደል አጻጻፍ (Spelling) ይጠየቃል፤ እሱ ግን አልጠየቀኝም፡፡ የሰው ስም አጻጻፍ ደግሞ እንግሊዘኛ የማወቅ ብቃት ስላለ ብቻ የሚቻል አይደለም፡፡ ለምሳሌ፤ ዋለልኝ የሚለውን የእንግሊዘኛ አጻጻፍ ብዙዎች በትክክል አይጽፉትም፡፡
ይህን እያሰብኩ የእናቴን ስም ለማረጋገጫ ነገርኩት፡፡ ምክንያቱም የእናቴ ስም ጥምር ቃል ስለሆነ በተመዘገብኩባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ለማረጋገጥ ደጋግመው ይጠይቁኛል፡፡ በተለይ በእንግሊዝኛ ሲሆን ራሴ እንድጽፈው ወይም የጻፉትን አይቼ እንዳረጋግጥ ያደርጉኛል፡፡ ይህ ሰው ግን የእናቴን ስም ስነግረው ልክ እንደሚያውቃት ሁሉ ለማረጋገጥ ሳይጠይቀኝ ስልኩ ላይ ጻፈ፡፡ ዓላማው ፎርም እየሞላ ማስመሰል ነበር ማለት ነው፡፡
እስከዚህ ድረስ በነገርኩት መረጃዎች ምንም የሚፈጠር ነገር እንደማይኖር ስላወቅኩ (የነገርኩት መረጃዎች ምሥጢራዊ ሳይሆኑ ከየትም የሚገኙ ናቸው) ከዚህ በኋላ ያሉትን በጥንቃቄ መከታተል አስቤያለሁ። ‹‹ዞር በል!›› ካልኩት ደግሞ የሰውየውን ዓላማ ለማወቅ ስለማያስችለኝ እኔም የተሸወድኩ መስዬ መከታተል ጀመርኩ፡፡
ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ ስልኬን እንድሰጠው ጠየቀኝ፡፡ እንኳን እንዲህ አይነት ቦታ ላይ ቅርንጫፍ ላይ እንኳን ቁጥሩን እንጂ ስልክ የሚቀበሉበት (ከእጅ ላይ) አሰራር በጣም አልፎ አልፎ መሆኑን ስለማውቅ፣ መስጠት እንደሌለብኝ ባምንም የተሸወድኩ መምሰል ፈልጌያለሁ፡፡ ግራ የገባኝ በመምሰል ‹‹ግን ለምንድነው?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡ የነገረኝን ምክንያት በኋላ ስደርስበት በፍጹም የሌለ አሰራር ነው፡፡ ‹‹በሞባይል ባንኪንግ የሚከፈል ክፍያ አለ፤ ስትጨርሱ እዚያ ጋ ትከፍላላችሁ›› ብሎ የሆነ አነስተኛ ሰልፍ ያለበት ቦታ ጠቆመኝ፡፡ ያ ቦታ በኋላ ሳረጋግጥ አስቸኳይ ፓስፖርት ለሚያወጡ ሰዎች እንጂ ከእኔ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡
እኔም እንደ መደበሪያ አደረኩት መሰለኝ በመሃል በመሃል ስለሰልፉ እርዝመት እያወራሁ፣ ‹‹እንዲያው እስከ ስንት ሰዓት እንጨርስ ይሆን?›› እያልኩ ትኩረቴ ሰልፉ ላይ ብቻ እንዲመስል አደረኩ፡፡ ‹‹ግን እኮ ሞባይል ባንኪንግ እጠቀማለሁ፣ ቴሌብርም እጠቀማለሁ..›› አልኩት፡፡ ‹‹አክቲቭ›› የሚደረግ ነገር እንዳለ ነገረኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ቆይታችን ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ስልኬን እንደማልሰጠው ከሁኔታዬ አረጋገጠ መሰለኝ ስልኩን እየነካካ ወደኋላዬ ወዳለው ሰልፍ አለፈ፡፡
ይህኔ ከኋላዬ ያሉትን ሰዎች ከእናንተ ፊት ነኝ ብዬ፤ ከፊቴ ያሉትንም ከእናንተ ቀጥዬ ነኝ ብዬ መኖሬን አሳውቄ ወደ በሩ አካባቢ ፖሊስ ፍለጋ ሄድኩ፡፡ ሰውየውን ለማስያዝ ብቻ ሳይሆን ‹‹እንዲህ አይነት አሰራር አላችሁ ወይስ አጭበርባሪዎች ናቸው?›› ብዬ ለመጠየቅ ነው፡፡ በሩ አካባቢ ስደርስ ግን አንድ እንኳን ነፃ ፖሊስ ወይም አስተባባሪ የለም፤ ሁሉም የተዋከበ እና ከሰዎች ጋር የሚዳረቅ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መጠየቅ እንደማይቻል ሳውቅ ወደ ሰልፌ ተመለስኩ፡፡
‹‹ባንኮች እንዲህ አይነት አሰራር አላቸው ወይ?›› የሚለውን ለማወቅ ባንክ የሚሰራ አንድ ጓደኛዬን ጠየቅኩት፡፡ ከሰውየው ጋር የነበረንን የመረጃ ልውውጥና ሁኔታ ስነግረው ‹‹ሲቢኢ ብር›› የሚባለውን የንግድ ባንክ አሰራር አይነት የሚመስል ሙከራ ቢኖረውም በፍጹም የባንኩ ሠራተኞች አሰራር አይደለም፡፡ ስልክ ቁጥርን እንጂ ስልክን መቀበል በፍጹም አይቻልም፤ አስፈላጊ ከሆነም ቅርንጫፍ ላይ ብቻ ነው፡፡ ሙከራው በጣም የሚያስነቃ የማጭበርበር አይነት መሆኑን ከነገረኝ በኋላ ብዙ የዚህ አይነት ገጠመኞችን ነገሮኛል፡፡ አንዱን ገጠመኝ ልጥቀስ፡፡
አንዱ አጭበርባሪ ከአንዲት ሴትዮ ዕቃ የሚገዛ መስሎ ነው፡፡ ዋጋው ከ100 ሺህ ብር በላይ ነው። መጀመሪያ ስልኳን ተቀበለ፡፡ እሱ ግን የባንክ ሠራተኛ መስሎ ሳይሆን ስልኩ ሳንቲም የዘጋበት መስሎ ነው። ጓደኛው ጋ የሚደውል በመምሰል የራሱን ስልክ ቁጥር ስልኳ ላይ CBE ብሎ መዝግቦ ሰጣት፡፡ ከዚያም ሲከራከር ቆይቶ የተስማሙበትን ዋጋ ሊከፍል ስልኩን መነካከት ጀመረ፡፡ የእሱ ስልክ ከእሷ ስልክ ላይ በንግድ ባንክ ስም ተመዝግቧል፡፡ ብር ሲገባ የሚመጣውን መልዕክት (has been Credited) ጽፎ ያስቀመጠውን መልዕክት የብሩን መጠን አስተካክሎ ላከላት፡፡ በአንዳንድ ቅጽበቶች ልብ የማይባሉ ነገሮች አሉና (ቀሪ ሂሳብም አላየችም) ተጭበረበረች ማለት ነው፡፡
እኔን ያገጠመኝ ሰውዬ ሊያደርግ የነበረው ከአካውንቴ ላይ ብር ማስተላለፍ መሰለኝ፡፡ ተቀናሽ መሆኑን የሚያሳውቀውን የባንኩን መልዕክት ስልኬን ከመስጠቱ በፊት ሊያጠፋው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባንኩ መልዕክት ለመላክ ይዘገያል፤ ምናልባት ሰውዬው ቶሎ ከአካባቢው ይጠፋል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ስልክን ለመቀበል መጠየቁ የለየለት ማጭበርበር ነበር ማለት ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ለዚህ ዓላማ ሲሉ በር ላይ የሚታየውን አስፈላጊ ሰነዶች አሟልተው ገብተዋል ማለት ነው፡ ፡ እንዲህ አይነት አጭበርባሪዎች የመደበኛ አሰራሮችን ሥራ ያስተጓጉላሉ፤ መተማመን እንዳይኖር ያደርጋሉ፡፡ በእንዲህ አይነት ሰዎች ምክንያት ሁሉን ነገር ተጠራጣሪ መሆን የለብንም፤ ያም ሆኖ ግን ጥንቃቄና ሕጋዊነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2016 ዓ.ም