የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ለውጡ ከመጣ ወዲህ እንደ አዲስ የተዋቀረ ክልል ነው፡፡ በክልሉ የተለያዩ ማዕድናት፣ በማር፤ በቡና እና በቅመማ ቅመም በስፋት ይገኛሉ፡፡ ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀደም ብሎ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች አሁን ላይ በክልሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፤ እንዲሁም የሕዝብን ጥያቄዎች በመመለስ ሂደት ላይ ጫና መፍጠራቸው ይነገራል፡፡
ለአብነትም፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተፈለገው ልክ አለመኖር በክልሉ ሕዝብ በተደጋጋሚ የሚነሳ ቅሬታ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል የውሃ እና ማዕድን ቢሮ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን ኢንጂነር ፊልታሞ ዲብሎ አነጋግረናል፡፡ መልካም ንባብ፤
አዲስ ዘመን፡- የቢሮው የ2016 በጀት ዓመት ክንውን ካቀዳችሁት አንጻር በምን መልኩ የሚገለጽ ነው?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- ቢሮው ሁለት ዘርፍና ሁለት ተጠሪ ተቋማት አሉት፡፡ የመጀመሪያው የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳይኒቴሽ ዘርፍ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ የውሃ አስተዳደር ነው፡፡ በ2016 በጀት ዓመት በውሃ አስተዳደር ዘርፍ የተከናውኑ ተግባራትን ስንመለከት፤ በዘርፉ ሁለት ዳይሬክተሮች አሉት፡፡ አንደኛው የመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ሥራዎች የሚያከናውን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ሥራ የሚከውን ነው፡፡
በመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ዘርፍ ከተከናወኑ አብይ ተግባራት መካከል፣ የቦንጋ ከተማ ንፁህ የውሃ አቅርቦት አንዱ ነው፡፡ የቦንጋ ከተማ ንፁህ የውሃ መጠጥ አቅርቦት ችግር ያለበት ከተማ ነው። የመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ዘርፍ እንደ ቢሮ ከተቋቋመ በኋላ የከተማዋን የውሃ ችግር ለመፍታት የአጭር ጊዜ፤ የመካከለኛ ጊዜ እና የረጅም ጊዜ በሚል በሶስት ምዕራፎች አቅዶ እየሠራ ነው፡፡
ከረጅም ጊዜ እቅድ አኳያ የቦንጋ ከተማን የውሃ ችግር ሙሉ በሙሉ እና በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ከፌዴራል ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ሱፐርቪዥን ጋር የውል ስምምነት በመፈጸም ጥናቶችን አስጀምረናል። ከዚህ አኳያ በ2016 ዓ.ም ጥናቱን መቶ በመቶ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ነበር፡፡ የዘጠኝ ወር አፈጻጸሙ ደግሞ 50 በመቶ ነው፡፡
ከረጅም ጊዜ እቅድ አኳያ ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከል ሌላው የሚዛን አማን ከተማን የውሃ አቅርቦት ማሻሻል የሚል ነው፡፡ የሚዛን አማን ከተማን የውሃ አቅርቦት ማሻሻል ከዚህ ቀደም የነበረውን የዲዛይን ማሻሻያ ክለሳ ‹‹ሪቪው›› ሥራ ሰርተናል፡፡ የተሻሻለውን የዲዛይን ሥራ ሰነድ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ልከናል።
ምክንያቱም ይህ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፕሮጀክቱን የሚመጥን ሀብት አፈላልጎ እንዲመድብ ለማድረግ ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በተሰጠው የተሻሻለ ጥናት መሠረት ለፕሮጀክቱ ሀብት እያፈላለገ ነው፡፡ የተፈለገው ሀብት በተገኘ ጊዜ የሚዛን አማን ከተማን የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክትን ወደ ሥራ እናስገባለን፡፡
ሌላው በዚህ ዓመት ታቅዶ የነበረው ውሃን የማከም ሥራ ነው፡፡ ይህንንም መቶ በመቶ አከናውነናል፡፡ በቤሸኮ ‹‹የማዝ ፍሎራይድ ትሪትመንት›› የሚባለውም 76 በመቶ ተከናውኗል።
በመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳይኒቴሽን ዘርፍ 54 ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ነበር ያቀደው፡፡ በፕሮጀክቶቹ ስር የተለያዩ ፕሮግራሞች አሉ፡፡ እንደ ሀገር በዘላቂ የልማት ግቦች የሚሰሩ 14 ፕሮግራሞች አሉ፡፡ በክልል መንግሥት በጀት ምድቦች የሚሰሩ አምስት የገጠር ውሃ ተቋማት አሉ፡፡ በዚህ ዓመት እነዚህን ሥራዎች ጨርሰን 90 ሺህ የሚሆነውን ማህበረሰባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ፤ በዘጠኝ ወር ከ89 ሺህ 900 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በዚህም ክልሉን እንደ ክልል ስንረከብ የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅትን መስፈርት አሟልቶ የነበረው የንጹህ ውሃ መጠጥ ሽፋን 31 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በባለፈው ዓመት ብቻ 39 በመቶ ማድረስ ተችሏል።
ለማህበረሰባችን የንጹህ ውሃ ከማቅረብ በተጨማሪ በዘርፉ ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህም በዚህ ዓመት ለሦስት ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅደን በ9 ወራት ውስጥ ለሁለት ሺህ 500 ወጣቶች ጊዜያዊ እና ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ችለናል፡፡
በዚህ በኩል አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ያሉት በብድር ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቅቀው ወደ ሥራ በመግባት ብድሩን መመለስ አለባቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ለአራት የውሃ ፍሳሽ አገልግሎቶች የምዘና ደረጃ በመሥራት ወደ ሥራ ለማስገባት አቅደን ለሰባት ውሃ ፍሳሽ አገልግሎቶች የደረጃ ማሻሻያና ደረጃ ሰተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዓመት ከ89 ሺህ 900 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መደረጉን ገልጸዋል። በተጨባጭ የት እና በምን ያህል ገንዘብ የሚለውን ቢገልጹልን?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- በዚህ ዓመት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማግኘት ከቻሉ የክልላችን አካባቢዎች አንደኛው ተርጫ ነው፡፡ በተርጫ የንጹህ መጠጥ የውሃ ፕሮጀክት 268 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። ይሄንን ጨርሰን አስመርቀናል። በዚህም 24 ሺህ ሰዎችን የንጹህ ውሃ መጠጥ አገልግሎት ማግኘት ችለዋል፡፡
ሌላው ደግሞ ዋቻ የንጹህ መጠጥ የውሃ ፕሮጀክት ነው፡፡ ለዚህም 223 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ነው፡፡ ይህም 36 ሺህ ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው፡፡ በርግጥ አሁን ከተማዋ ላይ 36 ሺህ ሕዝብ የለም፡፡ ነገር ግን የከተማዋ እድገት ፈጣን ስለሆነ ፕሮጀክቱ በታሳቢነት 36ሺ ለሚሆን ሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ የተሰራ ነው፡፡
ሌላው በዚህ በተጨባጭ የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ መሆን የቻለው ደግሞ የቦንጋ ከተማ ነው፡፡ ከአጭር ጊዜ አንጻር በቦንጋ ከተማ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር ለማቃለል ‹‹የኢመርጀንሲ›› ሥራዎችን ስናከናውን ነበር፡፡ በዚህም ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት ነበር፡፡ ይህን ፕሮጀክት አጠናቀን አስረክበናል፡፡ በዚህም 13 ሺህ 200 የሚሆኑ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
‹‹ዋን ዋሽ›› ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር የተሰሩ እና ዘንድሮ ጀምረን ዘንድሮ የጨረስናቸው ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶችም በመጠናቀቃቸው ነው በድምሩ ከ89 ሺህ 900 በላይ የክልላችን ሕዝብ የንጹህ ውሃ መጠጥ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግንባታ ላይ ያሉ እና ለመገንባት በእቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን እንዴት ይገለጻሉ?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- በክልላችን በርካታ ግንባታቸው በሂደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች እና ለመገንባት በእቅድ ደረጃ የተያዙ አሉ። ግንባታቸው በሂደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል ዳውሮ ዞን የሚገኘው የላላ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በስኬት ፈንድ የሚሰራ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 74 በመቶ ነው፡፡ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚረዱ አብዛኛው እቃዎች ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ግማሹ እቃ ሞጆ ላይ ይገኛል፡፡ ግማሹም ሳይት ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል፡፡
ሌላው ግንባታቸው በሂደት ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀሰው በምዕራብ ኦሞ ላይ የሚገኘው ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህን ፕሮጀክት ዘንድሮ ለማጠናቀቅ እየሠራን ነው፡፡ አሁን ላይ ፕሮጀክቱ 92 በመቶ ያህል ሥራው ተጠናቋል፡፡
በዚህ ረገድ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፣ ከክልሉ በጀት ሲመደብ እኛ መሠረት የምናደርገው ሁለት ነገሮችን ታሳቢ አድርገን ነው፡፡ የመጀመሪያው የእኩል ተጠቃሚነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሁሉም የክልሉ ዜጎች ክልሉም ሆነ ሀገሪቱ ከምታመነጫቸው ሀብቶች እኩል ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ለማድረግ ይሰራል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በክልላችን አንዱ ከሌላው አንጻር በልማት በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረ ማህበረሰብ በመኖሩ ወደኋላ ለቀሩት የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በዚህም ምዕራብ ኦሞ አካባቢ የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እና በልማት ወደኋላ እንዳይቀሩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ብዙ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።
ከንጹህ መጠጥ ውሃ ጋር ተያይዞ በክልላችን ‹‹ኮዋሽ›› የሚባል ፕሮግራም አለ፡፡ ይህ ፕሮግራም ሁለት ወረዳና አንድ ዞን ይይዛል፡፡ ይሄ 40/60 በሆነ ፕሮግራም የፊሊላንድ መንግሥትና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ በመሆን የሚሰሩት ነው፡፡ 40 በመቶ ከፊሊላንድ መንግሥት፤ 60 በመቶ የሚሆነውን ወጪ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፍነው ነው፡፡ ከፊሊላንድ መንግሥት የሚመጣው ድጋፍ ለስልጠና የምንጠቀመው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጠውን ለኢንቨስትመንት እንጠቀመዋለን። በዚህ አንጻር በዚህ ዓመት 10 ለመሥራት አቅደን አምስቱ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ አምስቶቹም በተወሰነ ጊዜ ይጠናቀቃሉ፡፡
በ‹‹ኮዋሽ››ፕሮጀክት የፕሮጀክቶችን ጨረታ የሚያወጣው እና ሠራተኞችን የሚቀጥረው ህብረተሰቡ ነው፡፡ የኛ ሥራ የሚሆነው ‹‹ማች›› ወይም የወጪ መጋራትን ሥራ ማጠናቀቅ ነው። ማች ወይም ወጪ መጋራት ሥራ ማለት አንድን ፕሮጀክት ለመገንባት ይሄን ያህል ገንዘብ እኔ አለኝ፤ ቀሪ ይህን ያህል ገንዘብ ደግሞ ብትሰጡኝ አንድ ፕሮጀከት መገንባት እችላለሁ ብሎ የወጪ መጋራት የሚያስችል አቅም ነው፡፡
ከወጪ መጋራት በኋላ ያለውን ሥራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲከናወን ሲደረግ ብዙ ጥቅሞች አሉት። በተለይ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ችግርን በቀላሉ መፍታት ያስችላል፡፡ ህብረተሰቡ የኔ ነው ብሎ ከጀመረው ቀጣይነቱ የዛን ያህል ነው። ከጉልበት አኳያ ብንመለከትም በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት ወጪን ህብረተሰቡ በራሱ እንዲሸፍን ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ወደፊት ሁሉም ፕሮጀክቶች በዚህ መልኩ ቢከናወኑ አዋጭ ይሆናሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከነባሩ ደቡብ ክልል ጋር እንደ ቢሮ ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል የሀብት ክፍፍል ሂደቱ እንዴት ይገለጹታል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ማሽነሪዎች ስላልነበሩን በባለፈው ሁለት ዓመታት እንደቢሮ ሥራዎችን ለመሥራት ተቸግረን ነበር፡፡ ዘንድሮ የጥገና ማሽኖችን ከነባሩ ደቡብ ክልል በክፍፍል
ማግኘት ችለናል፡፡ ይህም ሞባይል ጋራዥ እና መሰል ሥራዎችን በቀላሉ እንድናከናውን አስችሎናል፡፡
ከሀብት ክፍፍሉ በፊት የቴፒን ሕዝብ ውሃ የምታጠጣው አንድ ጉድጓድ ብቻ ነበረች፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ በሀብት ክፍፍሉ ባገኘናቸው ማሽነሪዎች በመጠቀም ቴፒ ላይ ሶስት ተጨማሪ የውሃ ጉድጓዶችን መቆፈር ችለናል፡፡ ይህም ቴፒን ሕዝብ በአንድ ሴኮንድ ውስጥ ጊዜ 40 ሊትር ውሃ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበጀት እጥረት እንዳለበት ይታወቃል።ከዚህ አንጻር ማቺንግ ፈንድ ወይም ወጪ ማጋራት እንዴት ለመሸፈን አቅዳችኋል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- ክልሉ አዲስ የተደራጀ ክልል በመሆኑ የፋይናንስ ችግር አለበት፡፡ ያም ቢሆን ክልሉ የሚጠበቅበትን ማቺንግ ፈንድ እያዋጣ ነው፡፡ ነገር ግን ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች የሚጠበቅባቸውን እና የሚፈለገውን ያህል ማቺንግ ፈንድ ያለማዋጣት ችግር አለባቸው፡፡
ከወጪ መጋራቱ በተጨማሪ የኮንትራክተሮች የአቅም ውስንነት፤ የግንባታ እቃዎች መናር፤ የበጀት እጥረት፤ የውጭ ምንዛሬ ችግር፤ የኮንትራት መዘግየት ያጋጥማሉ፡፡ ይህም የሕዝባችንን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መፍታት እንዳንችል እክል እየፈጠረብን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቢሮው በቅንጅት ከመሥራት አንጻር ችግር እንዳለ ይነሳል። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያላችሁን የቅንጅት አሠራር እንዴት ይገልጹታል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- ቅንጅታዊ አሠራርን በሚመለከት ከፌዴራል ውሃና ኢነርጂ ጋር ጠንካራና ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ እነሱ ወርደው ይደግፉናል እኛም ድጋፍ ሲያስፈልግ ወደእነሱ እንሄዳለን፡፡
ከዞኖች ጋርም በትብብር እየሰራን ነው። ትላልቅ ፕሮጀክት ካልሆኑ በስተቀር የግንባታ ክትትልና የኮንትራት አስተዳደር ሥራዎችን ለዞኖች ነው የሚሰጠው፡፡ የዞኖን ባለሙያዎች በሚሰሩት ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ ሆነው የማሽነሪዎችን ተከላ ካልተመለከቱ በሜንቴናስ ኦፕሬሽን ላይም ችግር ይፈጠራል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ አጠቃላይ የግንባታ ክትትልና የኮንትራክት አስተዳደር ሥራ ለዞኖች ነው የሰጠነው፡፡ የተሰራውን ሥራ የሚለኩት፤ ክፍያ አጽድቀው የሚልኩትም ዞኖች ናቸው፡፡ ሌሎች ከባድ ሥራዎች ሲኖሩ ክልሉ በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በጣም በመናበብ የምንሰራው ይሆናል፡፡
በክልሉ ላይ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ የሚባል ቢሮ አለ፡፡ እነሱም የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ ስለሚሰሩ እንደግፋለን፣ እንናበባለን። እነሱ በአጠቃላይ አርብቶ አደር ላይ የሚሰሩት የንጹህ ውሃ አቅርቦት ሥራዎች ደጋፊ በመሆናቸው እንደጋገፋለን። ባጠቃላይ መንግሥታዊ ሆኑ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመናበብ ሥራዎችን እያከናወን ነው። ፕሮጀክቶችን ማንም ቢሰራቸው ህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እስከሆኑ ድረስ የጋራ ስምምነት እናደርጋለን፤ ዶክመንት እንገመግማለን፤ በቅንጅት እንሰራለን፡፡ ነገር ግን ክልሉ በቂ የሰው ኃይል እጥረትና የሎጂስቲክስ እጥረት አለበት፡፡
በርግጥ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ተደጋግፎ ከመሥራት አንጻር ክፍተቶች አሉ፡፡ በተለይ በሚዛን አማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ላይ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ ፕሮጀክቱ ትልቅ ሀብት የሚፈልግ ሆኖ ሳለ ይህን ፕሮጀክት ለማስቀጠል የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ለማነጋገር ብንሞክርም ሊደግፈን የሚችል አካል ግን አልተገኘም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቦንጋ ላይ ያለው ፕሮጀክት ግንባታው ካለቀ በኋላ የአይረን ልኬቱ ችግር እንዳለበት ሰምተናል፡፡ ይህ ችግር አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- ችግሩ ሙሉ በሙሉ አልተፈታም፡፡ ይህ ችግር ያጋጠመው ቦንጋ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ክልሉ የውሃ ችግር የለበትም። የከርሰ ምድርም ሆነ ገጸ ምድርም ውሃ በበቂ አለው፡፡ ነገር ግን በከርሰ ምድርም ሆነ በገጸ ምድሩ ላይ የሚገኘው ውሃ ለመጠጥነት ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ማዕድናት አለባቸው፡፡ በውሃ ውስጥ የሚገኙት የማዕድናት መጠን መብዛት ለክልሉ የንጹህ ውሃ መጠጥ አቅርቦት ፈተና ሆኖበታል፡፡
ለምሳሌ፣ ከፋ እና ዳውሮ ላይ የብረት መብዛት፤ ሸኮ ላይ የብረት እና ፍሎራይድ መጠን መብዛት ለንጹህ ውሃ አቅርቦቱ ማነቆ ሆኖብናል፡፡ የቦንጋ ውሃ ላይ የነበረውን የብረት መጠን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት በርካታ ሙከራዎች አድርገናል። ግን አልተሳካም፡፡ በመሆኑም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጨረታ ወጥቶ ጨረታውን አንድ የጀርመን ተቋራጭ አሸንፎ ነበር፡፡ የተወሰኑ ሥራዎችን ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን የጀርመን ኮንትራክተር ሥራዎችን አጠናቀኩ ካለ በኋላ የብረት መጠኑ በድጋሜ ሲመረመር ወደ ስታንዳርዱ አልመጣም፡፡
በመሆኑም የጀርመኑ ድርጅት ከህንድና ከኔዘርላንድ ሰብኮንትራክተር አስመጥቶ ሞክሮ ነበር። መሃል ላይ ኮሮና ሲመጣ ድርጅቱ ሥራውን ጥሎ ወጣ፡፡ አሁን ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግንባታ ሥራውን ለአርባ ምንጭ ከተማ ውሃ አገልግሎት የማማከሩን ሥራ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንዲሰሩ ሰጥቷል የሚል መረጃ ነው ያለን፡፡
በዓለም የጤና ድርጅት በውሃ ውስጥ የሚገኘውን የአይረን መጠን ተብሎ የተቀመጠው 0.3 እና ከዛ በታች ነው፡፡ ከዛ በላይ ከሆነ ለአገልግሎት አይመከርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቦንጋ የውሃ ጉድጓድ በስንት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ነበር የታቀደው? ምን ያህል ወጭስ ወቶበታል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- አጠቃላይ ሥራዎቹ እኛ እንደ ክልል ከመምጣታችን በፊት የተጀመሩ ናቸው። በምን ያህል ገንዘብ እና መቼ መጠናቀቅ አለበት የሚለውን ለማወቅ መረጃዎችንም ለማግኘት ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ ግን አልተሳካልኝም፡፡
የቦንጋ ውሃ ዲዛይኑ ከተሠራ ከ15 ዓመት በላይ ሆኖታል፤ የግንባታውም ሂደት ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተለያዩ የውጭ እና የውስጥ ኮንትራክተሮች እየተፈራረቁ ሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ ሾዶብ፣ ደቡብ፣ ወላይታ ውሃ አገልግሎት እና ሌሎች በርካታ ድርጅቶች እየተፈራረቁ ሰርተዋል። በመሆኑም ግልጽ የሆነ ፋይናንሻል ስቴትመንት አላገኘንም፡፡ ፋይናንሻል ስቴትመንቱን ለማግኘት በርካታ ጥረቶችን አድርገን ነበር፤ ግን አልተሳካም።
ቦንጋ ላይ ወደ አራት የሚሆኑ ጉድጓዶች የተቆፈሩ ቢሆንም፤ አንዱ ከፍተኛ አይረን ስላላው ታሽጎ ነው ያለው፡፡ ሌሎቹ ሶስቱም ቢሆኑ ከነችግሮቻቸው ነው ያሉት፡፡ እስካሁን ለነዚህን አራት ጉድጓዶች ወጪ የተደረገውን ሀብትም ማወቅ አልተቻለም፡፡
የግንባታው አጠቃላይ ወጪ ለማወቅ ከዞን እስከ ፌዴራል የሚገኙ የተለያዩ አካላትን አነጋግረን ነበር፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ተጫራቾች ስለሚፈራረቁ ፋይናንሻል ስቴትመንት ለማግኘት አልቻልንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በ2016 የበጀት ዓመት የክልሉ ቢሮ ምን ያህል በጀት ተበጅቶለታል? ምን ያህሉስ ሥራ ላይ ውሏል? ከአበዳሪ አካላትስ ምን ያህል ተገኝቷል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- ክልሉ በዘንድሮ በጀት ዓመት ለንጹህ መጠጥ ውሃ ዘርፍ ተጠሪ ተቋማትን ሳይጨምር 120 ሚሊየን ብር መድቧል። ይሄ ቁጥር ክልሉ ካለው በጀት አንጻር ትልቅ ቁጥር ነው። ፕሮጀክቶቹ ከሚፈልጉት በጀት አንጻር ሲታይ ያነሰ ይመስላል፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግሥት ለውሃ ዘርፉ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው ያለው፡፡
እውነት ለመናገር በክልል ደረጃ ከፍተኛ በጀት የተመደበው ለእኛ ቢሮ ነው፡፡ ነገር ግን ያደሩ ችግሮች አሁን ለምንሰራቸው ሥራዎች ችግር እየፈጠሩ ነው። ለዚህ ክልልም መመሥረት ዋነኛው ምክንያት ፍትሃዊ የመልማት እድል ባለመኖሩ ነው፡፡ በልማት ወደኋላ የመቅረት ችግር ነው፡፡ ከቀድሞው ክልል ሲንከባለሉ ከመጡ ችግሮች ጋር ተዳምሮ አሁን የክልሉ መንግሥት ያለው ውስን ሀብት መሠረተ ልማቶችን በተፈለገው ልክ ለማስኬድ አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ አዲሱ ክልል ለውሃ ዘርፉ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰቶት እየሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የክልሉን የመጠጥ ውሃ ሽፋን ምን ያህል ለማድረስ አቅዳችኋል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- በፌዴራልና በክልል ደረጃ ግልጽ የሆነ የስትራቴጂክ እቅድ አለ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ10 ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ለማዳረስ ታቅዷል፡፡ ክልሉም ይሁንኑ እቅድ ለማሳካት የራሱን እቅድ አዘጋጅቷል። ነገር ግን በየዓመቱ የታቀደውን እቅድ ለማሳካት የሚመጣው ሀብት በቂ መሆን አለበት፡፡ በነገራችን ላይ የመጠጥ ውሃ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ስለሆነ በሕዝብ ሞቢላይዜሽን ካለታከለበት በመንግሥት ወጪ ብቻ ማሳካት አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ላይ ኢንቨስተሮች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ምን ጥረት እያደረጋችሁ ነው?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- እኛ እንደክልል ብሩህ ተስፋ ያለን ነን፡፡ በርካታ ያወቅናቸውና ያላወቅናቸው ሀብቶች አሉን፡፡ ክልሉ በማር ምርት አንደኛ ነው። በወርቅ ምርት ሁለተኛ ነው። የድንጋይ ከሰል ማምረት ተጀምሯል፡፡ በክልሉ በርካታ ሀብት አለ፡፡ ግን እስካሁን በተፈለገው ልክ ጥቅም ላይ አልዋለም። የክልሉ መንግሥትም ባለሀብቶች መጥተው እንዲጎበኙ እና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሥራዎችን እየተሰሩ ነው፡፡
ለምሳሌ ወደ ምዕራብ ኦሞ በሁለትና በሶስት ዓመታት ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ከፍተኛ ባለሀብቶች መተው ወደ ሥራ እየገቡ ነው፡፡ ለወደፊት ግን ክልሉ ቀድሞ ማደግ የሚችል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቢሮው ያለበትን የሰው ኃይል ችግር ለመፍታት ምን እቅድ ይዛችኋል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- ሰው ለመቅጠር ሀብት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለሚቀጥሉት ዓመታት ሌላ የሰው ኃይል ከመቅጠር ይልቅ በታችኛው መዋቅር ውስጥ ያለውን የሰው ኃይል ለመጠቀም አቅደናል፡፡ ወረዳዎቹ አዲስ ስላልሆኑ እዚያ ያለውን የተደራጀውን የሰው ኃይል መጠቀም ያስፈልጋል። ያለንን የሰው ኃይል በአግባቡ እና በቅንጅት መጠቀም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ሀብት እስኪያፈራ ድረስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሥራውን ጉዳይ እንዴት ልታደርጉ አስባችኋል ?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- በክልሉ ያለው በአብዛኛውን ሕዝብ ውሃ እየጠጣ ነው፡፡ አሁን ምን ዓይነት ውሃ እየጠጣ ነው ያለው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ እኛ እንደ ክልል እቅደን እየሠራን ያለነው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁት ላይ ብቻ ሳይሆን በቀላል ወጪ በመሥራት ተደራሽ ሊሆኑ የሚችሉትን እንደ ምንጮች ያሉ አማራጮች ላይ ነው፡፡ ምንጮች ላይ ማዕድናት አይበዙም፡፡ ማዕድናት የሚበዙት በከርሰ ምድር ውሃ ላይ ነው፡፡
በስትራቴጂክ እቅድ ላይ አቅምን ማገናዘብ ስለሚያስፈልግ እኛ ቅድሚያ የምንሰጠው በምንጭ ውሃዎች ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የምንጭ ውሃ አንደኛ በቀላል ወጪ ይሰራል፤ ሁለተኛ ቀጣይነት አላቸው፤ ሶስተኛ ተደራሽ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወንዞችንስ አጣርቶ ለመጠቀም ምን እቅድ አለ?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- የወንዝ ውሃ መታከም (ትሪትመንት) ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ወንዝ በባህሪው ማኔጅ ማድረግ ይከብዳል፡፡ ብዙ ነገር ወደ ወንዝ ሊገባ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለወደፊቱ የቦንጋን ውሃ ችግር ለመፍታት ጉሜ የሚገባውን ወንዝ ለመጠቀም አስበናል፤ ዲዛይንም እያደረግን ነው፡፡ እንደ ለገዳዲ እና እንደ ገፈርሳ የወንዝ ውሃን በመጠቀም የንጹህ ውሃ ለማቅረብ፤ አሁን ማሻ ላይ ወንዝን ማልማት ጀምረናል፡፡ ግን የወንዝ ሥራው ከፍተኛ ካፒታል ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም በቀላሉ የመጠጥ ውሃ መሆን የሚችሉ ምንጮች ላይ እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቦንጋ የክልሉ መቀመጫ እንደመሆኗ የቦንጋ የውሃ ችግር መቼ ይፈታል?
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- ሙሉ በሙሉ የሚፈታው እኛ እያካሄድን ያለነው ጥናትና ዲዛይን ሙሉ በሙሉ አልቆ ሀብት ስናገኝ ነው፡፡ ዲዛይኑ በዚህ ዓመት ያልቃል፡፡ የሚፈልገው ሀብትም ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ይሆናል የሚል ግምት አለን፡፡ ሀብት ባገኘን ጊዜ ወደ ሥራ እንገባለን፡፡ ነገር ግን እስከዚያ ድረስ በገጸ ምድር ውሃ ጉሜ ወንዝ አክሞ በመጠቀም ችግሩን ለማቃለል እቅድ አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡
ኢንጂነር ፊልታሞ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
መክሊት ወንድወሰን ፣ ሞገስ ተስፋ እና ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም