አዲስ አበባ፡– በቱሪስት መዳረሻ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች በሚፈለገው መጠን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ አሠራሮችን ለመተግበር እየተዘጋጀ መሆኑን ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ምክክር እንደገለጹት፣ ወጣቶችን በማደራጀት በማሰልጠንና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና በሚፈለገው መጠን ወጣቱን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።
ሀገራችን ትልቅ የቱሪዝም ሀብት እንዳላት እና ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች የገለጹት ዳይሬክተሯ የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍና የውጭ ምንዛሬንም ለማሳደግ የቱሪዝም ሀብቱ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
ወጣቶች በቱሪዝም ተሳታፊ መሆናቸው ከሚያበረክትላቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተጨማሪ ኢትዮጵያ በዘርፉ ከዓለም ተወዳዳሪ እንድትሆን ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላትም አስረድተዋል። በመሆኑም በሀገር ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች በሚገባ ተለይተው እንዲለሙ ማድረግና ዘርፉን ማነቃቃት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ቱሪስቱ ሀገር ውስጥ ገብቶ እስከሚወጣ ድረስ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠሩላቸዋል ብለዋል። በዚህም መሠረት ወጣቶቹን በማደራጀት የሥልጠና፣ የብድርና የሥራ ቦታን በማመቻቸት እና ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አሠራሩን ማዘመን እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተነስቷል።
በተለያዩ አካባቢዎች በተበታተነ መልክ በቱሪዝምሥራ ላይ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ወጣቶች እንዳሉ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ በዘርፉ የሥራ ዓይነቶችን በማብዛት በርካታ ወጣቶችን በማደራጀት ኢንዱስትሪውን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። እያንዳንዱ ባለድርሻ አካልም የየራሱን ኃላፊነት እንዲወጣ በመድረኩ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የት አካባቢ ምን ዓይነት የቱሪዝም ሀብት አለን፣ ምን ያህል የሰው ሀብት በዘርፉ መሰማራት አለበት የሚሉትን በመለየት ወደ ሥራ መገባት እንዳለበትም ተመክሮበታል።
በውይይት መድረኩ ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ ሙያተኞች የተገኙ ሲሆን በየአካባቢያቸው የሚገኙ የቱሪዝም ጸጋዎች የሚፈለገውን ያህል ጥቅም እያስገኙ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሐረሪ ክልሎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች በደንብ ከተሰራባቸው ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማረጋገጥ እያንዳንዱን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ተወያዮቹ ቱሪስቶችን እየለመኑ አላስፈላጊ ጥቅም በማግኘት የሀገራችንን ገጽታ ከማበላሸት ይልቅ ለቱሪስቱ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል ሃሳብ ሰጥተዋል።
ዘርፉ ዕድገት ተኮር ቢሆንም እንደሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ትኩረት ያለማግኘቱን የተናገሩት ተወያዮቹ ቱሪዝም ሕይወታችንን ልንቀይርበት የሚያስችለን መሆኑን ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠትና ይህንን አዲስ የሥራ ዘርፍ በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በቱሪዝም መዳረሻዎች የሚታዩ የመሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታትና በዘርፉ ላይ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በማስወገድ የተጀመረውን ንቅናቄ ዳር ማድረስ እንደሚያስፈልግ ተመክሯል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ኢያሱ መሰለ