አዲስ አበባ፡- ድርጅቶችን በአሸባሪነት የመሰየም ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆን ሲገባው ለሌላ አካል መሰጠቱ አግባብ አለመሆኑንና በረቂቁ ላይ ሊታይ እንደሚገባ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በተካሄደ የአስረጅ መድረክ ተጠየቀ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመወሰን ሥልጣን እንዳለው እየታወቀ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 4 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርጅቶችን በአሸባሪነት እንዲሰይም የውሳኔ ሃሳብ ሲቀርብለት ማስረጃዎችን በመመርመር የውሳኔ ሃሳቡን ለመቀበል ወይም ውድቅ ለማድረግ ይቻላል የሚለው ድንጋጌ አግባብነቱ እንደገና እንዲታይ ተጠይቋል።
ከውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ ተስፋዬ ዳባ በረቂቅ አዋጁ ላይ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ሽብርተኝነትን የመሰየም ሥልጣን ከሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት መውጣት እንደሌለበት አስምረውበታል። ጉዳዩ እንደገና መታየት አለበትም ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ አያይዘውም ከዚህ በፊት በሽብርተኝነት ተሰይመው የነበሩ ድርጅቶች የአልሸባብና የአልቃይዳ ጉዳይ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት ሽብርተኛ ብሎ የሚሰይማቸው ላይ በረቂቅ አዋጁ እንዲታዩ አስተያየት ሰጥተዋል።
ሌላው የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ዘለቀ መሐሪ ሃሳቡን በማጠናከር በሰጡት አስተያየት ምክርቤቱ የግለሰቦችን፣ቡድኖችንና በአጠቃላይ የዜጎችን ሰብአዊ መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው ሽብርተኝነትን የመሰየም ሥልጣን ለምክርቤቱ መሰጠቱ መንግሥት ጉዳዩን በአግባቡ ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንደሚያስችለው አመልክተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ተወካይ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ አሻሚ የሆኑ ቃላትና ትርጉም የሚያስፈልጋቸው እንዲሁም ከመደበኛው የዳኝነት ሥርዓት እና ከሕገመንግሥቱ ጋር አንጻርም በረቂቅ አዋጁ ላይ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መታየት እንዳለበት አሳስበዋል።
ተወካይዋ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠውን በተለይ የሞት ቅጣትን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ የሞት ቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸው ግን ተፈጻሚ ባለመሆኑ ዜጎች በሥነልቦና እየሞቱና በከባድ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንዲሁም በዓለም አቀፍም የሞት ቅጣት ጉዳይ ጥያቄ እየቀረበበት መሆኑን በማስታወስ ጉዳዩ በትኩረት እንዲታይ አስተያየት ሰጥተዋል።
በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጽደቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ ከቋሚ ኮሚቴዎቹ ለቀረቡት የተለያዩ ጥያቄዎችና አጠቃላይ ስለረቂቅ አዋጅ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ በመስጠት አስረድተዋል።
የሞት ቅጣትን በተመለከተ ለተሰጠው አስተያየት አቶ በላይሁን የሞት ቅጣት አንዱ የቅጣት ዓይነት መሆኑንና በተናጠል አዋጅ መቀየር እንደማይቻል ገልጸው፣ የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል። በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰኔ19 ቀን 2011ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር መድረክ እንደሚኖርም በቋሚ ኮሚቴዎቹ ተወካይ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ለምለም መንግሥቱ