• 21 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለመሰብሰብ ታቅዷል
ጀልዱ፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በ2011/2012 ዓ.ም የምርት ዘመን በዓይነትም በብዛትም የተሻለ የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና ሌሎች የግብአት አቅርቦቶች ዝግጁ ሆኗል። 600ሺ14 ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል እንደሚሸፈን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል። በምርት ዘመኑም 21 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክቷል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገላና ኑሬሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በ2011/2012 ዓ.ም የምርት ዘመን እንዲቀርብ ከተጠየቀው 712ሺ ኩንታል ማዳበሪያ 523ሺ ኩንታል ‹ሲድ ዋን እና ሲድ ቱ› የተባሉ የማዳበሪያ እንዲሁም የምርጥ ዘር አቅርቦት ለዞኑ በወቅቱ ደርሷል። ቀሪውም በቅርቡ ይደርሳል።
እንደ አስተዳደሯ ገለፃ ከተጠየቀው 36ሺ ኩንታል መካከል 20ሺ ኩንታል የተለያየ ምርጥ ዘር ለዞኑ ደርሷል። ለተባይ እና ለአረም ማጥፊያ የሚውለው ፀረ ተባይም ሙሉ ለሙሉ እንደሚደርስ ከኦሮሚያ ግብርና ፌዴሬሽን መረጃው ለዞኑ የደረሰ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የግብአት አቅርቦት ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለና በዓይነትና በብዛት በመቅረብ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ ከከተማ በርቀት ላይ የሚገኙ እና የመንገድ ችግር ላለባቸው እንደ አቡናግንደበረት፣ ግንደበረት፣ባኮ፣ኖኖ እና ሌሎችም ቅድሚያ በተሰጣቸው ወረዳዎች ግብአቱ መሰራጨቱን ጠቅሰው የበቆሎ ዘር በተሳካ ሁኔታ ለመከወን ተችሏል። በቀጣይ ለሚከናወኑት የስንዴ፣ የአገዳ፣ የብርዕና የጤፍ ዘርም የማሳ ዝግጅት ተደርጓል።
በምርት ዘመኑ በዞኑ 6ሺ14 ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዓይነት ይሸፈናል ያሉት አቶ ገላና ግብአቱ በጊዜ መቅረቡና ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ መኖሩ የተሻለ ምርት እንዲጠበቅ አስችሏል። በምርት ዘመኑም 21 ሚሊዮን ኩንታል የተለያየ እህል ለመሰብሰብ ታቅዷል። እቅዱን ለማሳካትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በክላስተር እንዲሰራ ይደረጋል ብለዋል።
በዘንድሮ የምርት ዘመን ግብአት በብዛት፣ በዓይነትና በወቅቱ መድረሱ ካለፈው የምርት ዘመን የተለየ እንደሚያደርገው የጠቆሙት አስተዳዳሪው በተለይም አምና ካጋጠሙ ተግዳሮቶች የአረም መድኃኒት አቅርቦት ችግር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዝ እንደነበርና አርሶ አደሩ በችርቻሮ በውድ ዋጋ ለመግዛት ተገዶ እንደነበር ገልጸዋል። በረዶ የቀላቀለና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና የፀጥታ ችግሮች ለግብርና ምርቱ እንቅፋት እንደነበር አመልክተዋል። አምና ለመሰብሰብ በእቅድ ከተያዘው 19 ሚሊዮን ኩንታል 18 ሚሊዮን ኩንታል መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን የአቡናግንደበረት ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዘሪሁን ደባሣ በበኩላቸው በወረዳቸው የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ መድረሱንና አቅርቦቱ በምርት ዘመኑ ከፍተኛ ምርት ለመሰብሰብ ተስፋ ማሳደሩን ጠቁመዋል።
የአገዳ እህል የዘር ሥራ መጠናቀቁንና ለሌሎች ሰብሎችም የማሳ ዝግጅት ሥራ ከ85 በመቶ በላይ መከናወኑን አስረድተዋል። አርሶ አደሩን በቅርበት የሚረዱ 82 የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መኖራቸውንና በተሻለ ድጋፍ ውጤታማ ለመሆን በመስራት ላይ እንደሆኑም አስታውቀዋል። በአዲስ የአስተራረስ ዘዴ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንና የቅንጅት ሥራው ከዚህ ቀደም ያልነበረ መሆኑንም አመልክተዋል።
ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል በአቡናግንደበረት ወረዳ ሀሮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር አድማሱ ወልተጂ የዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ። ቀደም ሲል የማጓጓዣ፣ የተስተካከለ መንገድ አለመኖር፣ ከውጭ በጊዜ አለመምጣት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ሌሎችም ምክንያቶች እየተሰጠ በወቅቱ ይቀርብላቸው እንዳልነበር ገልጸዋል።
በወቅቱ ቀርቦ አምስት ኩንታል ማዳበሪያ ከአካባቢያቸው የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር (ዩኒየን) እንደወሰዱና ካላቸው ሁለት ሄክታር መሬት ላይ በሩቡ ላይ በቆሎ መዝራታቸውንና ቀሪውን ሄክታር ለስንዴና ለጤፍ አለስልሰው ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር ደሜ ከባ፣ታከለ ጀቤሳ፣ወይዘሮ ወርቂ ይልማ ግብአት በጊዜ በመድረሱ ቀድሞ የሚዘራውን በቆሎ መዝራታቸውንና ድንችም መትከላቸውን ጠቁመው፣ ግብአት በወቅቱ መድረሱ ቢያስደስታቸውም የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። 290 ሺ አርሶአደሮች በዞኑ ባሉ 22 ወረዳዎች እና 529 ቀበሌዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ለምለም መንግሥቱ