«መንግሥት በተለየ ሁኔታ አንዱን የሚንከባከብበት ሌላውን የሚያገልበት አሠራር የለውም»
– መንግሥት
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እና የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዚዳንቶች ለውጡ ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሀገር ውስጥ የነበሩትን በአንድ መነጽር እያየ አይደለም የሚል ቅሬታ አሰሙ። መንግሥት በበኩሉ በተለየ ሁኔታ አንዱን የሚንከባከብበት ሌላውን የሚያገልበት አሠራር እንደሌለው ተገለጸ።
የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እና የመኢብን ፕሬዚዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራው ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በሀገር ውስጥ የነበርነው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ ለመጣው ለውጥ ያበረከትነው አስተዋጽኦ እንደ ዋዛ ተረስቶ መንግሥት ከውጭ ለመጡት ፓርቲዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት እኛን ያገለሉ ውይይቶችንና ስብሰባዎችን ማድረጉ አሳዝኗቸዋል።
ለውጡ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ከውጭ የመጡትን በአንድ ሚዛን ላይ አላስቀመጠም የሚሉት የኢራፓው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ፣ ከውጭ ለመጡት ፓርቲዎች የሚደረገው ልዩ ጥንቃቄና እንክብካቤ ተገቢ ያለመሆኑን በመጥቀስ ዛሬም የፍትሐዊነት ጥያቄ እንደ ችግር ሊነሳ አይገባም ብለዋል። አያይዘውም መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስመልክቶ የሚያደርጋቸው ስብሰባዎችና ለፓርቲዎቹም የሚያደርገው ድጋፍ ያለ አድልኦ ማከናወን አለበት ይላሉ።
ኑሮውን እዚሁ ለማድረግ የሰላም ጥሪውን አክብሮ ሻንጣውን ሸክፎ የመጣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከዓመት እስከ ዓመት እንግዳ እየተባለ በሕዝብና በመንግሥት ገንዘብ ከፍተኛ ወጪ እየተሸፈነለት በሆቴል ውስጥ መቀመጡም ተገቢ አለመሆኑም ገልጸዋል።
ከሞላ ጎደል ሀገር ውስጥ ካሉት አንድና ሁለት ፓርቲዎች በስተቀር አብዛኛዎቹ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግሥት ስህተቱን በማረም ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎን በመቆም ማበረታታት እንደሚገባው ተናግረዋል።
የመኢብን ፕሬዚዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራሁ በበኩላቸው ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም ነገር እየተመቻቸላቸው በአንጻሩ አብዛኛዎቹ የሀገር ውስጥ ፓርቲዎች እየተገለሉ መሆኑን ተናግረዋል። ሁሉም ድርጅቶች እራሳቸውን ችለው እስከተመሰረቱ ድረስ ከውጭ የመጡ ድርጅቶችም እራሳቸውን ችለው መደራጀት አለባቸው ብለዋል።
በአዋጅ የተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአዋጅ ሳይፈርስ አዲስ የጋራ ምክር በትዕዛዝ እንዲቋቋም መደረጉም ከሕግ አንጻር ተገቢነት የለውም ሲሉ ልጅ መስፍን ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የኢራፓው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ግን የቀድሞው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሁኑ በስምምነት ያጸደቁት ሰነድ ያለመሆኑን በመግለጽ አሁን የተቋቋመው የጋራ ምክር ቤት ሁሉም ፓርቲዎች በተስማሙበት አንድ የጋራ ሰነድ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ቅሬታውን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፣ በለውጥ ሂደት መንግሥት አካታች የሆኑ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን በመጥቀስ በተለየ ሁኔታ አንዱን የሚንከባከብበት ሌላውን የሚያገልበት አሠራር እንደሌለ ተናግረዋል።
ከውጭ የመጡት ፓርቲዎች የተጠሩት ለይስሙላ ሳይሆን በሀገራቸው ፖለቲካ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ ለማስቻል እንደመሆኑ ሁሉም ተሟልተው እስኪመጡና ውይይት እስኪጀመር ድረስ መንግሥት እንደ እንግዳ እንደተቀበላቸው ገልጸው፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሆቴል ውስጥ ቁጭ ብሎ በመንግሥት አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅት እንደሌለ ተናግረዋል። መንግሥት በጀት መድቦ ፓርቲዎችን ወጪያቸውን ሸፍኖ በሆቴል የሚያስቀምጥበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም ብለዋል።
መንግሥት በሚመጡበት ጊዜ ጥበቃ ማድረግ፣ ቢሯቸውን እስኪከፍቱና እስኪደራጁ መደገፉ አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ «የጠራናቸው ለይሥሙላ ሳይሆን በሀገራቸው ፖለቲካ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ በመሆኑ በመጡበት ጊዜ እንደ እንግዳ ተቀብለናቸዋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሆቴል ውስጥ ተቀምጦ አገልግሎት የሚሠጠው የፖለቲካ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም። ቀደም ሲል ውይይት ይደረግ ስለነበር ተሟልተው እስኪመጡና ውይይት እስከሚደረግ እንደ እንግዳ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ግን አልቀጠለም። በአሁኑ ሰዓት አንዳንዶች የክልል ፓርቲዎች በመሆናቸው በሚሄዱበት ክልል አቀባበል ተደርጎ ሊሆን ይችላል» ብለዋል።
የቀድሞው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአዋጅ ሳይሻር አዲስ ምክር ቤት መቋቋሙ ተገቢ አይደለም በሚል መኢብን ላሰማው ቅሬታ አቶ ፍቃዱ ሲመልሱ፣ የመጀመሪያው ሰነድ አካታች እንዳልነበርና ግማሹን ድርጅት በአሸባሪነት የሚፈርጅ በመሆኑ የአሸባሪነት አዋጅ ሲነሳ በዚህ ስም የተፈረጁትን ድርጅቶችና ሌሎችንም የሚያቅፍ የጋራ ስምምነት አስፈላጊ በመሆኑ አዲስ የጋራ ሰነድ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው ብለዋል።
የሚዲያ ሕግ፣ የበጎ አድራጎት ሕግ፣ የምርጫ ቦርድ ሕግ ከለውጡ ጋር ተያይዘው እንደተሻሻሉ ሁሉ ይህም ማሻሻያ የለውጡ አካል እንደሆነ አስረድተዋል። አዲሱ ምክር ቤት በሕግ አግባብ ለመጽደቅ ገና በሂደት ላይ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ የቃል ኪዳን ሰነዱን ከፈረሙ በኋላ ትክክል አይደለም ብሎ መቃወም ለውጡን ለማደናቀፍ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር መወገንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ኢያሱ መሰለ