ኢትዮጵያውያን በደስታ ሆነ በሀዘን ጊዜያት የሚረዳዱበትና የሚደጋገፉበት ብዙ ማህበራዊ እሴቶች አሏቸው። በተለይ ሰዎች ችግር ወይም ሀዘን ሲገጥማቸውም ለመረዳዳትና ለመተጋገዝ እንደ እድር ያሉ ቀደምት ማህበራዊ እሴቶች ይጠቀማሉ። እድሮች ሞትና የመሳሰሉት አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጥኖ በመድረስ ቀብር ለመፈጸም፣ ለማጽናናት፣ ሌሎች ለመደጋገፍ፣ የግድ የሚሉ ችግሮችን ለመፍታት ከማህበረሰቡ ጎን በመቆም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረከቱ የኖሩ የኢትዮጵያውያን እሴቶች ናቸው።
አባላት ለክፉ ቀን በሚል በየወሩ በሚያዋጡት ገንዘብ ላይ ተመስርተው የፋይናንስ ችግሮቻቸውን ይፈታሉ። በዚህም ሀዘን የገጠመው አባል በቤቱ ውስጥ የጎደለውን ክፍተት ሙሉ በሙሉ መሸፈን ባይችሉም ሲደግፉ ኖረዋል። በኢኮኖሚ ከሚያደርጉት መደጋገፍ ባሻገር፣ ቤተሰቡን ተመላልሰው በማጽናናትና ሀዘኑ የሀዘን ዳርቻ እንዲሆንለት እየገለጹ በማጽናናት ስነ- ልቦናውን ይጠብቁለታል።
እድሮቹ አባሎቻቸው ሀዘን የደረሰበት ቤት እንዲደርሱ፣ ቀብርም እንዲፈጽሙ ጥሪ ያቀርባሉ፤ ይህን በማይፈጽሙት ላይም ቅጣት ይጥላሉ። በእድሩ ደንብ መሰረት የጉልበት፣ የሀሳብ፣ የገንዘብ ፣ ድንኳን፣ ወንበርና የመሳሰሉትን ከማቅረብ፤ በተጨማሪ የቀብር ሥርዓቱን ያስፈጽማሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ ለቀባሪዎች የትራንስፖርት ያቀርባሉ።
አባሎቻቸው እድሮቻቸውን እንደ አይን ብሌናቸው ነው የሚመለከቷቸው። የእድራቸው ወርሃዊ ክፍያ በምንም አይነት መልኩ እንዲስተጓጎል አይፈልጉም። ቆጥበውም ቢሆን ክፍያቸውን በወቅቱ ይፈጽማሉ። እድሮች ይህን ሁሉ ኃላፊነት በመወጣት የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት እሴት ሆነው ኖረዋል። ይህን ሰፊና ወሳኝ አገልግሎታቸውን በተለይ ቤተሰብ የመሰረቱ ጥንዶች ፈጥነው ይቀላቀሉታል። ማህበረሰቡም ቤተሰብ የመሰረቱ ዘመዶች፣ ጎረቤቶች፣ ወዘተ ፈጥነው እድሮችን እንዲቀላቀሉ ይጎተጉታል። ጥንዶቹም የሚኖሩበት አካባቢ ቋሚ መኖሪያ አካባቢያቸው ከሆነ ብዙም ሳያቅማሙ እድሩን ይቀላቀላሉ።
እድሮች የተለያዩ አይነቶች ናቸው። እንደ የአካባቢው እና እንደ አስፈላጊነቱ ትልቅ እድር ፣ ትንሽ እድር ፣ የወንዶች እድር ፣ የሴቶች እድር ፣ የአብሮ አደጎች፣ የመስሪያ ቤት እድር፣ ወዘተ በመባል ይቋቋማሉ። በተለያዩ ስያሜዎች እና ህብረቶች ሲቋቋሙም መረዳጃ እድር የሚል መጠሪያ አልያም ተመሳሳይ መጠሪያ ይሰጣቸዋል።
እነዚህ እድሮች ለየት የሚያደርጋቸው ሰዎችን ባላቸው የኢኮኖሚ ደረጃ ሃይማኖትም ሆነ ዘር ልዩነት ሳያደርጉ ሰውነትን ብቻ መሰረት አድርገው የሚቋቋሙ መሆናቸው ነው። እያንዳንዱ እድር በአባላቱ የጸደቀ የራሱ መተዳደሪያ ደንብ አለው። እናት፣ አባት፣ ልጆች፣…ወዘተ/እንደየእደሩ ደንብ/ የቤተሰቡን አባላት ማስመዝገብ እንዳለበት በደንቡ ላይ ይሰፍራል።
እነዚህ እድሮች ከአባሎቻቸው የሚሰበስቡትን ገንዘብም ሆነ ያላቸውን ሀብት ይዘው ከመቀመጥ እና አባሎቻቸው ሀዘን በገጠማቸው ጊዜ ቀብር ከማስፈጸም ውጪ የሚያከናውኑት ተግባር አለመኖሩ በብዙዎች ዘንድ ሲተች ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዚህ ኃላፊነታቸው በተጨማሪ እንደ ሠርግና የመሳሰሉት ሲኖሩ ደስታ የሚጋሩበት ሆነዋል። በቁም መረዳዳት ላይ አተኩረው የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠርም ጀምረዋል። አንዳንድ እድሮች አክሲዮኖችን በመግዛትና በተለያዩ የገንዘብ ማስገኛ ስራዎች በመሰማራት ለእድራቸው ፣ለአባላትና ለእድሩ የፋይናንስ አቅም መጠናከር እየሰሩ ይገኛሉ። በሀገር ልማትም ይሳተፋሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በአዋጅ ቁጥር 74 /2014 ተደራጅቶ በአዋጅ ቁጥር 84/2016 ማሻሻያ ተደርጎለት በተሰጠው ተግባር እና ስልጣን በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ሴቶች ፣ ሕፃናት ፣ አረጋውያን ፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ልዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች መብትና ደህንነታቸው ተጠብቆ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ዘርፈብዙ ተግባራትን መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ይሰራል።
ቢሮው የእድሮች እና የእድር ምክር ቤቶች ምዝገባና እድሳት አሰጣጥ መመሪያ 151/2016 ያወጣ ሲሆን፣ በቅርቡ በመመሪያው ላይ ለእድሮችና ምክር ቤቶቻቸው ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችል ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይም ከክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የተወጣጡ የእድሮች ምክር ቤት አመራሮች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ እንደተመላከተው፤ መመሪያው ለዚህ ታላቅ የማህበረሰቡ እሴት መጠበቅና መጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ አለው። መመሪያው የእድሮች የምዝገባ አሰራር እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የእድር ምክር ቤቶችን በመመዝገብ ህጋዊ እውቅና እንዲኖራቸው ማድረግ ፣ እድሮች ከቀብር ማስፈፀም ባሻገር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ አባሎቻቸውንና የከተማውን ነዋሪ ጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከተው አካል ድጋፍ የሚያገኙበትን ሥርዓት መዘርጋት እና ሕጋዊ እውቅና የሚያገኙበትን አሰራር በመዘርጋት የአባሎቻቸውን መብትና ግዴታ የሚያስከብር እንዲሁም ህገ ወጥ ድርጊቶችን መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት ማስፈን የሚሉ ዓላማዎችን ይዟል።
በመመሪያው ውስጥ የእድሮች እና የእድር ምክር ቤቶች የምዝገባ መስፈርት እና ሂደት ፣ የቢሮውን ተግባርና ኃላፊነት እና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል። መመሪያው ማንኛቸውም አዳዲስ እድሮችንም ሆነ ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እድሮችን ያስተናግዳል።
እድሮች ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ቢሮው የሚያዘጋጀውን የመመዝገቢያ ቅጽ በመሙላት በእድሩ ስራ አመራር ወይንም በህጋዊ ወኪሎቻቸው አማካኝነት በመመሪያው የተገለጹትን ማስረጃዎች ይዘው በየወረዳው ጽህፈት ቤት ማቅረብ ይኖርባቸዋል። የእድሩ አባላት ስምና አድራሻ ፣ በምዝገባ ወቅት የእድሩ ሀብት በዓይነት እና በጥሬ በእድሩ የቁጥጥር ኮሚቴ ተቆጥሮ በእድሩ አባላት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀ ሀብት ፣ እድሩ የሚገኝበትን ሙሉ አድራሻ ማቅረብ እና በአባሎቹ መልካም ፍቃድ ስምምነት የተመሰረተ የመመስረቻ ወይም የመተዳደሪያ ደንብ አልያም ሁለቱም ሰነድ ያለው መሆን የእድሮች የምዝገባ መስፈርት ተደርገው በመመሪያው የተቀመጡ ናቸው።
በመመሪያው ላይ እንደተመላከተው፤ በየደረጃው የሚገኙ የእድር ምክር ቤቶች የሚቋቁመበት መስፈርት ተቀምጧል። ማንኛቸውም የእድር ምክር ቤቶች በተወሰነ አካባቢ በሚኖሩ እድሮች ወይም በየደረጃው ባሉ የእድር ምክር ቤቶች በፈቃደኝነት ሊመሰረቱ ይችላሉ፤ በአንድ ወረዳ ውስጥም ሆነ በአንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከአንድ በላይ የእድር ምክር ቤት ማቋቋም አይቻልም።
በእያንዳንዱ የእድር ምክር ቤት የስራ አመራር አባላት ቁጥር ከ12 በላይ መብለጥ አይኖርበትም። ማንኛውም እድር ወይም የእድር ምክር ቤት ምዝገባውን ሲያጠናቅቅ የምዝገባ ማረጋገጫ የምስክርነት ወረቀት ይሰጠዋል። ምዝገባ ያከናወነ እድርም ሆነ ምክር ቤት ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ህጋዊ ሰውነት ይኖረዋል።
መመሪያው የእድሮች እና የእድር ምክር ቤቶችን መብት እና ግዴታ፣ የቅሬታ አቀራረብ እና የምዝገባ እድሳት ፣ እድሮች እና የእድር ምክር ቤቶች የሚሰርዙበትን አግባብም እንዲሁ አስፍሯል። እድሩ ወይንም ምክር ቤቱ በሀሰተኛ ሰነድ የተመዘገበ ከሆነና ይህም በቢሮው ከተረጋገጠ ፣ የእድሩ ወይም የእድር ምክር ቤቱ 2/3 ድምጽ ምዝገባው እንዲሰረዝ ጥያቄ ሲያቀርብ እና የእድሮቻቸውን እና የእድር ምክር ቤቶችን ደንቦች እና ህግ ጥሶ በመገኘቱ እንዲፈርስ ሲወሰን እና በሌሎች በመመሪያው ላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች የእድር እና የእድር ምክር ቤቶች ምዝገባቸው ይሰረዛል፤ ከተሰረዙበት ቀን ጀምሮም ህጋዊ እውቅናን ያጣሉ። መመሪያው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ እድሮች እና የእድሮች ምክር ቤቶች ተፈጻሚነት ይኖረዋል።
በመመሪያው መሰረት ያልተመዘገቡ እድሮች እና የእድር ምክር ቤቶች ህጋዊ አይደሉም ማለት ይሆን የሚል ጥያቄ በውይይቱ ላይ ተነስቷል። መመሪያው አዲስ በመሆኑ እና በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ እድሮች ብዙ በመሆናቸው የማስተዋወቅ እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።
በውይይቱ ላይ ከየክፍለ ከተማው የተወጣጡት የእድር ተወካዮች የእድር ምክር ቤት ጸሐፊዎች እና ሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን፤ ለእድሮች የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ የሕብረት ስራ ማህበር የማቋቋም ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎቻቸውን ለማሳካት ከሌሎች ተቋማት ጋር ውል የመዋዋል ፣ በልማት ስራዎች እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብት መሰጠቱ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት እንዲጠነክር ያደርጋል ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
አቶ ታምራት ገብረማርያም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ እና የሀገር አቀፍ እድሮች ጥምረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ናቸው። እድሮች ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ ሆነው ዜጎች በነዋሪነታቸው ላይ ብቻ ተመስርተው ለማህበራዊ የእርስ በእርስ አገልግሎት ብቻ የተቋቋሙ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣‹‹እድሮች ሲመሰረቱ ቀብር ማስፈጸምን መሰረት አድርገው እንደነበር ጠቅሰው፤ መመሪያው ዘመኑን እና ጊዜውን በጠበቀ መልኩ እድሮች እንዲንቀሳቀሱ የሚያግዝ እና የሚተዳደሩበትን ደንብም የሚያጎለብት ነው ›› ብለዋል ።
ፕሬዚዳንቱ መመሪያው እድሮች ላይ ጫና ያሳድራል ወይም በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ እድሮችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባል ይባላል የሚል መረጃ በአንዳንድ ወገኖች ይነሳል፤ በዚህ ላይ ማብራሪያ ይሰጠን በሚል ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤በመመሪያው ላይ ስልጣን የተሰጠው ቢሮ እድሮችን በተለያየ መንገድ የማገዝ ፣ ህጋዊ አቅም ኖሯቸው እንዲንቀሳቀሱ ከማድረግ ባለፈ በአሰራራቸው ላይ ጣልቃ ገብቶ የማደራጀት ፣ የማስመረጥ እና በተለየ ሁኔታ በውስጥ የአሰራር መመሪያዎች ላይ እንዲሄድ የተደረገበት ሁኔታ አለመኖሩን አስታውቀዋል። መመሪያው የእድሮች እና የእድሮች ምክር ቤቶችን መተዳደሪያ ደንብ መነሻ አድርጎ የወጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ከሰባት ሺህ 500 በላይ እድሮች ይገኛሉ። በሀገር ደረጃ ደግሞ ከ100 ሺህ በላይ እድሮች አሉ ተብሎ ይጠበቃል። መመሪያውም ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ እድሮችም አቅም የሚያሳድግ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በቦሌ ክፍለ ከተማ የጋራ እድሮች ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ መኮንን ቶላ የእድራቸውን ተሞክሮና በመመሪያው ላይ ያላቸውን ምልከታ አጋርተውናል። የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ነዋሪው አቶ መኮንን በሚኖሩበት ወረዳ የአካባቢ ተወላጆች በጋራ ሆነው ያቋቋሙት እድር አባልም ናቸው ።
በእሳቸው እድር ውስጥ ከአባላቱ ጋር ውይይት በማድረግ ከሚቆጥቡት ገንዘብ ላይ የባንክ አክስዮን ማዋል ችለዋል። በተጨማሪም እድሩ ወላጅ አልባ ህጻናትን ማስተማር ፣ በየአመቱ ከእድሩ ውስጥ እና ውጪ ያሉ አቅመ ደካሞችን ቤት ያድሳል። በሀገራዊ ልማት ውስጥ የአባይ ግድብ ቦንድ በመግዛትም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል። በእድራቸው ውስጥ ያሉትን እነዚህን ተሞክሮች እድራቸው ያገኘው ከሌሎች እድሮችና የእድር ምክር ቤቶች ጋር ባደረገው ውይይት መሆኑን አቶ መኮንን ይጠቅሳሉ።
አቶ መኮንን የእድሮች እና የእድሮች ምክር ቤት የምዝገባና እድሳት መመሪያ 151/2016 እድሮች ንብረታቸውን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ጥናት ተካሂዶ የተደነገገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ረጅም አመት የቆዩ እድሮች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እና አዳዲስ እድሮች ሲቋቋሙም በእድሮች ምክር ቤት እውቅና እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም እድሮች በሙሉ የቀብር ስነስርዓትን ብቻ የማስፈጸምን ስራ በዋናነት ይሰሩ እንደነበርም አስታውሰው፣ መመሪያው ግን እድሮች ባላቸው ሀብት ላይ ተመስርተው በኢኮኖሚ የሚያድጉበትን አማራጭ እንዲያሰፉ እና ወደ ልማት ስራዎችም እንዲገቡ እንደሚያበረታታ ገልጸዋል። ‹‹እድሮች የሚሰበስቡትን ገንዘብ በአንድ ቋት ሰብስቦ ከማስቀመጥ ይልቅ እንዲሰሩበት በማድረግ የእድር አባላት በሀዘናቸው ጊዜ ብቻ ሳይሆን በህይወት እያሉም እንዲጠቀሙበት እንዲደገፉበት ያደርጋል ›› ሲሉም ጠቁመዋል።
መመሪያው ይፋ ከተደረገ በኋላ እድሮች ባላቸው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ጣልቃ ይገባል አልያም ባላቸው ሀብትና ይዞታ የመጠቀም መብት ላይ ጥርጣሬና ስጋት ሊያሳድር ይችላል ወይ ብለን ላነሳልናቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ መመሪያው እድሮች ያላቸውን ይዞታ መጠቀም ማስተዳደር የሚችሉና የገቢ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ያግዛል ይተባበራል እንጂ ጣልቃ አይገባም፤ ይህም በመመሪያው ላይ በግልጽ ተቀምጧል›› ብለዋል።
አቶ መኮንን እና ወዳጆቻቸው ያቋቋሙት እድር በልማት ምክያንት መንደሩ ሲፈርስ እርስ በእርስ ለመገናኘት አስቸጋሪ ሆኖባቸው ለተወሰኑ ጊዜያት ተቋርጦ ነበር። አቶ መኮንን የእድራቸውን ሰነድ ለምክር ቤቱ በማቅረባቸው ችግሩ ተፈትቶ ወደ ምክር ቤቱም ሊቀላቀል ችሏል።
የእድሮች ምክር ቤት በአንድ ወረዳ ያሉ እድሮች የተመረጡ አባላት የሚሳተፉበት ሲሆን የምክር ቤቱ መቋቋም በአንድ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ እድሮች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ልምድና ተሞክሮ እንዲለዋወጡ ያደርጋቸዋል። አቶ መኮንን በሚኖሩበት በወረዳ 13 ብቻ 141 የሚጠጉ እድሮች መኖራቸውን አስታውቀዋል። የእድሮች ምክር ቤት መቋቋም እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ እንዲደጋገፉና በችግሮቻቸው ዙሪያ ተወያይተው መፍትሄ እንዲያስቀምጡ ያደርጋል ይላሉ።
እድራቸው ያለውን ሀብት ተጠቅሞ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ህጋዊ ፍቃድ እንዳለው የሚያረጋግጥ ሰነድ እንዲያቀርብ ይጠይቅና ወደፊት ለመራመድ ይቸገር እንደነበር አስታውሰው፣ በምክር ቤቶች ውስጥ መካተት የሚያገኘውን ጥቅምና በዚህ መመሪያ መሰረትም በነጻነት ኢኮኖሚውን ማሳደግ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ እድሮች ይዞታቸውን ለማስተዳደርና ጥያቄ ሲኖራቸውም በተናጠል ከሚያቀርቡ ይልቅ በእድር ምክር ቤት አማካኝነት ቢያቀርቡ በሚኖረው ተዋረድ መሰረት ወረዳ፣ ለክፍለ ከተማ ፤ ክፍለከተማ፣ ለከተማ በማቅረብ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ እና ጊዜያቸውንም እንዲቆጥቡ ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም