የጂኦተርማል እምቅ ሀብትን የመለየትና ማልማት ጥረቶች

የዓለም ከርሰ ምድር በጂኦተርማል ኢነርጂ የተሞላ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ከምድር ውስጥ የሚገኝ የሙቀት ኢነርጂ በማልማት ለማብሰያ፣ ለመታጠቢያ፣ ክፍሎችን ለማሞቂያ፣ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማምንጨትና ለመሳሰሉት ሁሉ እንዲያገለግል ማድረግ ይቻላል፡፡

ዓለም ከሚያስፈልጋትም በላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የጂኦተርማል ሀብት በከርሰ ምድር ውስጥ እንዳለም መረጃዎቹ ጠቁመው፤ ይህን ሀይል በተለይ ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት ስራ ማዋል ፈተኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያም የጂኦተርማል ሀብት ፍለጋ ከጀመረች ረጅም ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አማካኝነት ከ1960ዎች ጀምሮ የተለያዩ ጥናቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ጥናቶቹ እንዳመላከቱት፤ እስካሁን 27 የሚሆኑ ከፍተኛ ሙቀት ያላቸው የጂኦተርማል አለኝታ ቦታዎች ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይችላሉ ተብለው ተለይተዋል፡፡ በሀገሪቱ ከዘርፉ ከአስር ሺ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት እንደሚቻል ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የጂኦተርማል ዘርፍ እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች በ1990ዎቹ የመጀመሪያው የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአልቶ ላንጋኖ ተገንብቶ 7ነጥብ3 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ማድረግ ተችሏል፤ ይህ ማመንጫ በአሁኑ ጊዜ በጥገና ላይ ይገኛል፡፡ በአፋር ተንዳሆ ዱብቲ አካባቢ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት የጂኦተርማል ሀብት ልማቱን በራሱ ብቻ ማልማት ብዙ ካፒታል እንደሚጠይቅ በማመን፤ ስትራቴጂዎችን ፣ ፖሊሲዎችን ፣ አዋጆችን ፣ ደንብ እና መመሪያዎችን በመቅረጽ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም የሀገር ውስጥና የውጭ የግል ባለሀብቶችን የጂኦተርማል ሀብቱን እንዲያለሙ በመፍቀድ እና ምቹ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የጂኦተርማል ሀብት አዋጁም እንደተቀመጠው፤ ሁለት አይነት የጂኦተርማል ሀብት አለ፡፡ ደረጃ-1 የጂኦተርማል ሀብት ማለት ከፍተኛ ሙቀት (Temperature) ያለውን የጂኦተርማል እንፋሎት ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመቀየር ማመንጨት የሚያስችል ሲሆን፤ ደረጃ -2 የጂኦተርማል ሀብት ደግሞ ከጂኦተርማል የሚገኘውን የሙቀት ኃይል በቀጥታ ጥቅም ላይ ለሚውሉ አገልግሎቶች ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለአሳ እርባታ፣ ለማዕድን ልማት ፣ ለመዝናኛ፣ ለህክምና ፣ ገላ መታጠቢያ እና ለመሳሰሉት ሌሎች አገልግሎቶች ላይ የሚውል ነው፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ እስካሁን 27 የሚሆኑ ከፍተኛ ሙቀት ያላቸው የጂኦተርማል አለኝታ ቦታዎች ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይችላሉ ተብለው ተለይተዋል፡፡ በጂኦተርማል ዘርፍ ቀደም ሲል በተደረጉ ጥናቶች ላይ በመመርኮዝ በተዘጋጀው የጂኦተርማል የማስተር ፕላን ጥናት መሠረት በኢትዮጵያም ከዘርፉ አስር ሺ ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት የሚያስችል አቅም እንዳለ ታውቋል፡፡

በጂኦተርማል ዘርፍ በኩባንያዎች ደረጃ በ6 የተለያዩ አገራት የውጭ ባለሀብቶች እና የአንድ የመንግሥት ተቋም እየተሰማራ ሲሆን፤ ሌሎች 11 ደግሞ የፍለጋና የማልማት ፈቃድ በማውጣት በሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ፡፡

በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፉ በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በከበሩ፤ በብረት ነክ ፣ በኢንዱስትሪ ፤ በኮንስትራክሽንና በጨው ማዕድናት ልማት፣ ምርመራና የመሳሰሉት ላይ ለመሰማራት ፈቃድ በመውሰድ በርካታ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በማዕድን ዘርፍ እየሰሩ ያሉ ኩባንያዎች 208 ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ 134 በምርመራ ስራ ላይ፣ሌሎች 74 (ሰባ አራት) የሚሆኑት ደግሞ የምርት እና ቅድመ ምርት ስራዎች በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የጂኦተርማል ኢነርጂን ማልማት ከፍተኛ ሀብት ይጠይቃል፤ አብዛኛዎቹም በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በምርመራ ሥራ ላይ የሚገኙ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሁለት የውጭ ኩባንያዎች ግን ከመንግሥት ጋር የኃይል ግዥ እና የትግበራ ስምምነት መፈራረማቸውን ይገልጻሉ፡፡ እያንዳንዳቸው ኩባንያዎች በሁለት ፌዝ 150 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የቁፋሮ ስራ ዝግጅት እና ቁፋሮ እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተው፣ አንዱ ኩባንያ ሰባት ጥልቅ የምርመራ ጉድጓዶች አጠቃላይ ጥልቀቱ እስከ 15ሺ ሜትር የሚደርስ ቁፋሮ ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል፡፡ በመቀጠል ያለውን የእንፋሎት ኃይል ለማወቅ የጉድጓድ ፍተሻ ለማከናወን ዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በመንግሥት ኩባንያ በኩል አሥር ጥልቅ የምርመራ ጉድጓዶች ቁፋሮ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም አጠቃላይ ጥልቀታቸው ከ27ሺ ሜትር በላይ የሆነ የቁፋሮ ስራዎች መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡ ሁለት ተጨማሪ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተው፤ ከእነዚህ ውስጥ ስምንት የሚደርሱት የጉድጓድ ፍተሻ (well testing) ጥሩ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በማዕድን ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ ኩባንያዎች አንዳንዶቹ በአንዳንድ አካባቢዎች (በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ፣ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች) በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ስራ ያቆሙበት ሁኔታ ነበረ፤ አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ፈቃድ ወስደው የተሰማሩ አብዛኞቹ ኩባንያዎች ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተቆፈሩት ጉድጓዶች በትንሹ 25 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚቻል ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፣ ‹‹አምስት ሜጋ ዋት ዌል ሄድ ፕላንት›› በሚል ቴክኖሎጂ የማመንጨቱን ስራ ለመጀመር ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በማዕድን እና በጂኦተርማል ዘርፍ የምርመራና የጥልቅ ቁፋሮ ሥራ የሚከናወን እንደመሆኑ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ስራ ላይ የሚውልበት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህም ለሥራው ከሚደረገው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት አስችሏል፡፡ የማዕድን በተለይ የጂኦተርማል ሀብት ልማት ከፍተኛ የሆነ ካፒታል ፣ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግሥት ከተለያዩ አካላት ጋር የአጭር እና ረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በማመቻቸት የሰው ኃይል አቅምን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ነው፡፡

ዘርፉ በተለያዩ መስኮች ባለሙያዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ በቂ እውቀት ያላቸው የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እስካሉ ድረስ ሁሉም ኩባንያዎች የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የመቅጠር ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በዘርፉ በሀገር ውስጥ ልምድ ያለው ባለሙያ ባይገኝ እንኳን ከውጭ ከሚመጡ ባለሙያዎች ጋር በማቀናጀት ልምድ እንዲቀስም ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የሀገር በቀል ድርጅቶችን አዋዳድሮ የተለያዩ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ እየተደረገ መሆኑን አስታወቀዋል፡፡ ለአብነትም በመሠረተ ልማት (መንገድ፣ ካምፕ እና የውሃ ቁፋሮ በመሳሰሉት) ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ከፍተኛ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከፍተኛ እውቀት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ድርጅቶቹ የየአካባቢውን ማህረሰብ በተለያዩ ሥራዎች የማሳተፍ እና ለወጣቶች ስልጠና እንዲገኙ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ በጂኦተርማል ዘርፍ በአሁኑ ወቅት በድርጅቶቹ 300 ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በክልሎች የጂኦተርማል ሀብቱን ቀጥታ ጥቅም ላይ በማዋል ለብዙ ወጣቶችና ባለሀብቶችም የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በድርጅቶቹ የተለያዩ ሥራዎች ላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ብዙ ሰዎች እንደ ጨው፣ ፖታሽ ፣ ብሮሚን ፣ ሲሊካ ፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ እና የመሳሰሉት በማምረት ላይ ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ በመዝናኛና በቱሪዝም ዘርፍ በአፋር ክልል ወደ ዳሎል የሚደረገው ጉዞ የጂኦተርማል ቱሩፋት ከሆኑ መካከል አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ዘመናዊ እና ዘመናዊ ባልሆነ መልኩ ብዙ ሰዎች የሙቅ ውሃ ወይም ስቲም ባዝ በማዘጋጀት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ አመላክተው፤ ለእዚህም ፍል ውሃን፣ ሶደሬን ፣ ወንዶ ገነትን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በህክምና ዘርፍ ብዙ ሰዎች እንፋሎቱን እንደ ስቲም ባዝ እና ሻወር እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸው፣ በዚህ ሁሉ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል፡፡ ለአብነት የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት እና የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስትሩ በማዕድን ዘርፉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት አንዳንድ ግልፅ ያልሆኑ፣ለክትትልና ለቁጥጥር አመቺ ያልሆኑ አሰራሮችን በመለየት አዳዲስ አሰራሮችን የመዘርጋትና ተግባራዊ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እሴት የሚጨምሩ የፕሮሰስንግ እና ለኢንዱስትሪዎችና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃ ማምረት ለሚፈልጉ አምራቾች ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ማዕድናት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በዘጠኙ ወራት ተቋማዊ ብቃትን ማጎልበትና ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የማዕድን ምርትና ምርመራ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎችን በመከታተል እና በክትትል በተገኘው ሪፖርት መሠረት ለባለፈቃዶች የክትትል ውጤቱን ከፈቃድ ስምምነቱ ጋር በጽሁፍ እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ አቅም እና ልምድ ያላቸውን ባለሀብቶች በመሳብ በማዕድን ዘርፍ እንዲሳተፉ፣ የማዕድን አለኝታ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስርን ለማሳደግ ይረደ ዘንድ ሁለተኛው ዙር ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ከህዳር 14 እስከ 18 ቀን 2016ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በሲሚንቶ፣ በታጠበ ድንጋይ የከሰል ፣ በወርቅ እና በመሳሰሉት ማዕድናት ወደ ምርት ስራ የገቡ እና ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉ አምራች ኩባንያዎች የገጠሟቸውን ችግሮች በመቅረፍ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

በስራ ላይ ያለውን ተቋማዊ አደረጃጀት በጥልቀት በመገምገምና ችግሮቹን በመለየት እንደ አዲስ የማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እስካሁን የተሰጡ ፈቃዶችን አፈፃፀም በጥልቀት በመገምገም የቀጣዩን የፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ውጤት በሚያመጣ መልኩ ለመከወን የሚያስችሉ ስራዎች መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ የማዕድንና ነዳጅ ፖሊሲዎችን እና አዋጆችን አሁን ካሉት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ በማየት የመከለስ ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You