ባህል የአንድ አገር ልዩ መገለጫ ብቻ ሳይሆን ደስታን፣ ሃዘንን እና ሰላም የሚረጋገጥበት ትልቅ እሴት ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ባህልን ከፖለቲካ ትርፍ ባለፈ ዜጎችን በስነ ምግባር በማነፅ ምን ያህል ሰርታለች? ምን ያህልስ ተጠቅማለች? በተለይ ባህል ለሰላም ካለው አብይ ፋይዳ አኳያ አጉልተን ተጠቅመንበታልን?
የሰው ልጅ አካባቢው ወይም አዕምሮው የሚጠይቀውን ነገር ለመመለስ የፈጠረው ትልቅ የማህበረሰብና የአገር ሀብት ነው የሚሉት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በፎክሎር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመማር ላይ ያሉት መምህር ሕይወት አበበ ናቸው።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ እና የጋራ ባህል እሴቶች ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው ባህል አንድ ማህበረሰብ በኑሮው ውስጥ ጉዳዩን እየሰነደና እያቀነባበረ እርሱ በሚመቸውና በለመደው መንገድ ኑሮውን በሰላማዊ መንገድ የሚመራበት ስልት ነው ሲሉ ይበይኑታል፡፡
«ባህላችንን በአደባባይ ስንገልፅ፣ ስናስተዋውቅና ስናንፀባርቅ ያለውን የሰላም ትሩፋት ሳይሆን ‹እኔ የበላይ ነኝ› በሚል መልክ ነው፡፡ ይህ ሁኔታችን ደግሞ ትምክህት በውስጡ የያዘ ሆኖ ባህል ለሰላም ያለውን ፋይዳ ወደ ጎን ብለን ‹የእኔ ከአንተ ይሻላል› በሚል መልኩ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ብዙ ወጪ ተደርጎ ተሰርቶበታል፤» ሲሉ ያለፈውን ታሪክ ያስታውሳሉ- ወይዘሮ ሕይወት።
ባህል ውስጥ ጥቅም ላይ ዋሉ የሚባሉትም ቅንጣቱን ብቻ ነው ያሉት መምህሯ ጭፈራው፣ አልባሳቱ እና አመጋገቡ ላይ ብቻ ተወስኗል። ባህል ግን ለሥነአዕምሮ ግንባታ የሚውሉ እሴቶች ስላሉት እነዚያን መጠቀም ቢቻል ለሰላም ያለው አበርክቶ የጎላ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በባህል ውስጥ ያሉ እንደ የሽምግልና እና ሌሎች ከሰው ልጅ አኗኗር ጋር ተያያዥ የሆኑ እሴቶች ተቋማዊ ሆነው ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ አልተሰራም ሲሉ መምህሯ ወቅሰዋል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የግጭት አፈታትና የሰላም እሴት ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ እንደሚሉት፣ ከለውጡ በፊትም ሆነ ከለውጡ በኋላ መደበኛ የሚባሉት ተቋሞቻችን ባህልን ተጠቅመው ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ጠንክረው አልሰሩም ሲሉ የመምህሯን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የግጭት አፈታት ሁኔታ በሚገባ አጥንቷል፡፡ ከዘመናዊ የግጭት አፈታት ጋር እንዴት አብረው መሄድ እንደሚችሉ አንድ መጽሐፍ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ጅምር ሥራ ነው ብዙ ይቀራል፡፡ ሥራው ተቋማዊም አይደለም ያሉት አቶ አስቻለው፣ እስከአሁን በተሰራው ግን መንግሥት አሁን ከገጠመው ቀውስ አኳያ ባህላዊ እሴቶቻችን አገርን ከመፍረስ ታድገዋል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
«በተቋም ደረጃ የትኛው ባህላዊ ይዘት ለየትኛው ችግራችን ወይም እሴታችን ይጠቅማል የሚለው በወረቀትና በተወሰኑ መድረኮች ተወስኖ ቀርቦ ስንወያይባቸው ይታያል፤ ይሁን እንጂ በይዘት ደረጃ ተገቢው ቅርፅ ወጥቶለት ወደ ተግባር አልተቀየረም» ያሉት አቶ አለማየሁ ፣ ጥናቶቹ ጥቅም ላይ አልዋሉም ሲሉ የአቶ አስቻለውን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡
ባህልን ለሰላም በሚፈለገው መልኩ ያልተጠቀምነው ለባህል ያለን አረዳድ የተሳሳተ ከመሆኑ ጋር የተቆራኘ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ ባህልን የምንረዳው ለአልባሳት፣ ለአመጋገብና ለጭፈራ ካለው ጥቅም የዘለለ አይደለም፡፡ ይህም ባህል ካለው ጥቅም ውስጥ 10 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ቀሪው 90 በመቶ የባህል ዋናው ፋይዳ ተዘንግቷል፤ እየተጠቀምንበትም አይደለም ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ ይህ 90 በመቶ የሰውን ልጅ ሙሉ የሥነ አዕምሮ እና ሥነ ምግባር ለመገንባት ሚናው ከፍተኛ ነው፤ ነገር ግን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የመንግሥትም ሆነ የአብዛኛው ኅብረተሰብ ለባህል ያለው ግንዛቤ 10 በመቶ ለሚይዙት የአለባበስ፣ አመጋገብ እና ጭፈራ ላይ ብቻ ተገድቦ ለፖለቲካ ትርፍ ሲውል ቆይቷል ይላሉ፡፡ አቶ አስቻለውም የአቶ አለማየሁን ሃሳብ ይደግፋሉ፡፡
እንደ አቶ አስቻለው ገለፃ አንዳንድ አባቶችም ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የቀረበ ግንኙነት ኖሯቸው ትርፍ በመፈለግ ባህላዊ እሴቶቻችን የሚደበዝዙበት ሁኔታ አለ፡፡አባቶች እንደሚነግሩን የፖለቲካ አመራሩ በባህል ሥራዎች ጭምር ጣልቃ ይገባል፡፡ አመራሩ የተለያዩ ጥቅም በመስጠት እነዚህን ባህሎች ከጥቅም ውጪ አድርጓቸዋል። ከፖለቲካውም ከባህሉም ሆነው የሚያተራምሱ አሉ፡፡ እንደ የጋሞ አባቶች ያሉት ደግሞ ባህላቸውን ጠብቀው የሚሰሩ እንዳሉ መዘንጋት አይገባም፡፡
«ባህል ለባህል ባለቤቶች እየተተወ እንዲሰራ ባለመደረጉ አገራችን አሁን ወደገባችበት ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ ችግሩን ለማርገብ ደግሞ አንዳንድ የሚታዩ የእሳት ማጥፋት ሥራዎች ቢኖሩም አሁን ላለንበት የወረደ የሰብዕና ደረጃ ባልደረስን ነበር» ሲሉም መምህር ወቅሰዋል፡፡ «የዛሬው ትውልድ ያልተነገረውን፣ ያላወቀውን፣ ልቦናው ውስጥ ያልተዘራውን ነገር ዛሬ ላይ የመፍትሄ አካል አድርገን ብንመጣ አድካሚ ብቻ ሳይሆን ኪሳራም ጭምር ነው፡፡» ይላሉ- አቶ አስቻለው፡፡
አገራችን የባህል፣ የእምነት ሀገርና ለሰንደቅ ዓላማው የተዋደቀ ማህበረሰብ ባለበት በዚህ ወቅት እንዲህ ለመጠላላትና ለመገዳደል ያበቃን አንዱ ለባህላችን የሰጠነው ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ባህል ሰላማዊ አስተዋፅኦ አለው፤ ሰላማችን ደግሞ ለመኖራችን አስተዋፅኦ አለው የሚለውን ነገር ዋጋ ባለመስጠታችን የመጣ የሰብዓዊነት መንጠፍ ነው ይላሉ – መምህር ሕይወት፡፡
ባህል የሀገራችንን ሰላምና ልማት በማረጋገጥ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም መወጣት ያለበትን ሚና ግን አልተወጣም ሲሉ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ይናገራሉ። የጋራ የባህል እሴቶች ለሀገር ግንባታ ብሔራዊ መግባባትና ልማት በሚኖራቸው አስተዋፅዖና ፋይዳ፣ በኢትዮጵያ የዜጎችን መልካም ሰዕብና ለመቅረፅና ለሀገር ግንባታ የሚኖረው ሚና መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
«ባህል ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት እና ሰላም ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋፅዖ በመረዳት ባህላችንን በመጠበቅና በመንከባከብ አንድነታችንን ማጠናከር ብሎም የጋራ ሰላማችንን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደረጉን የሀገራችን ቀደምት የታሪክ አሻራዎች ያወረሱን በትጋት እና በአንድነት ሀገር መገንባትን ነው» ያሉት ዶ/ር ሂሩት፣ ብዝሀነታችን አንድነታችንን ሳያጠፋው አንድነታችንም ብዝሀነታችንን ሳይጎዳው ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ አሻራ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
«ችግሮቻችንን በቅጡ መረዳት አልቻልንም፤ ይህ መሠረታዊ ችግራችን ነው፡፡ አሁን የሚያጋጨን የኢኮኖሚ ችግር ነው ወይስ ሌላ ብሎ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት ማህበረሰባችን ያፈራው ሀብት ዝቅተኛ ሆኖ ቆሎ ቆርጥሞ እያደረ ይዞት የነበረው ታማኝነት ግን ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የወቅቱን ማህበረሰብ ሰብዕና ከፍ ያለ ያደርገዋል፤» የአቶ አለማየሁ ሀሳብ ነው፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ የሚስማሙበት የጋራ ምክረ ሃሳቦች አሉ፡፡ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ግብረገብ፣ የባህልና የሥነ ጥበብ እሴቶች በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ይካተቱ፡፡ ቤተሰብም ለባህሉ ዋጋ መስጠት አለበት፤ መገናኛ ብዙኃንም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ባህሎች ለሰላም ካላቸው ፋይዳ ጋር አያይዘው በማቅረብ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ ሁሉም ዜጋ ለባህል ያለው አረዳድ መቀየር አለበት፡፡ በዚህም ባህል ከጭፈራ፣ ከአልባሳትና ከአመጋገብ ውጪ ያለውን ጠቀሜታ ማወቅ አለብን፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደገለፁት መሰራት ያለባቸው ሥራዎች ካልተሰሩ በእጃችን ያሉትን የተለያዩ እሴት ያላቸው ባህሎቻችንን እናጣለን፡፡ በዚህ የመጣም ባህል አልባ ትውልድ ሆነን በመጤ ባህል ተገዝተን ወደከፋ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እንዘፈቃለን፡፡ ማህበረሰባዊ መረጋጋት አይኖርም፤ ሰላማችንም አሁን ካለበት ደረጃ ተባብሶ የከፋ ይሆናል፡፡
ተመሳሳይ አስተሳሰብ አይኖረንም፤ ተቀራራቢና ተመሳሳይ አስተሳሰብ ከሌለን፤የጋራ ፍልስፍና ከሌለን ሥነ ምግባራችን ከዚህ በታች ከዘቀጠ እንደሰው አብሮ መኖር አንችልም፡፡ አሁን ‹‹የእኔ ነው›› የምንለው ሃሳብ ወደ ከፋ ግለኝነት ይስፋፋል፤ አዎንታዊ የሆነው ይሉኝታም ይጠፋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ሀብታሙ ስጦታው