ባለቅኔው ገበሬ

የበሬው ጌታ የእርፍና ማረሻው ንጉሥ፤ ያን ገበሬ ማነው ባለ ቅኔ ያደረገው? ገበሬው አፈርን እንጂ ጥበብን ማገላበጥ አይችልም እያሉ ብዙዎች ቢያሙትም፤ ልኩን የሚያውቀው የለካው ብቻ ነው፡፡ ጥበብ የተወለደባት፤ ቅኔውም እትብቱን የተቆረጠበት መሆኑን አያውቁማ! ግጥምን የገጣሚው ብቻ ያደረገውስ ማነው? ገጣሚው ብቻ ከያዘውማ ምኑ ተገጣጠመ፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን የተመታው ቤት ሁሉ መፍረሱ አይቀርም፡፡ ጥበብን ለጠቢቡ፤ ቅኔውንም ለባለቅኔው ብቻ ከሰጠናቸው፤ እድሜያቸው ማጠሩ አይቀርም፡፡

ብዙ ጥበቦችን የማህበረሰብና ከማህበረሰብ ነው እንላለን፤ ግን ታዲያ ያ ማህበረሰብ የምንለው ማንን ነው? በጥቂት ሂሳባዊ ቀመር ለማስላት ብንሞክር፤ ይህ ማህበረሰብ የምንለው ክፍል፤ ገበሬና የገበሬ ልጅ ነው፡፡ እንኳንስ ድሮና አሁንም ቢሆን አብዛኛው ማህበረሰብ ከዚሁ ጎጆው የለቀቀ አይደለም፡፡ በዚህ ግዙፍ የማህበረሰብ ክፍል ውስጥ፤ ለቁጥር የሚታክቱ ትውፊተ ጥበባትን እናገኛለን፡፡ ጥበብ ከማህበረሰቡ የረዥም ጊዜ ትውፊት ውስጥ የበቀለ ካልሆነ፤ ከንቱ ዲስኩር ነው የሚሆንብን፡፡ ካልንም የኛ ማህበረሰብ ኪነ ጥበብን የሕይወት ልምምዱ አድርጎ በመኖርና በማኖር የሚታማ አይደለም፡፡

የብዙ ጥበብና ቅኔዎች የኋላ በር ብንከፍት፤ ቀድሞ እዚያ ማህበረሰቡ ውስጥ የነበሩ ስለመሆናቸው እንረዳለን። አሁን አሁን በየጎራውና ፊናው፤ ጥበብ በየጠቢባኑ ተይዛ ስንመለከት፤ በዚያ ዓይን ሌላውን አይቶ ለመገንዘብ አዳገትን እንጂ፤ እንደ እውነታው ከሆነ ግን ከሁሉ ቀድሞ ያያት እርሱ ነበር፡፡ ከዚያ ጎበዝ ታታሪ ዘንድ ስለመኖሯ፤ ሌላው ቢቀር በሬው ከነማረሻ ቀንበሩ ምስክር ናቸው፡፡ በአዳፋው ልብሱ እስኪፎክት ድረስ ማሳውን በላቡ እያራሰ የሚውለውን ምስኪን ገበሬ፤ ከእህል ጎተራው እንጂ ከጥበብ አቁማዳው ጋር ማንስ ያስታውሰውና…

ኢትዮጵያ በግብርና ከኋለኞቹ ጋር እያየናት ቢሆንም በአጀማመሩ ከፊተኞቹ ነበረች፡፡ ጥንቱን ገበሬ ሆኖ ሲኖር ሲኖር ይሄው ዛሬም፤ አብዛኛው ገበሬ እንደሆነ አለ፡፡ ይሄ ገበሬም፤ ከገጣሚው ሁሉ በፊት ነበር፡፡ ከአዝማሪውና ከባለቅኔውም አስቀድሞ ገበሬ ነበር፡፡ ሙዚቃ ተብሎ ሙዚቃ ሳይተለም በፊትም፤ ገበሬው ያዜም ያንጎራጉር ነበር፡፡ ጥበብና ስለ ጥበብ ሲነሳ በመጀመሪያው ከዚሁ ገበሬ ዘንድ ነበር፡፡ መማርና መፈላሰፍ፤ መሰልጠንና መዘመን፤ ለጥበብ መጠራትና ባለተሰጥኦ መባል፤ አርቲስት ተዋናይ፤ ገጣሚ ሙዚቀኛ ሁሉም የመጡት፤ ከገበሬው ኋላ ነበር፡፡

በዚህች መንገድ እያሳበርን ስንግተለተል፤ በመጀመሪያም ጥበብ ከወዴት እንደነበረች እንረዳለን፡፡ እህሳ…ስንልም፤ በመጀመሪያም ጥበብ ከገበሬው የልብ ማሳ ውስጥ ነበረች፡፡ ቅኔም እያሸተች በአዝመራው ላይ ከንፋስ ጋር ትጫወት ነበር፡፡

በገበሬው ዘንድ ያለው ጥበብ፤ እንደ ጠቢቡ ሁሉ በእውቀትና በንባብ አሊያም በረዥም የምናብ ህልም ውስጥ የተወለደና የሚወለድ አይደለም፡፡ ከጥልቅ የስሜት ባህር ውስጥ በመጥለቅ የሚፈጥረውም አይደለም፡፡ የገበሬው ሕይወቱ ሥራው ነው፡፡ በዙሪያው ያሉትም ማሳውና በሬዎቹ ናቸው፡፡ የኑሮው ጅራፍ በጮኸች ቁጥር ሁሉ የሚቀሰቅሱትን እነሱኑ ነው፡፡ እናም ገበሬው ከእነዚህ ጋር የተለየ የስሜት ተጋምዶና ቀጭን የትስስር ገመድ አለችው። ለማንም የማይገባው፤ የበሬው ጉርምርምታ ለእርሱ ግልጽ ቋንቋ ነው፡፡ ሰማዩን ለማየት ባንጋጠጠ ቁጥር ከደመናው ጋር የሚተሙት ቀለማት ሳይቀሩ አንዳች ነገርን ይገልጡለታል፡፡

የንፋሱ ሽውታ ለጆሮው ጥለውለት የሚያልፉት መልዕክት አለ፡፡ እጽዋቱ በነፋስ ሽውሽውታ ለዓይኑ ሰላምታን ያቀብሉታል፡፡ የአዕዋፋቱን ዜማ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ የገበሬው ሕይወት ከእያንዳንዱ ጋር የነፍስን አዱኛ ትቋረሳለች፡፡ ይረዱታል፤ ይረዳቸዋል፡፡ የገበሬው ባለቅኔነት የሚጀምረውም፤ የሚለየውም እዚህ ጋር ነው፡፡ ድንገት ዞር ብሎ በሬውን ያነጋግረዋል፤ በልምድና በውርስ ካገኘው የቅኔ ጎተራ እየዘገነ፤ ለበሬው ሙገሳን እንካ ይለዋል። ወደማሳው ወርዶ ቡቃያውን እየተመለከተ፤ የቅኔውን የባህር ማዕበል እያስነሳ ከሰማዩ ዝናብን ያዘንብላቸዋል፡፡

በዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ቢል፤ ከእርሱም ጋር ማውጋቱን አይተውም፡፡ ሆድ የባሰው እንደሆን ግን፤ የማዕበሉ ኃይል ከሁሉም የባሰ ነው፡፡ ታዲያ ጥበብም ቢሉት ቅኔ፤ ለገበሬው የሕይወት ገመዱ የተሳሰረበት የኑሮ ዘዬው እንጂ ባለ ቅኔ አሊያም የጥበብ መልህቅ ለመሆን አይደለም፡፡ ከአንደበቱ ቃላትን እያስወነጨፈ፤ ከጅራፉ ጋር በሬውን በቅኔ ሲያበረታው፤ ግጥም እየገጠመ ለትጋት ሲጋብዘው፤ ገጣሚ ለመሆን አስቦ አልነበረም፡፡ ግጥሙን እንጂ ስለገጣሚነት የሚያውቀው አንዳችም ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ነገ ላይም የኑሮውን እንጀራ የሚቆርስበት እንደሆነ በማሰብም አይደለም፡፡ ከላዩ ያረፈበት ትልቁ ያለማወቅ ዱላ ግን ይህ ነው፤ በእጁ ወርቅ ይዞ ወርቅ ምን እንደሆነ አለማወቁ ነው። ያወቁና የነቁቱም ጥበብን ከእርሱው ተምረው ጠቢብ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ገበሬው አስተማሪ፤ አሁንም ገበሬ ነው፡፡

ተማሪው ግን ድንጋዩን ወደ ወርቅነት ቀይሮ፤ እንደዚያው አብረቅርቆበታል፡፡ ከጊዜ ኋላም ቀለመኛው መጥቶ በቀለሙ ነከረውና ያልተመለከቱትን ሌላ ነገር ለማስመልከት ቻለ፡፡ ነገሩ ልክ በሳይንሱ ዓለም እንደምንመለከተው ዓይነት ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የሳይንስ ንጋት ነግቶ በምርምር ስለ ጨረቃና ክዋክብት ነጋሪ ሳይንቲስቶች ተፈጠሩ፡፡ ይህ ግን እውነት እንጂ ትልቁ እውነት አይደለም፡፡ ከዚያ ሳይንስ በፊት፤ ስለ ክዋክብት፣ ስለ ጨረቃም ሆነ ፀሐይ፤ አባቶች ስለ እያንዳንዱ ባህሪና ግብር ጠንቅቀው ከማወቃቸውም፤ በተፈጥሯዊ የሂሳብ ቀመርም አስቀምጠውታል፡፡ እና ታዲያ ሳይንቲስቶቹ ሲመጡ አባቶች የተባሉት ምን ነበር? “ኮከብ ቆጣሪ…የጨረቃ አማልክት አምላኪ…” ተባሉ፡፡ ጥበብ አዋቂው ደብተራ ሆነ፡፡ በአሁን ሰዓት ያልተማሩት እኚያ አባቶች ሳይንቲስት ነበሩ ቢባል ምጸትና ቀልድ ነው፡፡

ከዚህ መልስም፤ ገበሬው ባለ ቅኔና የታችኛው ማህበረሰብ፤ የጥበብ ፍኖት ባለ ክሩ አውታር ነበር እንድንል ካስገደዱን ልማዶቹ መሀከል ጥቂቱን እንኳን በጨረፍታ እንዳብሳቸው፡፡ ገበሬው ያንኑ በሬውን ጠምዶ ከማሳው ላይ ሲሰማራ፤ ጅራፉንም አንግቶ እርፉን ሲጨብጥ እርሱም ሆኑ በሬዎቹ ዝምታን አይወዱም፡፡ ይሄኔ አንደበቱ ለጥበብ ይከፈታል፡፡

«በርዬ በርታልኝ! ትንፋሽህ ምንድነው፤

ምርቱ ለኔ ቢሆን ገለባው ላንተ ነው፡፡»

እያለ ሲገጥምለት፤ ሳተናው በሬ ልቡ ትርክክ ይልና ድንገት ወኔው ውልብ ይልበታል፡፡ ደግሞ እንደገና፤ ከጅራፉ ጋር አብሮ የሚያንተከትከውን የሽለላና የፉከራ መሳይ ድምጽ ያሰማዋል፡፡ ይሄ ማንም የማያውቀው፤ በሁለቱ መሀከል ብቻ ያለ ሳይንስ ነው፡፡ በሌላ ጊዜ የለገመበት እንደሆን፤ አባብሎ ወደ መስመሩ ለማስገባት ሲሻ ድምጹን አለስልሶ፤ በሚያባብሉ የዜማ ቃላት፤ በፍቅር ይገራዋል፡፡ በተጨማሪም ባለቅኔው ገበሬ፤ ባለውለታውን በሬ ማመስገኑን አይዘነጋምና፤ ፍቅርና ክብር ከሙገሳ ጋር ይቸረዋል፡፡

«እሹሩሩ በሬ እሹሩሩ

አንተ በሠራኸው ይኖራል ሀገሩ”

በሬ ለገበሬ ሕይወቱ ነውና ሳያመሰግነው ውሎ አያድርም፡፡ አሁንም ግጥምን በዜማ እየደረደረ ይቀኝለታል፤ እንዲህ እያለ

«በሬ አንተን የጠላ፤

ጎኔ አንተን የጠላ፤

የገና የጥምቀት፤ ይለምናል ጠላ” በዚህ ግጥም ውስጥ፤ ገበሬው በሬውን “ጎኔ” ሲለው፤ የኔ ማረፊያ ሲል እየገለጸው ነው፡፡

ትውፊታዊ የጥበብ ድግስ የሚሰናዳበት ሌላኛው መድረክ፤ በባሕላዊው የደቦ ሥርዓት ውስጥ ነው፡፡ ደቦ፤ የአንድ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ በጋራ አንድ ጥምረት በመፍጠር፤ አንዱን ማሳ ለብዙ ሆነው በህብረት የሚሠሩበት ነው፡፡ በእቅዳቸው መሠረት ተራ በተራ እየዞሩ በማረስና በመዝራት ለብቻ የድንጋይ ሸክም የነበረውን ነገር በአንድነት ገለባ ያደርጉታል፡፡ ወጣቱን ኃይል አስከትለው፤ ከአባወራው እስከ እማወራው ሁሉ በየሥራ ድርሻው ይሳተፉበታል፡፡

ወደየትኛውም የሀገራችን ክፍል ብንወርድ፤ የደቦ ሥራ ያለ ዜማ አይከወንም፡፡ አንዱ ሲያወጣ ሌላው ሲቀበል፤ ሥራውን በሙዚቃ እያዋዙ በደስታና በወኔ ያጣድፉታል። ዜማው፤ ከልጅነት እስከ እውቀት ያደጉበት ነውና የዜማ ትንፋሽ አወጣጣቸውና የድምጽ ምታቸው፤ ከያዙት የእርሻ መሳሪያ አወራረድ ጋር እኩል እያስኬዱ፤ ከመላው አካላቸው ጋር የተዋሀደ ያደርጉታል፡፡ የሙዚቃውን ግጥሙ፤ እንደ ዘመንና ሁኔታው ሊጨምሩበትም ሆነ ሊቀንሱት ይችላሉ። ዜማው ግን በብዛት ተመሳሳይ ነው፡፡ የዚህን ጊዜ በጋራ እያዜሙ ላደመጣቸው፤ በአንድ የሙዚቃ ባንድ ተጠንቶ የቀረበ ህብር ዜማ እንጂ ከአንድ የመንደር ገበሬዎች አንደበት የሚወጣ አይመስልም፡፡ እነርሱም ኳየር የቆሙ እንጂ ማረሻ ጨብጠው መሬት የሚያገላብጡ አይመስሉም፡፡

በሌላኛው አቅጣጫ ሌላም መንገድ አለ፡፡ ከገበሬው ቀዬ ዘልቀው የማያዩት፤ ልብ ብለው የማያስተውሉት የለም፡፡ ተፈጥሮ መላ አካላቱን በጥበብ ስትገራው ለአፉ የፉጨትን ዜማ ሰጠችው፡፡ በሰለጠነው ማህበረሰብ ውስጥ “ፉጨት” ጥቂቶች ብቻ የሚችሏት የመግባቢያ ሙዚቃ ናት፡፡ በገበሬው ዘንድ ግን ከዚህም ያለፈ፤ ነፍስን ደስ የምታሰኝ ጥዑመ ዜማ አላት፡፡ ከወንዙ ዳርቻ፤ ከጉብታው ላይ ተቀምጦ፤ በዓይኖቹ ቁልቁልና ሲመለከት፤ ከናፍሩን እንዳሻው በማዘዝና ከትንፋሹ በማዋሀድ የውስጡን የሰላም ዜማ ያንቆረቁራል፡፡

የገበሬው ትንሽ ልጅም፤ በጠዋቱ ከብቶቹን ከመስኩ ላይ ሲያሰማራ፤ የፉጨት እንጉርጉሮ የልጅነቱን መልክና ጣዕም ትሰጠዋለች፡፡ ማራኪውን ድምጽ ተከትሎም፤ ጥበብ ወደ ቀርክሃው ጫካ መራችው፡፡ አንዲቷንም ቆርጦ፤ እያንዳንዱን ቀዳዳ በልኬቱ ነድሎም ጥበብን አስደሰታት፤ ዋሽንትን አበጅቶ ነፍስያውን በገነት ማማ ላይ አነሆለላት። ዛሬ ላይ፤ በዘመናዊው ሙዚቃ አስተማሪ ተመድቦለት ባንቲ አንቺሆዬ፤ አምባሰል ትዝታ እየተባለ፤ ዜማው ከቅኝቱ በእውቀት ከመቋጠሩ በፊት፤ በዚያ ባለቅኔ እጅ ነበረች፡፡

ቅኔንማ እሱ ይዝረፋት፤ ሞፈሩን ከቀንበሩ ጋር አገጣጥሞ መሰካካቱ ብቻ አይበቃውም፤ ቃላትን ከግጥም አሰካክቶ፤ ግጥምን ከዜማ አድርጎ እርሱ ያዋህድ፡፡ ገበሬው ባለቅኔ፤ ገበሬው ባለወኔ እርፉን ጨብጦ፤ አፈሩን አልስልሶ፤ ጥበብን እየዘራ ጥበብን ከአዝመራው ጋር ያብቅላታል። እስቲ እውነቱን እንነጋገር፤ እቁጩን አውርተን በሀቁ እንወራረድ! ያን ጎበዝ ገበሬ፤ በቅኔ እኔ እቀድመዋለሁ የሚል ይምጣ፡፡ ቃላትን አንኩሬ፤ ስንኝን ቋጥሬ ከእርሱ በፊት፤ ጥበብን ባይኔ በብረቱ አይቻታለሁ ብሎ የሚል አሊያም ሌላ አለ የሚል ማነው እሱ? ገበሬው ያለቅኔና ጥበብ መኖር አይችልም ባንልም፤ ከእርሱ ዘንድ መኖራቸው ግን ርግጥ ነው፡፡ ጥበባቱ ወጥነት ያላቸውና ባለመሆናቸው አይቶ ለመረዳት የሚከብዱ ናቸው፡፡

በጥበብ ባለቤቱ ዘንድ እንደምንመለከተው ሁሉ በቅርጹ ተበጃጅቶ፤ ለታዳሚው እንደሚቀርብ ዓይነት ጦማርም አይደለም፡፡ ቅኔው ለእርሱ ልክ እንደምግብ ጨው ነው። በዘልማድ “ቅኔ” እያልን የምንጠራቸው በርካታ ቢሆኑም፤ በጥቅሉ ግን ሁለት ዓይነት ትርጓሜ አለው፡፡ ቅኔን መቀኘት እና ቅኔን መዝረፍ፤ ሁለቱም የተለያዩ እሳቤዎች ናቸው። በመጀመሪያው ትርጓሜ መሠረት ቅኔ ስንል፤ በግጥምና በዜማ የተዘጋጀ መዝሙር አሊያም ሙዚቃ ነው፡፡

ቅኔ ተቀኘ፤ ዘመረ ወንም ሞዘቀ እንደማለት ነው።ሁለተኛው ደግሞ፤ ፊደላትን ከፊደላት ቃላትን ከቃላት አዋቅሮ፤ በሰምና ወርቅ ታሽቶ የሚዘጋጅ አንደኛው የአነጋገር ዘዬና ዘይቤ ነው፡፡ ሁለተኛው ቅኔም ከገበሬው ጋር የተሻለ ቅርበት አለው፡፡

ባለቅኔው ገበሬና የአሁኖቹ የጸደይ ወራት ልዩ የሆነ ቀጠሮ አላቸው፡፡ ገና ሳትመጣ ቀድሞ፤ ሀሩር ንዳዱን ሳይፈራ መሬቱን እየቆፈረ ይጠባበቃታል፡፡ ጸደይም፤ የሰማዩን ፊት አጥቁራ ከደመናው ንፋሱን እየቀዘፈች ትመጣለች፡፡ እሷኑ ለመቀበል ከማሳው ላይ ወርዶ፤ በሬውን ጠምዶና እርፉን ጨብጦ፤ የወኔውን መብረቅ በጅራፉ እያስተጋባ በቅኔው መሬቱን ሳይቀር ያረሰርሰዋል፡፡ እላይ ላለው ሰማይ ከላይ ለሚወርደው ዝናብ፤ በእጁ ለጨበጠው ማረሻ ከፊቱ ለሚተጋው ጥማድ በሬ፤ ለአፈሩና ለአምላኩም ሳይቀር፤ የቅኔ ዜማ፤ የቅኔ ግጥም….ሁሉንም እያንፎለፎለ ያወርደዋል። እራሱን እያጀገነ የበሬውን ወኔ ይቀሰቅስበታል፡፡ የሰማይ የዝናቡን ጌታ፤ አዶናዩን እየተማጸነና እያመሰገነ ባለቅኔው ገበሬ፤ ከቅኔው ጋር ውሎ፤ አምሽቶም ይገባል፡፡

በሬው ገበሬውን ባለቅኔ አደረገው፡፡ የበሬው ሻኛም የጥበብ አቁማዳ ሆነ፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲሠራ ሲደክም የዋለው ገበሬ፤ ውሎ ውሎ ምሽት አዳሩን ከቤቱ ይገባል፡፡ እርሱ ቢገባም፤ ከእርሱ ላይ ያለችው የቅኔ ጥበብ ግን ከጀንበር ጋር አብራ አትጠልቅም፡፡ ፀሐይ ጠልቃ ጨረቃ ስትወጣ ከወለሉ ላይ ሌላ የጥበብ ሶራ፤ ተዘርግቶ ይነጠፋል። ገበሬው፤ በሥራ የበከተውን ሰውነቱን ተጣጥቦ፤ ጎኑን ካሳረፈ ወዲያም ያለ በሬው ሃሳብ እሽ ብሎ ቀልቡ አይሰበሰብምና የዚህን ጊዜም ከቅኔው ማዕድ ይቆርሳል፡፡

«በሬዬ ምሩቁ ምርቁ

«አንተ ካልዞርክበት አይሰበር እርቁ፤

በዱላ ቢመቱህ በመንሽ ቢደልቁ፡፡

የበሬን ውለታ መጫወት ነው ማታ፤

በሰፊ ገበታ በዋንጫ ጋጋታ፡፡»

ባለ ቅኔው ገበሬ፤ እያለ ዋንጫውን ያነሳለታል። የደስታውንም ጽዋ፤ ሁለቱ ብቻ ከሚግባቡበት የቋንቋ ቅኔ ውስጥ እያለፈ ከሁለቱም ልብ ላይ ይፈሳል፡፡ ጥበብ በገበሬው ልብ ውስጥ ታድራለች፡፡ ገበሬውም፤ ቅኔውን ከጥበብ ጋር በበሬው ደምስር እየረጨ፤ በመላ አካላቱ ያሰራጨዋል፡፡ ሞፈርና ቀንበሩን ብቻም ሳይሆን፤ ባለቅኔው ገበሬ ጥበብንም ተሸክሞ እንደዋተተ ሲኖር… ሲኖር ይሄው ዛሬም ድረስ አለ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You