በተሠማሩበት የሙያ መስክና ምርምር ግሩም ሥራ በመሥራት የሀገራቸውን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስጠሩና ታሪካቸውን በደማቅ ቀለም ማፃፍ የቻሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት አይደለም። ከእነዚህ እንቁ ግለሰቦች መካከል የግዕዝ የኮምፒዩተር ፅሁፍ አባትና የእንስሳት ሐኪሙ ዶክተር አበራ ሞላ አንዱ ናቸው።
የተወለዱት በቀድሞው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት መናገሻ አውራጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰንዳፋ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሰንዳፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በደብረ ብርሃን ከተማ ኃይለማርያም ማሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የከፍተኛ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው የውጭ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው ኬንያ ናይሮቢ ሄደው ተምረዋል። በመቀጠልም ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት ተጨማሪ ትምህርት ተምረው አጠናቀዋል።
ዶክተር አበራ ወደ ሥራው ዓለም በመቀላቀልም በሀገር ውስጥ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለይም በአሜሪካ በርካታ ሥራዎችን የሠሩ ታላቅ ምሁር ናቸው። በሥራቸውም ከዓለም የእንስሳት ሐኪሞች አንዱ ለመሆን በቅተዋል። የግዕዝ ፊደልን በኮምፕዩተርና በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ በማስገባት መጠቀም እንዲቻል በማድረጋቸውም ሰባት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካና የኢትዮጵያ የባለቤትነት መብት ለማግኘት የቻሉ ሊቅ ናቸው። ከእዚህ ባለፈ የግዕዝ አልቦ አሃዝ ቀለሞችና የግዕዝ አሥር ቤት አኃዛዊ ቍጥሮች ፈጠራንም የሠሩ ሰው ናቸው። ለእነዚህ ለሠሯቸው ታላቅ ሥራዎችም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለመቀበል ችለዋል።
አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ የግእዝ ፊደላትን ለጽሑፍ አገልግሎት የሚጠቀሙ ቋንቋዎች የጽሑፍ አሊያም የትየባ ስልት በሥነ ቴክኒኩ ዘርፍ ወጥነት አይስተዋልበትም። በግእዝ ፊደላት በኮምፒውተር ለመጻፍ የሚያገለግሉ ሶፍትዌሮችን የሚያበለጽጉ ተመራማሪዎች የሚመሩበት የጋራ መስፈርት ባለመኖሩም አንደኛው ጽሑፍ ከሌላኛው ጋር ሲጣረስ ይታያል። እንዲያም ሆኖ በኮምፒውተር እና ሌሎች ዘመናዊ የሥነ-ቴክኒክ ውጤቶች ላይ ፊደላቱን ጊዜ እና ጉልበትን በመቆጠብ አቀላጥፎ ለመጻፍ የማስቻል የሶፍትዌር ማበልጸግ ሙከራዎች በተለያዩ ተመራማሪዎች ሲደረጉ ይስተዋላል።
ዶክተር አበራ በኮምፕዩተር ግዕዝ ፊደልን መጠቀም እንዲቻል ያደረጉት የአማርኛውን የጽሕፈት መሣሪያ (ታይፕራይተር) ለሚያውቁት ቀላል እንዲሆን በ“a”፣ “b”፣ “c”፣ “d” ምትክ “ሀ”፣ “ጠ”፣ “ሸ”፣ “ዘ” እና እንግሊዝኛ ለሚያውቁ በ“A”፣ “B”፣ “C”፣ “D” ምትክ “አ”፣ “በ”፣ “ቸ”፣ “ደ” ቀለሞችን በመመደብ ዓይነት ሠላሳ ሰባቱን የግዕዝ ቤት ኆኄያት ለ37 የኮምፕዩተር መርገጫዎች ስሞችም በማድረግ ነበር። ስምንቱን የፊደል ቤቶች ወይም እንዚራን ስምንት ፎንቶች ላይ በተኗቸው። በእዚህ ዘዴ በእጅ ጽሑፍና ማተሚያ ቤቶች ብቻ ይታተሙ የነበሩት የግዕዝ (Ethiopic) ፊደላት ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምፕዩተር ተከተቡ።
መጀመሪያ መሥራት የሚቻለውም የአማርኛ ታይፕራይተር ዓይነቱን ቅጥልጥል ፊደል እንደ አማርኛው ታይፕራይተር በአንድ የላቲን ፊደል ምትክ መተካት ስለነበረ ያንን ስለልፈለጉ እንጂ ቅጥልጥሉንም ከማንም በፊትም ሊሠሩበት ይችሉ ነበር። ተሠርቶበታልም። እያንዳንዱ ቀለም አንድ-ወጥ የሆነውን የማተሚያ ቤቶች ዓይነት ትክክለኛ የግዕዝ ፊደላችንን ለመጀመሪያ ጊዜ በማቅረብና እያንዳንዱም በሁለት መርገጫዎች እንዲከተብ በመፍጠር ግዕዝ ከማተሚያ ቤቶች ወደ ኮምፒዩተር እንዲገባ አደረጉ። ሞድኢት (ModEth) በመባል የታወቀውን የቃላት ማተሚያ የማይክሮሶፍትን ዶስ በመጠቀም በአሜሪካ ውስጥ ለገበያ አቀረቡ።
ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሊቆች፣ ሚኒስትሮችና ደራስያን የእንግሊዝኛውን የታይፕ መጻፊያ ለአማርኛ መክተቢያ እንዲያገለግል ወደ ሰማንያ ዓመታት ግድም ሲመራመሩ ቆይተው ባይሳካላቸውም ዶክተር አበራ ጥረቶቻቸውን በኮምፕዩተር አሳክተዋል።
ዶክተር አበራ የግዕዝን ቀለም (Glyph) በኮምፒዩተር በቀላሉና በቀልጣፋ ዘዴ ማቅረብ ስለቻሉ ሕዝቡ ከማተሚያ ቤቶች በተሻለ ሁኔታ በፊደሉ መሥራት ችሏል። በእዚህም የተነሳ ሕዝቡ መጻሕፍትንና የመሳሰሉትን ለማሳተም በየማተሚያ ቤቶች ወረፋ ከመጠበቅና ከመንግሥት እገዳ ተርፎ የእራሱ አታሚ ሆኗል። ዘዴውም በአማርኛ ሳይወሰን ለሁሉም የግዕዝ ቀለሞች መክተቢያና ማተሚያ ከሌሎች የዓለም ፊደላት እኩልና ጎን በሚገባ ሥራ ላይ እየዋለ ነው።
የግዕዝ ኮምፒዩተራይዜሽን ፈር ቀዳጅ የሆኑት ዶክተር አበራ የኮምፒዩተርን ሃይል እና እምቅ አቅም የተገነዘቡ እና ከዘመኑ በፊት የነበሩ ባለራዕይ ናቸው፡፡ ከ1982 እኤአ ጀምሮ ወይም ላለፉት ዓመታት በግዕዝ ፊደል ኮምፒዩተራይዜሽንና የአፃፃፍ ዘዴ ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
ዶክተር አበራ እኤአ በ1982 ለመጀመርያ ጊዜ ግዕዝን በኮምፕዩተራይዝድ በማድረግ የግእዝ ስክሪን እና የፕሪንተር ፊደሎችን ለመሥራት አንድ ዓመት ፈጅቶባቸዋል። ይህም የተሳካው ከ400 በላይ የግዕዝ የፊደል ቀለማትን በስምንት የኮምፒዩተር ቁልፎች ላይ በዘዴ በማሰራጨት ነው። ጠቅላላ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅም የፈጠሩት የመጀመሪያው የግዕዝ ኮምፒዩተራይዝድ የፊደል ገበታና የኮምፒዩተር መተየቢያ ሶፍትዌር በ1987 እ.ኤ.አ ይፋ ሆነ።
ዶክተር አበራ በፈር ቀዳጅነት የጀመሩት ጥረትና ፈጠራ ባይኖር ኖሮ የአማርኛና ግዕዝ ፊደላትን የኮምፒዩተር ፅሁፍ ማዘመን፣ በዩኒኮድ ደረጃ እንዲመደብ ማድረግና አሁን ያለውን በኮምፒዩተሮችና ኢንተርኔት ላይ አማርኛንም ሆነ በግዕዝ ፊደላት የሚፃፉ ቁንቋዎችን በቀላሉ ለመተየብም ሆነ ለማንበብ የሚያስችል መንገድ ላይ መድረስ ባልተቻለ ነበር።
በላቲን ፊደላት መተየቢያ የኮምፒውተር የጽሑፍ ገበታ ላይ ከ«ኤ» እስከ «ዜድ» 26 (A -Z)የተደረደሩ ፊደላት አሉ። ዶክተር አበራ ሞላ የኮምፒውተር የመጻፊያ ገበታ ላይ የሚገኙትን እነዚህን 26 የላቲን ፊደላት ጨምሮ ከ 1 እስከ 0 የተደረደሩ ቁጥሮችን እንዲሁም ቀሪ ምልክቶችን፤ በጥቅሉ 47 ምልክቶችን ልክ እንደ እንግሊዝኛው በግእዙም በአንድ ጥቁምታ እንዲጻፉ ማድረግ ችለዋል።
ዶክተር አበራ በአማርኛ ቋንቋ በሳድስ የሚነገሩ ቃላት በርካታ መሆናቸው ሳድስ ፊደላትን ኮምፒተር ገበታ ላይ በአንድ ምት ወይንም ጥቁምታ መተየብ የአጻጻፍ ፍጥነትን ያሻሽላል የሚል እሳቤ አላቸው። ለአብነት ያህልም ምግብ፣ ልብስ፣ ብርድ፣ ትምህርት፣ ድርቅ፣ የመሳሰሉት ቃላት ሙሉ ለሙሉ በሳድስ ድምጾች (ፊደላት) የሚጻፉ ናቸው። በተለምዶ ሳድስ ፊደላት በውስጣቸው የያዝዋቸውን አናባቢዎች በዶክተር ለማ የፊደል ገበታ መፃፊያ ስልት መተየብ አያስፈልግም።
ለአብነት ያህል ምግብ የሚለውን የአማርኛ ቃል ብንመለከት ኮምፒውተር ላይ ለመተየብ «ኤም»፣ «ኢ»፤ «ጂ»፣ «ኢ»፣ «ቢ»፣ እና «ኢ» የተሰኙትን በጥቅሉ ስድስት የላቲን ፊደላት መጠቀም ያስፈልጋል። ሆኖም ስድስቱን የፊደል ቊልፎችን ከመጫን ይልቅ አናባቢው «ኢ»ን በማስቀረት «ኤም»፣ «ጂ» እና «ቢ» ፊደላትን ብቻ በመጫን ምግብ የሚለውን ቃል በሦስት ፊደላት በአማርኛ መጻፍ እንዲቻል ነው ያደረጉት። ከ47ቱ የተቀሩት ፊደላት በሁለት ምት አለያም ጥቁምታ የሚጻፉ ናቸው።
ዶክተር አበራ ሞላ አዲስ ፈጠራ ተብሎ የባለቤትነት መብት ዕውቅና በዩናይትድ ስቴትስ ካሰጣቸው ሌላኛው እመርታ መካከል የኮምፒውተር የጽሑፍ ገበታ ላይ በላቲን ፊደላቱ «ኤ» እና «ኢ» 14 ቀለማትን እንዲጻፍ ማስቻላቸው ነው። ቀደም ሲል የመተየቢያ ገበታው ላይ ሁለቱ ፊደላት በሁለት ጥቁምታ አለያም ምት ሲጻፉ ፊደላቱ ሊሰጡ የሚችሉት ስድስት ቀለማትን ብቻ ነበር።
“ዶክተር አበራ እርስዎ የተማሩት የእንስሳት ህክምና ነው፤ እንዴት ወደ ኮምፒዩተር ትምህርት ሊያዘነብሉ ቻሉ ምክንያትዎ ምን ይሆን? “ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሸ ሲሰጡ፦ “ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን በርካታ ሀብቶች ያሉን ሕዝብ ነን። ምን ያህል እየተጠቀምን ነው? የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ ከእነዚህ ሀብቶች ውስጥ አንዱ የግዕዝ ቋንቋችንና ፊደል ነው። ይህ ፊደላችን ቀደም ባለው ዘመን ትኩረት ተሰጥቶት በትምህርት ቤቶች፤ በብሔራዊ ፈተናም ጭምር ይሰጥ ነበር። ምናልባት የዛሬውን ሁኔታ የምናየው ቢሆንም ቀደም ባለው ጊዜ የነበረበት ግን በተሻለ ደረጃ የምናውቀው ነው፤ ያም ሆኖ የእዚህ ቋንቋና ፊደል ዕድገቱ ያን ያህል ነው? ከእዚህ ባለፈ ቀደም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራተኞች በተለይም የቢሮ ፀሃፊዎች አማርኛን ቋንቋ በጽሕፈት መኪና ላይ ሲጽፉ የእንግሊዝኛው ገበታ እንዳስቸገራቸው ተመለከትሁ፤ ይህ በውስጤ ጥያቄ አስነሳ “ ይላሉ።
በተጨማሪም የሚጽፉት የአማርኛ ጽሑፍም ትክክለኛው አይደለም፤ በይመስላልና በይሆናል የሚጻፍ ስለሆነ ችግሩ የጐላ መሆኑን አየሁ። ቋንቋውም መፃፍ ያለበት በደንበኛው የእራሱ ፊደል እንጂ በሚቀጠል ፊደል መሆን የለበትም ስልም አሰብኩ። ስለዚህ አሜሪካ ሄጄ ትምህርቴን መማር ስጀምር እ.ኤ አ በ1975ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምፒዩተርን አየሁ። ኋላም ለምርምሬ የምጠቀመው ይሄው መሣሪያ ሆነ። ከእዚያ መሣሪያው ለወደፊቱ ብዙ ጥቅም እንዳለው ሳይ ሃሳብ ማውጣትና ማውረድ ጀመርኩ ይላሉ። በእዚህም እኔ የምሠራው ነገር አዲስ በመሆኑ እራሴ ዘዴውን መፍጠር ነበረብኝ፤ ሆኖም ግን በግዴታም ቢሆን በእራሴ ጥረትና ተነሳሽነት ሥራው ሊሳካ ችሏል ይላሉ።
ዶክተር አበራ በእንስሳት ሕክምና ሙያቸውም በተለይ በኢምዩን ደፊሸንሲ Immune Deficiency Patent ይታወቃሉ። ባደረጉት ምርምርና ውጤት ኢምዩን ደፊሸንሲን በማስወገድ በየዓመቱ ሲጠፉ የነበሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንስሳቶችን ሕይወት ማትረፍ ችለዋል።
ከሰው ልጅ እናቶችና ከአንዳንድ የጦጣና ውሻ ዝርያዎች በስተቀር የሌሎች እንስሳት ማህጸኖች ኢምዩኖግሎቡሊን (Immunoglobulin) የሚባለውን የበሽታ መከላከያ ፕሮቲን ለጽንሶቻቸው በእርግዝና ጊዜ አያስተላልፉም። አጥቢ እንስሳት በእርግዝና ጊዜ በአካባቢው ለሚገኙት በሽታዎች መከላከያዎች በእንገርነት ያከማቹላቸውና አራሶቻቸው እንደተወለዱ ጡት ሲጠቡ የበሽታ መከላከያዎቹ ፕሮቲኖች ሳይለወጡ ከአንጀት ወደ ደም በመግባት ለጥቂት ሳምንታት ከበሽታዎች ይከላከሉሏቸዋል።
ጥጆቹ እንገሩን ሳያገኙ ከቆዩ ግን ወደ ደም መግባታቸውና መከላከያነታቸው ቀርቶ እንደ ተራ ፕሮቲን ምግብ ብቻ ይሆናል። ስለዚህ ጥጆች ሲወለዱ የኤድስ ቫይረስ የበሽታ መከላከያቸውን እንደጨረሰ ሰው ምንም መከላከያ ስለሌላቸውና አካባቢው ያሉትን የበሽታ ጀርሞች እየቀማመሱ በተለያዩ በሽታዎች የእራሳቸውን መከላከያ መሥራት እስከሚጀምሩ ድረስ እየተጠቁ አብዛኛዎቹ ይታመማሉ፣ ወደ አሥር ከመቶም ይሞታሉ። ታክመው የሚድኑትም አይጠረቁም። በኮሎራዶ እስቴት ዩኒቨርሲቲ (Colorado State University) የዶ/ር አበራ የድህረ ዶክትራል ምርምር ይህን ችግር ለመቋቋም መፍትሔ ሆኖ መጣ። በዶ/ር አበራ ሞላ ግኝት እስከ ለዘመናት ጠንቅ ሆኖ የቆየውን መድኃኒት የሌለውን የእንስሳትን ኤድስ ዓይነት ሁኔታ (Failure of Passive Transfer / FTP) ሃምሳ በመቶ መቆጣጠርና ማስወገድ ተችሏል።
የዶክተሩ ዘዴ ለተለያዩ ለማዳና የዱር እንስሳት ጥቅም ላይ እየዋለ እስከ ዛሬ ቀጥሏል። ዩናይትድ እስቴትስ ውስጥ በየዓመቱ ከሚወለዱት 40 ሚሊዮን ጥጃዎች 4 ሚሊዮን የሚሆኑት በመድኅን ማነስ ሊሞቱ ይችሉ የነበሩት በዶክተሩ ግኝት ባለፉት አርባ ዓመታት ሊተርፉ ችለዋል። በተጨማሪም ሰላሳ በመቶ ጥጃዎች ሕክምና እንዲያገኙ ሆኗል።
እኛም በዚህ ለሀገርና ሕዝብ በሙያቸው የሠሩና ታላቅ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ኢትዮጵያውያን በሚመሰገኑበት አምዳችን የግዕዝ የኮምፒዩተር ፅሁፍ አባትና የእንስሳት ሐኪም የሆኑትን ዶክተር አበራ ሞላን አመሰገንን። ሰላም !
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም