“የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ የዞኑንና የክልሉን ሁለንተናዊ ገጽታ ይቀይራል” – አቶ ሀብታሙ ካፍትን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር

የቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ከሚገኙ ስደስት ዞኖች አንዱ ነው። የዞኑ መቀመጫ የሆነችው ሚዛና አማን ከተማ ከአዲስ አበባ በ585 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፤ በ6 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረች ነች። ዞኑ በማር፤ በቡና፤ በቅመማ ቅመምና በሌሎች የግብርና ዘርፎች እምቅ ሀብት እንዳለው ይነገራል። ካለው ሀብት አንጻር የዞኑ ሕዝብ ያለው የልማት ተጠቃሚነት፤ የመልካም አስተዳደር፣ የትምህርት፣ የጤና ተደራሽነትና መሰል ጉዳዮች ላይ ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ጋር ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ እንደ ክልል ከተዋቀረ አንስቶ በዞኑ ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ሀብታሙ፡- የቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች መካከል አንዱ ሲሆን ሚዛን አማን ከተማን ማዕከል አድርጎ የተመሰረት ነው። በዞኑ ሸኮ፣ ጉራፋርዳ ፣ ደቡብ ቤንች ፣ ሰሜን ቤንች፤ሼ ቤንች ፣ ሲስካካ ከተማ አስተዳደር፤ ሚዛን አማን እና ጊቤንች በሚባሉ ሁለት ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ስድስት ወረዳዎች በአጠቃላይ ስምንት ወረዳዎችን በስሩ የያዘ ነው።

ክልሉ እንደክልል ሲመሰረት ሕዝቡ በርካታ የልማት ጥያቄዎች ያነሳ ነበር። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ መጀመሪያ በክልል፤ በዞን እና በወረዳ ደረጃ የሚመለሱ ጥያቄዎችን የመለየት ስራዎችን አከናወነ። ቀጥሎም ጥያቄዎችን ኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊና እና ፖለቲካዊ በሚል በዘርፍ የማስቀመጥ እና የመለየት ሥራዎችን አከናወነ። በልየታው መሰረት ወደ ሥራ ገባን። ይህም የህብረተተሰቡን ጥያቄዎች ሁሉንም ባይሆን አብዛኛውን መፍታት አስችሎናል።

የቤንች ሼኮ ዞን ለክልሉ በግብርናው እና በማዕድን ዘርፉ ዋና የኢኮኖሚ ስበት ማእከል ነው ብለን እናምናለን። ይህን ሀብት በዘላቂነት ለማልማት እና ለመጠቀም ደግሞ ከምንም በላይ ሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ ነው። በመሆኑም በኢኮኖሚ ፣በማህበራዊ፣ በፖለቲካና በአስተዳደር ዘርፍ ያሉ ልዩነቶች በማጥብብ አንድነቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ፣ የቀጣናውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ቁልፍ፣ቁልፍ ተግባራትን በስፋት ተከናውነዋል።

ለአብነት ያህል በኢኮኖሚው ዘርፍ በግብርናው ላይ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል፤ እየተከናወኑም ነው። በግብርናው ዘርፍ የቡና፣ የቅመማ ቅመም፣ ዓመታዊ ሰብል እና ማር በዞኑ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ይመረታሉ። በ2013-2014 ዓ.ም የምርት ዘመን ዞኑ ከ30ሺ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል። ይህን ለማስቀጠል በማሰብ በዘንድሮው ዓመት በርካታ የቡና ችግኞችን ለመትከል ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጓል፤ ያረጁ እናት የቡና ተክሎችን የማስጎንድል ሥራ ተሠርቷል፤ በተጨማሪም በቡና ጥራት ላይ የቡና አሰባሰብ፣ ክምችትና ግብይት ላይ ከፍተኛ ሥራዎች ተሠርተዋል።

በቅመማ ቅመም ዘርፍ (ቁንዶ በርበሬ፤ ሔል፤ እርድ፤ ኮረሪማ እና መሰል ቅመማ ቅመሞችን) በከፍተኛ ደረጃ ለማእከላዊ ገበያ የሚያቀርብ ዞን ነው። በዚህ ዘርፍ ባለሀብቶች እና አርሶ አደሮችም በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ። ዞኑም ምርቱን የማስፋት እና ጥራቱን የማስጠበቅ ሥራ እያከናወነ ነው።

ሌላው በግብርናው ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራባቸው ከሚገኙ መስኮች አንዱ የፍራፍሬ ምርት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በዞኑ የሙዝ ማሳዎችን ጫካ በሚባል ደረጃ በኩታ ገጠም በማረስ በርካታ ሺህ ሄክታር መሬትን እየለማ ይገኛል። ከሙዝ በተጨማሪ በዞኑ የአቮካዶ ምርት በከፍተኛ ደረጃ እየተመረተ ነው።

ቀደም ሲል የነበረው የአቮካዶ ዝርያ ለዘይት ምርት ጥሩ ስላልነበር አሁን ላይ በተሻሻሉ የምርጥ ዘሮች ተተክተዋል። ይህም ከአቮካዶ ፍሬ ዘይት ያመርት ለነበረው የጅማ ዞን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ምርት በማቅረብ ኢንዱስትሪያል ፓርኩ የነበረበትን ከፍተኛ የግብዓት ችግር መፍታት ተችሏል። አሁን ላይ አቮካዶን በንቅናቄ ለማልማት የዘመቻ ሥራዎች ተጀምረዋል።

ዓመታዊ ሰብል በተመለከተ በቆሎ፣ ሩዝ እና መሰል ሰብሎችን እያመረትን ነው። ለአርሶ አደሩም የምርጥ ዘር፤ ማዳበሪያና ሌሎችን ግብአቶች በማሟላት ላይ እንገኛለን። ከ20ሺ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያዎችን ማሰራጨት ተችሏል። በዘንድሮው የበልግ ወቅት ብቻ ከ90 ሺህ ሄክታር በላይ የበቆሎ ማሳዎችን ማልማት ተችሏል።

አዲስ ዘመን፡- የቡናና ሻይ ባለስልጣን በሚያርገው የቀጥታ የገበያ ትስስር ቡና ለዓለም ገበያ እየቀረበ መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህ አሰራር አምራቹን እና ነጋዴውን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገ መሆኑ ይነገራል። ይህ ምንያህል እውነት ነው ?

አቶ ሀብታሙ፡- የቀጥታ ትስስሩ እንደተጀመረ በነበሩት ዓመታት በተለይም በ2013-2014 ዓ.ም የምርት ዘመን በቡና ግብይቱ ጥሩ ውጤት ተገኝቶ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ የቀጥታ የትስስር ግብይት ሥርዓት በቡና ግብይት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው። አርሶ አደሮች በየጊዜው ወደ ቢሮ በመምጣት ቡናቸው ተወስዶ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ይናገራሉ። በቡና ግብይት ሥርዓቱ ላይም እኛም እንደ ዞን እየተቸገርን ነው።

ከዚህ ቀደም ግብይቱ የሚፈጸመው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢ.ሲ.ኤክስ) ነበር። በዚህም አንድ የቡና አልሚ ለቡና ገዥው ሲሸጥ አቅራቢውም ኤክስፖርተሩም ሁለቱም ይታወቃሉ። ቡናውም ደረጃ ስንት እንደሆነ ይታወቃል። ከደረጃ በመነሳትም ቡናው ለሀገሪቷ ገቢ ማስገኘት ይችላል አይችልም የሚለውም ይታወቃል። ቡናው ከሀገር ውጭ ሲላክም ወዴት ሀገር እንደተላከ ምን ያህል ገቢ እንዳስገኘ ይታወቃል።

ይህንንም መረጃ በመያዝ ቡናው ከደረጃ በታች እንዲሆን ያደረጉ ሰዎችን በመያዝ ማጠቢያ ማሽኑን በመለየት፤ ማከማቻው ከማን እንደሚረከብ በመጠየቅ የተለያዩ ስልጠናዎችም ይሰጣቸው ነበር። አሁን ግን ግብይቱ በምርት ገበያ ስለማይፈጸም ከላይ የተጠቀሱትን ልየታዎች ለማከናወን ተቸግረናል።

በተጨማሪም ቡና በኢሲኤክስ ሲሸጥ ምን ያህል ምርት ከየት አካባቢ እንደሚሰበሰብ የመለየት ሥራ ይከናወን እና ወረዳዎች ለማእከላዊ ገበያ ባቀረቡት ልክ ነጋዴዎች ለወረዳው ገቢ ያስገባሉ። በገባው ገቢም ወረዳዎች የተለያዩ የልማት ተግባራትን እንዲያከናውኑ ይደረግ ነበር። አሁን ላይ ግን ነጋዴዎች እና ግለሰቦች እንኳን ለወረዳው ገቢ ሊያስገቡ ይቅርና ምርቱን ለሚያቀርብላቸው ገበሬም ክፍያ መፈጸም አልቻሉም። ምክንያቱም በቀጥታ ትስስር በሚደረገው የግብይት ሥርዓት ነጋዴዎች ከሸጡት ቡና ብር ማግኘት አልቻሉም።

ለምሳሌ ሸኮ ወረዳ 29 ሚሊዮን ማግኘት ከነበረበት ገቢ ውስጥ ያገኘው 9 ሚሊዮን ነው። በዚህም አርሶ አደሮች ፣ ነጋዴዎች እና ዞኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል።

አዲስ ዘመን ፡- በቀጥታ ትስስሩ ከነጋዴዎች ተረክቦ ወደውጭ የሚሸጠውን ሰው ነጋዴዎች እንደማያውቁት ይናገራሉ። በተጨማሪም በሀገሪቱ ያለው የነጻ ገበያ ሥርዓት ነው ቢባልም “ኢሲኤክስ” በፈለገው ዋጋ መግዛት እንዳይችል በመከልከሉ አምራች ገበሬዎች እና ነጋዴዎች አማራጭ ገበያ እንዳይኖራቸው እና ብድር ማግኘት እንዳይችሉ ማድረጉ ይነገራል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

አቶ ሀብታሙ፡- በዚህ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቻለሁ። ነገር ግን ይህ አሰራር በፖሊሲ የተቀመጠ አቅጣጫ ነው። መስተካከልም ያለበት ነው። ዞኑ ከፍተኛ የቡና ምርት ለገበያ አቅራቢ እንደመሆኑ የቡና ጥራትን የማስጠበቁን ሥራ በከፍተኛ ደረጃ እያከናወነ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ባለው የቡና ግብይት ሥርዓት የነጋዴው ኢኮኖሚውም ሆነ ህይወቱ ተዛብቷል። አርሶ አደሮችም ተሰብረዋል። በዩኒየንና በአርሶ አደር፣ በአርሶ አደርና በነጋዴ መካከል ያለው ትስስርም ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ገብቷል።

እኔን በጣም እያሳሰበኝ ያለው ቀጥታ ትስስሩ በፈጠረው ችግር ምክንያት ከዚህ ቀደም ለማእከላዊ ገበያ ይቀርብ የነበረው ቡና አሁን ላይ የት እንደሚገባ አለመታወቁ ነው። በአንጻሩ ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን ለመጠገን እና ገበያውን ለማረጋጋት እንዲሁም የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ዶላር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነች። ይህ ችግር ሲጨመር ደግሞ ነገሮችን ከባድ ያደርጋቸዋል። ምክንያቱም ቡና በሀገር ውስጥ ገበያ ሲሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አይቻልም።

አሁን ያለው አሰራር የሀገርን፣ የአርሶአደርን እና የነጋዴን ኢኮኖሚ የሚጎዳ ሆኖ ነው ያገኘነው። የማን ቡና ጥራት አለው፤ የማነው የሌለው የሚለውን ለማወቅ የሚያስችለውን አሰራር የተወሳሰበ አድርጎታል። አጠቃላይ ጉዳዩ ለዚህ ቀጣና አደገኛ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የዞናችሁ ገበሬዎች እና ነጋዴዎች ለማእከላዊ ገበያ ብዙ ሺህ ቶን ቡና ቢያቀርቡም ያቀረቡት ቡና ግን የዚህ አካባቢ ተብሎ ስም እንደሌለው ቅሬታ ያቀርባሉ። ለምንድን ነው ስም ያልተሰጠው?

አቶ ሀብታሙ፡- እኔ ቡና ዘርፉ ላይ የቆየሁ ባለሙያ ነኝ። ይህ የስም ጉዳይ የረጅም ጊዜ ፈተና እና መመለስ ያልቻለ ጥያቄ ነው። ማንን እንደሚጎዳ ባላውቅም በተደጋጋሚ ጥያቄው ይቀርብ ነበር። እየቆየ ሲሄድ አንድ መፍትሄ ተብጅቶ ነበር። ይህም ዩኒኖችን በአካባቢው ስም በመፍጠር ቡናውን በዩኒየኖች ስም መሸጥ የሚል ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ የቀጥታ ትስስር በፈጠረው ችግር ዩኒየኖቹ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክመዋል። ሥራ ያቆሙም አሉ።

የግብይት ሥርዓቱ ዩኒየኖቹ የባንክ ብድር ለማግኘት ተጽእኖ ፈጥሮባቸዋል። ለምሳሌ የቤንች ማጂ ጫካ ቡና እና የቤንች ማጂ አንድነት ዩኒየን ቡና ‹‹ብራንድ›› ሆኖ ነበር። ብዙ አርሶአደሮች ፈረንሳይ፤ ጀርመን፤ አሜሪካ ድረስ ሄደው ትስስር ፈጥረው ነበር። አሁን ላይ ዩኒየኖች ብድርና ሥራ ማስኬጃ በማጣታቸው እየፈረሱ ‹‹ኮላፕስ›› እያደረጉ ነው። በዚህ ጉዳይ አሁንም ለማእከላዊ ገበያ የሚቀርበው ቡና ‹‹በብራንዱ›› እንዲሸጥ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን ፡- አሁን ባለው የቡና ገበያ ሥርዓት የቡና ቅምሻ የሚያከናውኑ እና ደረጃ የሚሰጡ ተቋማት በቅርበት ባለመኖሩ ነጋዴዎች ላልተፈለገ ወጪ እና እንግልት መዳረጋቸውን ይገልጻሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ሀብታሙ፡- የነጋዎች ቅሬታ ትክክል ነው። በዚህ ዞን ከፍተኛ የቡና ምርት ይገኛል። 30 ሺህ ቶን ቡና ከዚህ ተጭኖ ወጥቶ ሌላ ቦታ ደረጃ እና ስም እንዲወጣለት ከማድረግ እዚሁ ደረጃ ወጥቶለት ቢሄድ ወጪ ከመቀነስ አንጻር ጥሩ ነው። እዚህ የደረጃ መስጫ ማእከል ቢኖርም ጥሩ ነው። ለነጋዴዎችም ወጪ ቆጣቢ ነው። ከዚህ በፊት ኢሲኤክስ ደረጃ መስጫ እዚህ ከፍቶ ነበር። አሁን በተፈጠረው የግብይት ሥርዓት ማእከሉ የለም።

ማእከሉ ባለመኖሩ አሁን ላይ ከዚህ ዞን ቡና ጭነው የሄዱ ተሽከርካሪዎች የጫኑት ቡና ደረጃ እስከሚያገኝ እና የቡናው እርጥበት እስከሚቀንስ ተብሎ ሁለት ሶስት ወራት የሚጠብቁበት ሁኔታ አለ። በዚያ ጊዜ ለእያንዳንዱ ቀን ተሽከርካሪው ለቆመበት የሚከፍለው ነጋዴው ነው። ይህ ደግሞ ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርግ እና ነጋዴውን ከገበያ የሚያስወጣ ነው።

በዞኑ በርካታ ቡና አልሚዎችና ምርት መኖሩን ታሳቢ በማድረግ እና ነጋዴውም በቅርበት ምርቱን ደረጃ አስወጥቶ እንዲሸጥ የደረጃ ማእከል መገንባት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን ፡- በቅመማ ቅመም እና ማር ምርት የንግድ ሥርዓት ባለመፈጠሩ አምራቾች ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ይነገራል። ይህ ምንያህል እውነት ነው?

አቶ ሀብታሙ፡- በዞኑ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች በስፋት ይመረታሉ። ነገር ግን ደረጃ/ ስታንዳርድ ወጥቶለት ለምርት ገበያ (ኢሲኤክስ) ማእከል ለግብይት አልቀረበም። ባለሀብቶች ሲመጡም ሰብልና ቡና የማልማት ጥያቄ ይዘው ነው የሚመጡት። ቅመማ ቅመምን በኢንቨስትመንት ደረጃ ለማልማት የመጣ ባለሀብት የለም።

ዛሬ ላይ ግብርና አርሶ መኖር ብቻ አይደለም ንግድ ነው። የትኛውን ባመርት ፣ የትኛው ያዋጣኛል? ተብሎ ነው የሚሰራው። አምራቾች በአርሶአደር ደረጃ ነው ያሉት። ምርቱ ሲሰበሰብ ግን ከፍተኛ ነው። በዚህ ላይ የገበያ ትስስር ከመፍጠር አኳያ ክፍተት አለ። እስካሁን ያለው ትስስር ደካማ ነው። በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይህን ችግር መፍታት እንዳለብን ይሰማኛል።

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ያለው የጤና ጣቢያ ተደራሽነት ምን ያህል ነው?

አቶ ሀብታሙ፡- በጤናው ዘርፍ ከተደራሽነት አንጻር የመሰረተ ልማት ተደራሽነትና የአገልግሎት ተደራሽነት በመባል ይከፈላል። ከመሰረተ ልማት ተደራሽነት አንጻር በዞናችን ሁለት ሆስፒታሎች አሉ። አንዱ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚተዳደር የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሆስፒታል ሲሆን ፣ በቤንች ሼኮ ዞን የሚተዳደረው ደግሞ ሁለተኛው ነው። በተጨማሪም በዞኑ ጤና ጣቢያዎች በየወረዳውና በየክላስተሩ አሉ።

ሚዛን አማን ላይ የተሰራው እና ዩኒቨርሲቲው የሚያስተዳድረው ሆስፒታል የተገነባው በደርግ ዘመነ መንግሥት ሲሆን፣ ለአርባ ሺህ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ታሳቢ በማድረግ ነበር። አሁን ላይ ግን ሆስፒታሉ ከአቅሙ በላይ ለሁለት ሚሊዮን ሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ተገዷል። በዙሪያ ያሉ ዞኖች እና ክልሎች በሙሉ ሪፈራር የሚጽፉት ለዚህ ሆስፒታል ነው።

የሚዛን ሕዝብ ከ170 ሺ በላይ ነው። በመሆኑም ሚዛን ጤና ጣቢያ አንድ ጤና ጣቢያ መስጠት ካለበት አምስት እጥፍ በላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በየወረዳው ያሉት የጤና ጣቢያ አገልግሎቶች እንዳሉ ሆኖ ሚዛን አማን ላይ ከፍተኛ ችግር አለ።

በጤና ተቋማቱ በመሠረታዊነት የመድኃኒት አቅርቦት ችግር አለ። የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅት በሚፈለገው ልክ መድኃኒት የማቅረብ ችግር አለ። ይህ ደግሞ ከጤና መድህን ክፍያ ጋር ተያይዞ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

በዞኑ ውስጥ በተደረገው ግምገማ ማህበረሰቡ ማግኘት ያለበትን በተለይም በእናቶች ጤና ኤክስቴንሽን ላይ የመቀዛቀዝ ሁኔታ አለ፤ ይህን ለማስተካከል ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠና ተሰጥቷል። በአዲሱ የጤና ፍኖተ ካርታ የተቀዛቀዘውን የጤና ኤክስቴንሽን ለመመለስ በንቅናቄ ሥራዎች ተከናውነዋል።

አዲስ ዘመን፡- በጤና ጣቢያ ላይ ያለው ችግር የመድኃኒት አቅርቦት ብቻ ነው? የሚሰራጨውንስ በተገቢው ሁኔታ ከመጠቀም አንጻር ያለው ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሀብታሙ፡- ጤና ጣቢያ ላይ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዳለ ሆኖ የቀረበውን መድኃኒትም በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር አለ። ይህም በቀጣይ መታረም ያለበት በመሆኑ እንደአቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ ነው። በጤና ጣቢያዎች በእርዳታ መልኩ የሚመጡና በግዥ የሚመጡ መድኃኒቶችን በአግባቡ ለኅብረተሰቡ የመስጠት ችግር አለ። አልፎ አልፎ በተወሰኑ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ አካባቢያቸው ላይ የራሳቸው የግል ድርጅት በመክፈት መድኃኒቶችን ወደ ራሳቸው ድርጅት የመውሰድ ዝንባሌም ተስተውሏል፤ ይህንን ለማስተካከል እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ያለው የትምህርት ተደራሽነትና የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል ሥራ ምን ላይ ተሰርቷል?

አቶ ሀብታሙ፡- በትምህርት ዘርፉ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ ዞንም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በዞኑ በ2015 ዓ.ም በነበረው የስምንተኛ ክፍል ፈተና 10 ሺ 397 ተማሪዎች ፈተና የተቀመጡ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 2 ሺ 22 ተማሪዎች ፈተናውን አልፈዋል። በዚህም ውጤት መሠረት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የማለፍ ሁኔታ 26 በመቶ ላይ ይገኛል። በዚህ ተመሳሳይ ዓመት የ12ኛ ክፍል 4 ሺ 190 ተማሪዎች ፈተና ተፈትነው 94 ተማሪዎች በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። ይህም ሁለት በመቶ ነው። በሪሚዲያል 342 ተጨማሪ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል።

ይህ የሚያሳየው ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ነው። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና አካባቢው ላይም ብቁና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ሰፊ ጥረት እያደረግን ነው። ይህን ለማሳካት በዩኒቨርሲቲና በኮሌጅ ልዩ ድጋፍ እያደረግን ነው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪና የመጽሐፍት ጥምረታውን አንድ ለአንድ አድርሰናል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ከሕዝቡ 48 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የወረዳ በጀትን ጨምሮ 37 ሚሊዮን ሰብስበናል። ከዚህም በ22 ሚሊዮኑ ብር መጽሐፍት ታትመው ስርጭት ተከናውኗል።

አዲስ ዘመን፡- የዞኑን ሕዝብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊው መስክ ተጠቃሚ ለማድረግ ከዩኒቨርሰቲዎችና ሌሎች ተቋማት ጋር ያለው ትስስር እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሀብታሙ፡- ዩኒቨርሲቲዎች ከሚቋቋሙበት ዓላማ መካከል አንዱ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት መስጠት መቻል ነው። በዞኑ ለልማት ያለው ጸጋ እንዴት በተገቢው ሁኔታ ማልማት እንደሚቻል በጥናት ላይ የተደገፈ ሥራ በመሥራት ኅብረተሰቡን ማገዝ መቻል ነው። በዚህ ረገድ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሚዛን ካምፓስ በተመለከተ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው በቂ ምርምር ድጋፍ እየተደረገ አይደለም የሚል ነው።

በግብርና ዘርፍ ጉራ ፈርዳ ወረዳ ላይ 500 ሄክታር ለምርምር የሚሆን መሬት አለ። ይህ ቦታ ለዩኒቨርሲቲው ከተሰጠ 15 ዓመት ገደማ ይሆናል። ነገር ግን እስካሁን ምንም አይነት ልማት አለማበትም። በቦታው የሚጠበቀው በርካታ ምርምሮች ተሰርተው ማህበረሰቡን መጥቀም መቻል ነው። ነገር ግን ይህ ሊሆን ባለመቻሉ ለሌላ ድርጅት እንዲያለማው ተደርጓል። እየለማ አይደለም የሚል ሃሳብ ሲነሳ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ጣልቃ እየገባችሁ ነው የሚል ቅሬታ ስለሚነሳ የማህበረሰብ ችግር እንዲፈታ ለማድረግ ብዙም አልተቻለም።

አሁንም ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግር በቅንነት እንዲፈታ እንጂ ከዛ ያለፈ ምንም አይነት ፍላጎት የለንም። ከዚህ ውጪ በግብርና ላይ ‹‹ሸኮ ብሪድ›› የሚል ዝርያ ላይ ጥሩ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ እናውቃለን።

አዲስ ዘመን፡- የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለዞኑ ምን አንድምታ ይኖረዋል?

አቶ ሀብታሙ፡- የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታው እየተፋጠነ ነው። ለወሰን ማስከበር ዞኑ 112 ሚሊዮን ብር ክፍያ ፈጽመዋል። የኤርፖርት አጠቃላይ የግንባታ ወሰን ማስከበር 300 ሚሊዮን ይወስዳል። ይህ ሁሉ ግንባታ እየተከናወነ ያለው በውስን የመንግሥት በጀት ላይ ማህበረሰቡን በማስተባበር ነው።

ቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉ ዞኖች ለመልማት የሚያስችል ዕምቅ ሀብት ያለው ነው። የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታው ሲጠናቀቅ በብዙ ዘርፎች አካባቢው ይቀየራል። እዚሁ የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶች ወደ ማዕከል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደርሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተጨማሪም በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ አካባቢው እንዲመጡ እድል ይሰጣል። የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ዞኑን ብሎም የክልሉን ሁለንተናዊ ገጽታ ይቀይራል።

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋልና የፀጥታው ሁኔታ በተጨባጭ ምን ይመስላል?

አቶ ሀብታሙ፡- ከዚህ ቀደም ከቴፒ ጋር ተያይዞ ሸኮ ወረዳ፤ ደቡብ ቤንችና ጉራ ፈርዳ ወረዳዎች የፀጥታ ችግሮች ነበሩባቸው። ችግሩን ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፤ በተደራጀ መልኩ ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩ በመፈታቱ አሁን ላይ ለፀጥታ ስጋት የሆነ አንድም ቀበሌ የለም። አሁን ላይ በዞኑ ሁሉም ከፀጥታ ስጋት ወጥቶ ልማት ውስጥ ነው። አርሶ አደሩም ሆነ ኢንቨስተሮች በሙሉ አቅማቸው ልማት ውስጥ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ህዝብን ያሳተፈ ልማት ከማከናወን አኳያ የእናንተ ዞን በተጨባጭ ምን እያደረገ ነው?

አቶ ሀብታሙ፡- የዞኑ ሕዝብ ለልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ለዚህም ሼኮ ቤንች ላይ ማህበረሰቡ በራሱ ሙሉ ወጪ የ28 ሚሊዮን ብር ድልድይ እየገነባ ነው። ሼኮ ላይ በ22 ሚሊዮን ብር፣ ደቡብ ቤንች ላይ በ28 ሚሊዮን ብር ጤና ጣቢያ እየገነባ ነው። ለስፖርቱ ዘርፍም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በ80 ሚሊዮን ብር የስታዲየም ግንባታ እያካሄደ ነው። ማህበረሰቡ የሚችለውን በሙሉ እያደረገ ነው።

የሚቀሩ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆኖ አርሶ አደሩ ቡና በኪሎ እንዲያወጣ በማድረግ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ሼኮ ላይ 30 ሚሊዮን ተሰብስቧል። ቅድም ያልናቸው የመጽሐፍ ህትመት ወጪዎችን ከማህበረሰቡ በተሰበሰበ ገንዘብ ነው የተሰራው። በልማቱ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

በተለይ ከአውሮፕላን ማረፊያ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ማድረግ ያለብንን ግንኙነት እና ንግግር እያደረግን ነው። ለአውሮፕላን ማረፊያ ልማቱ ከፍተኛ ፍላጎት ስላለን ከፍተኛ ትኩረት ወስደን እየሰራን ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩንም በዚህ አጋጣሚ በዞኑ ሕዝብ ስም ማመስገን እንወዳለን። ምክንያቱም መሰረተ ድንጋይ ከማስቀመጥ ጀምሮ ሥራውም ትኩረት አግኝቶ በዚህ ልክ እና ፍጥነት እንድንሰራ ያስቻሉን እርሳቸው ናቸው።

የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በገበታ ለትውልድ የሚሠራው ‹‹ደንቢ ሎጅ›› ከተጠናቀቀ ቀጣናው ከፍተኛ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል ይሆናል። ስለዚህ እኛ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለን የአውሮፕላን ማረፊያውን እና ሎጁን እናስጨርሳለን።

አሁን ላይ ዞኑ አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ቢሄድም የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሙት ነው። የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቱን የገንዘብ ሚኒስቴር እና ፕላን ሚኒስቴር ድጋፎች እንዲያደርጉልን እንፈልጋለን።

አዲስ ዘመን፡- ዞኑ ለቱሪዝም ምቹ ከመሆኑ አንጻር የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ምን እየሰራችሁ ነው ?

አቶ ሀብታሙ፡- በዞኑ ከፍተኛ የቱሪዝም እምቅ ሀብት አለ። ወደ ደንቢ ሀይቅ ፣ በበቃ ፣ ሸካ እና ደቡብ ቤንች ብትሄዱ ተፈጥሮን ምንም ሳይነካ እና ሳይበረዝ ታገኙታላችሁ። ሌሎች ዓለማት ላይ ተፈጥሯዊ ነገሮችን ፈልጎ ማግኘት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። በመሆኑም ዞኑ ለቱሪዝም በጣም ምቹ ነው። ግን በፀጥታ ምክንያት ቀድሞ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘው ነበር። አሁን ላይ የአካባቢው ሰላም ወደነበረበት በመመለሱ ቱሪስቶች መጥተው እንዲጎበኙ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወንን ነው።

ክብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልዩነት ‹‹የደንቢን ሎጅ›› ፕሮጀክት ያስጀመሩት ዞኑ ባለው የቱሪዘም ሀብት በመደመማቸው ነው። ይሁንና አሁንም ዞኑ ካለው እምቅ ሀብት አንጻር የቱሪዝም ቦታዎችን የማስተዋወቅ ሥራ ላይ ክፍተት አለ። በተለይ ባህል እና ቱሪዝም ላይ ከፍተኛ የማስተዋወቅ ክፍተት አለ የሚለውን በግምገማ ለይተናል።

በቀጣይ በእርግጠኝነት በቱሪዝም ዘርፉ በርካታ ገቢ የሚያስገኙ ለዞኑ ብሎም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚደግፍ ሥራዎችን እናከናውናለን። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሚዛን ወዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ መጠየቁ ቀርቶ ሚዛንን ካለየሁ የሚልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

አዲስ ዘመን ፡- የአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቀደም ብሎ በደቡብብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሥር በነበረበት ጊዜ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚ አልነበረም የሚሉ አሉ። እዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው ?

አቶ ሀብታሙ፡- ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚ አልነበረም በሚለው ላይ ምንም አከራካሪ አይደለም። በእርግጥ የደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በነበርንበት ጊዜ መልካም ነገሮችም ነበሩ። ብሔር ብሔረሰቦች በመተሳሰብ የኖሩበት ሂደቶች ጥሩ ነበር። ይሁን እንጂ ከፍትሐዊ ተጠቀሚነት አንጻር ቅሬታዎች ነበሩ።

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከማዕከላዊ መንግሥቱ እና ከበፊቱ የክልል መቀመጫ ሀዋሳም ሩቅ ነው። በመሆኑም ቀደም ብሎ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አካባቢ ነባራዊ ሁኔታ የሚረዳ አካል ነበር የሚል እምነት የለንም። ይህ በትክክል የታዘብነው ነው። በደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በነበርንበት ወቅት ከአካባቢያችን የተመረጡ በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የመንግሥት ኃላፊነት የተቀበሉ ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ ዞኑ ወይም ኅብረተሰቡ ምን ይፈልጋል የሚለውን ይረዱ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ ይህ ስላልነበር የክልሉ አመራሮች ኅብረተሰቡ ምን እንደሚያስፈልገው አያውቁም ነበር። በዚህም የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ከልማት ተጠቃሚነት እርቆ ቆይቷል።

በወቅቱ አመራር ስለነበርኩ አብዛኛውን ነገር አውቀዋለሁ። ለግማሽ ቀን ስብሰባ ሁለት ቀን ተጉዘን ሀዋሳ እንሄድ ነበር። ሁለት ቀን ጉዞ ያደረክበት ስብሰባ ሶስት ሰዓት ተጀምሮ አምስት ሰዓት ላይ አልቋል ሊባል ይችላል። በዚህም አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የሀብት ፣ጉልበት እና ጊዜ ብክነት በተደጋጋሚ ያጋጥመው ነበር። በዚህ የተነሳ በወቅቱ የማህበረሰቡን ጥያቄ የሚሰማ እና የሚፈታ እንዲሁም የሚረዳ መዋቅር እና አደራጃጀትም አልነበረም። አሁን ላይ እነዚህ የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል። ይህ ደግሞ ለሕዝባችን ታሪካዊ ምላሽ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- በአዲስ ክልል ውስጥ እንደመገኘታችሁ ዞኑን ብሎም ክልሉን ለማስተዳደር አዲስ መመሪያዎች መቅረጽን ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር የሚፈጠሩ ክፍቶችን እንዴት እየፈታችሁ ነው?

አቶ ሀብታሙ፡- በአዲሱ ክልል በርካታ እየተሻሻሉ ያሉ መመሪያዎች፣ ሕጎች እና ደንቦች አሉ። በሂደት ላይ ያሉም አሉ። ከሠራተኛ ጋር ተያይዞ የመዋቅር ሪፎርም ተድርጓል። አሁን በቅርብ ጊዜ ደግሞ የገጠር መሬት ግብርና የተመለከተ ማሻሻያ እየተደረገ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

አቶ ሀብታሙ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

በሞገስ ተስፋ፣ ሙሉቀን ታደገና መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You