በአዲስ ዘመን ድሮ የትውስታ ማህደር ውስጥ ብዙ መልክና ቁመና ያላቸውን የዘመን መስታወቶች ከፊት ያቆምልናል፡፡ የቀድሞውን ዘመን የሀገር፣ ራስንና ዓለምን ገፅታ እንድንመለከትበት ያደርገናል፡፡ ዛሬ ከሚያስታውሰን ጉዳዮች መካከል አንዱ የሴቶች አውሮፕላን አለመንዳት ጉዳይ ቅሬታን አስነስቷል የሚል ነው፡፡ “ታኑስ ተገለበጠች ቮልስ ተጋጨች” ከእነዚሁ ጋር ማህበረሰባዊና ማህበራዊ ጉዳዮችም ይኖራሉ፡፡ “አምቡላንሱ እንዴት ተመለሰ?”፤ አካልን ከአካል ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ከተደረገው ሴራ መልስ፤ ለኤርትራ ህዝብ ከቀረበው የሰላም ጥሪ ተቀንጭቦ የሰፈረው ጉዳይም ከዚሁ ተካቷል፡፡
የሴቶች አውሮፕላን አለመንዳት ቅሬታን ፈጠረ
“ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ከጓዳ ከመደበቅ፤ ዳዊት ከመድገም አልፈን ዘመናዊ ዕውቀትን በመሳተፍ ከሚኒስትርነት ማዕረግ በደረስንበት የሥልጣኔ ዘመን፤ በአውሮፕላን ነጂነት ተግባር ላይ ተሳታፊ አለመሆናችን የሚያሳዝን ነው” ሲሉ የመጀመሪያዋ አውሮፕላን ነጂ የነበሩት ወይዘሮ ሙሉ እመቤት እምሩ ቅሬታቸውን ገልጠዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከአፍሪካ የመጀመሪያይቱ አውሮፕላን ነጂ የነበሩት ወይዘሮ ሙሉ እመቤት፤ አውሮፕላን ለመንዳት የበቁት ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ፈረንሳዊት ወይዘሮ አውሮፕላን ነዳች የሚል ዜና በጋዜጣ ላይ አንብበው እኔስ እንደ እሷ ለመሆን ምን ይከለክለኛል በሚል መንፈሳዊ ቅናት ተነሣሥተው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ሙሉ እመቤት አውሮፕላን ለመንዳት የቻሉት እንዴት እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ “በመጀመሪያ በጋዜጣ ላይ የሠፈረውን ዜና አነበብኩ፡፡ አሣዳጊዬ ለነበሩት ደጃዝማች መንገሻ ይልማ፤ ለጃንሆይ ነግረው አውሮፕላን መንዳት እንድማር እንዲጠይቁልኝ ለመንኳቸው፡፡ እሳቸውም ግርማዊነታቸውን በማስፈቀድ እንድማር ተደረገ፡፡ በካፒቴን ባህሩ ካባ አስተማሪነት “ሞት” በተበላቸው አውሮፕላን መንዳት ተማርኩ፡፡ ትምህርቱም የፈጀብኝ ሁለት ወር ብቻ ነበር” ብለዋል፡፡(አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 1963ዓ.ም)
ታኑስ ተገለበጠች ቮልስ ተጋጨች
ግንቦት 8 ቀን ለትናንት አጥቢያ ሌሊት በደብረዘይት መንገድ ከትሪኒ ዳድና ቶቤጎ ኤምባሲ አጠገብ ቁጥር 24335 የሆነ ታኑስ አውቶሞቢል ተገልብጧል፡፡ እንዲሁም አፍንጮ በር አጠገብ ሰሌዳዋ 4825 የሆነ ቮልስ ከኮረንቲ እንጨት ጋር ተጋጭታ ከባድ አደጋ ደርሷል፡፡
ታኑስ በደብረ ዘይት መንገድ ከጎዳናው ውጪ የግራ በኩል ድልድዩን ጥሳ ከጉድቢያው ውስጥ በጎኗ ተጋድማ ግማሽ አፍንጫዋን ከመሬት ቀብራ ታይታለች፡፡ ቮልስዋገኗም ከአፍንጮ በር አጠገብ ከሚገኘው ድልድይ አንጻር ከምሰሶ ጋር ተዋዳ ለብዙ ደቂቃዎች ቆይታለች፡፡
….
ታኑስ በጎኑ ተጋድሞ ለጥቂት ሰዓቶች በወጪና በወራጁ ከተጎበኘ በኋላ፤ በሕዝብ እርዳታ ተቃንቶ ከጉድቢያው ሲወጣ፤ ከግንባሩ በስተኋላ የሚገኘው ፓራውልት ከመሰርጎዱ በስተቀር፤ በሰው ላይ አደጋ ባለመድረሱ፤ እንደወጣ ወዲያው እየተነዳ ለመሔደ ችሏል፡፡
ቮልስዋገኗ የተጋጨችው ከሌሊቱ 8 ሰዓት ገደማ ሲሆን፤ መኪናዋ ከአገልግሎት ውጪ ስትሆን፤ መቀመጫዎች ተገለባብጠዋል፡፡ ከመሪው አጠገብ የደም ነጠብጣብ ታይቷል፡፡
(አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 193ዓ.ም)
አምቡላንሱ እንዴት ተመለሰ?
ለሲዳማ ክ/ ሀገር ሰፊ ሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በታኅሳስ ወር 494 (አራት) የአምቡላንስ መኪኖችና 6 ሞተር ብስክሌቶች ለክ/ሀገሩ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በርዳታ መገኘታቸው የሚታወስ ነው። ከዚሁ ርዳታ ውስጥ ለቦረና አውራጃ አንድ አምቡላንስና 1 ሞተር ብስክሌት ተመድቦ ነበር። ነገር ግን ይኸው አምቡላንስ 2(ሁለት) ወር ተኩል በክ/ሀገሩ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከቆየ በኋላ የአውራጃው አስተዳደር ለመለዋወጫና ለማስመጫ ወይም ለማንቀሳቀሻ ከሕዝብ ገንዘብና የአውራጃው ቀይ መስቀል ባሟላው ወጪ ለሁለት ወር ያህል አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ ባለፈው ግንቦት ወር እንዲመለስ ተደርጓል። አምቡላንሱ የመጣው ለሰፊው የነገሌ ከተማ ሕዘብ በቋሚነት አገልግሎት እንዲሰጥ ነው ወይስ ለ2 ወር ኮንትራት?
ማሪዎች ጥላሁንና ደረጀ (ከነገሌ)
(አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 1968ዓ.ም)
ስማኝ ወገኔ
“…መከፋፈል ለአድኅሮት ጥቃት ተመቻችቶ መገኘት መሆኑን ጠንቅቀን ስለምናውቅ፤ ማንኛውንም የመገንጠል አዝማሚያ ስንታገል ቆይተናል። በተለይ አሁን የምንገኝበት ታሪካዊ ሁኔታ ዳግም መገንጠል ፍጹም ጎጂና ፍላጎታችንን የሚፃረር መሆኑን ስለምንገነዘብ አጥብቀን እንታገለዋለን…
…በስደት ኑሮ ከቤተሰቦቻችሁ ተነጥላችሁ ከሀገራችሁ ርቃችሁ ከምትኮሩበት ባህላችሁ ተገልላችሁ የሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሆናችሁ መኖር ይብቃችሁ እንላለን”…
…በተሳሳተ ዓላማ ሥር ሆናችሁ ኤርትራን ከእናት ሀገሯ በመገንጠል የሕዝቡን አንድነት ለማዳከም ተሰልፋችሁ ቆመንላችኋል የምትሉን ወገኖች እኛ የኤርትራ ክፍለሀገር ሕዝብ አጥብቀን የምንመኘው ሰላምን፤ አንድነትን እንጂ ጦርነትን የተገነባውን ማፍረስንና መገነጣጠልን አለመሆኑን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ግልፅ ሊሆንላችሁ ይገባል።
…መብታችሁና ጥቅማችሁ ሳይከበር በሰቀቀን ሕይወታችሁን የምትገፉ ወገኖቻችን የስደት ኑሮ ያብቃ እንላለን…እናንተ በባዕድ ሀገሮች ባክናችሁ፤ ዝርያዎቻችሁም ሀገር አልባ ሆነው መጥፋት የለባቸውም። እንላለን።
ስለዚህ የተያያዝነውን ሕዝቡ ራሱን ለማስተዳደር የሚያስችለውን የኤርትራን ራስ ገዝ የማቋቋም ታሪካዊ ተግባር በጥሞና በማስተዋል የሰላም ጥሪውን ተቀብላችሁ ወደ ሕዝባዊ ዓላማ እንድትመጡ ዳግመኛ እናስገነዝባችኋለን።
የኤርትራ ሕዝብ የሰላም ጥሪ
(አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 1980ዓ.ም)
አንድ ጥያቄ አለኝ
-ጳውሎስ ኞኞ
* ከባላገር እየኮበለሉ ከተማ ስለሚገቡት ሴቶች ምን ዘዴ ይገኛል?
አድማሱ ለማ(ከጂማ)
-ዘዴው በመጠናት ላይ ነው።
* ከአንዲት ልጅ ጋር ተዋደናል። እንዳንጋባ ሃይማኖታችን የተለያየ በመሆኑ እንቢ አለች። በሃይማኖት የተለያየ ሰው እንዳይጋባ የሚከለክል ሕግ አለ?
በፍቅር የሚዋኝ(ከአሥመራ)
-የለም
* በመንገድም ሆነ በማንኛውም ቦታ ሴቶች ሲያዩኝ ያደንቁኛል። ምን ይሻለኛል?
አዛገ አድማሱ
-ምናልባትም ምን ዓይነት አስቀያሚ ነው እያሉ ይሆናል የሚያደንቁህ። ራስህን አታኩራ።
(አዲስ ዘመን መስከረም 5 ቀን 1963ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም