‹‹የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ የፀጥታ ሥራው ከሰዎች አልፎ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሚታገዝ ይሆናል››-አቶ ጌታሁን አበራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ም/ ቢሮ ኃላፊ

አዲስ አበባ ከተማን በሕዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት ሰላምና ፀጥታ የሰፈነባት፤ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ለኑሮ፣ ለሥራ እና ለመዝናኛ ተመራጭ የሆነች ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በተለይም ከተማዋ ሰላምና ፀጥታዋ የተረጋገጠ ይሆን ዘንድም በብዙ እየተለፋ ይገኛል። ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ከሚወጡ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ካሉ ተቋማት መካከል ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ አንዱ ነው።

አቶ ጌታሁን አበራም በቢሮው የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ናቸው። አቶ ጌታሁን ወደዚህ ተቋም ከመምጣታቸው በፊት በተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል በክፍለ ከተማ ደረጃ የፍትህ ጽህፈት ቤት አቃቤ ሕግ፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት በኃላፊነት የሠሩ ሲሆን፤ በቼሻየር ፋውንዴሽን ውስጥም የድርጅቱ የፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአዲስ አበባን የጸጥታ ሁኔታ በመምራት ላይ ይገኛሉ። እኛም የአዲስ አበባን ሰላምና ጸጥታ በተመለከተ ከአቶ ጌታሁን አበራ ጋር ቆይታ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፦ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ተግባርና ኃላፊነቱ ምንድን ነው? ከሚለው እንጀምር

አቶ ጌታሁን፦ ቢሮው በአዋጅ 74 /2014 የተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት አለ፤በዚህ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ቢሮው የከተማዋን ሰላም ደህንነት ማስጠበቅ አንዱ ኃላፊነቱ ሲሆን፤ ሕዝቡን በጸጥታ ጉዳይ ላይ ማሳተፍ ደግሞ ሌላው ተግባርና ኃላፊነቱ ነው። በዚህም ሕዝቡን ማወያየት፤ ማደራጀት የሰላም ባለቤት ራሱ እንዲሆን የማቀናጀት ሥራንም እንሠራለን።

በሕጉ ላይ እንደተቀመጠው የከተማዋን ሰላም እንዲጠበቅ ማድረግ ሰዎች በሰላም ሰርተው፣ ተምረው፣ ነግደው እንዲገቡ ማስቻል በጠቅላላው ከተማዋ ከየትኛውም አዋኪ ነገር ወጥታ ሰላሟ የተረጋገጠ ለመኖሪያ ምቹ የሆነች እንድትሆን ማስቻል ይጠቀሳል።

በሌላ በኩልም በፀጥታ ጉዳዮች የከተማው አስተዳደር ዋና የፀጥታ አማካሪ ሆኖ ይሠራል፤ ለፀጥታና ሰላም አስጊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ተገቢ የሆነ አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም እንደ አግባብነቱ ራሱ ወይም ከሚመለከተው አካላት ጋር በመቀናጀት የእርምት እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል።

የግጭት መንስዔዎችን በጥናት ይለያል፣ ግጭት እንዳይከሰት ይከላከላል፤ ሲከሰትም ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም ይፈታል፤ በከተማው ልዩ ልዩ ሃይማኖትና ቤተ-እምነት ተከታዮች መካከል ሰላምና መከባበር እንዲሰፍን ለማድረግና ግጭትንም ለመከላከል እንዲቻል አግባብነት ካላቸው የፌዴራልም ሆነ የከተማው አስተዳደር አካላት፣ የሃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ይሠራል፤

እነዚህ ሥራዎች እየተሠሩም ኅብረተሰቡን በየሚያውኩ ጉዳዮች ሲከሰቱም በሕግ አግባብ ሥርዓትን የማስያዝ በዚህ ደግሞ ለነዋሪው ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ሥራን ይሠራል። ከዚህም በተጨማሪ እንደ ትምህርት ተቋማት፣ የእምነት ተቋማትና ሌሎችም የሚሰጡት አገልግሎት ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ አዋኪ ድርጊቶችን የማስቀረትና የማረም ተግባራት ይሰራሉ።

በግጭት መከላከል፣ አያያዝም ሆነ አፈታት፣ በነዋሪው ደኅንነት፣ ሰላም እና ፀጥታ አጠባበቅ ጉዳዮች ዙሪያ አግባብነት ካላቸው የፌዴራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደር እና ሌሎች አካላት ጋር የሥራ ግንኙነቶችን ያደርጋል፤ እንደ አግባብነቱ ችግሮችን በተናጠል ወይም በጋራ የመፍታቱን ሥራ እየሠራ ይገኛል ።

በሌላ በኩልም የቢሮ ሕግና ሥርዓት መከበሩንና የህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት መጠበቁን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስና በስውር የነዋሪውንና የመንግሥትን ጥቅም ጉዳት ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችንና ድርጅቶችን በመከታተል ነዋሪውንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ይከላከላል።

ከፀጥታ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ቅሬታ እና አቤቱታዎችን ይቀበላል፣ ይመረምራል፣ እንዳግባብነቱ ራሱ ወይም በተጠሪ ተቋምና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቅሬታዎቹና አቤቱታዎቹ መልስ እንዲያገኙ ያደርጋል። ለሕግ አስከባሪ አካላት እና ለነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አቅማቸውን በመገንባት የሕዝብ አገልጋይነት ሚናቸውን እንዲወጡ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፦ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም ከሰላም እጦት ስጋት ነጻ እንድትሆን የምትሠሩት ሥራ ምን መልክ አለው?

አቶ ጌታሁን፦ በበጀት ዓመቱ ከያዝነው እቅድ ዋነኛው ኅብረተሰቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ ነው። ይህ ማለት እንግዲህ ሰፊ እቅድ ነው። መዲናዋ ትክክለኛ ነው ብሎ ማለት ባያስደፍርም ከ6 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ ይኖራል ተብሎ ነው የሚታሰበው። ይህንን ነዋሪ የሰላም ባለቤት ማድረግ ሲባል በከተማዋ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን ሕዝቡ እንዲያውቃቸው ማድረግ አንዱ በመሆኑ ይህንንም ሥራ የምንሠራው በተለያዩ ጊዜያት መድረክ እየፈጠርን በማወያየት ነባራዊውን ሁኔታ በማስገንዘብ ነው።

እንደ ከተማ አብዛኛው ነዋሪ ጋር መድረስ ፀጥታን ለማስከበር አይነተኛ መንገድ በመሆኑ ኅብረተሰቡን በሴቶች፣ በወጣቶች እንዲሁም መላ ነዋሪውን በማለት እየተከፋፈለም ሳይቋረጥ የሚሠራ ሥራ ነው። እስከ አሁን ባለው ሁኔታም በተሳካ ሁኔታ እየተሠራበት ያለ ሂደት ነው።

ከዚህ የሚቀጥለው ሕዝቡን ማደራጀት ሲሆን፤ ይህም በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረውና ኅብረተሰቡ በራሱ ፍቃደኝነት የሰላም ሠራዊት ሆኖ በምሽት እየወጣ አካባቢውን የሚጠበቅበት ሂደት ነው። እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳን ከክፍያ ነጻ ሆነው በሙሉ ፍቃደኝነት አካባቢያቸውን እየጠበቁ ቢሆንም የሚተዳደሩበት ሕግና ሥርዓት ደግሞ አለ። ስልጠናም ያገኛሉ። ከስልጠናው ባሻገር በጎ ፈቃደኛ የሰላም ሠራዊቶችን በሥራው ላይ መሠማራታቸውን የሚገልጽ መለያ ተዘጋጅቶላቸው የፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ከምናረጋግጥባቸው መንገዶች መካከል ተጠቃሹ ነው።

በዚህ ሥራው ኅብረተሰቡ በአካባቢ ፤በመንደሩ ያለውን ጠቅላላ የፀጥታ ሁኔታ ከማረጋገጡም በላይ ለከተማዋ የፀጥታ ቢሮ ቀኝ እጅ በመሆን መረጃን ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን እያደረጉ ነው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ይህ የሰላም ሠራዊት ሁሉን የሚመለከት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በተለይም የገንዘብ አቅማቸው ጥሩ የሆኑ ሰዎች የአካባቢ ጥበቃዎችን በገንዘባቸው እየቀጠሩ እኛም አስፈላጊውን ስልጠና እየሰጠን ከማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ጋር ተቀናጅቶ የጥበቃ ሥርዓቱ እየተከናወነ ነው። ከዚህ አንጻር ገንዘብ የሌለው በጉልበቱ ገንዘብ ያለው ደግሞ በገንዘቡ ለሰላምና ፀጥታው የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ ነው ማለት ይቻላል ።

በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም ቁጥራቸው 833 ገደማ የሚደርሱ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ማእከላት አሉ። እነዚህ ተቋማት ደግሞ የፖሊስን አገልግሎት በየአካባቢው ተደራሽ ለማድረግ በተለይም ግጭቶች ሲኖሩ እንዲፈቱ በማድረግ አዋኪ ተግባራትም ከብሎኮች ሳይወጡ የሚፈቱበት መፍትሔ የሚሰጡ ናቸው። በመሆኑም የሕዝቡ ተሳትፎ ማሳለጫ ናቸው ማለት ይቻላል። ሕዝቡም እኔም ለአካባቢዬ ዘብ እቆማለሁ ብሎ ተሳትፎውን በማሳየት ላይ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፦ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በዚህ መልኩ ከታየ የፀጥታ አካላትስ የከተማዋን ሰላም በቅንጅትም ይሁን በተናጠል በተገቢው ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚሠሩት ሥራ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ጌታሁን፦ አዎ የፀጥታ መዋቅሩ ማለትም የከተማው ፖሊስ፣ሌሎች የፀጥታ ተቋም የከተማዋን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ሌት ተቀን ከመስራታቸውም ባሻገር ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያደርገው ጥረት የሚያበረታታና ብዙ ውጤቶች የታዩበት ነው። ይህ የፀጥታ ኃይል ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ከሚሠራው ሥራ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ዙሪያ የሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በአምስቱም መውጪያና መግቢያ በሮች ላይ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ የቅንጅት ሥራውንም በሚገባ እየሠራ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ሥራው ዘመን በወለዳቸው ቴክኖሎጂዎች እንዲደገፍ በማድረጉ በኩል የተሰራው ሥራ ምን ይመስላል ?

አቶ ጌታሁን፦ አዎ የፀጥታ ሥራውን የማዘመን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራዎች እየሠራን ነው። ከተማዋ ውስጥ ለፀጥታና ደህንነት ሥራ ጠቃሚ የሆኑ የደኅንነት ካሜራዎች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ እየተተከሉ ነው። በዚህም የደኅንነት ካሜራዎች በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ከማድረጋችንም ባሻገር በከተማዋ ውስጥ የሚገነቡ ትልልቅ ሕንፃዎች ካሜራ እንዲገጠምላቸው እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ በሕንፃው ባለቤቶች የሚከናወን ሲሆን፤ የሕንፃቸውን ሥራ ደኅንነት ከመጠበቅም አልፎ ከውጭ ያለውን የፀጥታ ሥራ ለመከታተል ከፍ ያሎ አስተዋጽኦን እያበረከተ ነው።

ከዚህ ባሻገር ካሜራውን መትከል ብቻ ሳይሆን በአንድ ማዕከል ላይ የመቆጣጠርና የማስተዳደር ሥራም እየተሠራ ነው። በቀጣይም የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ የፀጥታ ሥራው ከሰዎች አልፎ በሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ታግዞ የሚሠራ ይሆናል። ይህ ደግሞ የፀጥታው ሥራ ስማርት ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያደርገው እናምናለን።

አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ የፀጥታ ኃይሉ ከሕዝቡ አሁን ደግሞ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት ሥራዎችን እየሠራ ስለመሆኑ ነግረውኛልና እንደው በዚህ ቅንጅታዊ አሠራር የመጡ ለውጦችን ማንሳት እንችል ይሆን?

አቶ ጌታሁን፦ አዎ በሰላምና ጸጥታ ሥራ ላይ ቅንጅታዊ አሠራር ተኪ የለሽ ሚናን የሚጫወት ነው። ይህም በመሆኑ እኛም በልዩ ትኩረት የምንሠራው ሥራ ነው። ከዚህ አንጻር እስከ አሁን በተለይም ኅብረተሰቡንና ወጣቱን ወዳልተገባ መንገድ ይወስዱ የነበሩ እንደ ሺሻ ቤቶች፤ ቁማር መጫወቻዎች እንዲሁም ለሌሎች እኩይ ተግባራት ወጣቶችን የሚስቡና የሚሰበስቡ ቦታዎችን በጋራ በማሰስ ጥቆማዎችን በመቀበል ቤቶቹ እንዲዘጉ ንብረቶች እንዲወረሱ እና በሥራው ላይ የተሳተፉትም በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ አሁን ላይ ከተማዋ በአስተማማኝ ሰላም ላይ እንድትገኝ ማድረግ ተችሏል። ይህ ሥራም አንዴ ተከናውኖ የሚያበቃ ባለመሆኑ በየጊዜው ተከታታይነት ያለው ሥራ እየተሠራ ከተማዋን ወደተሻለ ደረጃ እያደረስን ነው ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፦ በጠቅላላው ግን ስናየው በተለይም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየተከናወነ ያለው የሰላምና የፀጥታ ሥራው ውጤታማ ነው የታለመለትን ግብ መቷል ማለት እንችላለን?

አቶ ጌታሁን፦ በነገራችን ላይ ከተማችንን ለማወክ ብዙ ዓይነት አስተሳሰቦች እየተንጸባረቁ ነው፤ እዚህም እዚያም ችግር ለመፍጠር ፍላጎቶች አሉ፤ ምናልባት አዲስ አበባ ላይ የሆነ ነገር ብንፈጥር በመላ ሀገሪቱ ላይ ችግር ለመፍጠር ይቀለናል ብለው የሚያስቡም ብዙ ናቸው። በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎችም ሙከራዎች ይደረጋሉ። እነዚህ ሙከራዎች ደግሞ የሚከሽፉትም ሆነ እየከሸፉ ያሉት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በሚሰሩ የሰላምና የፀጥታ ሥራዎች ነው። እኛም ውጤታማነታቸውን የምንለካው ከዚህ አንጻር ነው።

ይህንን በተጨባጭ ማሳየት ከተፈለገ በያዝነው ዓመት ብቻ ያከበርናቸውን የአደባባይ በዓላትና አንዳንድ ሁነቶችን ማንሳት በቂ ነው። ለምሳሌ የዘመን መለወጫ፣ እሬቻ፣ ደመራ፣ ጥምቀት አሁን ደግሞ በቅርቡ ኢድን ስናከብር በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ በጎዳናዎች ላይ ወጥቶ በዓሉን ተካፍሎ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ወደ ቤቱ ገብቷል።

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በየቀኑ በርካታ ሰዎች ያለምንም ስጋት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረውና ሠርተው በሰላም የሚገቡባት ከተማ ሆናለች። አሁን ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው ከተማን የማልማት የማዘመን የመለወጥ ሥራ አለና ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ነገሮች ስለሚኖሩ እንደ ፀጥታ ቢሮ ይህንን የልማትና የለውጥ ሥራ የሚመጥን አገልግሎት እየሰጠን ነው። በየጊዜውም አሠራሮችን እየፈተሽን ክፍተቶችን እያስተካከልን እየሄድን ነው። 24 ሰዓት የሚሠራው የልማት ሥራ ያለምንም ሳንካ እየተሠራ ነው፤ሕዝቡም በሰላም ወጥቶ እየገባ ነው።

በከተማዋ የትምህርት ተቋማት አካባቢም ያሉ አዋኪ ነገሮች በራሱ ለይተን እርምጃ እንድንወስድ ከፍተኛውን እገዛ ያደረጉልን ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ የሰላምና ፀጥታ አባላት ናቸው። እነሱ እገዛ ባያደርጉልንና እኛም በዛ ልክ እርምጃ መውሰድ ባንችል ኖሮ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው እየወጡ አልባሌ ቦታዎች እየዋሉ የትምህርት ሥርዓቱ ይታወክ ነበር። በጠቅላላው እነዚህና ያልጠቀስኳቸውም በርካታ የትብብር ሥራዎች በመኖራቸው ሥራው ውጤታማ ሆኗል።

አዲስ ዘመን ፦አንዳንድ ጽንፈኛ ኃይሎች የከተማዋን ፀጥታ ለማወክ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋሉ፤ሙከራዎችም ነበሩና እነዚህን ነገሮች እግር በእግር የመከታተሉ ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ጌታሁን ፦ ጽንፈኝነት ትርጉሙ ሰፊ ነው። ጽንፍ የወጣ አስተሳሰብ ግለሰብ ቡድን ሁሉ ለውይይት በር አይሰጥም፤ በማህበረሰቡ ላይ ሃሳቡን በጉልበት በኃይል መጫን ነው የሚፈልገው፤መንግሥትን ማስገደድ ነው ህልሙ፤ ይህ ደግሞ አሁን ባለንበት ሥርዓት ሊሆን የማይቻል ነገር ነው። መንግሥት በምርጫ ተወዳድሮ ነው ስልጣን የያዘው ፤ስለዚህ ይህንን መንግሥት ከስልጣን አወርዳለሁ የሚል አካልም በምርጫ ተወዳድሮ ነው ማሸነፍና ስልጣን መያዝ ያለበት። በጉልበት በትጥቅ መንግሥትን ማንሳት አይቻልም።

ይህም ቢሆን ግን አሁን እየታዩ ያሉት አንዳንድ አዝማሚያዎች የሚያሳዩት መጥፎ ሁኔታ አለ። በተለያዩ ክልሎች ላይ ያሉ ጽንፈኝነቶችንም ወደከተማ ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች ይስተዋላሉ፤ ነገር ግን እኛ እስከ መንደር ድረስ አደረጃጀትን የፈጠርን ከመሆኑ አንጻር የመረጃ ሥርዓቱ በእያንዳንዱ መንገድ እየተሰበሰበ ስለሚመጣ መረጃውንም መሠረት አድርገን ሕግ የማስከበር ሥራውን ስለምንሠራ ችግሩን በአጭሩ እንቀጨዋለን።

ይህም ቢሆን ግን የተለያዩ ሙከራዎች አይደረጉም ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ይዞ ወደከተማ ለመግባት መሞከር፣ እምነቶችን ሽፋን አድርጎ ለእኩይ አላማ መንቀሳቀስ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሽፋን አድርጎ መንቀሳቀስ አለ። ይህንንም እንደ ፀጥታ ቢሮ እግር በእግር እየተከታተልን ሕግ የማስከበር ሥራዎችን እንሠራለን።

በነገራችን ላይ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች አንግበው የተነሱትን አላማ በከተማዋ ላይ ለማራመድ የሚያደርጉትን ጥረት የከተማው ነዋሪ አይፈቅድም። ሰላሙን የሚያደፈርስ ነገርም አይቀበልም። ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ ገብቶ ሠርቶ ሕይወቱን መቀየር ነው የሚፈልገው። ከዚህ አንጻር ሕዝብ ውስጥ ተሸሽጎ እኩይ ተግባርን አስፈጽማለሁ ማለት የሚቻል አይደለም።

በጠቅላላው ማንኛውም ጽንፈኛ ኃይል መሄጃውም መዳረሻውም አፍራሽ ነው፤ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ የሚጠቅም ነገር የለውም፤ ሃሳቡን ይዞ ለሚንቀሳቀሰው አካልም ጥቅሙ ምንም ነው፤ በዚህ አግባብ ከተማችን ውስጥ ያለውን ሁለንተናዊ ሰላም እያረጋገጥን የምንሄድ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፦ እንደ ቢሮ በከተማ ደረጃ ሰላምና ፀጥታን በማስከበር ሂደቱ ላይ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው ? ከማንስ ምን ዓይነት እገዛን ትፈልጋላችሁ?

አቶ ጌታሁን፦ ሕዝቡ ሰላም ወዳድ ነው፤ ለሰላም የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ነው፤ እኛም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሥንሠራ የምንለው ነገር ሰላም ያለው በእጃችሁ ነው፤ አንዳንድ ግለሰቦች ይህንን ሰላማችሁን ሊነጥቋችሁ ያስባሉ፤በመሆኑም ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጉ ብለን እናስተምራለን።

በነገራችን ላይ አንዳንድ ሰዎች ከራሳቸው ጋር በሃሳብ ይጋጫሉ፤ ይህንን ሁኔታ ይዘው ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ችግር ይፈጥራሉ፤ ይህም ከፍ እያለ ሄዶ ወደማህበረሰብ ይደርሳል በመሆኑም ሰዎች መጀመሪያ ሊያረጋጉ የሚገባቸው ራሳቸውን ነው፤ ይህ ሲሆን በእጃቸው ያለውን ሰላም መጠበቅ ይጀምራሉ ሌሎችንም ከመረበሽ ይቆጠባሉ።

እንደ እኛ ሥራ ግን ፈታኝ እየሆነብን ያለው ነገር ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ያለው ጉዳይ ነው። ማህበራዊ ሚዲያ ለበጎ ነገር ከተጠቀምንበት ብዙ የሚያሠራ የመሆኑን ያህል ባልተገባ ሁኔታ የሚጠቀሙበት አካላት ግን ማህበረሰቡ ላይ የሌለ ነገር በመፍጠር ጫና እንዲያድርበት ያደርጋል።

የሰላምና የደኅንነት ጉዳይ የመንግሥት ሥራ ብቻ አይደለም ሕዝቡ በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ የሆነ ትግል ማድረግ አለባቸው። ሚዲያው እውነትን ከሃሰት እየለየ እያወገዘ ትክክለኛውን መረጃ ለማህበረሰቡ የሚያደርስበት አሰራር መከተል አለበት።

በሌላ በኩል ኅብረተሰቡ የከተማው ፀጥታ ባለቤት እንደመሆኑ ጎረቤቱ ማን እንዳለ ምን እንደሚሠራ በተቻለ መጠን ማወቅ ይኖርበታል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ቤት፤ ሕንፃ ፤መኪና የሚያከራዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተከራያቸውን ማንነት ማወቅ ለምን አገልግሎት ሊውል እንደተፈለገ መረዳት አለባቸው። በተጨማሪም መኪናም ሆነ ቤት አከራይተው የሚኖሩ ሰዎች የተከራዮቻቸውን ማንነት የሚገልጽ በቂ መረጃን እስካላገኙ ድረስ ንብረታቸውን አሳልፈው ባለመስጠት መተባበር ይገባቸዋል።

ያለችን አንድ ሀገር ናት ሀገራችን ችግር ገጠማት ማለት መግቢያ መሸሸጊያ አጣን ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሱዳንን በመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ላይ እየተፈጠረ ባለው ነገር ብቻ ማየት በቂ ይመስለኛል። በመሆኑም ችግር ፈጣሪዎችን ተባብረን አይሆንም በማለት ሁላችንም የከተማችን የሀገራችን ሰላም ይመለከተናል ብለን ልንነሳ የግድ ነው።

አዲስ ዘመን፦ የፀጥታ ኃይሉ ሥራዎችን የሚደግፍበት መንገድ ምን ይመስላል?

አቶ ጌታሁ፦ የልማት ሥራው ከተማችንን ከማዘመን፣ ከማበልጸግ እንዲሁም ከተማውን ከሌሎች የዓለም ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ከማድረግ አንጻር እየተሠራ ያለ ሥራ ነው። በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎቿ ብቻ ሳትሆን በዓለም የዲፕሎማቲክ መቀመጫ ሀገራት መካከል ሦስተኛዋ ከተማ ናት፤ከዚህ አንጻር ልማቱ ያንን የሚመጥን መሆን አለበት በማለት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ኅብረተሰቡም ይህንን በመረዳትና የመንግሥትን ሃሳብ በሙሉ ልብ በመቀበል ሥራውን እየደገፈ ነው ያለው፤ በልማት የሚነሱ አካባቢዎችም ይነሱ ሲባል ሕዝቡ እየተባበረ ነው ።መንግሥትም ቢያንስ ይኖሩ ከነበረው ኑሮ ሻል ወዳለ ኑሮ የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ እያመቻቸም ስለመሆኑ መናገር ይቻላል።

ለምሳሌ እዚህ ፊትለፊታችን ያለው የዶሮ ማነቂያ አካባቢ ምን እንደነበር ይታወቃል። በጣም የደከሙ ቤቶችን የያዘ፤ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በተገቢው ሁኔታ መስጠት የማይቻልበት ፣ በፀጥታው አንጻርም በርካታ አዋኪ ነገሮች በየቀኑ የሚፈጠሩበት አካባቢም ነበር፤ አሁን ከዚህ አካባቢ የተነሱ ሰዎች የተሻለ መኖሪያ አግኝተው መኖር እንዲችሉ እየተደረገ ነው።

ይህ ሁሉ ጥሩ ነገር ነው እኛም በፀጥታው ያለውን ሥራ በሚገባ እየሠራን በአንዳንድ ማህበራዊ ገጾች ላይ የሚለቀቁ እኩይ ተግባራትን የሚያስተላልፏቸውን የተዛቡ መረጃዎች ለማስተካከል በተጠናከረ የፀጥታ መዋቅር ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።

አቶ ጌታሁን፦ እኔም አመሰግናለሁ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም

Recommended For You