የኢኮኖሚ ዕድገቱን በተመለከተ ለመገምገም የሚያስችል ሙሉ መረጃ በአሁኑ ሰዓት ለማጠናቀር እንዳልተቻለ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ጠቆመ፡፡
ኮሚሽኑ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የ10 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት እንዳስታወቀው የ2011 በጀት ዓመት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱን በተመለከተ ለመገምገም የሚያስችል ሙሉ መረጃ በአሁኑ ሰዓት ለማጠናከር ያልተቻለ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የግል ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አዝማሚያ፤የካፒታል በጀት አፈፃፀም ፤ የኮንስትራክሽን በጀት አጠቃቀም፤ የመካከለኛና ከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ግምታዊ አመለካከቶች አዝማሚያ ፤የመኸር ወቅት የዋና ዋና ሰብሎች ምርት ትንበያ፤ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ አፋፃፀም እና የአገልግሎት ዘርፎችን አጠቃቀም ላይ በማተኮር ለ2011ዓ.ም በጀት ዓመት የተቀመጠውን 11.0 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ግብ ማሳካት እንደማይቻል በሪፖርቱ ላይ አብራርቷል፡፡
ከታህሳስ ወር ጀምሮ ከታየው የዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ በሪፖርቱ እንተገለፀው በ2011 ዓ .ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 16.2 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት ኮሚሽኑ ትኩረት በመስጠት በቅርቡ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ከተውጣጡ የስራ ሀላፊዎች ጋር የጥናት ግብረ ሀይል በማዋቀር በፕላንና ልማት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ሰብሳቢነት የዋጋ ግሽበቱን መንስኤዎች በማጥናት ለማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍፁም አስፋው እነዚህንና ሌሎች ኮሚሽኑ በ10 ወራት ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ከቋሚ ኮሚቴውና ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽን ሰተዋል፡፡
ሀይማኖት ከበደ