ለከተሞች መሠረተ ልማት አቅም የሚፈጥረው የጽዳትና አረንጓዴ ልማት ንቅናቄ

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በኢትዮጵያ ያለው የከተሜነት ዓመታዊ እድገት ከአምስት ነጥብ አራት በመቶ በላይ ነው። ይህ እድገት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የከተሜነት እድገት ከሚመዘገብባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ያደርጋታል። ይሁን እንጂ ይህ እድገት ከሀገሪቱ የሕዝብ ብዛት አንፃር ሲመዘን የከተሜነት እድገቱ በቂ የሚባል እንዳልሆነም መረጃዎቹ ያሳያሉ።

ከተሞች ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው የሥራና የመኖሪያ ሥፍራዎች በመሆናቸው፣ የነዋሪዎችን የሥራና የኑሮ እንቅስቃሴዎች ምቹ ማድረግን ይጠይቃል። ለእዚህም ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ነው። የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎች ደግሞ የከተሞችን የመሠረተ ልማት አቅርቦት ውጤታማ ከሚያደርጉት መካከል ይጠቀሳሉ።

በዚህ መነሻነትም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሰሞኑን ‹‹ጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ሃሳብ የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሀገራዊ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ተግባር ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ በባለድርሻ አካላትና በሕዝቡ ንቁ ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሠራር ሊተገበር እንደሚገባ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፣ በእምቅ ሀገራዊ አቅም እና በዜጎች ፍትሃዊና ንቁ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ የከተማና የገጠር ልማትን በማስተሳሰር ጤናማ ከተሜነትን ማስፋፋት ፋይዳው የጎላ ነው።

‹‹በሀገራችን ከተሞች በፍጥነት እየተስፋፉ ይገኛሉ፤ ይሁን እንጂ የከተሞች መስፋፋት ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ፣ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን በሚያፋጥንና በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎቶችን በሚያሟላ መልኩ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ ነው›› ይላሉ። መንግሥት የሀገሪቱ ከተሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ለኢትዮጵያ የሚመጥኑና ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ የተቀናጀ የከተማ ልማት ፕሮግራም በመንደፍ በተለያዩ የሪፎርም ርምጃዎች በማስደገፍ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝና ውጤቶችም እየተመዘገቡ እንደሆነ አቶ አደም ይጠቅሳሉ።

ለአብነትም ከተሞች ደረጃውን በጠበቀ ፕላን እንዲመሩ፤ በቂና የለሙ አረንጓዴ ስፍራዎች እንዲኖራቸው፤ የሌማት ትሩፋትን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ፤ ግልጽ፣ ዘመናዊና የከተሞችን አቅም ያገናዘበ የመሬት ልማትና አስተዳደር ሥርዓት እንዲዘረጉ፤ የከተማ መሠረተ ልማት አቅርቦቶችን በተቀናጀ ሁኔታ መምራት እንዲችሉ፤ ጽዱና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ፤ የገቢ አቅማቸውና የፋይናንስ ሥርዓታቸው እንዲዳብር፤ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የተደገፉ፣ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያላቸውና የሕዝብን ፍላጎት የሚያረኩ እንዲሆኑና ሙያዊ ብቃትን መሠረት ያደረገ ጠንካራ የከተማ አስተዳደር እንዲኖራቸው ለማስቻል የተጀመሩ የሪፎርም ርምጃዎች ውጤት ማምጣት ጀምረዋል።

በቀጣይም በከተሞች መካከል ያለውን የአፈፃፀም ልዩነት ማጥበብ ከተቻለና አመራሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሥራዎችን በእውነትና በእውቀት መምራት ከቻለ፣ ከተሞች በአጭር ጊዜ ለሀገር ኢኮኖሚ የድርሻቸውን በሚገባ የሚያበረክቱ መልካም አስተዳደር የሰፈነባቸው እንዲሁም ዘመናዊና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል።

አቶ አደም ‹‹የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራ ከተማን ከማስዋብ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት። ለአብነትም የከተሞች ጽዱና አረንጓዴ መሆን በሽታን ለመከላከልና የዜጎችን የፈጠራና የአምራችነት አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል›› ይላሉ።

የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በከፍተኛ የሕዝብ ንቅናቄ ለማስፈፀም የተያዘውን እቅድ በውጤታማነት ለመፈፀም በየደረጃው የሚገኙ የክልልና የከተማ አስተዳደር አመራሮች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ አደም፣ በተለይም በማዕከል የተዘጋጀውን እቅድ መነሻ በማድረግ ከየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የተሟላ እቅድ በማዘጋጀት፣ ተገቢውን አደረጃጀት በመፍጠር፣ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት፣ ባለድርሻ አካላትንና ሕዝቡን በማነቃነቅ የሀገራችን ከተሞች ዘላቂ በሆኑ መልኩ ጽዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ ማድረግ ከአመራሩ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪም አመራሩ የጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ከራሱ ተቋም በመጀመር ለግል ተቋማትም ሆነ ለነዋሪዎች አርዓያ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳስገነዘቡት፤ ለብዙ ሀገራት ተሞክሮ ሊሆን የሚችለውን ይህን በጎ ተግባር አመራሩ በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተለይም በጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎች ኃላፊነትን መወጣት የሰብዓዊነትን እሴት እንደመላበስና የዜግነት ግዴታን እንደመወጣት የሚቆጠር የሥልጣኔ ማሳያ ተግባር ነው። ሁሉም ባለድርሻ አካላትና የከተማ ነዋሪዎች ከተሞቻችንን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ ሥራውን ከሚያስተባብሩ አካላት ጎን በመሆን ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ኃላፊነታቸውን የሚወጡትን ማበረታታት እንዲሁም ግዴታቸውን በማይወጡት ላይ ደግሞ የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ በማድረግ ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል። ‹‹የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራ በተወሰኑ ጊዜያት በዘመቻ የሚሰራ ሳይሆን የሕዝብ ባለቤትነትን በማረጋገጥና ተቋማዊ አሠራርን በመዘርጋት ቀጣይነትና ዘላቂነት ባለው መንገድ የሚፈፀም የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል። ይህ የጽዳት ሥራ ሥርዓት ለመገንባት የሚረዳና ሁሉም ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችል መሆን ይኖርበታል›› ብለዋል።

የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር የአስተሳሰብ ለውጥ የማምጣት፣ የጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ከተለያዩ ዘርፎች (ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከሥራ እድል ፈጠራ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከጥናትና ምርምር…) ጋር የማስተሳሰር፣ ሕግ የማስከበር እና አሠራርን የማዘመን ተግባራት የንቅናቄው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ሊሆኑ እንደሚገቡም አመልክተዋል።

መንግሥት የህብረተሰቡንና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማስተባበርና በማቀናጀት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፣ ንቅናቄውን ውጤታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እንደሚያደርግም አቶ አደም አስታውቀዋል።

አቶ አደም እንዳሉት፤ መንግሥት በከተማ ልማት ረገድ በእቅድ የተያዙ ሥራዎች በውጤታማነት እንዲፈጸሙ በማድረግ፣ በተለይም ከተሞች ዘመናዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተጀመሩ የፅዳትና የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች በትኩረት እንዲፈፀሙ ንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ እንዲሆን በፌዴራል ደረጃ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር የከተማ አስተዳደሮችን አቅም የማጎልበት፣ የአሠራር ማሻሻያዎችን የማድረግ፣ ክፍተቶችን የመሙላት፣ ለመልካም ፈፃሚዎች እውቅና የመስጠትና የተሞክሮ ለውውጦችን የማመቻቸት ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፣ የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ከለውጡ ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው አስታውሰው፣ መንግሥት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በውል ተገንዝቦ ለከተሞች ዕድገትና መስፋፋት እንዲሁም ለዜጎችም ሕይወት ማማርና መቃናት በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፣ ሀገሪቱ እያስመዘገበች የምትገኘውን ፈጣን የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የከተሞች ፅዳት፣ ውበትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማረጋገጥ እጅግ ወሳኝ ተግባር ይሆናል። ይህም ሊሳካ የሚችለው በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠትና በመቀናጀት በሚያካሂዱት የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። ስለሆነም በከተሞች ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ በመፍጠር በዘርፉ በተገኙ ውጤቶች፣ እየተስተዋሉ ባሉ ተግዳሮቶች እና በወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በመወያየት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት በማሳተፍ በፍጥነት ወደ ተግባር ለመግባት እንዲቻል ንቅናቄው ወሳኝ ሚና አለው። የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ንቅናቄ ዋና ዓላማው በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ከተሞች ለኑሮና ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

በከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝን በሚመለከት እስካሁን ድረስ የተለያዩ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የቁጥጥር፣ የትምህርትና ግንዛቤ ሥራዎች እየተሠሩና በሂደትም የተወሰኑ መሻሻሎችና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ያሉ ቢሆንም፣ በብዛት ጎልቶ የሚታየው የከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እንዲሁም የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ክፍተት፣ የተሟላ ግንዛቤ በመፍጠር የሕዝቡንና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ከማሳደግ አኳያ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ ያመለክታል። ስለሆነም በየደረጀው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትና መላው ህብረተሰብ በአመለካከትና በተግባር የጋራ መግባባትና ግንዛቤ በመያዝ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን እጅግ አስፈላጊና አስገዳጅ ተግባር ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች በማኅበራት በመደራጀት አካባቢን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ የሚከናወኑ በጎ ተግባራት አሉ፤ በአንዳንድ ከተሞችም አመራሮች አርዓያ በመሆን በፅዳት ተግባራት ላይ ሲሳተፉ ይስተዋላሉ። በቀጣይም የከተማ ልማት ፖሊሲን መሠረት በማድረግ ሕጋዊ ማዕቀፎችን በሚገባ መተግበር፣ የተጀመሩ መልካም ተግባራትን ማስፋት እና በመዋቅሮችና አደረጃጀቶች መሠረት በቁርጠኛነት መሥራት ያስፈልጋል።

‹‹ሥራዎች በመንግሥት አደረጃጀት ብቻ የሚከናወኑ ባለመሆናቸው በባለድርሻ አካላትና በመላው የከተማ ሕዝብ ተሳትፎ መተግበር ይኖርባቸዋል። የመንግሥት ተቋማት፤ የተለያዩ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፤ የግልና የመንግሥት ማምረቻ ድርጅቶች፤ ትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማት አደረጃጀት በመፍጠር አካባቢያቸውን ውብና ጽዱ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም እነዚህን ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን አደረጃጀቶችን በማጠናከር፤ አሠራሮችን ማስተካከል እና ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል ጥልቅ ውይይት በማድረግ የጋራ ዕቅድ ይዞ ወደ ቀጣይ ሥራ መግባት ያስፈልጋል›› ብለዋል።

ዜጎች ከአረንጓዴ ልማት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ መቆየታቸውንና ለአረንጓዴ ልማት ሊውሉ ይገባቸው የነበሩ ቦታዎች ተገቢ ላልሆኑ ተግባራት መዋላቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለብዙ ዜጎች የሥራ እድሎች መፍጠራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ መዋቅሮችን ማጠናከር፣ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ የማኅበራትን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የግምገማና ክትትል ሥራዎችን የማጠናከር እና ንቅናቄውን በቋሚነት ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You