ስለ ልጅ ፍቅር …

አስፋው የብርቱ ገበሬ ሥም …

ምዕራብ ወለጋ የጊምቢ ገጠራማው ስፍራ አስፋው ደለቴራን የመሰሉ ብርቱዎችን አፍርቷል። በዙሪያ ቀበሌው ጠንካራ ገበሬዎች በሬዎችን ጠምደው ሲያርሱ ፣ ሲያዘምሩ ይውላሉ። አስፋው የስድስት ልጆች አባት ነው። ሶስቱ ሴቶች፣ ሶስቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ገበሬው አባወራ በላቡ ዋጋ በጉልበቱ ድካም አዳሪ ነው። ዓመቱን ሙሉ እጁ ነጥፎ፣ ጎተራው ጎድሎ አያውቅም።

አስፋው ግብርናን ከልጅነቱ ጥርሱን ነቅሎበታል። መሬቱን አርሶ ፣ አለስልሶ ምርቱን ሲያፍስ፣ በሙሉ መተማመን ነው። እሱ ትናንት ባለፈበት መንገድ ትውልዱ እንዲያልፍ አይሻም። ሁሌም ስለ ልጆቹ ነገ ያስባልና አድገው፣ ተምረው ለቁምነገር እንዲበቁ ምኞቱ ነው። ይህ እንዲሆን ስለልጆቹ ጤና ይጨነቃል፤ ቢያማቸው አይወድም። ጥቂት ቢያተኩሳቸው ደግሞ ሀኪም ዘንድ ይዞ መፍጠን ልማዱ ነው።

ትንሹ ቀነኒሳ…

ቀነኒሳ የቤቱ ትንሽ ነው። የሁሉም ዓይን ያርፍበታል። የመጨረሻ ልጅ መሆን ልዩ ትኩረት አለውና ሁሌም የላመ የጣፈጠውን፣ ያማረ የተዋበውን ያሰጣል። ቀነኒሳ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ያገደው የለም። እንደ ትንሽነቱ ሁሉም ይወደዋል፣ ያስብለታል። አስፋው ደግሞ ልጁን ባየ ቁጥር አፍላነቱን ያስታውሳል።

የዛኔ በእሱ ዕድሜ ስፖርት ወዳድ አፍላ ነበር። በዝላዩ ፣ በሩጫው መሳተፍ ደስ ይለዋል። ወጣትነቱ ላይ ሁሌም ብርቱ ነው። በያዘው መስክ አሸናፊትን አያጣም። ይህ ማንነቱ ዛሬ ላይ በግብርናው ተዋዝቷል። እንዲያም ሆኖ ትዝታውን አልረሳም። ሯጮችን ሲያይ ዘመኑን ያስታውሳል። ስፖርተኛነቱ ትዝ ይለዋል። አስፋው በተለይ ለእውቁ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የተለየ ፍቅር አለው።

ቀነኒሳ የኢትዮጵያ ምርጥ አትሌት ነው። ተፎካካሪዎቹን አሸንፎ በዓለም አደባባይ ዕውቅናን ተችሯል። ዛሬም ድረስ ለአትሌቱ ክብር የሚሰጠው አስፋው አድናቆቱ በውስጡ ነው። ለዚህ እውነት ማስታወሻ ይሆነው ዘንድ ትንሹን ልጅ በአትሌቱ ስም ይጠራዋል። ‹‹ቀነኒሳ›› የመጨረሻ ልጁ ስያሜ ሆኗል።

ይህን ስም ለልጁ ከሰጠ ወዲህ ላታላቁ አትሌት በልቡ ቋሚ ሐውልትን እንደተከለ ይሰማዋል። አባት ትንሹ ቀነኒሳ እንደ አትሌቱ ግብሩን ቢይዝለት፣ ስሙን ቢያስነሳለት ይወዳል። ቀነኒሳ ማለት የስፖርት ሕይወቱ ዐሻራ ፣ የልጅነት ታሪኩ እውነት፣ የሚያከብረው አትሌት ማስታወሻ ነው።

አሁን ትንሹ ቀነኒሳ በዕድሜው ማደግ ጀምሯል። እንደማንኛውም ልጅ ትምህርት ቤት ሊገባ ከቀለም ሊገናኝ ነው። ይህ እውነት ለወላጆች ደስታ ይሰጣል። እሱን መሰል ልጆች ተምረው አካባቢያቸውን እንዲያስጠሩ፣ ራሳቸውን እንዲቀይሩ ይጠበቃል።

2007 ዓም…

ይህ ዓመት ለብርቱው ገበሬ አስፋው ከሌሎች ጊዜያት የተለየ አልነበረም፤ ልክ እንደቀድሞው በሬዎቹን ጠምዶ ከእርሻው ይውላል። እንደዓምና ካቻምናው ለከርሞው ያስባል፣ ለነገው ያቅዳል። በላብ በወዙ የሚገኘው ምርት ከአውድማው እንዳያንስ፣ ከጎተራው እንዳይጎድል ዘወትር እንደበረታ ነው።

ከሰሞኑ ግን ዓይኖቹ ከትንሹ ቀነኒሳ ላይ አልተነሱም። ዘወትር የአንገቱን ስር ምልክት እያየ ያስባል፣ ይጨነቃል። አንገቱ ላይ ከዚህ ቀድሞ ያልነበረ ነገር እየታየው ነው። በየቀኑ ማበጥ የጀመረው አንገት ህመምን አስከትሏል። ይህ ስሜት ፈጣኑን፣ ቀልጣፋውን ህጻን ማሸማቀቅ፣ ማስጨነቅ ይዟል።

በየቀኑ ችግሩን ያዩ አንዳንዶች የራሳቸውን መላምት አመጡ። እንዲህ ሲያጋጥም የአበሻ መድሃኒት መሞከር ተለምዷል። እሱ ባይሳካ የሌላውን እጅ ማየት፣ መፈተሹ ያለ ነው። ቦታው ገጠር ነውና ዕድሉን መሞከር ፣ ባጋጣሚው ማለፍ ብርቅ አይደለም። አባት ግን በዚህ አማራጭ መጠቀምን አልፈለገም።

አስፋው ውሎ አድሮ የልጁ ጉዳይ ይበልጥ አሳሰበው። አሁንም የአንገቱ ስር እብጠት ጨመረ እንጂ አልጎደለም። ችግሩን እያየ ብቻ አብሮት መጨነቁን አልፈለገም። ሁሌም እንደሚያደርገው የሀኪምን እጅ ለማየት ወደደ። ቀነኒሳን ይዞ ወደ ሆስፒታል ሲዘልቅ በስፍራው ያሉ ሀኪሞች ልጁን ተቀብለው ምርመራ አደረጉለት።

አስፋውና ቀነኒሳ ለቀናት ከሆስፒታሉ ቆዩ። ሁኔታውን ያዩ ሀኪሞች አባትየውን ከየት እንደመጣ ጠየቁት። አስፋው መገኛው ከከተማ ወጣ ካለ የገጠር ቀበሌ ስለመሆኑ አስረዳቸው። ይህን ሲሰሙ በእጅጉ ተደንቀው አመሰገኑት። የልጁን ችግር ተረድቶ ሳይዘናጋ ሀኪም ዘንድ ፈጥኖ መምጣቱ መልካም ሆነለት።

የቀነኒሳ ሀኪሞች ለምርመራው ትኩረት ሰጥተው ቀናት ወሰዱ። የአንገቱ ላይ ዕብጠት አስጨንቋቸዋል፡ ፡ ውጤቱ መልካም ካልሆነ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሌላ ሆስፒታል ሊጻፍለት ግድ ይላል። አባት አስፋው ልጁን ይዞ ውጤቱን እየጠበቀ ነው። ለብዙ ያሰበው ቀነኒሳ በህክምና ዕጦት እንዲሰቃይበት አይፈልግም።

ልጁን ሲያስተውል ሁሌም ይጨነቃል፣ ያዝናል፣ ሆደ ቡቡው አባት ዓይን ዓይኑን እያየ ስለነገው ያስባል። ‹‹ቀነኒሳ›› ብሎ ስም ሲሰጠው እንደ አትሌቱ ፈጣን፣ ሯጭ ፣እንዲሆንለት እያሰበ ነበር። ዛሬ ይህ ህልሙ ከእሱ የለም። አሁን የዕለት ሥራው ተደናቅፏል። የዓመት ዕቅዱ ተሰናክሏል። እንዲያም ሆኖ ከልጁ ሕይወት አይበልጥበትም። ጊዜ ሰጥቶ፣ ጉልበት ገንዘቡን ከፍሎ እያሳከመው ነው።

ሀኪሞቹ የትንሹን ቀነኒሳ የምርመራ ውጤት ለማወቅ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይዘዋል። በየቀኑ ደሙ ይታያል፣ ከዕባጩ ፈሳሹ ተወስዶ ይመረመራል። ውጤቱ እየታየ ሌላው ምርመራ ይታዘዛል። አስፋው በሀኪሞቹ ተስፋ አልቆረጠም። ከዛሬ ነገ የሚሰማውን እውነት እየጠበቀ ነው። በቀጠሮ ምልልስ ህክምናው ቀጠለ። ለውጥ ባይኖረውም ሁኔታው ተስፋ የሚያስቆርጥ አልሆነም። ውሎ አድሮ ግን ለአባት የምርመራው ውጤት ተነገረው። በቀነኒሳ አንገት ላይ ከወጣው ዕብጠት የተገኘው ናሙና የካንሰር ምልክት እንደታየበት ታወቀ።

ሌላው እርምጃ…

አስፋው የትንሹ ቀነኒሳ የህክምና ውጤት ከተነገረው ወዲህ ውስጡ ተሰብሯል። ኀዘኑ ከፍቷል። እንደ ዓይኑ ብሌን የሚሳሳለት ልጁ በዚህ ህመም መጠርጠሩ ክፉኛ እያሳሰበው ተጨንቋል። ሀኪሞቹ ዛሬም አድናቆታቸውን እየሰጡት ነው። ገጠር ኗሪው አባወራ ለህክምና ቅድሚያ ሰጥቶ ለልጁ መድረሱ ለአካባቢው ተምሳሌ አድርጎታል።

ከምርመራው ውጤት በኋላ የአስፋውና የልጁ የሕይወት አቅጣጫ ተቀየረ። አባት ቤት ትዳሩን እርሻ አውድማውን ሊተዉ ቁርጡ ቀን ደረሰ ። ትንሹ ልጅ ጅምር ትምህርቱን ሊያቋርጥ ግድ ሆነ። አስፋው በተጻፈለት የህክምና ወረቀት ልጁን ይዞ አዲስ አበባ ሊሄድ ተዘጋጀ።

እሱ በዚህ ስፍራ አንዳች የሚያውቀው ሰው የለም። ለስሙ ‹‹ዘመድ ወዳጅ›› አለ ቢባል እንኳን በእንግድነት ልጁን ይዞ የሚከርምበት አይሆንም። ይህ ችግር ግን ከመንገዱ አልመለሰውም። ስለ ልጁ ጤና መሆን የትም ቢሆን ይሰደዳል፣ኑሮ ሕይወቱን ትቶ ማንነቱን ይሰጣል።

አስፋውና ቀነኒሳ አሁን አዲስ አበባ ናቸው። በተባሉት መሠረት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደርሰው ህክምናውን ጀምረዋል። ‹‹ለሀገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ›› የሆኑት አባትና ልጅ ውሏቸውን ከህክምናው ያሳልፋሉ። ከነበሩበት ሆስፒታል የተጻፈው የምርመራ ውጤት ዳግም ይረጋገጥ ዘንድ በቂ ጊዜ ይጠይቃል። ከዚህ ጥግ ለመድረስ ቀነኒሳ ራሱ ን ሰ ጥቶ ምርመራውን ጀምሯል።

ዳግም ምርመራው…

አባት አስፋው ለልጁ ከጎኑ የቆመ ብርታቱ ነው። ጭንቀቱን ተካፍሎ ህመሙን ይጋራዋል፣ ሁሌም ‹‹አይዞህ›› ለማለት አይሰንፍም፣ ‹‹አለሁልህ›› እያለ ቀነኒሳን ያጠነክረዋል። የአዲስ አበባው ሕይወት በህክምናው እንደቀጠለ ነው። አሁንም ምርመራው፣ ናሙናው በጥልቀት ቀጥሏል። ከቀናት በአንዱ የተሰማው ዜና ግን ለአባትና ልጁ መልካም የምስራች ሆነ።

የጥቁር አንበሳ የምርመራ ውጤት በቀነኒሳ አንገት ላይ የታየው ዕብጠት ዕጢ እንጂ ካንሰር ደረጃ ያለመድረሱን አሳወቃቸው። ይህ እውነት ቤት ትዳሩን ትቶ ሀገር አቋርጦ ለመጣው አባት ታላቅ ደስታን አቀበለ። ውጤቱ ብቻውን ግን ወደቤት ፈጥኖ አልመለሳቸውም። ዕጢው በቀዶ ህክምና መውጣቱን ተከትሎ ተከታታይ ህክምና መውሰድ ግድ መሆኑ ተነገራቸው።

ቀነኒሳ አዲስ አበባ ቆይቶ የኬሞ ህክምናውን ጀመረ። ይህ ጊዜ በእጅጉ ስቃይ ያለበትና የከፋ ነበር። የህክምናው ሂደት የሚያስከትለው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገፋ አልሆነም። ቀነኒሳ በልጅ አቅምና ጉልበት ህመሙን አሸንፎ ለመቆም ብዙ ታገለ። ስቃዩ ግን ለእሱ ብቻ አልሆነም። ከድካሙ እስኪነቃ፣ ከህመሙ እስኪያገግም አባት አስፋው ከልጁ ጋር ሊታመም ግድ ብሏል።

አስፋው ልጁን በምልልስ ለማሳካም ብዙ ደክሟል። ህክምናው በቂ መድሃኒት ያሻዋል። ዋጋው ደግሞ በቀላሉ አይቀመስም። ለእያንዳንዱ መድሃኒት ጥቂት የማይባል ገንዘብ መውጣቱ ግድ ነው። አስፋው አሁን ከቤት ትዳሩ ርቋል። ከጎኑ ሆኖ ጎዶሎውን የሚሞላ ሃሳቡን የሚካፈል ወገን የለውም። ልጁን ለማዳን ቤት ንብረቱ ላይ መፍረድ እንዳለበት ከራሱ መክሯል።

ብርቱው አባወራ የአዲስ አበባው ህክምና አቅሙን ፈትኖታል። ሙሉ ወጪውን ለመሸፈን ከተማ ላይ የሠራውን መኖሪያ ቤት ፣ ላሞቹንና በሬዎቹን ሸጧል። ጥሪቱን አሟጦ ልጁን ቢያሳክምም ሃሳቡ አላረፈም። እፎይታ የለሽ ሕይወቱ ከቤት፣ ከኑሮው ፣ ከታማሚ ልጁ በሃሳብ ያናውዘዋል።

አስፋው ስለ ልጁ ጤና በሬዎቹን ፈቶ፣ እርሻውን ትቶ ካገሩ ከወጣ ከራርሟል። ይህን የሚያውቁ የሰፈሩ ዕድርተኞች ግን ዝም አላሉም። የጎበጠ ትከሻውን ሊያቀኑ ፣ የደከመ ጉልበቱን ሊያበረቱ ከጎኑ ቆሙ። ችግር የፈታውን መሬት እያረሱ ጎተራውን ሞሉለት። የቅርብ ዘመዶቹ በጎዶሎው ተገኝተው ‹‹አለንህ›› አሉት። እሱም ቢሆን ባለው ጊዜ ለጉልበቱ አይሰስትም። ከእርሻው እየተገኘ እንደ ደንቡ ይውላል። አስፋው ሁሌም በዚህ ጥረቱ ውስጡ እንደጸና ነው። አሁንም ስለልጁ ጤና መሆን፣ ስለነገው ህልሙ ትግሉን ቀጥሏል።

አባወራው ልጁን በህክምና አቆይቶ ወደ ሀገሩ መመለስን የዓመታት ልምዱ ነው። ህክምናው ተከታታይ ነውና ፈጽሞ መቋረጥ የለበትም። ቀጠሮ በደረሰ ጊዜ ቀኑን ሳያሳልፍ ሀኪም ፊት ማቅረብ ግድ ይለዋል። ለእሱ ይህን ማድረጉ ሁሌም አልጋ በአልጋ አይሆንም። የአስፋው የትውልድ አካባቢ የጸጥታ ችግር ያለበት ነው። ዛሬ ሰላም ቢያድር የነገው ውሎ የከፋ ይሆናል።

አንዳንዴ በቀጠሮው ቀን ለመድረስ ቀድሞ ተዘጋጅቶ ልጁን ይዞ ይወጣል። የሁልጊዜ ሃሳቡ ልጁን አሳክሞ ለውጡን መናፈቅ ነው። ሆስፒታል ደርሶ ከህክምናው አድርሶ የእሱን ደስታ ለማየት ይጓጓል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን የመንገዱ መዘጋት ይሰማል። ይህኔ እሱን አልፎ መሄድ አደጋ እንዳለው ይረዳል። ተስፋ ይቆርጣል፣ ያስባል፣ ይተክዛል።

ይህ አይነቱ እውነት የአስፋውና የትንሹ ቀነኒሳ ክፉ አጋጣሚ ሆኖ ዓመታትን ዘልቋል። ይህ ከባድ ዋጋ ያስከፈለ መሰዋዕትነት ለአንድም ቀን አባት አስፋውን ቢያሳሳብ እንጂ አማሮት፣ አበሳጭቶት አያውቅም። ሁሌም መሽቶ በነጋ ቁጥር የልጁን አዲስ ጀንበር በጉጉት ይናፍቃል።

አሁን ትንሹ ቀነኒሳ ያሻውን ይመገባል። ሁለቱም ለጊዜው በተገኙበት አንድ ስፍራ ማረፊያ አግኝተው ‹‹እፎይ!›› ብለዋል። ህክምናው መሳካቱ ለአባት አስፋው መልካም ሆኗል። የልፋት ድካሙ ጉዳይ ዋጋ አለማጣቱ ሁሌም ፈጣሪውን እንዲያመሰግን ምክንያቱ ነው። ይህ ስለልጅ ፍቅር የተከፈለ ነው።

ዓመታትን የቆጠረው የአባትና ልጅ ምልልስ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል። በትንሹ ቀነኒሳ አካል ያለፈው ስቃይና መከራ ቀላል ይሉት አይደለም። በህመሙ ሳቢያ በየግዜው የሚቋረጠው ትምህርት፣ የሚያጋጥም ተስፋ መቁረጥ ከአዕምሮ በላይ ነው። የአባት አስፋው የሕይወት ትግል ደግሞ ከልጁ ማንነት ይለያል። ይህ ሰው ተስፋ የጣለበትን ፣ አስቀድሞ ህልሙን የቃኘበትን ልጁን በድንገቴ ህመም ተፈትኖበታል። ክፉ አጋጣሚው ግን እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ፣ ‹‹በእግዜር ያውቃል›› ብሂል ብቻ እንዲኖር ምክንያት አልሆነም።

አስፋው ፈጣሪውን ተማምኖ ልጁን በጤና ለማቆም ራሱን ለታላቅ ዋጋ አዘጋጀው። ንብረቶቹን ሸጦ፣ ጥሪቱን አሟጦ የጀመረው ጉዞ ፈተና ቢበዛውም አልተደናቀፈም። ከትንሹ ቀነኒሳ ጀርባ የሚያየው ታላቅ ተስፋ ዛሬን አሳድሮ የነገን ብርሃን አሳየው። በዚህ መንገድ ተመርቶ ጀመረው ጉዞም መልካም ሆነለት። ትከሻው ዝሎ እጅ ቢያጥረውም፣ ስለልጁ መኖር አስቀድሞ ተራመደ። ተሳካለትም።

ቤት ለእንግዳ…

አሁንም አባትና ልጅ ከጊምቢ አዲስ አበባ ምልልሳቸው ቀጥሏል። ቀጠሮው ሳብ እያለ ቢመጣም አስፋው አቅሙ እየተዳከመ እጁ እያጠረ ነው። እንደ ትናንቱ ከህክምናው የሚተርፍ በቂ ገንዘብ ከእጁ የለም። ሁሌም ከቤቱ ወጥቶ እስኪመለስ ይጨነቃል፣ ያስባል። አንድ ቀን ከሚመላለስበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር የእሱን ችግር የሚፈታ መፍትሄ ተገኘለት። አባትና ልጁን ሳይነጣጥል ተቀብሎ የሚያስተናግደው የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ሁለቱን ነፍሶች ተቀብሎ ‹‹ቤት ለእንግዳ›› ሲል መፍቀዱን አወቁ። ይህ እውነት በጊዜው ለአባት አስፋው ጆሮ የሚታመን አልነበረም። እንደተባለው ከስፍራው ደርሰው ቤተኞች ሆኑ። ንጹህ መኝታ፣ በቂ ምግብና መልካም መስተንግዶ ጠበቃቸው።

ይህ ቦታ እንደቀነኒሳ ያሉ በካንሰር የተጠቁ ህጻናትንና ወላጆቻቸውን በወጉ ተቀብሎ የሚያስተናግድ ተቋም ነው። ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ህሙማንና ቤተሰቦቻቸውን በማስተናገድ የህክምና ክትትል እንዲያገኙ፣ የመድሃኒት ድጋፍ እንዲኖራቸውና ደርሰው ለመመለስ የትራንስፖርት ወጪ እንዲሸፈንላቸውም ያደርጋል።

በዚህ አጸድ የሚገናኙ እንግዶች ሁሌም ቤተሰብ ሆነው ጉዳያቸውን ይከውናሉ። ዛሬ ቀነኒሳና አባቱ የዚህ ቤት እንግዶች አይደሉም። ይህ ዕልፍኝ በቀጠሯቸው ጊዜ ከፍተው የሚገቡበት፣ በፍቅር እያሰቡ የሚናፍቁት ማረፊያቸው ሆኗል።

አባት አስፋውና ልጁ ቀነኒሳ ዛሬ ላይ ቆመው የነገን ተስፋ እያሰቡት ነው። ሁሌም ከፊታቸው ገጽ ፈገግታ ይነበባል። ይህ እውነት የነገው ማንነታቸው ሆኖ ዛሬ ላይ ይደምቃል። ስለ ፍቅር የተከፈለው ዋጋም ዛሬ ፍሬው ሊበስል ከጫፍ እንዲህ ደርሷል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You