አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩትና ሃላፊዎቹ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 291/2005 መጤ ዝርያዎች አካባቢን እንዳይበክሉ በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት ባለመወጣት ለደረሰውና ለሚደርስ ሀገራዊ ጉዳት ተጠያቂ መሆን እንደሚገባ ዋና ኦዲተር ገለጸ።
የዋና ኦዲተር የውጭና የህዝብ ግንኙነት በላከልን መግለጫ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰኔ 05 ቀን 2011 ዓ.ም እትም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ ተቋማቸው የዋና ኦዲተር የክዋኔ ሪፖርት አልቀበል ማለታቸው ፈጽሞ ተገቢነት የሌለው መሆኑን አስታውቋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 101 እና በአዋጅ ቁጥር 982/2008 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የፌዴራል መስሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ያስገኙት ውጤት ህጉን የተከተለ፣ ኢኮኖሚያዊ በሆነ አሰራር የተፈጸመ መሆኑንና ተፈላጊውን ግብ መምታቱን ለማረጋገጥ እንደየአስፈላጊነቱ የክዋኔ ኦዲት ያደርጋል።
ዋና ኦዲተር በተሰጠው ስልጣን መሰረት ኢንስቲትዩቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአገሪቷ የብዝሀ ህይወት ሀብት ከውጭ በሚገቡ ልውጥ ህያዋን እና ወራሪ መጤ ዝርያዎች እንዳይበከልና ጥፋት እንዳይደርስበት ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ሃላፊነቱን መወጣቱን ኦዲት ተደርጎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደርና የቀረበውን ሪፖርትም የአመለካከትና የግንዛቤ እጥረት እንዳለበትና አካሄዱም ትክክል አለመሆኑ በመግለጽ ዋና ዳይሬክተሩ የሰጡት መረጃ ፍጹም ተገቢነት የሌለው መሆኑ ዋና ኦዲተር አመልክቷል።
የተሰጠው አስተያየት ተቀባይነት የሌለውና የራስን ድክመት ለመሸፈን የተደረገ ጥረት ነው ያለው ዋና ኦዲተር፣ ኢንስቲትዩቱ ድክመትን ከመሸፈን ይልቅ በኦዲት የተሰጠውን አስተያየት በመቀበል የሀገሪቱን የውሃ አካላትና የብዝሀ ህይወት ሀብቶቻችንን አሁን ካለውና በቀጣይም ከሚመጣው ችግር ለመታደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ የተሻለ መሆኑን በመግለጫው አስገንዝቧል።
ኢንስቲትዩቱ መጤ ዝርያዎችን መቆጣጠር በህግ የተሰጠው አንደኛው ተግባር በመሆኑ በዚህ ዙሪያ የቅድመ መከላከል፣ የቁጥጥርና የጥናት ስራ ማድረግ የሚጠበቅበት ተግባር ነው፡፡ ይህንንም ለማከናወን የሚያስችለውን አቅምም ሆነ መዋቅር መፍጠሩም አስፈላጊና ከራሱ የሚጠበቅ ስራ ነው፡፡
ለስራው አስፈላጊ የሆነውን ይህንን ተቋማዊ አቅምና አደረጃጀት አለመፍጠር የመጤ ዝርያዎችን ላለመከላከልና ላለመቆጣጠር እንዲሁም በዚህ ዙሪያ ተገቢውን ምርምርና ጥናት ላለማድረግ በጥቅሉም የተሰጠን ተልዕኮ ላለመወጣት በማመካኛነት የሚቀርብ ጉዳይ ከተጠያቂነትም እንደማያድን በመግለጫው ተገልጿል።
አጎናፍር ገዛኽኝ