አዲስ አበባ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የ2012 ዓ.ም ምርጫ ለማገዝ ከኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር የ40 ሚሊዮን ዶላር የትብብር ስምምነት አደረገ።
ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሲሆኑ ከተመድ የልማት ፕሮግራም ደግሞ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ቱርሃን ሳላህ ናቸው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የትብብር ስምምነቱ ከተካሄደ በኋላ ባደረጉት ንግግር አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር በወሰደው ተስፋ ሰጪ እርምጃ በጋራ መከባበርና መተማመን ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲ እንዲያብብ በር መክፈቱን ጠቅሰው፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ለማስፋት መንግሥት ባለው ቁርጠኝነት የፖለቲካ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአዲሱ ማሻሻያ ኢትዮጵያ አካታች፣ ሁሉም የሚወዳደርበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ከወዲሁ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በተወሰደ እርምጃ እና በመጣው ለውጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ አህመድ ሽዴ አያይዘውም የተፈራረምነው የ40 ሚሊዮን ዶላር የትብብር ስምምነት የምርጫ ቦርድን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር ኃላፊነቱን በአግባቡና በታማኝነት ለመወጣት ያስችለዋል ሲሉ አስታውቀዋል።
በስምምነቱ ላይ እንደተገለጸው ከ40 ሚሊዮን ዶላር ስምምነቱ ውስጥ 34 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በተለያዩ የልማት አጋሮች የሚደገፍ ሲሆን የተመድ የልማት ፕሮግራም በራሱ 2 ሚሊዮን ዶላር እና 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በምርጫው ፕሮጀክት ወቅት ለተዘዋዋሪ ፈንድ የተቀመጠ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ በመሠረታዊነት እና በስልታዊነት የምርጫውን ፕሮጀክት ለመደገፍ ፣ የምርጫውን ሂደትና የምርጫ ቦርድ እንቅስቃሴን ያግዛል። አዲሱ የምርጫ ቦርድ አመራር ባለፈው ኅዳር ኃላፊነት ከያዘ በኋላ የተመድ የልማት ፕሮግራም የቅርብ አጋራችን ሆኖ ሁለንተናዊ የማሻሻያ ፕሮግራሞችን በቅርብ ሆኖ ሲደግፈን ነበር ብለዋል።
ይህን የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት በምናቅድ ጊዜ በቅርብ ሆኖ ሲደግፈን ቆይቷል ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፣ ቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ ከቀደሙት የሀገራችን ምርጫዎች ይበልጥ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ብዙ ፖለቲካ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲሁም የሕግ ማዕቀፎችን በማርቀቅ ምርጫው በሀገራችን ታሪክ ውስጥ አንድ ጠቃሚ ሁነት ይሆናል ብለዋል።
ብቃታችንን ለማሻሻል ግልፀኝነትን ለመፍጠር አካታችነትን በመፍጠር ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊ ፣ታማኝና ስኬታማ እንዲሆን እንጥራለን ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከባለድርሻ አካላትና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ያለንን ግንኙነት እያጠናከርን ነው ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፣ ስምምነቱን ርዕያችንን ለማሳካት ይረዳናል ሲሉ ገልጸዋል።
ከባለድርሻ አካላትና ከልማት ድርጅቶች ጋር በመሆን ድጋፋችንን እናደርጋለን ያሉት የተመድ የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ቱርሃን ሳላህ የተመድ የልማት ፕሮግራም ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ