ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ መዳን ይችላል ወይስ ይዳፈናል?

/ክፍል አንድ/

ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም NBC ኢትዮጵያ በተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ዶ/ር ደምሴ ታደሰ የተባሉ “የስኳር በሽታ የሚድን ነው” ብለው ሰፊ ውይይት የተደረገበትን፣ በyoutube ላይ የተጫነውን ቪዲዮ አይቸዋለሁ። በሥነ ምግብ ከማስተርስ እስከ PhD ያሉ ተማሪዎችን ከ10 ዓመት በላይ ሳማክር ስለቆየሁ ከስኳር በሽታና ሥነ ምግብ ጋር በተያያዘ ብዙ ምርምሮችን ስለምከታተል የውይይቱ ሃሳብ ሳበኝና ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተነሳሳሁ። የአማርኛ ፊደላት አጠቃቀም ላይ የፈጠርኩት ግድፈት ካለ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

አንዳንድ የሕክምና ቃላቶችን ወደ አማርኛ መተርጎም አልቻልኩም። ካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲን እና ስብ (ፋት/ሊፒድስ) ለሚባሉት የምግብ ዓይነቶች ቀደም ብሎ የተሰጣቸው አቻ የአማርኛ ትርጉም በእጅጉ አሳሳች ስለሆነ (ኃይል ሰጭ የተባለው ካልተጠቀምንበት ገምቢም ስለሆነ፣ ገንቢ የተባለው በተወሰነ ደረጃ ኃይል ሰጭም ስለሆነ እና ስብ ምግቦች ለኃይል ምንጭነት ጭምር ስለሚውሉ) ካርቦሃይድሬት እና ፕሮቲን ሳይተረጎሙ እንዳሉ እንለማመዳቸው። ስንት አስቸጋሪ የታዋቂ ፈረንጆች ስም ስንይዝ መቼ ከበደን። Remis­sion ለሚለው በትክክል የሚገልፅ የአማርኛ አቻ ትርጉም ስላጣሁ (ሌላ በሙያው ላይ ያለ ሲኒየር ሐኪም አማክሬ) “ማዳፈን” በሚለው ትርጉም ተስማምተናል።

ለፕሮግራሙ አዘጋጆች (ዶ/ር አበባ የሺጥላ እና ዶ/ር ይሁን አየለ) እና ተጋባዥ እንግዳ ለነበሩት ዶ/ር ደምሴ ታደሰ ምስጋና እያቀረብኩ፣ ሶስቱም ባለሙያዎች ሕዝብም ሆነ ባለሙያ አስተያየት እንዲሰጥበት ስለጋበዙ (ሃሳቡን ለአስተያየት ክፍት ስላደረጉት) እኔም በትንሹ አስተያየት መስጠት በቂ ሆኖ ስላገኘሁት ትንሽ ዘርዘር ያለ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ወሰንኩ። የዶ/ር ደምሴን አስተያየት በተወሰነ ደረጃ ብጋራም የማልስማማባቸው ትንሽ ጠንከር ያሉና ጅምላ አስተያየቶች ስላሉ አድማጮችን እንዳያሳስቱ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚችሉት ነጥቦች ላይ የግል አስተያየቴን እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ።

ሁሉም ሰው ይህን የእኔን ጽሑፍ ከማንበቡ በፊት ውይይቱን ከyoutube ላይ ቢያይ ግንዛቤው ሙሉ ይሆናል። በውይይቱ ላይ የተገለፁ ብዙ ገንቢ ሃሳቦች በዚህ ጽሑፍ አልተካተቱም። ከሁሉ በፊት እንደዚህ ዓይነት ውይይት መጀመሩን ሳላደንቅ አላልፍም። ይህ የጤና ችግር የብዙ ሰውን ቤት አንኳኩቷል። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የተለያየ የማከሚያ መንገድ እያቀረቡ ሕዝቡን ለብይታ የዳረጉት አሉ። ስለዚህ ሳይንሳዊ እና አለማቀፋዊ የሆኑ የመከላከያ እና የማከሚያ ዘዴዎችን (Con­ventional prevention and treatment package) ሕዝቡ በግልፅ እንዲረዳ ሙያው የሚመለከታቸው ጭምር ርብርብ እንዲያደርጉ ለመጠቆም እኔም ይችን ጽሑፍ እንድታነቡልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ። ሕዝባችን በብዙ የጤና ችግሮች የሚጎዳው ስለ ጤናና ሕክምና በቂ ግንዛቤ ስለማያገኝ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።

በተለይ እንደ ዶ/ር አበባ ዓይነት (የጤና ባለሙያ የሆኑ ወይም በቂ ግንዛቤ ያላቸው አወያዮች) ቢበዙ የሚፈለገው ውጤት የሰመረ ይሆናል። የሕዝብ ቀዳሚ ችግር እየሆኑ በመጡት እና በብዙ መንገድ መከላከል በምንችላቸው የእድሜ ልክ በሽታዎች ላይ በቂ ግንዛቤ ገና አልሰረፀም። ለብዙ አስርት ዓመታት ተላላፊ በሽታዎች ላይ ትኩረት አድርገን ስለቆየን፣ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ጭምር የምዕተ ዓመቱ እና የዘላቂ እድገት መለኪያ የተደረጉት በቀዳሚነት ተላላፊ በሽታዎች፣ የእናቶችና የልጆች ጤና ስለነበሩና አሁንም ስለሆኑ፣ ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮች ወረርሽኝ በሚመስል መልኩ እየጨመሩ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ሀገራችን የሁለቱም ችግር ገፈት ቀማሽ እንድትሆን አድርጓታል። በዚህ ላይ በምግብ እጥረት፣ በሱስ አምጭ እና ተጓዳኝ ችግሮች ከፍተኛ ተጠቂ ሆና እንደቀጠለች ነው።

ወደ ተነሳሁለት ርዕስ ስመለስ በመጀመሪያ ሁለተኛው ዓይነት (የአዋቂዎች) የስኳር በሽታ (Type II Diabetes Mellitus) በአብዛኛው በጎልማሳነት እድሜ ላይ ባሉ ሊዳፈን (Remis­sion)፣ በተወሰነ ደረጃ ለረጅም ጊዜ ላይታይ (long-term remission) እንደሚችል በቂ ሳይንሳዊ መረጃዎች ስላሉ፣ የዶ/ር ደምሴ አስተያየት ከሞላ ጎደል ትክክል ቢሆንም ጨርሶ ሊድን (Cure) ይችላል የሚለው ገና ያልተረጋገጠ ነው። እስካሁን ባለው ሳይንሳዊ መረጃ፣ አንድ ሰው በወሰዳቸው ርምጃዎች ከምልክቶቹ ነፃ ሆነ ማለት ዳነ ማለት አይደለም (ዝርዝሩ ከታች ቀርቧል)። ይሁን እንጂ ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ “የማይመለስና” እየጨመረ የሚመጣ (ir­reversible and progressive) የሚለው የቀደመ አስተሳሰብን የለወጡ እጅግ ብዙ መረጃዎች መውጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፤ በተግባርም ከሰዎች እና ከሥራ ልምድ ማየት ተችሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት እአአ በ2016 መረጃዎችን አሰባስቦ ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ማዳፈን እንደሚቻል ገልጿል። በእንግሊዝ የስኳር በሽታ ማህበርም የካሎሪ መጠናቸው በጣም ያነስ ምግቦችን በመጠቀም፣ እንደዚሁ ካርቦሃይድሬት ምግቦችን በመቀነስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግና በኦፕሬሽን ማዳፈን እንደሚቻል ድምዳሜውን አስቀምጧል። የአሜሪካ እና የአውሮፓ የስኳር ማህበራትም ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ መዳፈን እንደሚቻል ካሳወቁ በኋላ ሙሉ በሙሉ ማዳፈን (Complete remission) ለሚለው ትርጉም ሰጥተዋል (ካለመድኃኒት ለ3 ወር የደም የስኳር መጠን ወይም ሌላው መለኪያ HbA1c ኖርማል ሆኖ መቆየት/Normoglycae­mia መዳፈኑን ለማወጅ ያበቃል የሚል ነው)።

በዚህ መልኩ ለሕዝብ መግለፅ አመቺ ስላልሆነ እንጂ እጅግ ብዙ ሳይንሳዊ መረጃዎችን (ከ10 ዓመት በላይ ክትትል የተደረገባቸውን ጨምሮ) ማቅረብ ይቻላል። ስለዚህ ጉዳይ የመጀመሪያው ሳይንሳዊ መረጃ የወጣው እአአ በ1992 ነበር (በቀዶ ሕክምና ማዳፈን እንደሚቻል የተረጋገጠበት ጊዜ)። እአአ በ2008 እጅግ የላቀ በሚባለው ሳይንሳዊ የምርምር ዘዴ (Random­ized controlled trial) የቀረበ ጥናት ማዳፈን እንደሚቻል ብዙዎችን ያሳመነ መረጃ አወጥቷል። ሌላው በውይይቱ ጊዜ ተጠቅሷል። ስለሆነም በተለይ በዚህ ዘመን ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሳይደርስ ከብዙ ሰዎች ላይ ማዳፈን እንደሚቻል እጅግ ብዙ ሳይንሳዊ መረጃዎች ስላሉ የሳይንሳዊ መረጃ ክፍተት የለም። ትልቁ ነጥብ እንዴት ይቻላል የሚለው ነው (ከታች በጥቂቱ ተጠቁሟል)።

እንዲያውም (በውይይቱ ጊዜም እንደተጠቆመው) ከሕይወት ተሞክሮ ጭምር እጅግ ብዙ መረጃዎች ስላሉ፣ በዚህ ርዕስ ላይ የመገናኛ ብዙሃን በስፋት ቢሰሩ፣ በከተሞች  አካባቢ እንደወረርሽኝ እየጨመረ የመጣውን የሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ እና ተጓዳኝ ችግሮች ማጥፋት ባንችል እንኳን በከፍተኛ ቁጥር ለማዳፈን ያስችለናል። በዚሁ መድረክ ከሀገር ውስጥ ወደየ ስፖርት ማዕከሎች እየሄዱ ቢጠይቁ ወይም ሌሎችም ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ቢመቻች እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ምስክርነት ሊሰጡ ይችላሉ። ቀድሞ ለዓመታት መድኃኒት ሲወስዱ የነበሩ ክብደት በመቀነስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የኑሮ ዘይቤ በማድረግ እና አመጋገብን በማስተካከል (በተለይ ጤናማ ያልሆነ የአንጀት ውስጥ ተህዋስያን አለመመጣጠን ችግር/Gut microbiota dysbiosis) የሚያስከትሉትን ምግቦች በመተው፣ ለዓመታት ከመድኃኒት ነፃ የሆኑ ሰዎችን ማግኘት እና ከልምዳቸው ብዙ መማር ይቻላል። ሕዝባችን ከዶክተር ከሚሰማ ልምዳቸውን ከሚያካፍሉ ሰዎች የበለጠ ማወቅ ይፈልጋል። በውጭ ሀገር ካሉት ደግሞ ከኢንተርኔት ላይ የብዙ ሰዎችን ልምድ ማንበብ እና ለሕዝቡ ማካፈል ይቻላል። እጅግ ብዙ ሰዎች ለራሳቸው ሐኪም ሆነዋል። ይህ እንደሚቻል ብዙ የሕክምና ባለሙያዎች ያውቃሉ።

ታዲያ መቼ ነው ሁለተኛውን ዓይነት የስኳር በሽታ ማዳፈን እንደሚችል በይፋ ለመናገር የምንደፍረው? ለዓመታት መድኃኒት ላይ ጥገኛ የነበሩ ከመድኃኒት ነፃ ሆነው የሕይወት ዘይቤያቸውን የቀየሩ ሕያው ምስክሮች እጅግ ብዙ እያሉን? ያው እንደብዙው ነገር ፈረንጅ መጥቶ እስኪነግረን መጠበቅ አለብን? እነሱ እዚህ መጥተው ባይናገሩ ከሰሯቸው ምርምሮች በቂ መረጃ አግኝተናል። እኛም ልምዳችንን በምርምር አስደግፈን ብናወጣው ጤና ሚኒስቴር ሀገራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር በፕሮግራም እንዲይዘው እና አጋሮችን እንዲያስተባብርበት ትልቅ መሳሪያ ይሆነዋል።

በስኳር ሕመም ሕክምና ስፔሻላይዝ ያደረጉና የብዙ ዓመት ልምዳቸውን (አንድ ሳይሆን ሶስት አራት ወይም ከዚያ በላይ) እንዲያካፍሉ ማድረግ ቀዳሚ ቢሆን ጥሩ ነው። የስኳር በሽታ ማህበር ልምድ ቢጠየቅ ብዙ የማናውቀው ልምድና ምክረ ሃሳብ ማግኘት ይቻል ይሆናል። መልዕክቱ ሳይንሳዊ መረጃዎችን እየመረመርን እና የሀገራችንን ልምድ በምርምር መልክ እያቀረብን ከዘመኑ ጋር መራመድ መቻል አለብን የሚል ነው። የዚህ ችግር ተጠቂዎች የሆኑ በሽታውን ለማዳፈን በራሳቸው ጊዜ ብዙ ነገሮችን ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ በባለሙያ (የሕክምና፣ የሥነ ምግብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የሥነ ልቦና) የተደገፈ ምክር እያገኙ ቢሆን ውጤቱ የሚባዛ ይሆናል። ሕዝብ ስለጤናው ጠያቂ እና ጤናውን ጠባቂ እንዲሆን በቂ ግንዛቤ ይኖረዋል።

የእኔ ስጋት (በውይይቱ ጊዜም እንደተጠቆመው) ሕዝባችን በዚህ መረጃ (በፕሮግራሙ ላይ ከቀረበው) ብቻ ተነሳስቶ ግብታዊ የሆነ ስህተት እንዳይፈፅም (መድኃኒት መውሰድ በአንድ ጊዜ እንዳያቆም) ነው። መሰል ክርክሮች ለሕዝብ ሳይሆን ጥናት ሰርቶ ቀድሞ እርስ በርስ ቢሆን መልካም ነበር (በጤና ጉዳይ ባለሙያዎቹን አንተ ምን ትላለህ? አንተ ምን ትላለህ? ብሎ መጠየቅ ሕዝብን ውዥንብር ላይ የሚከት ነው)። እንደዚያ ለማድረግ አሁንም አልረፈደም፤ አዲስ ጥናት ማካሄድ ባይቻል በብዙ ሀገሮች የተሰሩትን አሰባስቦ በዓመታዊ ጉባኤዎች ላይ በማቅረብ ብዙዎቹ ሐኪሞች ሃሳቡን እንዲገዙት እና ታካሚዎቻቸውን ሁሉንም የማዳፈኛ ዘዴዎች እንዲተገብሩ በአማራጭነት እንዲያቀርቡላቸው ማድረግ ይቻላል።

ስለዚህ የመጀመሪያው ሥራ መሆን ያለበት ሳይውል ሳያድር በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ሃሳቡን የጋራ ማድረግ እና ሕዝቡ ከሚያምናቸው ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ታካሚዎች መድኃኒት ከማቆማቸው በፊት በቅደም ተከተል ሊፈፅሟቸው የሚችሉትን ማሳወቅ ያስፈልጋል። ታካሚዎችም መድኃኒት ከማቆማችሁ በፊት እጃችሁ ላይ ባለው የግሉኮስ መለኪያ ማሽን ተማመኑ፤ ስኳር መቀነሻውን እየተገበርኩ ነው በሚል ስኳሩ ሳይቀንስ መድኃኒት ማቆሙ አደጋው የከፋ ይሆናል። ከአሁን በፊት የስኳር በሽታ ብቻ ሳይሆን ኤች አይ ቪን ጨምሮ በባህል ሕክምና እናድናለን፣ “መድኃኒት ወይም መንፈሳዊ ፈውስ (ፀበልን ጨምሮ) ምረጡ” በሚሉ ምክሮች ብዙ ሰው ተጎድቷል (ሁለቱም የእግዚአብሔር ሥራ ስለሆነ በተጓዳኝ ውሰዱ ቢሏቸው ባልከፋ ነበር)። ከመሰል ስህተት ለመዳን በቅድሚያ መድኃኒቱን እየወሰዱ ከመድኃኒቱ ነፃ ለመሆን የባለሙያ ምክረ ሃሳቦችን መተግበር እና የስኳር መጠንን በጥንቃቄ መከታተል ያስፈልጋል።

ርግጥ ነው ለሁለተኛው የስኳር በሽታ አባባሽ (Factors) የሆኑትን መተው ወይም ለበሽታው መቀነስ የሚያግዙትን መተግበር ስኳር በደም ውስጥ እንዳይበዛ ብቻ ሳይሆን ማዳፈን ያስችላል። ከሁሉ በፊት ሊተኮርበት የሚገባው ይህን ማሳካት (ማዳፈን) የሚችሉት ሁሉም የሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ያለባቸው ላይሆኑ ይቻላሉ (ቢያንስ በእድሜ የገፉ ሰዎች፣ መንቀሳቀስ የማይችሉ አካል ጉዳተኞች፣ የአእምሮ ታማሚዎች፣ ከሁለተኛው ወደ አንደኛው አይነት የስኳር በሽታ “የተቀየሩ”፣ በአብዛኛው በዘር ለሁለተኛው የስኳር በሽታ እና ተጓዳኝ ለሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑ እና Autoimmune poly­endocrine syndrome ተጠቂ የሆኑ ሰዎች በጣም እንዳይብስ ማድረግ ይችሉ ይሆናል እንጂ እስከ ማዳፈን ላይሳካላቸው ይችላል)። በመጀመሪያው ሶስቱ የሚመደቡት ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው ከሆኑ በኦፕሬሽን (Bariatric surgery) ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ።

ስለሆነም ምክሩን ስንሰጥ ለይተን መሆን አለበት። እንደዚያ ስል የስኳር በሽታ ያለባቸውን እንደማሳነፍ ተደርጎ እንዳይወሰድብኝ። አዕምሮ ትልቅ ኃይል አለውና አንድ ሰው እችላለሁ ብሎ ከተነሳ ብዙ ነገር ይችላል። ህዋሳቶቻችን ንቁ አዕምሯችን ካገዛቸው እጅግ ብዙ ዓይነት በሽታዎችን መከላከል እና ማዳፈን ይቻላል። ሁሉም ነገር ያለው ህዋሳቶች ላይ ነው። ህዋሳቶቻችን ችግኞች ናቸው።

የሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ መነሻው ሰውነታችን (ህዋሳቶቻችን) ካርቦሃይድሬት የበዛባቸውን ምግቦች መጠቀም ሲያቅተው (ሳይፈልግ) እንደሆነ ይታወቃል። ለምን ለሚለው ብዙ መላምቶች ቢሰጡም በትክክል አይታወቅም። አንዳንዱ በዘር የሚወረስ ነው። እዚህ ጋ የሚታወቀው (ለሁሉም ባይሆንም) አጋላጭ የሆኑትና ሂደቱ ነው (ሰውነታችን ካርቦሃይድሬት መጠቀም የማይችለው) 1. በመጀመሪያ ባለመንቀሳቀሳችን (ጡንቻችን ስላልሰራ) ወደ ኃይል (ATP) መቀየር ሳይችል ሲቀር ወይም 2. ግላይኮጅን በሚባለው መልኩ መከማቸት ከሚችለው በላይ ሲሆንበት እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ 3. ትርፍ የሆነው ካርቦሃይድሬት ወደ ስብነት መቀየር ሳይችል ሲቀር ነው። ካርቦሃይድሬት በቀዳሚነት ኃይል ሰጭ በመባል ቢታወቅም መከማችት ከሚችለው ወይም ለኃይል ምንጭነት መጠቀም ከምንችለው በላይ የሆነው ሁሉ ወደ ስብነት ይቀየራል።

እነዚህ ሶስት ሂደቶች በትክክል የሚከናወኑት በልጅነት እና በወጣትነት እድሜ ላይ እያለን፣ እድሜያችን ሲገፋም በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ውፍረትን ስንከላከል እና አመጋገባችንን ስናስተካክል ወይም በዘር ተጋላጭ ካልሆንን ነው። እድሜያችን ከፍ እያለ ሲመጣ እንቅስቃሴ አለማድረጋችን ብቻ ሳይሆን ትርፍ የሆነውን ካርቦሃይድሬት ወደ ጮማነት የመቀየር ሂደቱ ይቀንሳል፤ ኢንሱሊን ለሚባለው ሆርሞን በአንዳንድ ሰዎች ላይ አልታዘዝ ይላል። በቀላል አማርኛ ህዋሳቶቻችን እራሳቸው ውፍረትን መከላከል ይጀምራሉ፤ ጡንቻችን ስለማይሰራ የለሙ የካርቦሃይድሬት ንጥረ ነገሮችን መቀበል ይቀንሳል። በሁሉም ሰው ላይ ባይሆንም ይህም (ህዋሳት ለኢንሱሊን በጎ ምላሽ አለመስጠት) የህዋሳት እርጅና አንዱ ምልክት ነው።

በተለይ ቀድሞ በሥራም ይሁን አቅዶ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረ ሰው ሁሉንም አቁሞ ቢሮ መቀመጥ ሲያበዛ፣ ሁልጊዜ ሊፍት ላይ ሲንጠለጠል፣ የመኪና ወዳጅ ሲሆን፣ በትንሽ መጠንም ቢሆን ጤናማ አይደለም የሚባለውን አልኮል ሲያዘወትር፣ እድሜ ከፍ ሲል፣ ህዋሳቶች ግሉኮስ መጠቀም ይቀንሳሉ። ምክንያቱም ከግሉኮስ የሚያመርቱትን ኃይል (ATP) እየተጠቀምንበት አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ ከእናት ከአባቱ ያልወረሰው ወይም ሲወለድ የቀነጨረ ሆኖ ጤናማ ያልሆነ የሰውነት ክብደት ሲጨምር፣ አእምሮው በሥራ ጫና ሲወጠር፣ በረጅም ጊዜ ሂደት ግሉኮስ ለአንጎል እና ለልብ በብዛት እንዲሄድ ይደረጋል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሥራ የሚበዛባቸው እነዚህ አካሎች ስለሆኑ ግሉኮስ ወደነሱ እየተላከ፣ ስትረስ እየጨመረ፣ ስትረስ ለሰውነት ብግነት (Inflammation) እያጋለጠ፣ ቶሎ ቶሎ የማይቀየሩት የጡንቻ ህዋሳት እየሟሸሹ ሲሄዱ፣ የስብ ክምችት በጉበት እና በቆሽት ላይ ይጨምራል። የቅርብ ጊዜ ጠንካራ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በየትኛውም መጠን ያለ አልኮል ጎጂ እንጂ ጠቃሚ አይደለም። አልኮል ከፍተኛ ካሎሪ ካላቸው ምግቦች የሚመደብ ስለሆነ የስኳር በሽታ አባባሽ ነው። የስኳር በሽታም አልኮልም ጉበት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መሆናቸው ችግሩን “ከድጡ ወደ ማጡ” ሊያደርገው ይችላል።

በመሆኑም (ካርቦሃይድሬት መብላታችንን እስካልቀነስን ድረስ፣ ብንቀንስ እንኳን ሌሎች የምግብ ዓይነቶችንም አብዝተን ከወሰድን ወደ ግሉኮስ የሚቀየሩበት ሂደት ስላለ) በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን እንዲጨምር ያደርገዋል። በትክክል ብንገነዘበው (በውይይቱም እንደተገለፀው) የስኳር መጠን መጨመር ህዋሳት እንደቀድሞው አለመሥራታቸው አንዱ ምልክት ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካላደረግን የጡንቻ ህዋሳት ስለማይሰሩ ኃይል (ATP) የሚሰጥ የላመ ምግብ (ግሉኮስ) መቀበላቸውን ይቀንሳሉ፤ ጉበትና ጡንቻ ውስጥ በግላይኮጅን መልክ መከማቸት ከሚችለው በላይ የሆነው ግሉኮስ ወደ ስብነት መቀየሩ ይቀንሳል፤ ከስብ የሚገኙት የኃይል ምንጮች (Ketone bodies) ይጨምራሉ (ይህም በጥቅሉ ሰውነታችን ግሉኮስን ለመጠቀም ለኢንሱሊን አልታዘዝ አለ ይባላል (In­sulin resistance)። በርግጥም የጡንቻ ህዋሳቶች እንዳይሰሩ ያደረጋቸው ንቁ አእምሯችን ነው (ስንፍና)።

ሰውነታችን ያልተቃጠለ የካርቦሃይድሬት (ወደ ኃይል ምንጭነት ያልተቀየረ) ምግብን በግላይኮጅን መልክ መከማቸት የሚችለው እንደሰውነታችን ክብደት መጠን ከ300-500 ግራም ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከምንበላው ጋር ሲነፃፀር በጣም ትንሽ ነው። ሂደቱ እየሠራ ከሆነ እና ህዋሳቶች ለመደበኛ ሥራ ከሚያስፈልጋቸው (Basal metabolism) ውጭ የሆነው፣ በተጨማሪ የህዋሳት ሥራ (እንቅስቃሴ) ያልተቃጠለው በዋናነት ጉበት ውስጥ ወደ ስብነት ይቀየራል (Lipogenesis)፤ ስቡ በተለያየ የሰውነት ክፍል (ጉበትና ቆሽትን ጨምሮ) ይከማቻል።

ትንሽ ሰፋ ለማድረግ (ከይቅርታ ጋር) ካርቦሃይድሬት የሆኑ ምግቦች በኤንዛይሞች አማካኝነት በአብዛኛው ወደ ግሉኮስ ተቀይረው በደም ስር ይመጠጣሉ። ከዚያም ከረጅም ኬሚካላዊ ሂደት በኋላ በህዋሳቶች ውስጥ አሴታይል ኮ ኤንዛይም A (Acetyl CoA) ወደሚባለው ኬሚካል ይቀየራሉ። ቁልፉ ነገር እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ነው።

1. ከተንቀሳቅሰን ወደ ኃይል ምንጭነት (ATP) ይቀየራሉ (የበላነው ምግብ “ተቃጠለ” ይባላል)።

2. ካልተንቀሳቀስን እና ህዋሳቶች ለመቀበል ዝግጁ ከሆኑ (ለኢንሱሊን በጎ ምላሽ ከሰጡ) ወደ ስብነት ይቀየራሉ (እንወፍራለን)።

3. ካልተንቀሳቀስን እና ህዋሳቶች የተመረተውን Acetyl CoA ለመቀበል ዝግጁ ካልሆኑ ተጨማሪ ግሉኮስ ወደ Acetyl CoA አይቀየርም፤ እንዲያውም ህዋሳቶች የስብ ቅንጣቶችን መጠቀም ስለሚጀምሩ ፕሮፓዮኒል CoA (Propio­nyl-CoA) እና ሌሎችም የስብ ኬሚካሎች በህዋሳት ውስጥ ይበዛሉ። ይህ ደግሞ ግሉኮስ ወደ ህዋሳት እንዳይገባ ይከላከላል።

4. ግሉኮስ ደም ውስጥ እየበዛ ስለሆነ (Insulin resistance ወይም ለኢንሱሊን አለመታዘዝ ስላለ) እንዲቀንስ ለማድረግ የኢንሱሊን መመረት በከፍተኛ መጠን ይጨምራል (Hyperin­sulinemia)። ኢንሱሊን የሚያመርቱ የቆሽት ህዋሳት (Beta cells) ደም ውስጥ ስኳር መብዛቱን ሲያሸቱ ኢንሱሊን በማምረት ሥራ ይበዛባቸዋል። ነገር ግን የጡንቻ ህዋሳቶች እየሠሩ ስላልሆነ (ለኢንሱሊን አልታዘዝ ስላሉ) የተወሰነው ግሉኮስ በስብ መልክ ጉበት ውስጥ ይከማቻል። የቀረው ግሉኮስ ሳይቀየር በደም ውስጥ ይከማቻል (ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ተፈጠረ ይባላል)።

የድምር ውጤቱ (ጮማ በጉበት ውስጥ መከማቸቱ የሚቀጥል ከሆነ) ችግሩን የሚያብስ ይሆናል፤ ምክንያቱም ተጨማሪ የስብ ቅንጣቶች ወደተለያዩ ህዋሳት ይለቀቃሉ፤ ኢንሱሊን ከምታመርተው ቆሽት ጭምር ስብ ይከማችና ኢንሱሊን ማምረት ያቅታታል። የሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ምልክቶች መታየት ሲጀምሩ በደም ውስጥ ከፍተኛ ግሉኮስ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ኢንሱሊን ጭምር ይገኛል። በጊዜ ሂደት ኢንሱሊን የሚያመርቱ የቆሽት ህዋሳት በጮማ ክምችት እየደከሙ ሲመጡ የኢንሱሊን የመመረት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል (ከHyperinsulinemia ወደ Hypoinsulinemia)።

የኢንሱሊን የመመረት መጠን እየቀነሰ ሲመጣ በደም ውስጥ የሚከማቸው የግሉኮስ መጠን የበለጠ ይጨምራል። በዚህ ጊዜ ብዙ መጠን ያለው እና ዓይነቱም የበዛ የሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ መድኃኒት ቢወሰድ ውጤታማ አይሆንም። አንዱ አንዱን እያባሰ መመለስ ወደማይችልበት ደረጃ ያደርሳል ወይም አዙሪት ይፈጠራል/ጡዘቱ ይከርና ጉዳቱ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ይደርሳል። የቆሽት ህዋሳት በ0.5 ግራም ስብ ክምችት ከጥቅም ውጭ ሊሆኑና ኢንሱሊን ማምረት ከመቀነስ አልፈው ሊያቆሙ ይችላሉ። እዚህ ደረጃ ሲደርስ መድኃኒቱን ወደ ኢንሱሊን መቀየር ግድ ይሆናል። ታካሚውም የሁለተኛው ዓይነት ሳይሆን የአንደኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ያለበት ተብሎ ይመደባል። ለዚያ ነው ብዙዎች ኪኒን ሲወስዱ ይቆዩና ወደ መርፌ (ኢንሱሊን) የሚቀየርላቸው። ይሄ ጥሩ ምልክት አይደለም።

በእንደዚህ ዓይነት መድረክ ፍንጭ እንጂ ማብራሪያ ለመስጠት አመች ስላልሆነ የቀረበውን አስተያየት አስመልክቶ (ሁለተኛውን ዓይነት የስኳር በሽታ ለማዳፈንም ሆነ ቀድሞ ለመከላከል) ሰዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ በሚለው ላይ ትንሽ ልበል። በቅድሚያ ስድስት ነገሮችን ለመፈፀም መዘጋጀት ያስፈልጋል።

  1. የመጀመሪያውና ከሁሉም ቀዳሚው በቂና ዘላቂነት ያለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ነው።
  2. አመጋገብን ማስተካከልና የሚያብስብንን ምግብ ሁሉ ለይቶ መተው ነው።
  3. እፅ ከሚባሉ (አልኮል፣ ትምባሆ በሲጋራ ወይ በሺሻ፣ ጫት፣ ሱስ አስያዥ መድኃኒት እና ሌሎች) ሁሉ መታቀብ ያስፈልጋል።
  4. ስትረስን በሚቻለው ሁሉ መቀነስ (ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ስትረስ ለረጅም ጊዜ እንዳይቆይ ማድረግ ሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታ ጨምሮ ከብዙ ነገር መከላከል ያስችላል)።
  5. በቂ የፀሐይ ብርሃን ማግኘት (እጅግ ብዙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሁለተኛው ዓይነት ስኳር በሽታን ጨምሮ ከቫይታሚን ዲ እጥረት ጋር እንደሚገናኙ ብዙ አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ነው)። ሳይታወቀን ለቀናት በቂ የፀሐይ ብርሃን ሳናገኝ እየቆየን ብዙዎቻችን (የቢሮ ሰዎች) ለቫይታሚን ዲ እጥረት የተጋለጥን ነው።
  6. በቂ እንቅልፍ ማግኘት (አንዱ የስትረስ እና የደም ስኳር መጠን መቀነሻ መፍትሔ ስለሆነ)

ይፍሩ ብርሃን (ፕ/ር)

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You