አዲስ አበባ፡- የዓለም አቀፍ የልማት ማህበር (IDA) 19ኛው ሀብት የማሰባሰብና የመተካት ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ፣ ለልማት አጋርነት ዋስትና የሰጠና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የለውጥ ሃዋርያ የሆነ መንግስት በመኖሩ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው ማስቻሉን የዓለም ባንክ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር ክርስታሊና ጂዮርጄቫ መሰከሩ፡፡
ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለውን፣ የታዳጊ አገራት የልማት ፋይናንስ አማራጮች ላይ ለሶስት ቀናት የሚመክረውን የዓለም አቀፍ የልማት ማህበር (IDA) 19ኛው ሀብት የማሰባሰብና የመተካት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሲከፍቱ እንተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡
ትግበራው ለልማት አጋርነት ዋስትና እንደሆነና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር አግዟል፡፡ ድጋፉ የኢኮኖሚ እመርታ እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡
ማህበሩ ከሚያደርገው ትብብር የተነሳ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ለውጥ ማስመዝገቧን ጠቁመዋል፡፡ ድጋፉ ለማህበረሰብ ልማት፣ ለገጠር ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡ በገጠር የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ ድርቅን በመከላከልና እገዛ የሚፈልጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን መደገፍ መቻሉንም ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉን ያካተተ የኢኮኖሚ እመርታ እያስመዘገበች መሆኑን አንስተው፣ እ.ኤ.አ ከ2004 እስከ 2018 በአማካኝ 10 ነጥብ አራት በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን ጠቁመዋል፡፡ ዕድገቱ የተመሰረተው በግብርናና በመንግስት የልማት ተቋማት አማካኝነት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ድህነትን በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደነበረውም ገልጸዋል፡፡
እኤአ በ2000 በአማካይ 52 ዓመት የነበረው የዕድሜ ጣሪያም በ2016 ወደ 65 ዓመት ከፍ ማለቱን አስታውሰው፣ የህጻናት ሞት ምጣኔ መቀነሱንና በሁሉም ደረጃ የትምህርት አገልግሎት እንዲስፋፋና ተማሪዎች ሳያቋርጡ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
የዓለም ባንክ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር ክርስታሊና ጂዮርጄቫ፤ በኢትዮጵያ የለውጥ ሃዋርያ የሆነ መንግስት በመኖሩ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው ማስቻሉን መስክረዋል፡፡ የአገሪቱ የዕድገት መጠን በአማካኝ ከ10 በመቶ በላይ ከፍ በማለቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ መንግስት ለግል ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ ተግባራዊ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡ ሰፊ የስራ ዕድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው ኢንቨስትመንት አበረታች ነው ያሉት ሃላፊዋ፤ ፕሮጀክቱ 13 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት የሚደረግበት መሆኑንና በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታትም ወደ 18 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ 75 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደተያዘ በመጠቆምም፤ ሀብቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር ለመቅረፍ፣ በአፍሪካ ውስጥ የተያዙ ፕሮጀክቶችን ተፈጻሚ ለማድረግና የግል ባለሀብቶች የአሰራር ስልታቸውን እንዲያዘምኑ እንደታሰበም አብራርተዋል፡፡
ለስደተኞች ድጋፍና ለድንገተኛ አደጋዎች ለመጠባበቂያነት እንደሚውልም አክለዋል፡፡ በጀቱ በተለይም ለአፍሪካ ቀንድ የታሰበ መሆኑን በመጠቆምም፤ የቀጣናው አገራት ግጭትን አስወግደው የሰላምና የትብብር ቀጣና እንዲሆን እንደሚያስችላቸውም ነው የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያ እመርታዊ ለውጥ እያሳየች በመሆኗ ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር የማያቋርጥ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ይገባል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ ኢትዮጵያ ሰፊ ሪፎርም በማካሄድ ላይ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡ ልማቱን የበለጠ ለማጠናከር አጠቃላይ የልማት አቅሞችን በኢኮኖሚ ውስጥ ለማሳደግ እየተጋች መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ በተለይም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎን የበለጠ የሚያበረታታ ሰፊ የስራ ዕድል ፈጠራና አጠቃላይ ኢኮኖሚውን የሚያሳድጉ ሰፋፊ የሪፎርምና የልማት እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የዓለም ባንክ ለአህጉራዊ ትስስርም ሰፊ ትኩረት በመስጠት ሰፋፊ አዳዲስ ፋይናንሶችን በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር አማካኝነት በተለይም ለአፍሪካ ቀንድ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ለታዳጊ አገራት የሚደረገው የልማት ፋይናንስ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግ ያላቸውን ተስፋም ጠቁመዋል፡፡
ጉባኤው በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተወሰነው ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለውን እርምጃ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል፡፡ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታትም በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር (IDA) ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆናቸውንም አቶ አህመድ አስታውሰዋል፡፡
ሀብት የማሰባሰብና የመተካት ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሱ የበለጸጉ አገራት በየሶስት ዓመቱ በልገሳ የሚያዋጡት ሀብት ሲሆን፤ የዓለም ባንክ አዲስ ፋይናንስ የሚያሰባስብበት ነው፡፡ ገንዘቡ የዓለም ባንክ ለታዳጊ አገሮች ቀላል ብድርና በስጦታ መልክ ለሚያበረክተው ተግባር ይውላል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011
ዘላለም ግዛው