ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በከፍተኛ ጥረት ውስጥ ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች። ግብርና መር በሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመመራት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያስመዘገበችው ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገትም የዚህ ማሳያ ነው። በቅርቡ ደግሞ አገሪቱ የጀመረችው የለውጥ እንቅስቃሴ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ጭምር የሳበና ለሁለንተናዊ እድገቷ መሠረት የጣለ ነው።
በየዓመቱ በአማካይ በ2ነጥብ 6 በመቶ እያደገ የሚገኘው ሕዝቧንም ከድህነት ለማውጣት የዘረጋቸው የልማት አቅጣጫ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጓዘ ነው። ለምሳሌ የሚሌኒየም የልማት ግቦችን ለማሳካት የሄደችባቸው መንገዶችና የተገኙ ውጤቶች ለዚህ አንድ ማሳያ ናቸው። በዚህም የእናቶችና የሕፃናት ሞትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ የተቻለ ሲሆን፣ አማካይ የዕድሜ ጣሪያንም በ20 ዓመት ውስጥ ከ43 ወደ 64 ማሳደግ ተችሏል። የትምህርት ተደራሽነትም ላይ የተመዘገበው ውጤት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከእነዚህም ጎን ለጎን ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ ሚሊየነር አርሶ አደሮችን ማፍራት ተችሏል። በቀጣይም ለግብርናው ልዩ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መንግሥት 20 ቢሊዮን ብር ለግብአት መድቦ የግብርና ልማት ሥራዎች ማከናወን መጀመሩ ኢትዮጵያ ለፀረድህነት ዘመቻው የሰጠችውን ልዩ ትኩረት ያመላክታል።
ከዚህም ጎን ለጎን ለዓለም ማህበረሰብ ጭምር አስጊ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ለመቋቋም ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በማከናወን ዓለምአቀፍ ትኩረትን መሳብ ችላለች። የተፋሰስ ሥራዎች፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ የከተማና የመጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን እንዲሁም የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችም የዚሁ አካላት ናቸው። በነዚህ ሥራዎች ላይ በተደረገው ርብርብም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ እነዚህንና መሰል የልማት ሥራዎችን ለማከናወን በምታደርጋቸው ጥረቶችም የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በተለይ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እና ለገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ድጋፍ ከፍተኛ ነው።
ይሁን እንጂ በአገራችን በየዓመቱ ወደማህበረሰቡ የሚቀላቀለውን ከ2ሚሊዮን ያላነሰ ሥራ ፈላጊ ኃይል ጥያቄ ለመመለስ የልማት ሥራዎችን አሁን ከተጀመረው በላይ በፍጥነት ማስኬድን የሚጠይቅ ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ዓለም ባንክ ዓይነት ትላልቅ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ ነው።
ትናንት ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር (አይዳ) ከ2021 እስከ 2023 ለታዳጊ ሀገራት ለሚያደርገው ድጋፍ ከለጋሽ ሀገራት ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችለውን ስብሰባ በአዲስ አበባ ለማድረግ የመወሰኑም ምስጢር ማህበሩ በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ያለውን እምነት የሚያሳይ ነው። በዚህ ስብሰባ መክፈቻ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ በተደረጉ ድጋፎች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ወይም አይዳ በኩል ድጋፍ ከሚያደርግላቸው 75 ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ድጋፉም በእርሻ፣ እንስሳት ሀብት ልማት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ እና ልማት፣ የከተማ እና የመጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን፣የገጠርና የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ላይ ያተኮረ ነው።
ከዚህም ባለፈ አይዳ ባለፉት ዓመታት በትምህርት፣ ጤና፣ ማህበራዊ ዋስትና፣ የፆታ እኩልነት፣ መልካም አስተዳደር ግንባታ እና ሌሎች ዘርፎች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ በአገራችን ለኢኮኖሚያዊ ሽግግሩ ትልቅ ተስፋ በተጣለባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመንገድ እና ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ያልተቆጠበ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የልማት የፋይናንስ ድጋፍ በእርዳታና በብድር አግኝታለች። በአሁኑ ወቅትም በዓለም ባንክ ድጋፍ ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ አገሪቱ ለጀመረችው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው።
በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነት ድጋፎች ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለማሳካትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቶችን በማፋጠን ሁለንተናዊ እድገት ለማስመዝገብ ከፍተኛ አቅም ይሆናታል።
ለታዳጊ አገራት የሚውል ድጋፍ ማሰባሰብ ላይ ያተኮረው ጉባኤም በአዲስ አበባ መካሄዱ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የልማት እቅስቃሴ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት የሚያሳይ ነው። ይህ ደግሞ በቀጣይ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በተሻለ ፍጥነት እንድታከናውን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ስለኢትዮጵያ አጠቃላይ የሪፎርም እንቅስቃሴ በቂ መረጃ ይዞ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያግዝ ነው።
ከዚህም ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተጀመሩትን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በሚፈለገው ፍጥነት እንዳታከናውንና የሪፎርም ሥራዎችም በተፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዙ እንቅፋት የሚፈጥር ሲሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ተከትሎ እያጋጠመ ያለው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትም እንዳይባባስ እንደ ዓለም ባንክ ዓይነት ትልቅ አቅም ያላቸው ተቋማት ድጋፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይታመናል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሪፎርም ሥራዎች አጠናክራ ለማስቀጠልና የልማት ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ ብሎም እድገቷን ለማፋጠን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚደረግላት ድጋፍ ከፍተኛ እገዛ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያደረገልን ያለውን ድጋፍና ይህንንም ተከትሎ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ፊታችንን ወደልማት ማዞርና ፈጥነን ከድህነት መውጣት የእያንዳንዳችን ግዴታ በመሆኑ በየተሰማራንበት የሙያ መስክ ለሰላምና ለልማት እንትጋ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011