አዲስ አበባ፡- ‹‹ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላም አበክራ መስራቷን ትቀጥላለች›› ሲል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 68ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ጠንካራ ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ትብብር ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡ ሱዳን ባለፉት ወራት በገጠማት ቀውስ ሱዳናውያን በሰላማዊ መንገድ ልዩነታቸውን እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
በተለይም በተቃዋሚዎች (በለውጥ ሃይሎች) እና በወታደራዊ ምክር ቤት መካከል በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን ልዩነት ለማጥበብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ካርቱም በማቅናት የሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ አስማምተው መምጣታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
እንደ አቶ ነቢያት ገለፃ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰየሙት አምባሳደር መሃሙድ ድሪር ከነፃነት ሃይሎች እና ወታዳራዊ ሽግግር መንግስቱ ጋር በተናጥል ባደረጉት ውይይት በተወሰኑ ነጥቦች ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከተግባቡባቸው መካከል ሁለቱ ወገኖች ድርድራቸውን ከማቋረጣቸው በፊት በሽግግር መንግስቱ አወቃቀር ስልጣን እና ሃላፊነት ዙሪያ ደርሰውበት ወደ ነበረው ስምምነት እንዲመለሱ ማድረግ ላይም ውይይት መካሄዱን ቃል ዓቀባዩ ተናግረዋል፡፡
በሉዓላዊ ምክር ቤት ምስረታ እና ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች ዙሪያ ተቋርጦ የነበረው ውይይት በበጎ መንፈስ ልዩነቶችን ለማጥራት እንዲቀጥል ለማግባባት ጥረት የተደረገ መሆኑን ያመለከቱት ቃል አቀባዩ፤ ሁለቱም ወገኖች ጠብ አጫሪ ከሆኑ ንግግሮች እንዲታቀቡ፤ የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈቱና በሁለቱ ወገኖች መካከል የመተማመን መንፈስ እንዲጠነክር፣ የነፃነት/የለውጥ ሃይሎችም የህዝብ እምቢተኝነት ጥሪያቸውን እንዲያረግቡ ውይይት መካሄዱን አብራርተዋል፡፡
68ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ ነቢያት፣ በጉባኤው በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፤ የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚም በሱዳን ጉዳይ ላይ እንደሚመክር ጠቁመዋል፡፡
የኢጋድ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም የኢጋድ ሊቀመንበር በመሆኗ ሪፖርት ታቀርባለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በ68ኛው ጉባኤ የደቡብ ሱዳን ጉዳይም ውይይት የሚካሄድበት መሆኑን ጠቁመው፤ ከአንድ ወር በፊት በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የተካሄደው 67ኛው የኢጋድ ጉባኤ ላይ ለስድስት ወር የተሰጠው የቅድመ ሽግግር ጊዜ በአንድ ወር ውስጥ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ እና ችግሮች ካሉም አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ውይይቱ እንደሚካሄድም አመልክተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጀርመኑ አቻቸው ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት እ.አ.አ ከሰኔ 21 እስከ 25 ቀን 2019 ድረስ በጀርመን ይፋዊ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አመልክተዋል፡፡ ጉብኝቱ በኢትዮጵያና በጀርመን የጋራ ጉዳዮች ላይ መምከርን ማዕከል ያደረገ መሆኑን እና በሁለቱ አገራት ከፍተኛ አመራሮች በተደረሰው ውሳኔ መሰረት የጋራ ኮሚሽን እንዲቋቋም በጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሄኮ ማስ እና በአቶ ገዱ አማካኝነት የፊርማ ሥነሥርዓት እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
የወቅቱ ሊቀመንበር የሆነችው ግብፅ የአፍሪካ ህብረት ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤትን በሱዳን ጉዳይ ላይ ለመምከር ስብሰባ የጠራች ሲሆን፤ ሰኔ 13 ቀን በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቃል ዓቀባዩ አቶ ነቢያት ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011
ምህረት ሞገስ