አዲስ አበባ ፦ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ምክንያት በአንድ ዓመት 95 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማጣቷን ጥናት አመለከተ፡፡ ከዚህ ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና የንግድ ኩባንያዎች 17 ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር አጥተዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሃይል መቋረጥ በኢንዱስትሪዎችና የንግድ ኩባንያዎች ላይ ያስከተለውን ጉዳት አስመልክቶ ያስጠናውን ጥናት በትናንትናው እለት በአዝማን ሆቴል አቅርቧል፡፡
በወቅቱ ጥናቱን ያቀረቡት አቶ ፍቅረማሪያም ይፍሩ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በ2010 ዓ.ም ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ 259 ጊዜ ሃይል ሲቆራረጥ፤ ከ212 ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳልነበር ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የኢንዱስትሪዎችና የንግድ ኩባንያዎች በአንድ ዓመት 95 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ምክንያት እንዳጡ ተናግረዋል።
የሃይል መቆራረጡ በተለየ መልኩ ኢንዱስትሪዎችና የንግድ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ፍቅረማሪያም በግሉ ዘርፍ የደረሰው ክስረት በአሁኑ ወቅት ያለውን የፈረቃ አገልግሎት ያላካተተ መሆኑንና ይሄ ታሳቢ ቢደረግ የችግሩ ከፍታ በእጅጉ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል።
በጥናቱ እንደተብራራው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የውጭ ባለሀብቶችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥያቄዎች እየቀረቡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የሃይል መቆራረጡ እንቅፋት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
የሚቆራረጥ ሃይል ይዞ ጥያቄ ማቅረቡ ደግሞ ራሱን የቻለ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ያሉት አቶ ፍቅረማሪያም የሃይል መቆራረጡ ከአምራች
ኢንዱስትሪዎች ማግኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሬ እንዳይገኝ፤ በቂ ምርት እንዳይመረት፣ ምርቶች ጥራት እንዳይኖራቸው እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች እንዲከሰት አድርጓል ብለዋል። ኪሳራው ወደ ገንዘብ ሲቀየር ኢንዱስትሪዎችና የንግድ ኩባንያዎች በአንድ ዓመት ብቻ 17 ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር እንዳጡም አብራርተዋል።
ጥናቱ የችግሩን ምክንያች መለየቱን የገለጹት አቶ ፍቅረማሪያም፤ የኤሌክትሪክ መስመሮች አያያዝና የትራንስፎርመሮች ያረጁ መሆን ዋነኛ መንስኤ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ የሃይል አቅርቦቱን በተወሰነ ደረጃ ወደ ግሉ እንዲገባ በማድረግ ስር ለሰደደው ችግር መፍትሄ መስጠት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን አሰራር በተሞክሮነት በመውሰድ ከሱ ጋር አብሮ መሄድ ይገባልም ብለዋል።
አቶ ፍቅረማሪያም በተጨማሪም በተቋሙ አካባቢ የሚታየው ሙስና ለችግሩ በቶሎ መፍትሄ ለመስጠት ሳንካ መሆኑ በጥናቱ ግኝት መመላከቱን ገልጸዋል። በተቋሙ አንዳንድ ሙያተኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦ ዳግም ስራ ለማስጀመር የንግድ ተቋማትና ኩባንያዎች እጅ መንሻ በመጠየቅ አገልግሎቱን የሚሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ጉቦ አንሰጥም በማለት እስከ መዝጋት የደረሱ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል። በመሆኑም የችግሩን ስፋት መሰረት በማድረግ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል እንደሚገባ በመፍትሄነት መቅረቡን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011
ዳንኤል ዘነበ