የኤሌክትሪክ መኪኖች ፋይዳ

የትራንስፖርት አገልግሎት ከሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ቀዳሚውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሰፋና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ የመጣ ነው። ዘርፉ ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መሠረታዊ ሚና ይጫወታል። የሰዎች እንቅስቃሴ፣ ንግድ፣ የሰው ልጆችን ከአደጋ መታደግ ዕድገትና ሥልጣኔን ከትራንስፖርት አገልግሎት ውጪ ማሰብ ይከብዳል።

ሰውና እቃን በጋማ ከብት ከማጓጓዝ አንስቶ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችንም አልፎ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ዛሬ ላይ በአደጉ ሀገራት ዘንድ፣ ሰው ሳያሻቸው በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ፣ በኤሌክትሪክ ገመድ ላይ የሚጓዙ፣ በተጨናነቀ የትራፊክ እንቅስቃሴ መካከል አልፈው መሄድ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን ማምረትና ሥራ ላይ ማዋል ተችሏል።

ሀገራችን ደግሞ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከነዳጅ ውጪ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖችን እየተዋወቀች ትገኛለች። መኪኖቹ በነዳጅ ከሚሠሩ መኪኖች ይልቅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኙ ስለመሆናቸው ምሁራን ያስረዳሉ።

የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርኼ (ዶ/ር)፤ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች በተለይ ነዳጅ አምራች ላልሆኑ ሀገራት ለነዳጅ የሚያወጡትን ወጪ በከፍተኛ መጠን በመቀንስ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ እንዳላቸው ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣው ለነዳጅ ግዢ መሆኑን ያነሱት ዶ/ሩ፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመነጨት አቅም ላለው ሀገር፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖችን መጠቀሙ የትራንስፖርት ዘርፉን በራስ አቅም የማንቀሳቀስ መልካም ጅምር ነው ይላሉ።

መኪኖቹ የአየር ብክለትን የማያስከትሉ መሆናቸውም ሌላው ጠቀሜታቸው እንደሆነም ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) አንስተዋል፣ ይህም የተፈጥሮ አካባቢን ከመጠበቅ አንጻር ሀገራችን የፈረመችውን ስምምነት ለማክበር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኤሌክትሪክ መኪኖች በነዳጅ ከሚሠሩ መኪኖች ይልቅ በተሻለ ዋጋ መገኘታቸውም እንዲሁ ሌላው ጠቀሜታቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

መኪኖቹን የመጠቀም ፍላጎት እንዲጨምር በተለይም፣ መኪኖቹን ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች ልክ እንደ ነዳጅ ማደያ ሁሉ መሟላት አለባቸው ይላሉ፤ ገንዘብ እያስከፈሉ መኪኖቹን ቻርጅ የሚያደርጉ የግል ዘርፍ ድርጅቶች ሊኖሩ እንደሚገባም ይመክራሉ።

በሌሎች ሀገራት ዘንድ የኤሌክትሪክ መኪኖችን መጠቀም የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በርካታ ወጪ እያፈሰሱ እንደሚገኙም አንስተዋል።

ስለመኪናው እውቀት ያላቸው ጋራዦች ጥቂቶች ናቸው ያሉት ዶ/ሩ፤ በዚህ ላይ እውቀት ያላቸው በቴክኖሎጂ የታገዙ ጋራዦችን ማስፋት እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ ዝግጅት ትግበራ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አዶሼ በበኩላቸው፣ ልክ እንደ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ሁሉ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በብዛት መጠቀም ይቻል ዘንድ ምቹ መሠረተ ልማትን መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

መኪኖቹ በተለይም በነዳጅ ሳቢያ የሚመጣውን የአየር ብክለት ለመቀነስ ጥሩ አማራጭ ናቸው ያሉት አቶ መሐመድ፣ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት የራሳቸው የሆነ እቅድ አዘጋጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያም የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ የሚያስች የራሷ ዕቅድ አላት ያሉት አቶ መሐመድ፣ እንደ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ባቡር፣ የኤሌክትሪክ መኪና፤ ያለሞተር የሚሠሩ ሳይክል እና መሰል ተሽከርካሪዎችን መጠቀም የዕቅዱ አካል መሆኑን ያስረዳሉ።

የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ በአየር ብክለት ሳቢያ ጤና ላይ የሚመጡ ችግሮችን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ያብራራሉ። እንደ ቻይናና ሌሎች መሰል ያደጉ ሀገራት ከተሞቻቸው በበካይ ጋዝ እየተሞላ ነዋሪዎቻቸውም ለከፍተኛ የጤና ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን በማሳያነት ያነሱት አቶ መሐመድ፣ እነዚህን መኪኖች ጥቅም በቀላሉ የሚገለጽ አለመሆኑን ያሰምሩበታል።

አቶ አሸናፊ አሰፋ፣ በአውቶ ኤሌክትሪክ የመኪና ቴክኖሎጂ ላይ ዕውቀቱ ያላቸው በሙያም ላለፉት 25 ዓመታት የሠሩ ናቸው፤ እርሳቸው እንዳሉት፣ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ዘመኑ ያመጣቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች የመጠቀም ተገቢነት ላይ አጽንዖት ሰጥተው ይገልጻሉ። ቴክኖሎጂ ካፈራቸው ምርቶች መካከል የኤሌክትሪክ መኪኖች ከነዳጅ ከሚሠሩት ይልቅ የበለጠ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይናገራሉ።

እንደ አቶ አሸናፊ ማብራሪያ፣ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖች የሚያመነጩት መርዛማ ጋዝ ተፈጥሮን የሚያዛባ፣ የሰውን ልጅ እስከ ሞት አደጋ ሊያደርስ የሚችል ነው። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ የሚመጣን ነዳጅ ነው የሚጠቀሙት። ሌላው መኪኖቹ በሚበላሹበት ጊዜም መለዋወጫቸውን ለማግኘት የውጭ ምንዛሬን ይጠይቃል። ለመለዋወጫ የሚወጣው ገንዘብ ደግሞ እንደ ሀገር፣ ምጣኔ ሀብትን ያዛባል። ከመለዋወጫ ከሚወጣው ወጪ በተጨማሪ የነዳጅ መኪኖች ቶሎ ቶሎ የሰርቪስ አገልግሎት የሚያሻቸው መሆናቸውም ሌላው ችግራቸው ነው።

የኤሌክትሪክ መኪኖች ግን የአየር ንብረት ብክለትን የማያስከትሉ መሆናቸው ትልቁ ጠቀሜታቸው ሲሆን፣ የውስጥ እቃዎቻቸው በነዳጅ እንደሚሠሩ መኪኖች ብዙ ባለመሆኑ፣ ለመለዋወጫ ችግር እምባዛም አይዳረጉም። መለዋወጫቸው ብዙ ባለመሆኑም ቶሎ ለብልሽት የሚዳረጉ አይደሉም፤ ተጠቃሚውንም ከወጪ የሚታደጉ፣ መኪናን ለማስጠገን የሚወጣውን ጊዜም የሚቆጥቡ ናቸው።

አቶ አሸናፊ እንዳሉት፣ የኤሌክትሪክ መኪና የተራቀቀ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ናቸው። በነዳጅ ከሚሠሩ መኪኖች በተሻለ ሁኔታ ለአሽከርካሪው ነገሮችን የሚያቀሉ ሆነው የተሠሩ በመሆናቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል።

የኤሌክትሪክ መኪኖች ከላይ የተጠቀሱና ሌሎችም ተመራጭ እንዲሆኑ የሚያደርጓቸው ባህሪያት ቢኖሯቸውም በእኛ ሀገር ሁኔታ ተፈላጊነቱን ለመጨመር ከመሠረተ ልማት ላይ የተያያዙ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች መቀየር እንደሚያሻ ይመክራሉ።

መኪኖቹን በፍጥነት ቻርጅ የሚደረጉባቸው ቦታዎች አለመኖርን አቶ አሸናፊ ትልቁ ችግር ነው ብለው ይጠቅሳሉ። ለመኪኖቹ መለዋወጫ በሀገር ውስጥ በቀላሉ አለመገኘት፣ የኤሌክትሪክ መኪኖች የደረሱበትን ቴክኖሎጂ የሚመጥኑ የጋራዥ አገልግሎት በስፋት አለመኖርም በሀገራችን የመኪኖቹን ተፈላጊነት የሚቀንሱ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ለዚህም ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች በየቦታው ሊኖሩ ይገባል በሚለው ሃሳብም ከዶ/ር ቆስጠንጢኖስና ከአቶ መሐመድ ጋር ይስማማሉ። ከዚሁ ጋር አያይዘው በሌሎች ሀገራት የኤሌክትሪክ መኪና አሽከርካሪዎች በየካፌው የቻርጅ አገልግሎት እንደሚያገኙም አንስተዋል።

ከዕውቀቱና ከመሠረተ ልማቱ በፊት ቴክኖሎጂው ቀድሞ ገብቷል ያሉት አቶ አሸናፊ፣ መኪኖቹ ከሚያስገኙት ጥቅም ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ላይ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት በሚለው ሃሳብ አስተያየታቸውን አሳርገዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You