ሃሳብ፣ ኃይል፣ ትጋትና ቁርጠኝነት በአንድ ላይ የሚገኙት ወጣቱ ጋ ነው

ወጣቱን ከልማት እና ከሥራ ፈጣሪነት ጋር ያጣመረ አዲሱ የስታርት አፕ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ድጋፍ ተሰጥቶት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሯል፡፡ ይሄ አዲስ ወጣት ተኮር እንቅስቃሴ ማህበረሰቡን ከሃሳብና ከሥራ ፈጣሪነት ጋር አዋህዶ የኢኮኖሚ ግስጋሴን የሚያፋጥን ነው። ከጥቅም አኳያም የብዙሃኑን ሕይወት የሚቀይር፣ ወጣት ባለሀብቶችን ከመፍጠር፣ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ከማፍራት እና ሀገርን ከድህነት ከማውጣት አኳያ ላቅ ያለ ተስፋ ያለው ነው፡፡

አፍሪካን ጨምሮ ብዙ የዓለም ሀገራት በዚህ ወጣት ተኮር የሥራ ፈጣሪነት ጽንሰ ሃሳብ ስር ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ማህበረሰባቸውን ከተረጂነት የታደጉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በቀጣይም ብዙዎች እንደ አንድ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ አድርገው ሊጠቀሙበት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡ የዚህ ንቃት ተሳታፊ ከሆኑ ሀገሮች ውስጥ ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች ፡፡

ለዘመናት ያለንን የወጣት ኃይል ሳንጠቀምበት፣ ሥራ ፈጣሪዎችን ሳናበረታታ፣ በእውቀታችንና በተፈጥሮ ሀብታችን ሳንጠቀም፣ መሥራትና መቀየር እየቻልን ግን ሳንቀየር ሰንብተናል፡፡ ለዚህ እንደ ዋና ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ የወጣቱን አቅም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችሉ እድሎችን/አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አለመቻላችን ነው፡፡

በቀደሙት ጊዜያት የነበረው ሀገራዊ እውነታ የፈጠራ ሃሳቦችን ይዞ በቀላሉ ወደ ሥራ መግባት የሚያስችል አልነበረም፡፡ አይደለም ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ቀርቶ በዘርፉ ላይ ለሰነበቱ እንኳን ተግዳሮቱ የበዛ ነበር፡፡

በዚህ ምክንያት እንደ ሀገር፣ እንደ ማህበረሰብ፣ እንደ መንግሥት ብዙ ጥቅሞች ቀርተውብናል፡፡ ራሳችን ጠቅመን ሌሎችን የምንጠቅምበት ሃሳብ፣ ተሰጥኦ፣ የሥራ ፈጣሪነት ወኔ ሁሉ እንዳልነበረ ሆኗል፡፡

መንግሥት እነዚህን ሁሉ ነባር ችግሮች በመመልከት ከዛም በላይ ጊዜና ቦታ በመስጠት በሰፋና በዳበረ መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ በሚያስችል የስታርትአፕ ጽንሰ ሃሳብ ወጣቱ ራሱን ጠቅሞ ለሌሎች የሚተርፍበትን አቅጣጫ ቀይሶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ይህ የመንግሥት መነሳሳት በቀጣይ የወጣቱን የመፍጠር፣ የማሰብ፣ የመከወን ትኩስ ኃይል ለሀገር ግንባታ ለመዋል የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡

ይሄን መሰሉ በመንግሥት በጀትና አቅጣጫ እየተመራ ያለ ወጣት ተኮር እንቅስቃሴ ለትውልዱ ተስፋ ከመሆን በተጨማሪ ሞዴልና አርአያ የሚሆኑ ወጣት ባለሀብቶችን በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና የሚኖረው ነው፡፡ ወጣቱን በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በክህሎት፣ በቴክኖሎጂ፣ በሥራ ፈጣሪነት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር የተሻለ አማራጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡

ሀገርና ወጣት፣ ማህበረሰብና ወጣት፣ ልማትና ወጣት፣ ፖለቲካና ወጣት በአንድ የተሳሰሩ አንዳቸው ያለአንዳቸው ብቻቸውን መጽናት የማይችሉ እውነቶች ናቸው፡፡ ለወጣቱ እድል መስጠት ማለት ብዙ የተዘጉ ሀገራዊ በሮችን መክፈት ማለት ነው፡፡

ወጣት ያልሳተፈበት ልማት፣ ያልተሳተፈበት ፖለቲካ፣ ያልተሳተፈበት ዲፕሎማሲያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ሊኖር አይችልም፤ ይኖራል ተብሎ ቢታሰብ እንኳን የጸና ሊሆን አይችልም። እኛ ደግሞ በወጣት ሀይላቸው ከታደሉ ጥቂት የዓለም ሀገራት ግንባር ቀደሞቹ ነን፡፡

እንደ ስታርት አፕስ ያሉ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ይህንን ኃይል በዋነኛነት በማሳተፍ፤ በሥራ ፈጣሪነት ተጀምረው በትላልቅ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ መነሻቸው ሀገር ቢሆንም መድረሻቸው ዓለም አቀፋዊነት ነው፡፡ ከሃሳብ መንጭተው፣ በሃሳብ ዳብረው በኢኮኖሚና በተሰሚነት ለሀገር ሉዓላዊነት ዘብ የሚቆሙ ናቸው። ከራስ በሆነ ታታሪነት ለብዙዎች እንጀራ በመሆን በሀገር ላይ በጎ ዐሻራን ማስቀመጥ የሚያስችል ነው።

ኢትዮጵያን ያለ ወጣቱ እንቅስቃሴ ማሰብ ሻማን ያለ ክር ለማብራት ከመሞከር ጋር አንድ ነው፡፡ ሻማ ያለ ክር እንደማይበራ ሁሉ ሀገርም ያለ ወጣት ንቃት ምንም ናት፡፡ ወጣቱን ማንቃት ሀገርን ማንቃት፣ ማህበረሰቡን ማብቃት ነው፡፡ ትውልዱን ማንቃት ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን፣ ዲፕሎማሲውን፣ ማህበራዊ መስተጋብሩን ማንቃት ነው፡፡ ወጣቱን ማሳተፍ ሰላምን ማምጣት፣ አንድነትን ማወጅ፣ ወንድማማችነትን ማስቀደም ነው፡፡

ስታርት አፕ ደግሞ ለዚህ ፍቱን ሆኖ የቀረበ ከወጣቱ በወጣቱ የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ አንቂና አበረታች ያልሆነውን የሥራ ፈጣሪነት ሥርዓቶች በመቅረፍ ወጣቱን በሃሳብ፣ በሥራ ፈጣሪነት፣ በእውቀትና በምክንያታዊነት ወደ ሀገራዊ ተሳትፎ የሚያስገባ የእድልና ድል መንታ ገጽ ነው። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ለወጣቱ እጅግ የተሻለ የለውጥና ራስን የመግለጫ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ ሃሳብ ይዞ መንገድ ላጣው፣ በዚህም ተስፋ ሊቆርጥ ለተቃረበው ወጣት ድል ማድረጊያ ፍኖቱም ነው፡፡

ስታርት አፕ ሃሳብና ቴክኖሎጂ የተዋሃዱበት ዘመን ወለድ አስተሳሰብ ነው፡፡ ማንኛውም በአነስተኛ የሥራ መስክ የተጀመረ የሥራ ዓይነት ካለ ቴክኖሎጂ ብቻውን ስታርት አፕ ሊባል አይችልም።ከቴክኖሎጂ መስፋፋትና መናር ጋር አብሮ የመጣ አዲስ እና ወጣት ተኮር የሥራ ንቃት ነው፡፡

በስታርት አፕ የሥራ ፈጠራ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጡ አራት የ‹መ› ሕጎች መኖራቸው በባለሙያዎቹ ይነገራል። የትኛውም የሥራ ዘርፍ ውጤት ተኮር ሆኖ እንዲቀጥል ‹ፍላጎት፣ ትጋት እና ተስፋ አለመቁረጥ› አስፈላጊዎቹ እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ከዚህ እውነታ ጋር በማቆራኘት የስታርት አፕን አራት የውጤታማነት ሕጎች ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

የመጀመሪያው ሊሰሩት ያሰቡትን የሥራ ሃሳብ መውደድ ነው፡፡ የምንወደው ነገር ትጋትና ንቃትን አለመዛልንም በማጎናጸፍ ወደፊት የሚወስደን እንደሆነ ይታመናል፡፡ የትኛውም ሥራ ፈጣሪ በሚወደው ሥራ ዘርፍ ላይ ሆኖ ደከመኝና ታከተኝ ሊል የሚችልበት አጋጣሚ አይኖርም፡፡ በዚህም የተነሳ ለመሥራት ያሰብነውን ሥራ መውደድ መቻል እንደ መጀመሪያ የስታርት አፕ የውጤታማነት የመ ሕግ ሆኖ ከፊት ይመጣል፡፡

ሁለተኛው መቻል ነው፡፡ አንድን ነገር ወደ ስኬታማነት ለመቀየር ከመውደድ እኩል መቻል ያስፈልጋል፡፡ የወደድነውን ነገር ካልቻልነው መውደዳችን ብቻውን ውጤት አያመጣም፡፡ የምንወደውን ነገር ወደመሆን የሚቀይር የብቃትና የፈጻሚነት መቻል ግድ ይላል፡፡ ዛፍ እንወዳለን ብንል የምንወደውን ዛፍ እውን ሆኖ ለማየት አሊያም በጥላው ለመጠለል ዛፉን መትከል መቻል አለብን፡፡ ዛፍ መውደድ ቀዳሚው ሲሆን ዘር ዘርቶ ዛፍ ማብቀል ግን የድርጊት ውጤት ነው፡፡ መውደድ እና መቻል በአንድ ላይ ሲመጡ በዚህ ምሳሌ መቃኘት ይችላሉ፡፡

ቀጣዩ መፈለግ ነው፡፡ ይሄ ደረጃ መጠይቅ የሚያስነሳ ነው፡፡ የወደድነውና እና የቻልነው የሥራ ዘርፍ በማህበረሰቡ ተፈላጊ ነው እንዴ? ገበያ አለው ወይ? ተስፋ ሰጪነት ምን ያክል ነው? ስንል ትርፋማነቱንና አዋጭነቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶ መመልከት ተገቢ እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡ ሥራ ፈጣሪነት አመርቂ እና ተስፋ ሰጪ ሆኖ እንዲቀጥል የማህበረሰቡን ጥያቄ መመለስና የብዙሃኑን ፍላጎት የሚነካ መሆን አለበት፡፡ መፈለግ የሚለው ሕግም ከዚህ ጋር የተሰናሰለ ነው፡፡

የመጨረሻ ሆኖ የተቀመጠው መሸጥ ነው፡፡ የሁሉም የሥራ ፈጣሪዎች የመጨረሻ ግብ ውጤት ተኮር ፍጻሜ ነው፡፡ ወደን፣ ችለንና አስፈላጊነቱን አጢነን ማረፊያችን ሊሆን የሚችለው ውጤት ነው። ውጤት ደግሞ ከመሸጥ፣ ከመለወጥ፣ ከመገብየት የሚነሳ ነው፡፡ ሃሳባችን እኚህን ደረጃዎች አልፎ መጨረሻ የሆነው የትርፍ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው አንድ ሥራ ፈጣሪ ተሳካለት የሚባለው፡፡ መሸጥ ገንዘብ ከማምጣትና ትርፍ ከማግኘት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ሃሳባችን ዳብሮና ጠንክሮ ገንዘብ ሊያመጣልን ከቻለ ስኬታማዎች ነን፡፡

ከላይ በተነሳንባቸው የባለሙያዎች የስታርትአፕ የሥራ ፈጣሪዎች የስኬት ሕጎች በመንተራስ ወጣቱ ሃሳቡን እንዲወድ፣ መቻሉን እንዲያምንና ተፈላጊነቱን እንዲያጤን በስተመጨረሻም ገንዘብ ሊያመጣለት የሚችል መሆኑን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ባለሙያዎቹ የትኛውም ባለሃሳብ በስታርት አፕ ስም ወደ ሥራ ፈጣሪነት ሲያዘግም በነዚህ የ“መ “መርሆዎች ሥር ራሱን ቢያስቀምጥ መልካም እንደሆነ ይመክራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን የሥራና የሥራ ፈጣሪዎች መፍለቂያ እንድትሆን በመንግሥት በኩል ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ አትኩሮት መጪውን ጊዜ ብሩህ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ በሃሳብ ማሸነፍ፣ በሃሳብ መበለጥ ባጠቃላይ ለሃሳብ ልዕልና ቅድሚያ የሚሰጥን ምህዳር በመፍጠር የተሳካ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደ ጅማሮ በርካታ ተስፋዎች እየታዩበት ነው፡፡

ከላቀ ሃሳብ ውጪ ዋጋ እንዳይኖረን የሆንን ሀገርና ሕዝብ ነን፡፡ ለውጥ ሃሳብን ታኮ፣ ትጋትን ተመርኩዞ በላቁ አእምሮና ልቦች በኩል የሚንጸባረቅ እንደሆነ፣ ዘመናዊነትና ስልጣኔ በራስ አቅም፣ በራስ ተፈጥሮ ወደሌሎች መፍሰስ እንደሆነ፣ ምቹና ቀና ሕግና ደንቦች ለመጪው ትጋት፣ ላለው ተስፋ በመሆን ሀገርን የሚያጅቡ እንደሆኑ በሁሉም ዘንድ ይታመናሉ፡፡ ሃሳቦቻችንን ወደሥራ ለውጠን ከግለሰብ ወደ ማህበረሰብ፣ ከሀገር ወደ አህጉር እንድንሰፋ ስታርት አፕ ጥሩ አጋጣሚ ስለሆነ በእድሉ ተጠቃሚ መሆን ይገባል፡፡

የዓለም ዝማኔ በሃሳብ መበላለጥ የመጣ ነው። ሃሳብ ያለው ወጣት ወደ ልማት እንጂ ወደ ጥፋት አይገባም፡፡ እጆቹን በሥራ አእምሮውን በሃሳብ ያፈረጠመ ወጣት ከምንም በላይ ያስፈልገናል። የጦርነት ታሪኮቻችንን በዚህ መንገድ ካልሆነ አንሻገራቸውም፡፡ ወጣቱ እንዲያስብ፣ እንዲያሰላስል፣ በተመቸና ወደኋላ በማይመልስ ሥርዓት በኩል ወደፊት እንዲገሰግስ መንገድ ሊሰጠው ይገባል፡፡

በሃሳብ ካልሰፋን በምንም አንሰፋም፡፡ ሥርዓቶቻችንን ለሃሳባውያን ቀና ማድረጋችን ለለውጥ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ወጣቱን በልማት አሰማርተን መጪውን ጊዜ መጠበቁ ከውሳኔዎቻችን ሁሉ ምርጡ ውሳኔ ሆኖ የሚጠራ ነው፡፡ ሃሳብ፣ ኃይል፣ ትጋትና ቁርጠኝነት በአንድ ላይ የሚገኙት ወጣቱ ጋ ነው፡፡ ለወጣቱ መንገድ አለመስጠት ማለት በእነዚህ እድሎች አለመጠቀም ነው፡፡

ለወጣቱ እንዲሆኑ መንገዶቻችንን እንክፈት። ሥርዓቶቻችንን እንመርምር፡፡ ሕጎቻችንን እናሻሽል፡፡ መንግሥት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የዳበረች ኢትዮጵያን በመፍጠር ትጋት ላይ ነው። ስታርት አፕ ደግሞ መነሻው ሃሳብና ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ሃሳብን ከቴክኖሎጂ ጋር ያስተሳሰረ ወጣት ደግሞ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ዓይነት አላማ ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል ራሱን ይጠቅማል በሌላ በኩል ሥራ ፈጣሪነትን ከቴክኖሎጂ ጋር በማቆራኘት መንግሥት ለያዘው የዲጅታላይዜሽን ተልዕኮ መንገድ ጠራጊ ይሆናል፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You