«የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመውሰድ በክልሉ ከተሞች የመልሶ ማልማት ሥራዎችን እየሠራን ነው» – ኢንጂነር የማታለም ቸኮል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ

የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል እንደ ክልል ራሱን ችሎ ሲቋቋም በቢሮ ደረጃ ከተመሠረቱ መሥሪያ ቤቶች መካከል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አንዱ ነው፡፡ እናም በክልል የሚገኙ ከተሞች እንዲዘምኑና የከተማነት ደረጃ እንዲያሟሉ የማድረግ ኃላፊነት ለዚህ ቢሮ ተሰጥቷል፡፡

ከዚህ አንጻር የዛሬው የተጠየቅ ዝግጅታችን ቢሮው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተሞች በፕላን እንዲመሩ ለማድረግ ምን ሠራ? ምን ፈተናዎችስ ገጠሙት? አሠራሩን በማዘመን የሕዝብ ጥያቄዎችን ከመመለስ አኳያ ምን ጥረቶችን አደረገ በሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን ከክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ቢሮው ምን አቅዶ ምን ሠራ?

ኢንጂነር የማታለም፡- ቀደም ብሎ በነበረው ሥርዓት የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ዋና መቀመጫ ሀዋሳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሀዋሳ ከተማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር በክልል የሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎች ይገኙባት ነበር፡፡ ይህም ከሀዋሳ ከተማ በርቀት ላይ የሚገኙ ዞኖችን እንዲሁም ከተሞችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ እና በእኩል ደረጃ የልማት ተደራሽ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡

አሁን እንደ ክልል በተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ከተሞች እና ዞኖች ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ ሊሆኑ፤ እና በእኩል ደረጃ አስተዳደራዊ ተደራሽ ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡ ይሄን መነሻ በማድረግም በአሁኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ዜጎች የፍትዊ ተጠቃሚነት እና ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ በማንሳታቸው፤ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ክልል መሆን ቻሉ፡፡

ከተሞችን ለማደግ በሚደረጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተደራሽነት ችግር የነበረባቸው። በሀዋሳ ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች አንጻር ብዙም ማደግ ያልቻሉ ናቸው፡፡ ይህ ሁነት የፈጠረውን ቁጭት መነሻ በማድረግ አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት ያለውን ሀብት በመጠቀም እና ሕዝቡን በማሳተፍ በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል የመሬት አቅርቦት እና ዝግጅት ሥራዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ከነበረው የመሬት አቅርቦት እና አሠራር የተሻለ ነገር አለ፡፡ በአጠቃላይ ከመሬት ጋር ተያይዞ በአቅርቦትም በዝግጅትም ክልሉ እንደ ክልል የተሻሉ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዲስ ክልል እንደ መሆናችሁ የቅድሚያ ቅድሚያ የሰጣችሁት ተግባር ምንድን ነው?

ኢንጂነር የማታለም፡- ሁሉም ሰው እንደሚገነዘበው ከመሬት ጋር ተያይዞ አሠራሩ በጣም ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙታል፡፡ ከመሬት ጋር የተገናኙ አሠራሮች ደግሞ በተፈጥሯቸው ሌብነት እና አድሎዓዊነት ይበዙበታል። ይህንን ዓይነት ፈተና የተሞላበትን ተቋም ደግሞ በሥርዓት እና በእቅድ መምራት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም መሬት ውድ ሀብታችን ነው፡፡ የከተሞቻችንም ትልቁ ሀብት መሬት ነው፡፡

እንደ ክልል መሬትን በአግባቡ ለመምራት እና ለመቆጣጠር በመጀመሪያ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት የተሠራው የመሬት ምዝገባ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የከተሞቻችን የመሬት ምዝገባ ስንጀመር 500 ‹‹የመሬት ፓርሴሎች›› ብቻ ነበሩ የተመዘገቡት፡፡ አሁን ላይ ግን ከስድስት ሺህ በላይ መመዝገብ ተችሏል፡፡ ከዚህ የበለጠ መሥራት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባጋጠመው የሰው ኃይል እጥረት እና የሀብት ውስንነት ምክንያት በተፈለገው ልክ መሥራት አልተቻለም፡፡

በተለይ ከመሬት ምዝገባ ጋር ተያይዞ ያን ያህል ብዙ ሰርተናል ማለት አንችልም፡፡ ክልሉ እንደ ክልል ከመቋቋሙ በፊት ከነበረው ልምድ ሕብረተሰቡ መሬቱን የማስመዝገብ ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ይሁን እንጂ ከምስረታ በኋላ ቢሮው ባከናወናቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች አሁን ላይ የተሻለ ነገር አለ። በዚህም ቀድሞ ከነበረበት አኳያ ሥራውን ማሳደግ ተችሏል፡፡ ይሄ በመሆኑም ለነዋሪዎቹም ጭምር ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት፡፡

የከተማም ይሁን የገጠር መሬት ከተመዘገበ በቀላሉ ለብልሹ አሠራር እና ሌብነት አይጋለጥም፡፡ መንግሥትም ከወሰን ማስከበር እና መሰል ጭቅጭቆች ነፃ ይሆናል፡፡ የማዘጋጃም ሥራ ይቀንስለታል፡፡ በሕግ በተፈቀደለት አካል መሬቱን ያስመዘገበ ሰው ሀገሪቱ ብሎም ክልሉ የሚሰጧቸውን የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ያስችሉታል፡፡ የባንክ ብድር እና መሰል አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት ይችላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የሥራችሁ አፈጻጸም እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር የማታለም፡- አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ እየሄድን ነው፡፡ ከተሞች ከነበሩበት ድባቴ ወጥተው የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ህብረተሰቡም የከተሞች እድገት የተሻለ እንዲሆን ከፍተኛ ጉጉት እና ፍላጎት አለው፡፡ ይሁንና ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያጋጠመው የሰው ኃይል እጥረት እና የሀብት ጉድለቶች ቢሮው ሥራውን በተፈለገው ልክ ለማስኬድ አልቻለም፡፡ በቀጣይ ግን እነዚህን እጥረቶች ችግር ሆነው እንይዳነሱ ለማድረግ ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ በተለይ የሠራተኞችን አቅም የመገንባት ሥራዎች በሰፊው እየተሠሩ ነው፡፡

ከመሬት ምዝገባው ጎን ለጎን የፕላን ማስከበር ሥራ በከፍተኛ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ እንደ ክልል ከመመስረታችን በፊት የከተሞቻችን የፕላን ማስከበር ሥራዎች በአግባቡ የተሠሩ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም በተለያዩ አካላት በርካታ ሕገ ወጥ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ በፕላን በአረንጓዴ ሥፍራ እና መናፈሻነት የተመላከቱ ቦታዎችን መውረር፣ ትርፍ የመንግሥት ቦታዎች ማጠር እና በከተማ ዙሪያ በሚገኙ የአርሶ አደር ቦታዎች ላይ ከፕላን ውጭ የመስፈር ሁኔታዎች ነበሩ፡፡

ይህ አካሄድ ፕላንን የሚጣረስ በመሆኑ አሁን ላይ እንደ ክልል ፕላን የማስተግበር ሥራ እያከናወን ነው። ፕላን በደንብ ካልተተገበረ ሌብነት ይበራከታል፤ ሕገ ወጥ ሥራዎች ይስፋፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ውሃ፣ መብራት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለህብረተሰባችን ማቅረብ እንዳይቻል እክል ይፈጥራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ምን ያህል መሬቶችን መመዝገብ ችላችኋል?

ኢንጂነር የማታለም፡- አሁን በክልላችን በመንግሥት በኩል ሕጋዊ እውቅና እና ሰነድ የሌላቸውን ወደ 32 ሺህ የሚደርሱ የከተማ መሬቶችን መመዝገብ ተችሏል፡፡ ሆኖም ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ አልቋል ልማት አይደለም፡፡ አሁንም ያልተመዘገቡ የከተማ መሬቶች አሉ፡፡ እነሱን በመመዝገብ ሕጋዊ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ ቢሮው ባከናወናቸው ሥራዎች ሕጋዊ ሰርተፍኬት የሌላቸውን ቦታዎች እና ሰዎች ተለይተዋል። አሁን የሚቀረው የፕላን ጥሰት ያለባቸውን ሰዎች ከቦታው ማንሳት እንዲሁም የተነሱትን ደግሞ ቦታ በማዘጋጀት ማስፈር ነው። የፕላን ጥሰት የሌለባቸውን ደግሞ በሊዝ አሠራር መሠረት ወደ ተገቢው ሥርዓት የማስገባት ሥራዎችን እያከናወን ነው፡፡

በነገራችን ላይ ከመሬት ጋር ተያይዞ ችግሮች ሲነሱ እጁ የሌለበት ሰው የለም፡፡ ደላላው፣ አመራሩ፣ የተለያዩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ይነካካሉ፡፡ ይህ ደግሞ የተጀመሩ ሥራዎችን በተፈለገው ልክ እንዳንጨረስ ሌላኛው ተግዳሮት ነው፡፡

የክልሉ ከተሞች ከተመሠረቱ በርካታ እድሜ ያላቸው ቢሆንም፣ ለበርካታ ጊዜያት ተረስተው እና ትኩረት ተነፍጓቸው መልማት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ በአንጻሩ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ከተመሠረቱ አጭር እድሜ ያላቸው ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት ሲያድጉ እና ሲለወጡ ነበር፡፡ ይህን ሲሆን የበይ ተመልካች የነበረው ሕዝባችን ‹‹የእኛ ከተሞችስ በእነዚያ ከተሞች ልክ የማይለወጡት ለምንድን ነው?›› በማለት ሲጠይቅ ነበር፡፡ ጥያቄው ደግሞ መልስ አግኝቷል። ጥያቄው መልስ ያገኘው ሕዝብም አሁን ላይ ከተሞች ተለውጠው እና አድገው ማየት ይፈልጋል፤ የሚፈልገው ለውጥ በአጭር ጊዜ እንዲመጣ በማሰብ ለክልሉ መንግሥት ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ በዚህም የቢሮውን ሸክም በተወሰነ ደረጃ እንዲቀል አድርጓል፡፡

በክልል ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለከተሞቻቸው እድገት የሚደርገው አስተዋጽኦ በጣም ነው የሚበረታታው፡፡ የትኛውም አካባቢ ላይ ያለው ማህበረሰብ በጣም ለውጥን ይደግፋል፡፡ አሁን ኮብልስቶን በምንሰራባቸው አካባቢዎች፤ ዲሽ ቦዮች በአብዛኛው የምንሠራው ሕብረተሰቡ ባዋጣው ገንዘብ ነው፡፡ ምክንያቱም የሀብት ውስንነት አለ፡፡ አሁን ለምሳሌ ቦንጋ ላይ ድልድይ ለመሥራት ካሳ እየተከፈለ ነው፡፡ የካሳውን ክፍያ የከፈለው ሕዝቡ በራሱ አዋጥቶ ነው፡፡ መንግሥት ትንሽ ነው ያዋጠው፡፡ ኮንታ፤ ሚዛን፤ ቦንጋ፤ ጨና እና ሌሎችም የሕብረተሰቡ መነቃቃት ለአመራሩ ሞራል እየሆነን ነው፡፡ እንዳለ አመራሩ ይህንን ሞራል መጠቀም አለበት፡፡

መንግሥት ከየትም ሀብት አያመጣም፡፡ የመንግሥት የሀብት ምንጭ ከተለያዩ የግብር ዓይነቶች የሚሰበሰብ ሲሆን፤ የመሬት ግብር አንደኛው ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ መሬቱን አስመዝግቦ ሕጋዊ በመሆን ለመንግሥት ግብር መክፈል አለበት፡፡ ሁሉም ሰው መሬትን በሕጋዊነት ሊጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛው መሬታችን በማዘጋጃ አልተመዘገበም፡፡ ስለሆነም ሕዝባችን መሬቱን አስመዝግቦ ሰርተፍኬት መያዝ እና በትክክል ለመንግሥት ግብር መክፈል አለበት። ምክንያቱም መንግሥት ከግብር የሰበሰበውን ገንዘብ የትም አይወስደውም፡፡ እዚያው ውሃ፤ መብራት፤ መንገድ ነው የሚሠራበት፡፡

እኛም፣ እንደ ሀገር በአዲስ አበባ የጀመረውን ከተሞችን መልሶ የማልማት ሥራ እንደተሞክሮ በመውሰድ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የመልሶ ማልማት ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቦንጋ እና በሚዛን አማን ከተሞች አበረታች ጅምሮች አሉ፡፡ በመልሶ ማልማቱ ተነሽ ለሆኑ ሰዎች ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ከተሞች እንዲለሙ እና እንዲለወጡ ባለው ጉጉት የተነሳ የተጋነነ ካሳ አይጠይቅም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ መንግሥት ካሳ እያዘጋጀን ነው፡፡ ሥራው የተሳለጠ እንዲሆን እና የካሳ ክፍያው ሳይቆራረጥ እንዲሠራ ለማድረግ ሕብረተሰቡ በፍላጎቱ ገንዘብ እያዋጣ ነው፡፡ እንደ ሀገር የተጀመረው ከተሞችን የመልሶ ማልማት ሥራዎች የሕዝባችንን አስተሳሰብ የለወጡ መሆናቸውን ያየንበት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?

ኢንጂነር የማታለም፡- ከተማዋን የሚመጥኑ እና ቱሪስቶችን ሊስቡ የሚችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ፕላንን መሠረት ያደረጉ ለቱሪዝም ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከቱሪዝም ጋር ተያይዞ የአስተሳሰብ ለውጥ ሕብረተሰቡ ላይ ተፈጥሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ ቢሮው ምን ፈታናዎች ገጠሙት ?

ኢንጂነር የማታለም፡- ሁሉም እንደሚያውቀው ክልሉ ውስን ሀብት ነው ያለው፡፡ ከፌዴራል የሚበጀተውም ሆነ ከቢሮው የሚሰበሰበውም ሀብት በጣም ውስን ነው፡፡ ደቡብ ክልል በነበርንበት ጊዜ የተጀማመሩ ነገር ግን ያልተጠናቀቁ፤ በርካታ ገንዘብ የሚፈልጉ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች አሉ፡፡ በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ የጤና ጣቢያ ግንባታ የቴክኒክ እና ሙያ ግንባታዎች እንዲሁም መንገዶች አሉ፡፡

እነዚህ ሳይጠናቀቁ ነው ወደ ክልልነት የመጣነው። አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህን ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ የክልሉ ፈተና ሆኗል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የሀብት ውስንነት መኖሩ ነው፡፡ አሁን ላይ ለክልል የሚመደበው በጀት ከደመወዝ ተርፎ ለልማት የሚውል አይደለም። በመሆኑም አሁን ላይ ክልሉ እንደ ክልል እና ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ በበጀት እጥረት እየተፈተኑ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቦንጋ ከተማን በከተሞች መስፈርት ልክ ለመገንባት ምን እየተሠራ ነው?

ኢንጂነር የማታለም፡- ቦንጋ ለመልማት ብዙ ኢንቨስት ማድረግን የማትጠይቅ ከተማ ናት፡፡ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ላይ የተወሰነ ኢንቨስት ቢደረግ ማራኪ እና ምቹ ከተማ ማደረግ ይቻላል፡፡

ከተማዋን ለመቀየር ትልቁ ነገር አስተሳሰብ ነው። በቀላሉ መለወጥ እንደሚቻል ማመን ያስፈልጋል። ይህንን ለሕዝቡ ማስገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ለልማት የሚሳሳ አመራር መፍጠር የግድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለኢንቨስትመንት የተሰጡ የከተማ ቦታዎች ምንም ልማት ሳይከናወንባቸው እንዲሁ ታጥረው ይቀመጣሉ፡፡ በእነዚህ ኢንቨሰተሮች ላይ በተጨባጭ ምን ዓይነት ርምጃዎችን እየወሰዳችሁ ነው?

ኢንጂነር የማታለም፡- ከዚህ ቀደም በኢንቨስትመንት ስም ለባለሀብቶች የተሰጡ መሬቶች በአግባቡ እንዲለሙ ከባለሀብቶቹ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በተቻለ መጠን ወደ ግንባታ እንዲገነቡ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወን ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማይችሉትን ሥርዓት የማስያዝ ርምጃዎችን እየወሰድን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ለባለሀብቶች አንድ ጊዜ መሬት ከተሰጠ በኋላ ክትትል አይደረግም፡፡ ይህ ደግሞ ባለሀብቱ መሬቶችን አጥሮ ሳያለማ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡ አሁን ላይ ይህንን የማስተካከል ሥራ እየሠራን ነው፡፡

አሁንም በኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ ‹‹አቅም አለኝ ማልማት እችላለሁ›› የሚል አካል ሲመጣ በራችን ክፍት ነው። ከክልል እስከ ዞን ኢንቨስተሮች በከተሞች ልማት ዙሪያ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ፍላጎቱ አለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጀመሩ ነገሮች አሉ፡፡ ሆቴሎች በየቦታው እየተጀመሩ ነው፤ ግንባታቸው ተጠናቆ የተመረቁም አሉ፡፡

በአጠቃላይ መገንባት ያቃታቸው ላይ ርምጃ እየወሰድን ነው፡፡ አዲስ የሚመጡ ባለሀብቶችን ለማበረታታት አገልግሎታችንን የማሻሻል ሥራዎች እንሠራለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቦንጋ ከተማ የክልሉ መቀመጫ እንደመሆኗ ባለሀብቶች የሪል ስቴት ቤቶችን እንዲገነቡ ለማድረግ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ኢንጂነር የማታለም፡- ሪል ስቴቶችን የሚሠሩ ባለሀብቶችን ክልሉ ይፈልጋል፡፡ በሪል ስቴት ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስኮችም የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንየቢሮ ባለሀብቶችን ለመሳብ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን በቦንጋ ከተማ ላይ ምንም የተጀመረ ነገር የለም፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ እንደ ቢሮ ሰርተናል ብዬ አልገምትም፡፡ ስለዚህ ቀሪ ሥራችን እንዴት ባለሀብቶችን እንሳብ የሚለው ይሆናል፡፡ የሕግ ማቀፎችም ስለሚያስፈልጉ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ መዲና እና በዞን ከተሞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን (ኮንዶሚኒየሞችን) ለመሥራት ምን አቀዳችሁ?

ኢንጂነር የማታለም፡- በክልሉ የሚገኙ የተለየዩ የመንግሥታዊ ተቋማትን ሰው ኃይል እንኳን ለመሙላት የሀብት እጥረት አለብን፡፡ ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ ለሕዝቡ ማሟላት የነበረባቸውን ነገሮች እንኳን ያላሟላናቸው በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ ቦንጋ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር አለ። በክልሉ አስቸኳይ የጤና ጣቢያ እና ሆስፒታል የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች በርካታ ናቸው፡፡ መንገድ እና መሰል የመሠረተ ልማቶችም የክልሉ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ከማሳበችን በፊት እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ በስትራቴጂክ ፕላን ደረጃ የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ፍላጎቱ አለን። ነገር ግን አሁን ላይ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ዘርፍ መሰማራት የፈለገ ባለሀብት ካለ ለማስተናገድ በራችን ክፍት ነው፡፡

በነገራችን ላይ የከተማ ልማት ሚኒስቴር እስከታች መዋቅር ድረስ አደረጃጀት አለው፡፡ ከዚህ አንጻር በሁሉም ደረጃ የሚገኙ መዋቅሮች መንግሥት ፖሊሲ ጋር የተናበቡ ናቸው፡፡ የአቅም ውስንነት ካልሆነ በቀር በፌዴራል ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በሚገኙ በከተሞች ይሠራሉ፡፡ የአቅም ውስንነት ግን የትኛውን ቅድሚያ ሰጥቼ ልሠራ የሚለውን ፈተና ያደርገዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በነባር ክልሎች ልክ አገልግሎቶቻችሁን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሰዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የአውሮፕላን ጣቢያዎች በክልላችሁ እንዲኖሩ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምን እየሰራችሁ ነው?

ኢንጂነር የማታለም፡- አዎ! አገልግሎቶቻችን ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር የአውሮፕላን ጣቢያ እንዲኖረን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሚዛን አማን ከተማ ላይ እየተሠራ ነው፡፡ በቦንጋ ከተማም የሄሊኮፕተር እና ቀላል አውሮፕላን ማረፊያ እየተሠራ ነው፡፡ ሌሎች ከተሞችም ላይም ፍላጎቱ አለ፡፡ ቴፒ ላይ የግል አውሮፕላን እያረፈ ነው፡፡ የሚዛን እና ቦንጋ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክቶች በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዲስ ክልል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከየሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተናቦ ከመሥራት አንጻር በተጨባጭ ምን እየሰራችሁ ነው ?

ኢንጂነር የማታለም፡- ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተናቦ መሥራት ግዴታ ነው፡፡ ተናቦ መሥራት ካልተቻለ ነገሮች ሁሉ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆኑት፡፡

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መንገድ፣ ቴሌ፣ ውሃ ልማት እና መብራት በራሱ አቀናጅቶ በኦንላይን ነው የሚመራው፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግን መንገድና ትራንስፖርት የራሱ ቢሮ አለው፡፡ የውሃ ልማትም ለብቻው የራሱ ቢሮ አለው፡፡ ቴሌና መብራት ደግሞ በርዕሰ መስተዳደሩ ልዩ አማካሪ ስር ነው የሚተዳደሩት። ስለዚህ የተቀናጀ እና ተናብቧ ሥራ ለመሥራት መሥሪያ ቤቶችን ትንሽ ሰብሰብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ ከአዲስ ከመሆኑ አንጻር አስተማማኝ ነው ባልልም ግን ቅንጅቱ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

በፌዴራል ደረጃ በየጊዜው መድረኮች አሉ፡፡ በመሆኑም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በቅንጅት ተናበው ይሠራሉ፡፡ አሠራራቸውም ተቋማዊ ነው፡፡ እኛ ላይ ግን ተቋማዊ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱን መሠረተ ልማት በፕላኑ መሠረት ይመራል። ገጠር ላይ እስካሁን እንደዚህ ዓይነት ፈተና የለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከልማት ተነሽዎች ጋር በተያያዘ ምን ችግር ገጠማችሁ? የልማት ተነሽዎች ልማቱ የኔ ነው ብለው እንዲስቡ ከማድረግ አኳያ ምን ያህል ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሰርታችኋል ?

ኢንጂነር የማታለም፡- እስካሁን የጎላ ችግር አልገጠመንም፡፡ ምክንያቱም ከልማት ተነሺ ማህበረሰባችን ጋር በተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርገናል፡፡ አሁን ቦንጋን ከተማ አስተዳደርን እንኳን ብንወስድ ከመልስ ማልማቱ ጋር ተያይዞ ያልተወያየ ዜጋ የለም፡፡ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተወያይቷል። ይህን በማድረጋችን ማህበረሰባችን ለልማቱ ያለውን አመለካከት በአውንታዊ መልኩ መቀየር ተችሏል፡፡ በዚህም ለልማት ተነሺዎች ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ ካሳ መክፈል የቻለ ማህበረሰብ ፈጥረናል፡፡ ስለዚህ ያን ያህል ፈታኝ ችግር አልተፈጠረም፡፡

አልፎ አልፎ ከራሳችን ብልሹ አሠራር አጋር ተያይዞ የተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች ሲፈጠሩ ይታያል። እነዚህን ችግሮች በጥንቃቄ እንዲታዩ እና በአጠረ ጊዜ እልባት እንዲያገኙ ለማስቻል ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተዘጋጅቷል። ከዞን ጀምሮ እስከ ላይኛው ድረስ መዋቅሮች ተዘርግተዋል፡፡ የክልሉ ቢሮም እስከታች ድረስ ወርዶ ቅሬታ የሚፈታበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን ከተሞች እንዲለሙ የሕዝቡ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ያን ያህል የተጋነነ ችግር አልገጠመንም። እስካሁን በመጣንበት እና በተከተልነው አሠራር ሕዝቡ ደስተኛ ነው፡፡ ምን አልባት በግለሰብ ደረጃ ግን የሚነሱ ቅሬታዎች ይኖራሉ። በግለሰብ ደረጃ ብዙ ጊዜ የሚነሳው ቅሬታ ንብረቴን እስከማነሳ ጊዜ ይሰጥኝ የሚል ነው፡፡

ማዘጋጃ ቤቱ ከሌብነት ነፃ ነው ብሎ ማንም ሰው በትክክል ሊገመግም አይችልም፡፡ ብዙ ነገሮች ገና ይቀሩታል፡፡ ስለዚህ የማዘጋጃ ቤትን ሥርዓት ማስያዝ እና የሠራተኛውን አመለካከት በመቅረጽ ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ከመሬት ምዝገባ አገልግሎት እና የሕንፃ አዋጅን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ከእጅ ንክኪ ነፃ ለማድረግ የጀመርናቸው ነገሮች አሉ፡፡

በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ወደ ሲስተም ለመግባት ግን አሁንም ዳተኝነት አለ፡፡ ከሕዝብ የሚመጣውን ቅሬታ ግን ለመፍታት ሰው እንደፈለገ ሊያደርገው ከሚችለው የቆየ አሠራር መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ነገር ዲጂታላይዝድ ተደርጎ ቢሠራ ከሕዝባችን የሚነሱ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት እንችላለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሥራዎችን ወደ ዲጂታል ለማስገባት ከሌሎች ክልሎች እና ሀገራት ልምድ ከመለዋወጥ አንጻር ያላችሁ ተሞክሮ ምን ይመስላል?

ኢንጂነር የማታለም፡- በክልሉ ቢሮ ስር የሚገኙ አሠራሮችን ለማዘን እንቅስቃሴ ላይ ነን፡፡ ለምሳሌ የቦንጋን የመሬት አስተዳደር ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የመሬት ጉዳይ ‹‹በኮምፒውተር ሲስተም›› ይሠራል። በሌሎች ከተሞች ላይ ውጤታማ የሆኑ በከተማና ልማት ሚኒስቴር የተረጋገጡ ተሞክሮዎን በሶፍትዌር ዴቨሎፕ አድርገን በቦንጋ እና ሚዛን ማዘጋጃ ቤቶች ላይ እየዘረጋን ነው፡፡ ኔትወርክ ዘርግተን ባለሙያዎች እና ቁሳቁሶችን አሟልተን ሙከራ ጀምረናል፡፡

የመረጃ አያያዝ ሥርዓታችን ደካማ በመሆኑ የተለያዩ ፋይሎች የት እንዳሉ እንኳን አይታወቅም፡፡ በመሆኑም በሁሉም ከተሞች ላይ ሰነዶችን ‹‹ስካን›› ተደርገው ወደ ‹‹ሶፍት ዶክመንት›› ተቀይረው እየተደራጁ ነው። ሶፍትዌር ዴቨሎፕ አድርገው ወደ ትግበራ መግባት የማይችሉ የሥራ ክፍሎች አቅም አግኝተው ወደሲስተም እስኪገቡ ድረስ ይህንን እያደረጉ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቢሮው ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተባብሮ ከመሥራት አንጻር ያለው ሂደት እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር የማታለም፡- በከተማችን የቦንጋ ሙዚየም ይገኛል፡፡ ይህን ሙዚየም በማልማት ሕዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እየሠራን ነው፡፡ ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ከተማው የነሱ እንደመሆኑ መጠን መዋቅሮቻችን የሚጠይቋቸውን ድጋፎች በአቅማቸው ያደርጋሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰ ግናለን፡፡

ኢንጂነር የማታለም፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ሙሉቀን ታደገ፣ ሞገስ ተስፋና መክሊት ወንደወሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You