ኮሚሽኑ ከ14ሺ በላይ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን አስመርጧል

አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስከአሁን ከ14ሺ በላይ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን ማስመረጡን ገለጸ፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው እና በቀጣይ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ከ940 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታና በአጀንዳ ግብዓት ማሰባሰቢያ ሕዝባዊ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጡ ተግባር ሲሠራ ቆይቷል፡፡

850 በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ ሥራው ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ገልጸው፤ በሂደቱ 130ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ተሳትፈው ከ14ሺህ በላይ ተወካዮች መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አዲስ አበባ፣ ጋምቤላ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የተወካዮች መረጣ ሙሉ ለሙሉ የተከናወነባቸው ሲሆኑ በሶማሌ ክልል 25 የሚሆኑ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከ70 በማይበልጡ ወረዳዎች የማጠናቀቂያ ሥራዎች እንደሚቀሩ አመላክተዋል፡፡

ይህ በክልል፣ በድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁ በፌዴራል ተቋማት የሚወከሉትን እንደማይጨምር የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ በዚህ ደረጃ ያሉ ተሳታፊዎች ሲጨመሩ በአጀንዳ ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመዋል፡፡

በቀሩት ወረዳዎች የሚደረገው ልየታ ሲጠናቀቅ ከአጠቃላይ ስራው ከ70 እስከ 75 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን እንደሆነ ተናግረው፤ ቀሪው ከ 25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች ባልተጀመረባቸው የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የሚከናወን ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ ፤ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው፡፡ በክልል ደረጃ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የሚስተናገዱባቸው በመሆናቸው በሰው ኃይል፣ በሎጂስቲክ እና በሌሎች ዝግጅት ማድረግ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፤ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮቹ ከ8 እስከ 10 ቀናት ሊወስዱ ይችላሉ ብለዋል፡፡

በመድረኮቹ የአጀንዳ ግብዓት ከማሰባሰብ በተጨማሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ ተወካዮች ይመረጣሉ፡፡ በአጀንዳ የመሰብሰቢያ መድረክ እንዲሳተፉ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ ተወካዮች አስቀድመው ከየማህበረሰቦቻቸው ጋር በመወያየት የአጀንዳ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ እንዲያከናውኑ ቃል አቀባዩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማት ስለ ኮሚሽኑ የሥራ እንቅስቃሴዎች ግንዛቤ ለመፍጠርና መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እያደረጉ ላለው ከፍተኛ ጥረት ምስጋና ያቀረቡት ቃል አቀባዩ፤ በቀጣይም ይህንን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You