ሩህሩህ ልብ የሚሹ ድጋፍ ፈላጊዎች

በጎነት በራስ ተነሳሽነት በሚመነጭ ሰብዓዊ ስሜት ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖር ነው፡፡ ይህም የበጎነት ተግባር መስፈርቱ የመልካም ልብ ባለቤት መሆን ሲሆን ያለምንም ተለዋጭ ነገር ካለን ገንዘብ፣ ጉልበት፣ እውቀትና ጊዜ ለሌሎች መስጠትና ማካፈል ነው፡፡

በዚህ የመልካምነት መገለጫ በሆነው በጎ ፍቃድ አገልግሎትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጋ እና የክረምት የበጎፍቃድ ንቅናቄ መርሀግብር በማካሄድ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ተሳታፊ ሲሆኑ በዚህም በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚስተዋለው የበጎፍቃድ አገልግሎት ባለፈ ዋና ዓላማቸው ሰውን መርዳት ያደረጉ የበጎ አድራጎት ማህበራት የሚጠቀሱ ሲሆን ማህበራቱ በተወሰነ መልኩ የእርዳታ ሰጪዎች ቁጥር መቀዛቀዙን ይናገራሉ፡፡

የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገሪቱ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ርዳታ ፈላጊ በብዛት እየጨመረ ሲሆን ርዳታ ሰጪዎች ቁጥር በተቃራኒው እየተቀዛቀዘ ነው፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት ለ19 ልጆት በነጻ ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ልመና ላይ ለነበሩ ሃያ አንድ ሴቶች የሥራ እድል በመፍጠር የተጀመረው ይህ የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር፤ አሁን ላይ ለ650 ህጻናት እና ለ450 እናቶች የመጠለያ ፣የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም እስካሁን ሁለት ሺህ ለሚሆኑ ሴቶች በተለያየ ዘርፍ ሙያ እንዲሰለጥኑ በማድረግ የሥራ እድል በመፍጠር የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ወይዘሮ ሙዳይ አስታውቀዋል፡፡

ማህበሩ በሥልጠና ከሚያበቃቸው እናቶች የሚሠሩ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም እንጀራ ምርትን በመሸጥና ወደውጭ ሀገራት ኤክስፖርት በማድረግ የራሱን ገቢ የሚያገኝ ቢሆንም፤ ለቤት ኪራይ እንዲሁም ለተለያዩ ወጪዎች ይገኝ የነበረ ርዳታ መቀዛቀዙን ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ሙዳይ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገሪቱ ባሉ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ክስተቶች ምክንያች ብዙ ሰው ርዳታ ፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ከግለሰቦች ብሎም ከለጋሽ ማህበራት በኩል ይገኝ የነበረው ርዳታ እና ማህበሩን ይጎበኝ የነበረው ሰው ቁጥር በጣም ተቀዛቅዟል ብለዋል፡፡

በተለይም ገንዘብ ስለለሌኝ ማገዝና መርዳት አልችልም በሚል የተሳሳተ እሳቤ ምክንያት የጎብኚዎች ቁጥር ቀንሷል ያሉት ወይዘሮ ሙዳይ፤ አንድ ሰው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጸሎት ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ሃሳቦችን በማቅረብ መርዳትና መጎብኘት የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአብዛኛው ሰው በዓላትን ጠብቆ የሚለግስ መሆኑንም ተናግረው፤ የበጎ አድራጎት ተግባር በማንኛውም ጊዜ የሚተገበር በመሆኑ ተሳታፊ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በየትኛውም የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኝ የማህበረሰብ ክፍል ጊዜን፣ እውቀትን እና ገንዘብን ለሌሎች በማካፈል በዚህ በበጎነት ተግባር ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ትኩረቱን ልጆችን ለፍሬ ማብቃት ላይ ያደረገው የአስካል በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ ንጉሤ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በተለይም ሀገር በቀል ድርጅቶች እና ለጋሶችን መሠረት አድርጎ የተመሠረተ በመሆኑ የርዳታው መቀዛቀዝ ማህበሩን ለመቀጠል ከባድ አድርጎታል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የርዳታ ሰጪዎች ቁጥር እየተቀዛቀዘ ሲሆን ለዚህም በሀገሪቱ ያለው የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጫናዎች ምክንያት እንደሚሆን አቶ በላይ ተናግረዋል፡፡

ይህም በተለይም ለጋሶችን መሠረት አድርጎ የተመሠረቱ ማህበራት ላይ ከፍተኛ ጫኛ እና ችግር የሚያጋላጥ ሲሆን እንደድርጅት ማህበሩን ለማስቀጠል ከርዳታ ተቋማት ከመጠበቅ በማህበሩ ያለውን የሰው ሃይል በመጠቀም እየሠሩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ሀገር ተረካቢ ልጆችን በትምህርት በማብቃት ሀገርን ማሳደግ ይገባል የሚለው የማህበሩ መስራች፤ ሁሉም ማህበረሰብ ከገንዘብ ባለፈ እውቀትንና ጊዜን ባለው አቅም ማካፈል ቢቻል የበጎ አድራጎት ማህበራትን ህልውና ማዳን እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

ይህ የበጎ አድራጎች ተግባር ከራስ ቀንሶ ለሌሎች የሚሰጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በችግር ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት፣ ሴቶችን እና እናቶችን በማሰብ የመስጠትና የማካፈል ባህላችንን አጎልብተን እንቀጥል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአስካል በጎ አድራጎት ማህበር በ2011 ዓ.ም የተመሰረት ሲሆን ችግር ላይ ያሉ ህጻናት ባሉበት ሁነው በትምህርት አቅርቦት እና በጤና ላይ አስፈላጎውን ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራን የሚሰራ የበጎ አድራጎት ማህበር ነው፡፡ እስካሁንም ማህበሩ ስድስት መቶ ለሚደርሱ ህጻናት በትምህርት እና በጤና በኩል የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት ማሟላት እንደተቻለ አቶ በላይ አስታውቀዋል፡፡

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You