ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሃይል ትስስር በመፍጠር የመሪነት ሚና እየተጫወተች ነው

አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሃይል ትስስር በመፍጠር የመሪነት ሚና እየተጫወተች ነው ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በቅርቡ በአቡዳቢ እ.አ.አ በተካሄደው ወርልድ ፊውቸር ኢነርጂ ሰሚት (world Future Energy Summit) የጎንዮሽ መድረክ ላይ በመገኘት ባደረጉት ገለጻ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሃይል ትስስር በመፍጠር የመሪነት ሚና እየተጫወተች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፓንአፍሪካዊ ትብብር ሚና የታዳሽ ሃይል ልማትን ማሳለጥና የኢነርጂ ዋስትናን ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማው አድርጎ በተካሄደው መድረክ ላይ ሚኒስትሩ ቀጣናዊ የሃይል ትስስር መሠረት የመጣልና የማጠናከር ጉዳዮች ኢትዮጵያ በቀጣናው ለትብብርና ቅንጅት የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸው፤ እንደተጨማሪ ማሳያም ሱዳናውያን የገጠማቸው ውስጣዊ ችግር ክፍያ እንዲፈጽሙ ባያስችላቸውም የሃይል አቅርቦት መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የምስራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል ለማጠናከርና ለማስቀጠል አይነተኛ ሚና እየተጫወተች ነው ያሉ ሲሆን፤ የሃይል መስመሮች መንገዶችና የቴሌኮም ኔትወርኮችን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተዘርግተው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ብሔራዊ እቅድ ቀጣናዊ ቅንጅታዊ ስትራቱጂ መካተቱንና በአህጉር ደረጃ ማሳደግ ታሳቢ መደረጉን አንስተው፤ እንደሀገር ያለን የሃይድሮፓወር እምቅ አቅምና የማልማት ልምድ፤ እንዲሁም በሃይድሮ ፓወር ልማት የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ተቋም መገንባት መቻሉ፤ የምስራቅ አፍሪካ የአረንጓዴ ኢነርጂ ማእከል ለመሆን እንድንሠራ አስችሎናል ብለዋል፡፡

የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት በመተግበር የግሉን ዘርፍ በሃይል ልማት ዘርፍ ለማሳተፍ ያለው ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያ መሆኑን ያነሱት ክቡር ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን አሕጉራዊ የሃይል ሲስተም ማስተርፕላን መሠረት በማድረግ ለሶስት ጎረቤት ሀገራት የሃይል ትስስር መፈጠሩንና ሌሎች ሀገራትን በማካተት ወደ አሕጉራዊ ትስስር ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሃይል መሠረተ ልማት ግንባታና ዝርጋታ ከፍተኛ መዋእለንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ የልማት አጋሮች ቁርጠኝነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በሃይል ልማት ኢንቨስትመንት መሰማራት በቀጣናው የሥራ እድል ፈጠራ እና የሰላምና የጸጥታ ጉዳች ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You