የንግድ ሥራ ማለት ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ለዋጋ ሲባል መሸጥ፣ ማስተላለፍና መለወጥ ነው። ይህ ሁሌ የሚከናወን የግብይት ሂደት ሲሆን፤ ለትርፍ ሲባል የሚከናወን ነው። በዋናነት ደግሞ ርግጠኛነት የሌለው የመክሰርና የትርፉማነት ውጤት ሊያስከትል የሚችል ባህሪም እንዳለው በንግድ ሥራ ላይ የተካሔዱ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የሀገሪቱን ንግድ ሕግና ሕገ-መንግሥት ስናይ፤ ንግድ የሰው ልጆች የዕለተ ተዕለት ኑሮን ለማሻሻልና ብሎም ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማራመድ የሚያስችል የኢኮኖሚ ግንኙነት እንደ መሆኑ መጠን ይህን የንግድ ግንኙነት በተፈለገው መንገድ ለማስኬድ የግድ በሕግ መገዛትን ይጠይቃል። ይህንን መሠረት በማድረግ በሀገራችንም በ1952 ዓ.ም የንግድ ሕግ ወጥቶ እንሆ ለግማሽ ምእተ ዓመት ገደማ እየተሠራበት ይገኛል።
በሕገ-መንግሥቱም አንቀፅ 43(1) ላይም “የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአጠቃላይም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በተናጠል የኑሮ ሁኔታቸውን የማሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ነው። ” በማለት የደነገገውን መሠረት በማድረግ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራው ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክሮ እየተሠራበት ይገኛል።
በዚህ ሂደት የበለጠ ንግዱን ስኬታማ ለማድረግ እና ሸማቹን እንዲሁም ሀገርን በሚጠቅም መልኩ ለማካሔድ ከሚወጡ ደጋፊ ሕጎች መካከል ከሰሞኑ የችርቻሮም ሆነ የጅምላ ንግድ ላይ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የተፈቀደበት አዲሱ አዋጅ አንደኛው ነው።
በገቢ፣ በወጪ፣ በጅምላ እና በችርቻሮ ንግድ ላይ የውጪ ባለሀብቶች እንዲሠማሩ የሚፈቅድ ምንም ዓይነት የአሠራር ሥርዓትም ሆነ ደጋፊ ሕግ እና መመሪያ አልነበረም። ይህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሰሞኑን የኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ ለውጭ ባለሀብቶች መፈቀዱን አስመልክቶ መግለጫ በሰጡበት ወቅት አስታውቀዋል።
የፈቃዱ መሰጠት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል እና በተሻለ ውድድር ሸማቹ በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዛ ያደርጋል ብለዋል። በርግጥ በወጣው መመሪያ ለውጪ ባለሀብቶች ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት ሊያሟሏቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ተብራርቷል።
አዲሱን የውጭ ባለሀብቶች የንግድ ፈቃድ አስመልክቶ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚሉት አላቸው። በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚናገሩት፤ ለውጭ ባለሀብት ዝግ ተደርጎ የቆየው የግብይት ሥርዓትን መከፈቱ ትልቅ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው። ምክንያቱም በሀገር በቀል ባለሀብቶች ብቻ ተይዞ የነበረው፤ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሲደረግ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር እና ጥራትን እና የተሻለ አገልግሎት ሕዝቡ እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ይህ ማለት የውጭ ነጋዴዎች ሲመጡ፤ ሀገር ውስጥ ያሉትም ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ እና አብሮ ለመልማት እንዲሁም ለጋራ ዕድገት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ማለት መሆኑን ይናገራሉ። እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር ገለፃ፤ የውጪዎቹ ሲመጡ እና ሲሳተፉ አዲስ የግብይት ሥርዓትን ያስለምዳሉ። ቴክኖሎጂን መጠቀም እና የአሠራር ሥርዓትን ለንግዱ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሸማቹም በአዲስ መልኩ የሚያስለምዱ ይሆናል።
ሌላው በረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር የተገለፀው፤ ባለሀብቶች መጥተው በግብይቱ ውስጥ ሲሳተፉ ዋናው እስከታችኛው ማህበረሰብ ድረስ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ። አዳዲስ ምርቶችን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና አዳዲስ አሠራሮችን እና የግብይት ሥርዓቶችን ለነጋዴው ብቻ ሳይሆን ለሕብረተሰቡም ያስተዋውቃሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ ሲመጡ ለሥራው ይዘው የሚመጡት ካፒታልም ለኢኮኖሚ መነቃቃት የሚኖረው ድርሻ የሚናቅ አይደለም።
በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪው ሙህዲን መሐመድ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሀብቶች መፈቀዱ ያልተለመደ አዲስ ነገር ነው። በርግጥ ጥቅም እና ጉዳቱ ተጠንቶ፤ ጉዳቱን ለመቀነስ ጥቅሙን ለመጨመር በርካታ ሥራዎች መሠራት አለበት ይላሉ።
እንደ መምህሩ ገለፃ፤ የትኛውም ነገር ጥቅም እና ጉዳት ይኖረዋል። ዋናው ጉዳይ ያንን ሚዛን ለማስተካከል የመጫወቻ ኳሶችን መጠቀም ነው። እነዛን ኳሶች ይዞ በአግባቡ መጫወት ከተቻለ የተሻለ ጥቅም ማግኘት ይቻላል። በኢትዮጵያ ትናንሽ ነገሮችን ጨምሮ ብዙ ነገሮች የሚመጡት ከውጭ ነው። ባለው የፀጥታ ችግርም ምክንያት እንቅስቃሴው የተገደበ በመሆኑ እና በሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ በውጭ ምርት ላይ ጥገኛ ሆናለች።
ከዚህ ቀደም በጣም ጥቂት ሰዎች ምርትን ከውጭ እያመጡ ገበያውን ይቆጣጠሩ ነበር። በእነርሱ ምክንያት በተጋነነ ዋጋ ለዛውም በብዛት የማይገኝበት ሁኔታ ነበር። አሁን ግን በሰፊው ሊገኝ ስለሚችል፤ የውድድር መንፈስን ያመጣል። ይህ ሸማቹን በእጅጉ የሚጠቅም ይሆናል። ስለዚህ ንግዱ ለውጭ ባለሀብት ሲፈቀድ የውጭ ምርቶች በአነስተኛ ዋጋ በተሻለ ጥራት የሚገኙበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን መምህር ሙህዲን አብራርተዋል።
ሌላኛው ጥቅም የውጭ ባለሀብቶች መምጣታቸው የሚያመጣው የሥራ ዕድል አለ የሚል እምነት እንዳላቸው በመጠቆም፤ እነዚህ ሰዎች ሲመጡ ሙሉ ለሙሉ ሠራተኞቻቸውን ከውጭ ይዘው አይመጡም። ስለዚህ ኢትዮጵያውያንን መቅጠራቸው አይቀርም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይኖራል። አሠራራቸውንም ለማወቅ ያስችላል ብለዋል።
ለውጭ ባለሀብቶች በርን በመክፈት እንዲነግዱ መፍቀድ የነፃ ገበያ ሥርዓት መገለጫ መሆኑን አስታውሰው፤ እዚህ ላይ በአብዛኛው ሸማች ተጠቃሚ ይሆናል። አንድ ሸማች ወደ ገበያ ሲሔድ የሚያያቸው ነገሮች አሉ። አንደኛው የተሻለ ዋጋ፤ የተሻለ ጥራት እና በቀላሉ መግዛትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለመግዛት ይዘጋጃል። የውጭ ባለሀብት መግባቱ እንደሸማች እነዚህን የተሻሉ ዕድሎች ይሰጣል። ይህንን ሸማቹ ካገኘ የሻጩ ማንነት አያገባውም። ኢትዮጵያዊም ሆነ አሜሪካዊ ወይም ቻይናዊ ቢሆን ምንም ችግር የለውም። በተጨማሪም ሀገር ውስጥ ያለውን ምርት በቀላሉ ለማሰራጨት ይጠቅማል በማለት መምህር ሙህዲን ጥቅሙን አስመልክቶ አስረድተዋል።
ነገር ግን የውጭ ባለሀብቶች መሳተፍ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም ሊኖረው እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ አመልክተዋል። አንደኛው ተወዳዳሪ መሆን ያልቻሉ እንጭጭ (አነስተኛ) የሀገር ውስጥ የንግድ ማህበረሰብ አካላት ከግብይት ሊወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር ገልጸዋል። በሌላ በኩል የውጭ ባለሀብቶች ሀገር ውስጥ ነግደው እና አትርፈው ያገኙትን ሀብት ወደ ውጭ ሀገር የማሸሽ ዝንባሌ ካላቸው እና ይህ በሕግ ሥርዓት ካልታሠረ ምናልባትም የሀገር ሀብት በቀላሉ ከሀገር እንዲሸሽ ያደርጋል ብለው እንደሚያስቡም ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር አመላክተዋል።
መምህር ሙህዲን በበኩላቸው፤ በጉዳትነት የጠቀሱት የሀገር ውስጥ ምርትን ያዳክማል የሚል ነው። በዚህ ሳቢያ የውጭ ምርት ማራገፊያ የመሆን ዕድል ሊያጋጥም ይችላል ይላሉ። በተጨማሪ ከባዱ ጉዳይ በእነዚህ አካላት ላይ የዋጋ ቁጥጥር ለማድረግ ይከብዳል የሚል ስጋትም አለባቸው። ቀደም ሲል መንግሥት በንግድ ላይ ቁጥጥር ያደርግ ነበር። እነዚህ ግን የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ናቸው። ዓለም አቀፍ ገበያውን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው መንግሥት ሊቸገር ይችላል ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ምርት ከተዳከመ አምራቾች እንደቀድሞ ማምረት ካልቻሉ እና አነስተኛ ነጋዴዎችም ከሥራ ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ የሚፈጥረው ጫናም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ይህንን ሚዛን ለማስጠበቅ በቅድሚያ የሀገር ውስጥ አምራቾች የመወዳደር አቅማቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል። የማበረታቻ ዘዴዎችን መጠቀም የግድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
‹‹ የሀገር ውስጥ አምራችም ሆነ ነጋዴ መኖሩ ሀገር በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ ትሆናለች። ›› ያሉት መምህር ሙህዲን፤ ሁሉንም ነገር ለውጭ ካምፓኒ መተው ማለት ሀገርን አደጋ ላይ መጣል በመሆኑ ሚዛኑን ማስጠበቅ እንደሚገባ አስረድተዋል። የመንግሥት ሕግን የማስፈፀም አቅምም ማደግ እንዳለበት ጠቁመዋል። የውጭ ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ እንዳይቆጣጠሩት እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ ከገበያው ውጭ እንዳይሆኑ አስቀድሞ ሕግን የማስከበር ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል።
ትልቁ ጉዳት እና ጫናው በአምራቹ ላይ መሆኑን በማስታወስ፤ በጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ላይ በሚሳተፉ ሰዎች ላይ ጫና ይፈጥራል። የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ተፎካክረው የሚነግዱበትን ዕድል መፍጠር ከተቻለ ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል ብለዋል። በሸማቾች በኩልም እነዚህ ሸማቾች ገብተው ሙሉ ለሙሉ የሀገር ውስጥ ምርትን የሚቆጣጠሩ ከሆነ በሂደት የገበያ ሥርዓቱ በትክክል ካልተመራ ሁሉንም ግብይት መቆጣጠር (ሞኖፖሊ) ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ይሄ ደግሞ በረዥም ጊዜም ቢሆን አሁን ያለው ችግር ተመልሶ የመከሰት ዕድል ሊኖረው ይችላል። ይህ ችግር እንዳይፈጠር ሕግን የማስከበር አቅማችን ወሳኝነት አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን የግብይት ሥርዓት እጅ ባህላዊ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር፤ ሻጩ ብቻ ሳይሆን ሸማቹም ላይ ያለውን ክፍተት ያብራራሉ። በምሳሌ ሲያስረዱ ሳይንስም ሆነ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው በአንድ ምርት ላይ ዋጋ ሲጨመር ፍላጎት ይቀንሳል። ማለትም በምክንያትም ሆነ ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ ካጋጠመ ገዢ አይኖርም። በኢትዮጵያ ግን የአንድ ምርት ዋጋ ቢጨምር ሸማቹ ምንም ዓይነት ምላሽ አይሰጥም። ነጋዴው ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት ዋጋ ሲጨምር ሸማቹ ከመግዛት አይቆጠብም። ዋጋ ቢጨምርም ሸማች ከመግዛት ወደኋላ አይልም። ነጋዴዎች ይህንን በመረዳታቸው ዋጋ ሲጨምሩ ሽያጭ አይቀንስባቸውም። ስለዚህ ከመጨመር ወደኋላ አይሉም። በዚህ ሂደት ውስጥ ትርፋቸው በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይመጣል። ነገር ግን ሰፊው ማህበረሰብ ክፉኛ እየተጎዳ ይሄዳል። ስለዚህ ሥርዓት የተበጀለት የግብይት ሥርዓት የለም ብለዋል።
በሕግ በተቋም ደረጃ የተስተካከለ የግብይት ሥርዓት የለም። የሆነ ሰው ተነስቶ ይጨምራል። ኢኮኖሚው ነፃ ኢኮኖሚ ነው የሚል ነገር አለ። ነፃ ኢኮኖሚ ማለት ግን ማህበረሰቡን ክፉኛ ማንገላታት እና መበደል ማለት አይደለም። ንግድ ፍቃድ የሚሰጠው ለማገልገል ነው። የሚያገለግልበት ደግሞ ማዕቀፍ አለው። ከዛ ማዕቀፍ ሲወጣ የግብይት ፈቃድ መከልከል እና ከግብይት ሥርዓት ውስጥ ማስወጣትን የመሳሰሉ ርምጃዎች ይጠበቃሉ። እናም እስከ አሁን ድረስ ገበያው ልቅ መሆኑ አነስተኛ እና ጥቂት ባለሀብቶች በአንድ ሌሊት ቱግ ብለው ከፍተኛ ባለሀብት የሚሆኑት በሰፊው ሕዝብ ላይ በሚያደርጉት ብዝበዛ ነው። ከዚህ በኋላ ይህ ይቀንሳል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
‹‹የሌሎቹ ማለትም የሽያጭ እና የግዢ ሂደቱ ዘመናዊነት ይታይበታል። በእኛ ሀገር ግን በግብይት ሠንሰለት ውስጥ አላስፈላጊ ወጭዎች አሉ። በመሃል የደላላ፣ የውል ማሰር፣ የመስማማት እና የትራንስፖርት እንዲሁም ሌሎችም በጣም ብዙ ወጪዎች አሉ። ‹‹ሀ›› የሚባል ነጋዴ ቢኖር እና ተገቢውን አገልግሎት ባይሰጥ፤ ሸማቹ ‹‹ለ›› የሚባል ነጋዴ ጋር ቢሄድ የተሻለ አገልግሎት አያገኝም። ሸማቹ ሌላ ‹‹መ›› የተባለ አገልግሎት ሰጪ ጋር ቢሄድም ከሁለቱ የተለየ አገልግሎት አይሰጠውም። ሻጮች ግንኙነት (ኔትወርክ) ያላቸው ናቸው። የመረጃ ፍሰት አላቸው። ይህ ሸማቹን ሲጎዳ መኖሩን ረዳት ፕሮፌሰር አመልክተዋል።
ንግድ ተወዳዳሪነት አምስት ብርም ቢሆን ቀንሶ ሽጦ ማትረፍ ቢያስፈልግም የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ግን በተቃራኒው ዋጋቸው አንድ ዓይነት ነው። ስለዚህ ገዢ የሚገዛው ነጋዴ ባለው ነው። ሸማቹ አማራጭ የለውም። ሁሉም አንድ ነው። ነገር ግን አሁን በቀላሉ ወዲያው የውጭ ባለሀብቶች ወደ ንግድ ሲገቡ በሸማቹ ላይ አሁን እንዳለው በግንኙነት (ኔትወርክ) ተፅዕኖ ለማምጣት ጊዜ ይወስዳል። ስለዚህ ይህ ችግር እንዳይመጣ የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ከገበያ ከመውጣታቸው በፊት ቀድመው ዝግጅት ማድረግ አለባቸው።
በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ እንደተናገሩት፤ የውጭ ባለሀብቶች በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ በመሳተፋቸው ተጠቃሚው የሚሆነው መላው የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ነው። ገዢም ሻጭም ይጠቀማሉ። በገዢው በኩል አማራጭ ይገኛል። የተሻለውን መርጦ የመግዛት ዕድል ይኖረዋል። ሻጭ አዳዲስ ቴክኖሎጂ እና የግብይት ሥርዓቶችን ይማራል። ያልተለመዱ የአሠራር ሥርዓቶችን ያውቃል፤ ራሱን አሻሽሎ ተወዳዳሪ ለመሆን ይሞክራል። ተወዳዳሪነትን ማሳደግ በራሱ አንደኛው ጥቅም ነው። ጥራትንም ያሳድጋል። ሸማችም ይጠቀማል፤ ደንበኛ ንጉስ ነው የሚለው በእውን የሚታይ ይሆናል ብለዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም