ብዙ ጊዜ የምግብ አይነቶች፣ የአልባሳት አይነቶች ወዘተ ሲባል እንጂ ስለ ትምህርት አይነቶች በአደባባይ ሲነገር አይሰማም። ከሚመለከተው ተቋም በስተቀር ጉዳዩን ጉዳዬ ብሎ ሲብሰከሰክ የሚውልና የሚያድር ቀርቶ የሚያረፍድ እንኳን የለም። ማንም ልብ አይበላቸውም እንጂ የትምህርት አይነቶች ሁሌም የመነጋገሪያ ርእስ ከመሆን አምልጠው አያውቁም።
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት የሚታሰበው በ1898 ዓ.ም “እስከ አሁን ማንም የእጅ ሥራ አዋቂ የነበረ ሰው በውርደት ሥም ይጠራ ነበር። ስለዚህም ማንም ሰው ለመማርና ለመሠልጠን የሚደክም አልነበረም። … ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ለወደፊትም ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ሁሉ ከስድስት ዓመታቸው በኋላ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይሁን።” የሚል አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
የትምህርት አይነቶች፣ በተለይም በዚህ ዘመን እጅግ አነጋጋሪ፣ እጅግ ወስብስብ፣ ሲበዛ በፖለቲካል ርእዮት የተነከሩ የፖለቲካ መሳሪያዎች፣ የማንነት ማጥቂያ ምሳሮች፣ የማንነት መፈለጊያ ማይክሮስኮፖች ወዘተ በመሆን ነገር ዓለሙን ሁሉ በአራቱም ማእዘን እየናጡት ይገኛሉ። አሜሪካ የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን ሞት (በነጩ ፖሊስ መገደል) ተከትላ ያነጣጠረችው “የትምህርት አይነቶች” ላይ ሲሆን፤ አወዛጋቢው “ክሪቲካል ሬስ ቲዎሪ” ን እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ ወስና በመሰጠት ላይ ትገኛለች፡፡
ድሮ ድሮ አሜሪካ ወደ ህዋ የመምጠቅን ስኬታማነት በሩሲያ በመነጠቋ ምክንያት እርር፣ እርር ድብን ማለቷን ተከትሎ በብርሃን ፍጥነት ፊቷን ያዞረችው ወደ ትምህርት አይነቶቿና የጎደሉቱ እንደ ነበር በታሪክ በደማቁ ከመፃፉም በላይ፤ በተለይ በሥነ- ትምህርት ባለሟሎች ዘንድ ሁሌም ሲነሳ ይውላል፤ ያድራልም።
ከመልካም መልካሙ ለመነሳት ብለን አሜሪካንን አነሳን እንጂ፣ በኃይል ሥልጣን የተቆጣጠሩ መንግሥታት ሁሉ ገና ወንበራቸው ላይ በአግባቡ ሳይቀመጡ ዓይናቸው የሚያነጣጥረው የትምህርት ሥርዓቱና የትምህርት አይነቶች ላይ ነው። በምሳሌ ማየት ካስፈለገ በደርግ ሥርዓት ወቅት ሲሰጡ የነበሩ የትምህርት አይነቶች (ክበባት ሳይቀሩ) በኢህአዴግ እየተነቀሉ እንደተጣሉ መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው። በተለይ ከላይ በጠቀስነውና የማንነት ጥያቄ ጎልቶ በወጣበት የወቅቱ ፍልስፍና (ከተባለ) ከትምህርት አይነቶች ሁሉ እንደ “የቋንቋ ትምህርት” መከራውን ያየ አለ ለማለት ድፍረቱ አይኖርም።
የታሪክ፣ የባዮሎጂ (ከሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ)፣ የኃይማኖት እና ሌሎችም ምን ያህል የእሰጥ አገባ አጀንዳዎች እንደ ሆኑ እያየን−ተመለከትን እንገኛለን። የግብርና እና የገበሬ ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ ግብርና (እርሻ) የተባለው የትምህርት አይነት ከነክበቡ ከትምህርት ቤቶች መነቀሉን ለምናውቅ ሰዎች ነገሩ ሁሉ ግልፅ ሲሆን፤ ሙዚቃ፣ እጅ ሥራ፣ እንጨት ሥራ እና ሌሎችም ተመሳሳይ እጣ እንደ ገጠማቸው ይታወቃልና የትምህርት አይነቶች የመደብ ትግል የሚካሄድባቸው የፍልሚያ ሜዳዎች የሆኑ እስኪመስለን (ካልሆኑ ማለት ነው) ድረስ የየዘመኑ ንቅናቄና ስር ነቀል አብዮቶች ሰለባዎች ናቸው።
ቀጥሎ የምንጠቅሰውን ሰነድን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚመለከታቸውን ካነጋገረ በኋላ “በአዲሱ የሥርዓተ-ትምህርት ትግበራ ከአንደኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤት ያሉ ትምህርቶች ላይ የሚቀነሱ እና እንደ አዲስ የሚጨመሩ የትምህርት አይነቶች መኖራቸው ተገለጸ።” የሚል ዜና ለአየር አብቅቶ የነበረ መሆኑን ስናስታውስ ከላይ እየተነጋገርንበት የመጣነው ጉዳይ ይበልጥ ግልፅ እየሆነ፤ “የሚቀነሱ” እና “የሚጨመሩ” የሚሉትም፤ “ለምን?” የሚል ጥያቄን በማጫር ይበልጥ ጥርት እያሉ ይሄዳሉ፡፡
ወደ ሰነዱ ከመሄዳችን በፊት ግን “መቀነስ” ም ሆነ “መጨመር” የሚቻለው በሕግ እና በሕግ አግባብ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ፋይዳ አለው። ለምሳሌ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ርምጃ የተወሰደበትና 6ኛ እና 8ኛ ክፍሎችን እንዳያስፈትን የተከለከለው ጊብሰን አካዳሚ ከቀረቡበት በርካታ ክሶች አንዱ ከመስተዳድሩ እውቅና ውጪ “የትምህርት አይነት ጨምሮ ማስተማር” ሲሆን፤ ከቋንቋ ትምህርት (“የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሀገራችን እንግሊዘኛ ነው’ ብሎ ስታንዳርድ እስከመያዝ መድረስ”፤ “የሀገር በቀል ቋንቋ ጠል መሆን”፤ “የትምህርት ቋንቋ አለማክበር” እና ሌሎችም) ጋር በተያያዘም ስህተት ሆነው የተገኙበት ተግባራቱ ቀላል አይደሉም።
ከዚህ አኳያ “ከ2015 ዓ∙ም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የሚገባው አዲሱ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት [ሰነድ] ምን ምን ጉዳዮችን አካቷል?” ብለን ስንጠይቅ ከላይ የገለፅናቸውንና እየተነቀሉ የተጣሉትን መልሶ የመትከል ተግባርን ያካተተ ስለ መሆኑ “ከመዋለ ሕፃናት አንስቶ የግብረገብ ትምህርት መስጠት” ግዴታ መሆኑን፤ እንዲሁም፣ “ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ 6ኛ የግብረገብ ትምህርት አይነት፣ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ የሥነዜጋ ትምህርት እንዲወስዱ ያስገድዳል።” ሲል ማስፈሩ፤ የጤና እና የግብርና ትምህርት አይነቶችንም ማካተቱ ተጠቃሽ ነው። (እዚህ ጋ፣ የግብረ-ገብ ትምህርት፣ በተለይ በንጉሡ ዘመን “ወሳኝ” ከሚባሉት የትምህርት አይነቶች አንዱ እንደ ነበር ማስታወስ ይገባል።)
በአዲስ አበባ ለ9ኛ እና 10ኛ ክፍል የሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት “ፐርፎርም ኤንድ ቪዥዋል አርት” በሚል መተካቱ፤ በ11ኛ እና 12ኛ ክፍል በድጋሚ ከሚሰጡ የትምህርት አይነቶች በተጨማሪ ሥራና ቴክኒክ ላይ የሚያተኩሩ የማኑፋክቸሪንግና ኮንስትራክሽን የትምህርት አይነቶች በየደረጃው ተለይተው መጨመራቸው እና ሌሎችም ተገቢ ማሳያዎች ናቸው።
ከ322 ሺ በላይ ተማሪዎች ለፈተና ከተቀመጡበትና ከሰኔ 6 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም የተሰጠውን ፈተና (እና አስከትሎ የነበረውን ችግር ያስታውሷል) በተያያዘ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አኳያም «ተማሪዎችንም ፍትኃዊ በሆነ መልክ ሊያወዳድር እና ከእነሱ ችሎታ ባሻገር ምንም መበላለጥን ሊያስከትል የማይችል ሆኖ ስላገኘነንው እነዚህን ተጠቅመን ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ መመደብ እና የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ወስነናል» በማለት መነሻውን ካስቀመጠ በኋላ “ከተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፊዚክስ፣ ከማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ የጂኦግራፊ ፈተናዎች ለመመዘኛነት ተመርጠዋል።” የሚለው የወቅቱ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ መግለጫና ሌሎችም ከዚሁ ከትምህርት አይነቶች ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸውና “የትምህርት አይነቶች” ጉዳይ የዋዛ ፈዛዛ አለመሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
ባደጉት ሀገራት “የተሻለ ገንዘብ ማስገኘት የሚችሉ የትምህርት አይነቶች ተብለው [የሚመረጡ አሉ]። ብዙውን ጊዜ ጥሩ ገንዘብ ማግኘት የሚፈልግ ሰው “ስቴም” (STEM) ተብለው የሚታወቁትን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ የትምህርት አይነቶችን እንዲማር ይነገረዋል።” የሚል ምክር ሲሰነዘር መሰማቱም የትምህርት አይነቶች ሚና የተለያዩ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ጠብሰቅ ካለ ገቢ አኳያም የየራሳቸው ሚና አላቸውና የትምህርት አይነቶችን “የትምህርት አይነቶች” ብቻ ብሎ ማለፍ ከስህተት እንዳይጥል መጠንቀቅ ያስፈልጋል ።
ከስቴም ጋር በተያያዘ፣ በድሬዳዋ አስተዳደር ስር ከሚገኙ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሳይንስ (ፊዚክስ፤ ባዮሎጂና ኬሚስትሪ) እና ሒሳብ የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች በመመልመል በተግባር የተደገፈ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥልጠና የሚሰጠውን፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማዕከል (STEM Center)ን በማሳያነት መውሰድ ይቻላል።)
“ግብርና 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲማሩት፤ በብሔራዊ ፈተናነትም የ12ኛ ክፍል ፈተና እንዲፈተኑት ይደረጋል” የሚለውም “ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን” እንደሚለው የአንድ ኤፍኤም ሬዲዮ መሪ ቃል፣ የነበረውን፣ በኋላም የተነቀለውን የትምህርት አይነት ወደ ነበረበት የመመለስ ሥራ ነውና የአሁኑን ሥርዓተ ትምህርት ያስመሰግነዋል። በተለይ፣ ወደ ከፍተኛ የግብርና ትምህርት ተቋማት (ግብርና ኮሌጆች) የሚገቡና በሙያው ሠልጥነው የሚወጡ ምሩቃን እስኪጠፉ ድረስ የነበረውን ክፍተት ያየ የትምህርት ሥርዓት ከመሆኑ አኳያ የበለጠ ያስመሰግነዋልና ይበል ሊባል ይገባል።
ወደ አሁኑ፣ ወደ ወቅታዊው ጉዳይ ስንመጣ የአሁኑ የትምህርት አስተዳደርን ውሳኔዎች የምናገኝ ሲሆን፤ አንዱም ተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት የመረጠ ተማሪ ሰባት የትምህርት አይነቶችን ለአካዳሚክስ (ለ12ኛ ክፍል ፈተና) የሚጠቀም መሆኑ ሲሆን፤ እነሱም እንግሊዝኛ፣ ሂሳብ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ እና ግብርና ናቸው። ከእነዚህ ከሰባቱ ውጭ ደግሞ በምርጫ ተማሪዎች አምስት የትምህርት መስኮችን መርጠው መከታተል የሚችሉ ሲሆን፤ የትምህርት መስኮቹም ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ጤና ሳይንስና ግብርና ሳይንስ መሆናቸው በሰነዱ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
የኢኮኖሚክስ እና የሥነ-ዜጋ ፈተናዎች ውጤቶች ውድቅ ወደ ተደረጉበት፤ ወደ የማህበራዊ ሳይንስ ስንመጣ ደግሞ ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል ፈተና የሚቀመጡባቸው ስድስት የጋራ ትምህርቶች ያሏቸው መሆኑን የምንመለከት ሲሆን፤ ከእነዚህም በአንዱ ጥሩ ነጥብ ካላቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት መሆኑ ነው። ይህ ከ30ኛው የሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ላይ የተገኘው ሰነድ እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ በዚሁ ስትሪም ያሉ ተማሪዎች ከቋንቋ እና ማህበራዊ ሳይንስ፤ ቢዝነስ፤ ሥነ-ጥበባት መካከል በራሳቸው ፍላጎትና ዝንባሌ አንዱን መርጠው ይማራሉ።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ከተማ ጥላሁን በነሀሴ ወር 2014 ዓ.ም ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉር ቆይታ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው በ2015 የትምህርት ዘመን ሥልጠና የሚሰጥባቸው አዳዲስ የትምህርት አይነቶች የተለዩ ሲሆን፤ እነሱም በማዕድን፣ በቱሪዝም እንዲሁም በግብርና ተፈጥሮ ሀብቶች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ይህ ልየታ፣ አካባቢውንና ያለውን እምቅ ሀብት የምናውቀው እንደ መሆኑ መጠን፣ ተገቢ ልየታና አካትቶ ነው ብለን እናምናለን፤ ይህ በሌሎቹም፣ ለምሳሌ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲን በመሳሰሉና አርብቶ አደር አካባቢ ያሉ ተቋማት ዘንድም፣ አርብቶ አደሩን በሚመለከትና በሚጠቅም መልኩ (አርብቶ አደሩን የሚመለከቱ የትምህርት አይነቶችን በማካተት) ይደረጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ይህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት አይነቶችን መንቀልና መትከል በትምህርት አይነቶች ብቻ የታየ ሳይሆን በራሳቸው በተቋማቱም ተፈፅሞ የነበረ ትልቅ ስህተት ሲሆን፤ ለዚህም በእውቁ “ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ” (አሁን “ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ”) ላይ ተፈፅሞ የነበረውን የነቀላና መልሶ ተከላ ተግባር ማስታወስ በቂ ይሆናል።
ወደ ሰሞኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ውሳኔ ስንሄድ የምናገኘው ተመሳሳይ ውሳኔን ሲሆን፤ እሱም፣ ክልሉ በማህበራዊ እና ተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች በጥናት መስክነት ይወሰዱ ዘንድ የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን አካትቶ መገኘቱ ነው። ከተካተቱት የትምህርት አይነቶች መካከልም፣ በተፈጥሮ ሳይንስ በኩል አኒማል ፕሮዳክሽን፣ ማህበረሰብ ጤና፤ በማህበራዊ ዘርፍ በኩል ደግሞ ጆርናሊዝምን እና ሥነልቡናዊ ህክምና ጥቂቶቹ ናቸው።
እንደ ዘመናዊው ሁሉ፣ ከጥንት ጀምሮ አሁንም ድረስ እየተሰጠ ወዳለው፣ መሠረታችን ወደ ሆነው፣ ወደ አብነት ትምህርት ቤት ደግሞ እንሂድና የሀገራችንን የትምህርት ታሪካዊ ዳራ ከ“የትምህርት ዓይነቶች” አኳያ እንመልከት። ከሚመለከታቸው መረጃዎች ሁሉ መረዳት እንደ ተቻለው፣ በአብነት ትምህርት ቤት (ብዙዎቻችን “የቆሎትምህርት ቤት” የምንለው) የሚሰጡ የትምህርት አይነቶች የአንድን ሕዝብ ሁለንተናዊ የዕውቀት ዘርፎች ያካትታሉ።
በሀገራችን የአብነት ትምህርት ቤቶች (በእስልምናው መድረሳም የተለያዩ የትምህርት አይነቶች እንዳሉ ይታወቃል)፡፡ ከሚሰጡት ትምህርቶች ዋና ዋናዎቹ ከዚህ የሚከተሉት (ከአሁኑ ፒኤች∙ዲ ጋር በአቻነት የሚታየውን “ትርጓሜ” ትምህርት አይነትን ሳንጨምር) የፊደል እና የንባብ ትምህርት ቤት፣ የቋንቋ ትምህርት ቤት፣ የዜማ ቤትና የቅኔ ትምህርት ቤት ናቸው፡፡
የፊደል እና የንባብ ትምህርት ቤት ፊደል፣ ንባብ፣ ዳዊት እና የመጀመሪያ ደረጃ የዜማ ትምህርት ይሰጣል። ይህም የንባብ እና የጽሑፍ መነሻ የሚሆን የትምህርቱ መሠረተ ነው። ትምህርት ቤቱም ከፊደል ማስቆጠር ስለሚጀምር “የቁጥር፤ የንባብ ትምህርት ቤት” እየተባለም ይጠራል።
የቋንቋ ትምህርት ቤት በቅኔ ቤት ግዕዝ ከነአገባቡ ይሰጣል፤ መምህራኑም ግዕዙን ወደ አማርኛ በመተርጎም ግዕዝን እና አማርኛን አስተባብረውና አዛምደው ያስተምራሉ። ይህም የትምህርት አይነት ሥነ ጽሑፍን፣ አገባብን፣ ንባብን፣ ምሳሌአዊ አነጋገርን እና የንግግር ችሎታ ማሳወቅን ያካትታል። (ይህ የትምህርት አይነት እዚህ እባለቤቶቹ ጋር ተጣለ እንጂ በርካታ ሀገራት እስከ 3ኛ ዲግሪ ድረስ እየሰጡት ይገኛሉ።)
በዜማ ቤት ከውዳሴ ማርያም ዜማ ጀምሮ በመስተጋብር፣ በአርባዕቱ፣ በሠለስቱ፣ በጾመ ድጓው፣ በድጓው፣ በዝማሬና መዋስዕቱ፣ በአቋቋሙ፣ በቅዳሴው እና በሌሎችም ከዜማ ጋር የተያያዙ የትምህርት አይነቶች ኢትዮጵያዊ ዜማ እዚህ የደረሰበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። የዚህ ትምህርት አባትም ቅዱስ ያሬድ ነው። ይህም የደስታና የኀዘን ጊዜ ዜማዎችን፣ መዝሙርን፣ ማኅሌትን፣ ዘፈንን፣ ወየታን፣ ምሥጋናን፣ እንጉሩጉሮን እና ሌሎች፣ ከዜማ ጋር የተያያዙ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የዜማ ቅኝቶችን ሁሉ ያካትታል። (ከ1983 ዓ∙ም ወዲህ ተነቀለ እንጂ እስከዛ ድረስ እንደ አንድ የትምህርት አይነት የሙዚቃ ትምህርትም ከ7ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ይሰጥ ነበር።)
በቅኔ ቤት የፈጠራ ችሎታ (creativity) ወቅታዊ ሁኔታዎችን የመረዳት ችሎታ (perspective and understanding) የአእምሮን ጥበብ ተከትሎና ቋንቋን መርጦ፣ አጋኖ ወይም አዋርዶ፤ እንዲሁም፣ መካከለኛ ደረጃ ሰጥቶ ሁኔታዎችን የመግለጥ ችሎታ፤ ታሪክን እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ የማቅረብ፣ የፍልስፍና፣ የአስተሳሰብ ችሎታ ትምህርት (critical thinking) ይሰጥበታል። የቅኔን ባሕርይ እና የአሰጣጥ ስልት ልብ ብሎ ላስተዋለው ከላይ የዘረዘርናቸውን እና ሌሎችንም ጥበቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያጠቃልላል። ከዚህ በተጨማሪ ቅኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገዶች ያሉት በመሆኑ እንደየመንገዱ ልዩ ልዩ የአቀራረብ ስልትን እና የቋንቋን አገባባዊ መዋቅርን እና ቋንቋዊ ሙያን ለመማር ያስችላል።
ባጠቃላይ፣ ከላይ የትምህርት አይነቶች ብለንና አጥብበን በመነሳት የትምህርት አይነቶችን እንደየ አውዳቸው ወስደን ሃሳብ ተለዋውጠናል። ከአሀገራችን የትምህርት ታሪካዊ ዳራ አኳያም አጠር ባለ መልኩ ለመዳሰስ ተሞክሯል። የትምህርት አይነቶች እና ርዕዮተ ዓለማት ያላቸውን ተቃርኖ እና ተዛምዶ ጠቅሰን የትምህርት አይነቶችን የመነቀልና መተከልን እጣ ፈንታ አጋርተናል። የመልሶ ተከላና መልሶ ነቀላ ሂደት ምን መልክ እዳለውም ለመቃኘት ሞክረናል። በሂደቱም ሀገራችን ሁሉንም ያለፈችና እያለፈች ያለች ሀገር መሆኗን እያስረገጥን፤ መንቀልም ሆነ መትከል እየተስተዋለ መሆኑን እያሳሰብን የዛሬውን በዚሁ እናጠቃልላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም