በሕግ ቋንቋ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ቢኖሩትም፤ በደምሳሳው ስናየው አዋጅ ማለት የአንድን ጉዳይ አሠራር ለሕዝብ ማሳወቅ ማለት ነው። አንድ ተቋም የሚሠራቸውን ሥራዎች በምን አይነት መንገድ እንደሚሠራቸውና በምን ላይ የተወሰነ እንደሆነ ማዕቀፉን ማሳወቅ ማለት ነው። በዚህ ማዕቀፍ መሠረት ይጠየቃል ማለት ነው፤ ከማዕቀፉ ውጭም አይጠየቅም ማለት ነው። ይህን አሠራሩን ለሕዝብ የሚያሳውቅበት የሕግ አሠራር አዋጅ ይባላል። ይህም ምቹ እና ቀልጣፋ አሠራር እንዲኖር ያደርጋል።
ችግሩ ግን በሀገራችን የአዋጅ ብዛት እንጂ የተፈፃሚነት አሠራር የለም። በአንድ ውስን ጉዳይ ላይ አዋጅ መኖሩን ስትሰሙ ‹‹ይህም ለብቻው አዋጅ አለው እንዴ?›› ትላላችሁ። ብዙ ውስን የሆኑ ንዑስ ጉዳዮች ሁሉ አዋጅ አላቸው። አዋጆቹ ግን አይታወቁም፤ የሚታወቁት ምናልባትም በዚያው ንዑስ ዘርፍ ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች (ለዚያውም ምናልባትም በአመራሮቹ) እና በዚያ ጉዳይ ላይ የሚሠራው ሥራ ባለው የሕግ ባለሙያ ነው። በብዙዎች ዘንድ ላለመታወቃቸው ምክንያቱ ስለማይሠራባቸው ነው። አዋጁን ካወጡ በኋላ በአዋጁ መሠረት ነገሮች ሲፈጸሙ ስለማይታይ ነው።
ከስድስት ይሁን ሰባት ዓመታት በፊት ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ላይ የሕግ ባለሙያው አብዱ አሊ ጂራ እና መዓዛ ብሩ ሲወያዩ፤ ስለአሽከርካሪዎች ቅጥ ያጣ ክላክስ አደራረግ አዋጅ ጠቅሰው ሲያወሩ ስሰማ ‹‹ይህም አዋጅ አለው እንዴ?›› ብየ ተገረምኩ። በሠለጠነው ዓለም ትራፊክ ተቆጣጣሪው አካል አንዱ ሥራው ክላክስን መቆጣጠር መሆኑን፣ ያለአግባብ ክላክስ ያደረገ አሽከርካሪ የሚጠብቀውን ከባድ ቅጣት ሲያወሩ ስሰማ በጣም ቀናሁ። በኢትዮጵያ አዋጁ ቢኖርም (አሁን ምን ላይ እንዳለ ባላውቅም) በነዋሪው ግን አዋጅ መኖሩን ራሱ የሚያውቀው ምን ያህል ይሆን? ጆሮው ላይ ሲያንባርቅበት ‹‹ቆይ በዚህ አዋጅ ልጠይቀው›› የሚል ይኖራል? አይኖርም! ምክንያቱም አዋጁ ከነመኖሩም አይታወቅም። አልተሰራበትማ! ከፊቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች የትራፊክ መብራት ይዟቸው እያየ ያለማቋረጥ ጡሩንባ ሲያጮህ ማንም ምንም አይለውም።
አንድ አዋጅ የሚታወቀው በዚህ አዋጅ መሠረት እንዲህ ተደረገ ሲባል ነበር። አዋጁን የጣሰ ሲቀጣ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ስንፍናን ለመሸፈን ‹‹አዋጁ ይከለክለኛል›› ሲባል ይሰማል። ይህ የሚባለው ግን መሥራት ያልቻሉትን ነገር ለማሳበብ እንጂ ህግ ለማክበር አይደለም። አዋጁ የሚከለክለውን ብዙ ስህተት የሠሩ ናቸው መሥራት የማይፈልጉት ነገር ላይ አዋጁን የሚያሳብቡበት።
ለመሆኑ ግን አዋጅ በበዛ ቁጥር የመታወቅ ዕድሉ አይጠብም? ሕዝቡስ የንዑስ ጉዳዮችን ሁሉ አዋጅ እንዴት ተሸክሞ ይዘልቀዋል? እሱም ይሁን ችግር የለውም፤ ሥራቸው ነውና አስገዳጅ ደንብ ነው በሚል ንዑስ ጉዳዮች ሁሉ አዋጅ ሊያወጡ ይችላሉ። ግን አዋጁ መታወቅ ያለበት ሕዝቡ የእያንዳንዱን ጉዳይ አዋጅ በመግዛት ነው ወይስ በምንድነው?
የአዋጁን ዝርዝር ጉዳዮች እንኳን ተራው ሕዝብ የሕግ ባለሙያዎችም ላይዙት ይችላሉ። ዳሩ ግን ቢያንስ የሆነ ተቋም በዚህ ጉዳይ ላይ አዋጅ አለው የሚለውን እንኳን ለማወቅ በተግባር ቢያሳዩ ሁሉም ዝርዝሩን ያነበው ነበር። ለምሳሌ፤ አንዳንድ አዋጆች መኖራቸው ራሱ የሚታወቀው ብዙ ስለሚወራባቸው ነው። የሁሉንም ሰው ሕይወት የሚነኩ ስለሆነ ነው። እርግጥ ነው የትኛውም ጉዳይ ማንኛውንም ሰው ይመለከተዋል። ሐኪሙ የጤና አዋጆች ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም፣ የማህበራዊ ጉዳይም፣ የፖለቲካዊ ጉዳዮችም አዋጆች ይመለከቱታል። ችግሩ ግን በአዋጆቹ መሠረት ሲሠራ ስለማይታይ ማንም ልብ አይለውም።
አዋጆችን አለማወቅ ለስህተትም ይዳርጋል። የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ጉዳይ ወሰን እንዳይታወቅ ያደርገዋል። ለምሳሌ፤ የስደተኞችና ተመላሾች አዋጅ የሚባል አለ። በሀገር ውስጥ ሰዎች ብዙም የሚታወቅ አይመስልም። ይህ አዋጅ ስደተኛ ማለት ምን እንደሆነ እና ማን እንደሆነ፣ ተመላሽ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና እነማን እንደሆኑ ይገልጻል። በውስጡም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች አሉት።
ይህ አዋጅ ባለመታወቁ ግን የስደተኛ ትርጉም ሲደበላለቅ ይታያል። ተፈናቃይን ከስደተኛ፣ ጥገኝነት ጠያቂን ከስደተኛ ሲደበላለቅ ይታያል። በዚህ ምክንያት ተቋሙ (የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ማለት ነው) ሥራው ባልሆኑ ነገሮች ይወቀሳል። ጉዳዩ እሱን ነው የሚመለከት ብለው የሚያስቡ ሰዎች በድፍረት ይጠይቁታል።
በመንግሥትና በተቋማት በኩል ያለው ችግር አዋጅ ማውጣት እንጂ ማስፈጸሙ ላይ ትኩረት አይደረግም። በየንዑስ ጉዳዩ አዋጅ ይወጣል፤ ይታተማል። ከዚያ ግን ሼልፍ ላይ ይቀመጣል። መኖሩ የሚታወቀው ምናልባትም እግረ መንገድ ሌላ ነገር ሲፈልጉ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ሁሉ ግን ይህን አዋጅ የጣሰ እንዲህ ተቀጣ፣ ይህን አዋጅ በመተላለፉ እንዲህ ተደረገ… ቢባል ኖሮ ማንም አይረሳውም ነበር። ችግሩ ግን ነገሮች ሲታገዱም ሆነ ሲፈርሱ አዋጁ አይነገርም፤ ምናልባትም ማገዱም በአዋጁ ምክንያት ላይሆን ይችላል ማለት ነው። ስለዚህ የሆነ ነገር ሲደረግ፤ ሕዝቡ አዋጁን ከማየት ወይም በአዋጁ ሊሆን ይችላል ብሎ ከማሰብ ይልቅ የመንግሥት ፍላጎት ብቻ አድርጎ ያየዋል ማለት ነው።
በሕዝቡ በኩል ደግሞ ያለው ችግር፤ ሕጎችና ደንቦች ወጡ ሲባል ይመለከተኛል ብሎ አለማየት ነው። አዋጁ የወጣው ምን ለማድረግ ነው ብሎ ማየት ያስፈልጋል። በአዋጁ መሠረት መንግሥትንም መጠየቅ ይቻል ነበር። አዋጁን ማወቅ መብትና ግዴታን ለማወቅ ይጠቅማል። መወቀስ ያለበትን እና መመስገን ያለበትን ለመለየት ያስችላል። ለምሳሌ፤ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ አዋጅ አለ። ብዙ ሰው ግን ምን እንደተከለከለ፣ ምን እንተደፈቀደ አያውቅም። ብቻ በደፈናው ‹‹ንግግር ተከለከለ›› ብሎ የሚረዳውም ይኖራል። ዝርዝሩን ማወቅ ግን ‹‹ይህ አስፈላጊ አይደለም›› ብሎ ለመከራከርም ይመቻል ማለት ነው።
ብዙ ጊዜ ወቀሳ የሚሰነዘረው የአዋጁን ዝርዝር ጉዳይ ሳያዩ ጭምር ነው። ምንም እንኳን የንባብ ልማዳችን ኋላቀር መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፤ በተለይ አዋጆችንና ደንቦችን የማንበብ ከፍተና ችግር አለ። ዝም ብሎ በደፈናው ‹‹ምን ሕግ አለው!›› እያለ ወቀሳ የሚሰነዝረው ይበዛል። ሕግ ሲባል ደግሞ በወንጀል ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚመስለው ብዙ ነው። በደንብ መተላለፍ ላይ ያሉ ሕጎች ትኩረት አይሰጣቸውም። ያንኑ ወቀሳውንም ቢሆን ለወንጀል ነክ ጉዳዮች ብቻ ነው የሚያስታውሱት። አንድ ሰው ደንብ ሲተላለፍ የግል ባህሪውን ጠቅሶ ከመሳደብ ያለፈ የአዋጅ ደንብ መተላለፉን የሚነግረውም ሆነ የሚያውቅ የለም።
ስለዚህ አዋጆችን ማብዛት ብቻ ሳይሆን አዋጆችን ማሳወቅና መተግበር ይሻላል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም