የግል ሴክተሩን በማብቃት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል

– በለገሃር የአራት ሺህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ፡- የግል ሴክተሩን በማብቃት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡በለገሃር የአራት ሺህ የ30/70 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በለገሃር የ30/70 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ትናንት ተካሂዷል፡፡ አራት ሺህ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ሥራ የገባው ጊፍት ሪል እስቴት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ግንባታውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤የግል ሴክተሩን በማብቃት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

የግል ሴክተሩን በማብቃትና የመሪነት ሚናውን በማሳደግ ያለውን እድል ወደ ልማት መቀየር ወሳኝ ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤በመኖሪያ ቤቶች ላይ የተጀመረው የመንግሥትና የግል አጋርነት የልማት ፕሮጀክት ለዚህ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በከተማው ያለውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቅረፍ ባደረገው ጥረት በርካታ ቤቶች ገንብቶ ለተጠቃሚው ማስረከብ ችሏልም ብለዋል።

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፤ በከተማው የመኖሪያ ቤት እጥረት ሙሉ በሙሉ መቅረፍ በመንግሥት ጥረት ብቻ የማይቻል በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ለቤት ግንባታ የሚሆኑ ግብዓት በማሟላትና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከግል አጋር ድርጅቶች ጋር እየሠራ ይገኛል።

ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የድጋፍና የክትትል ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አመልክተው፤ በቀጣይም የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማጣጣም በግል አልሚዎች፣ በማህበር፣ በሪል እስቴት እንዲሁም በተለያዩ አማራጮ እንዲለማ ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዘርፉ የግል ሴክተሩ የበለጠ እንዲጠናከር የሚያስችል ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በከተማው የቤት ችግር ለመቅረፍም ከሌሎች የመኖሪያ ቤት አልሚ ድርጅቶች ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጊፍት ሪል እስቴት ማህበር መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብረኢየሱስ ኢጋታ በበኩላቸው፤ የግል ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በጋራ መሥራት መቻላቸው በከተማው ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ከማቃለሉ ጎን ለጎን ጥራቱን የጠበቀና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያለው የመኖሪያ መንደር ለመገንባት ያግዛል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ዙር አራት ሺህ ቤቶች የሚገነቡ ይሆናል ያሉ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ገብረ ኢየሱስ አክለውም፤ የመኖሪያ መንደር ከፍታቸው ከ14 እስከ 22 የሚሆኑ ፎቆች የሚኖሩት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ እንደተጋመሰ በሁለተኛ ዙር ለሚገነቡ ተጨማሪ 8 ሺህ ቤቶችና የንግድ ማዕከላት ጊፍት ሪል እስቴት ከእህት ኩባንያዎቹና ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ አጋሮቹ ጋር በዲዛይን፤ ቴክኖሎጂና ፋይናንስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

እንደ አቶ ገብረኢየሱስ ገለጻ፤ የለገሃር የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት በላቀ ጥራትና ዘመኑን በዋጀ የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚገነቡ 3 ሺህ 540 የመኖሪያ ቤቶች 460 የሱቅ፣ ይገነባሉ፡፡ ግንባታው ትምህርት ቤትና ሌሎች ማህበራዊ መገልገያዎችን የሚያካትት ይሆናል ያሉ ሲሆን ፤ በስምንት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You