“ሴቶች ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል” -ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ:– ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ትርጉም ያለው የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶች ተሳትፎና ሚና ከባለድርሻ አካላት ጋር ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት፤ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ትርጉም ያለው የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ሴቶች ሀገርና ሕዝብን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ድምጻቸውን ሊያሰሙ ይገባል።

ከሴቶች የተሰወረ ሀገራዊ ጉዳይ የለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሴቶች በምክክሩ በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገር ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ ነው ብለዋል። እንደሀገር መነጋገርና ምክክርን አማራጭ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ሴቶች ለሀገር መፍትሔ ፍለጋ ላይ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሴቶች ሀገራዊ ወሳኔ በሚሰጥባቸው ሂደቶች ላይ በመገኘት በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ ችግሮችን ለመፍታት ከምክክር ሌላ መፍትሔ እንደሌለም አመልክተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገር ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ ሂደት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ፤ጥልን፣ ኩርፊያና ማግለልን በማራቅ ችግሮች ለመፍታትም ምክክርን አማራጭ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በግጭቶች ሳቢያ መከራ የሚፈራረቅባቸው ሴቶች መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሴቶች ሀገራዊ ወሳኔ በሚሰጥባቸው ሂደቶች ላይ በመገኘት በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ እውን እንዲሆን ትርጉም ያለው የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ ሴቶች ከ50 በመቶ በላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶች ከቤተሰብ እስከ ሀገር የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ፤ በምክክሩ በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ በኮሚሽኑ አካታችና ሁሉን አቀፍ ምክክር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ ሴቶች ተጨባጭ በሆነ መልኩ እንዲወከሉ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ሴቶች ለምክክሩ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ከፍተኛ መደላድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ሴቶች በምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መቀስቀስና ማንቃት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ሴቶች በሀገራቸው ጉዳይ ያገባናል ብለው የሂደቱ አካል ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። ሴቶች ቁልፍ ተዋንያን የሆኑበት ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You