አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የታዳጊ ሀገራትን የልማት ጥረት ለመደገፍ የሚውል ፋይናንስ ለማሰባሰብ እንዲረዳ የሚካሄደውን (አይ ዲ ኤ 19) ጉባኤ በዛሬው ዕለት እንደምታስተናግድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አስታወቀ።
የሚኒስትሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ትናንት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከ2021 እስከ 2023 ለሦስት ዓመታት የሚጸድቀው በጀት ላይ የሚወያየው ይኸው ጉባኤ በዛሬው ዕለት የሚጀምር ሲሆን፣ በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከ220 በላይ የለጋሽ ሀገራት ተወካዮችና ሰላሳ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎችና አመራሮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም ባንክ አካል የሆነው አይዲኤ (ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን) ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ሀገራትን ከድህነት ለማውጣት ሲረዳ የቆየ ሲሆን በኢትዮጵያም እ.አ.አ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ከሰባ በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች 20 ቢሊዮን ዶላር ለግሷል። በዛምቢያ ከተካሄደው አይ ዲ ኤ 18ኛ ጉባኤ በኋላ ብቻ በ2010 እና 2011 ዓ.ም አምስት ቢሊዩን ዶላር እርዳታ ለኢትዮጵያ ሰጥቷል። እርዳታው የሚሰጠው ዝቅተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው ሀገራት ተብለው ለተመደቡና ከአንድ ሺ አንድ መቶ ዶላር በታች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ላላቸው ሀገራት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 883 ዶላር ነው።
የአይ ዲኤ 19ኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገሪቱ ባቀረበችው ጥያቄና ለመመረጥ የቀረበውን መስፈርት መሠረት አድርጎ ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያ የተደረገላትን ልገሳና በድር በአግባቡ በመጠቀም ባለፉት ዓመታት ድህነትን ከ45 ነጥብ ስድስት ወደ 23 በመቶ መቀነስ በመቻሏ እንዲሁም ተከታታይነት ያለው ፈጣን ልማት ማስመዝገቧን ከግምት በማስገባት እንደሆነ ተናግረዋል።
ጉባኤው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ታዳጊ ሀገራት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ በአይዳ የካንትሪ ፕሮግራም አስተባባሪ ሚስ ኒኮል ክሊንገን ናቸው። እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ ማህበሩ እ.አ.አ በ1960 ዓ.ም የተቋቋመ ነው። ማህበሩ ከዚያ ጀምሮ በዓለም ላይ ድሃ የሆኑ 75 ሀገራትን ሲደግፍ የቆየ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 39ኙ ሀገራት በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው። ለእነዚህም እስካሁንም ድረስ ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር በማውጣት በየዓመቱ በአማካይ 19 ቢሊዮን ዶላር ለአንድ ሀገር የሚለግስ ሲሆን ከዚህ ወስጥም 50 ከመቶ የሚሆነው በአፍሪካ ለሚገኙ አገራት የሚሰጥ ነው።
ድጋፉ የሴቶች ተጠቃሚነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሽግግር እንዲሁም ግጭትና መፈናቀልን ለመቀነስና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የገጠርና የከተማ ሴፍቲኔትን ጨምሮ ሌሎች ልማታዊ ፕሮጀክቶችን መደገፍን አላማው ያደረገ ነው። በመሆኑም አይ ዲኤ 19 ጉባኤ በእነዚህ የልማት ሥራዎች ፖሊሲና ስትራቴጂ በመመልከት በምን በምን ላይ ድጋፍ እንደሚደረግ፤ እንዲህም ድጋፍ ማሰባሰብ ላይ የሚመክር በመሆኑ ለሁሉም ታዳጊ ሀገራት በተለይም ለኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ