ኢትዮጵያ አራተኛውን ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅት መጀመሯን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ አራተኛውን ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅት መጀመሯን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኅብረቱ የውጭ ምንዛሬ አካውንቱን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው በሚል የወጣው ዘገባ መሰረተ ቢስ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ ለመገናኛ ብዙኃን ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አራተኛውን ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤን በተለየ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጅት ጀምራለች፡፡ በመጪው ሀምሌ ወር የሚካሄደውን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡

እንደ አቶ ነቢዩ ማብራሪያ፤ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የዝግጅት ሥራዎች እየተደረጉ ነው፡፡ በጉባኤው ተሳታፊ የሚሆኑ አካላትን መምረጥና የትራንስፖርት ዝግጅቶችም ተጀምረዋል፡፡

በሞስኮ የብሪክስ አባል ሀገራት ማዕቀፍ የአባል ሀገራት ዋና እና ምክትል ተወካዮች የምክክር መድረክ ማካሄዳቸውን ቃል አቀባዩ አቶ ነብዩ አውስተው፤ በኢትዮጵያ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ስኬታማ ተሳትፎ እንደነበረውም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ ውስጥ አባል እንድትሆን ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የብሪክስ አባል ከሆኑ አቻ ተወካዮች ጋር የሃሳብ ምክክሮች መከናወናቸውንና በሁለትዮሽ ደረጃ ሥራዎችን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ በጋራ ምክክር መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አያይዘው እንደገለጹት፤ “ሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛ ህትመት ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በአፍሪካ ኅብረት ላይ የገንዘብ ማታለል ሙከራ መደረጉን ተከትሎ ዘገባ ማስነበቡን ጠቁመው፤ በዘገባው ኅብረቱ የውጭ ምንዛሬ አካውንቱን ከኢትዮጵያ ሊያዛውር እንደሆነ በኅብረቱ ውስጥ በስም ያልጠቀሳቸውን ምንጮች ዋቢ በማድረግ መዘገቡን ገልጸዋል፡፡ ይህ ዘገባ የተሳሳተና የሀገር ጥቅምን የሚጎዳ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም በአፍሪካ ኅብረት የገንዘብ ማታለል ሙከራ መደረጉንና መክሸፉን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ነቢዩ ገለጻ፤ “የሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዘኛው ህትመት ከፋይናንስ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አፍሪካ ኅብረት አካውንቱን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዛውር ነው በማለት ያወጣው ዜና መሠረተ ቢስ ነው፡፡ ትክክለኛ መረጃ አይደለም፡፡ እንዲሁም አሳሳች ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ጎጂ ስለሆነ መታረም አለበት” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትን የመሰለ ድርጅት እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥመው ጋዜጣው ያልተጠቀሱ መረጃዎችን ተጠቅሞ መረጃ ከማውጣት ይልቅ በቀጥታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ጋር መደበኛ የመገናኛ ሥርዓትን ጠብቆ የመረጃና የሥራ ልውውጥ ማድረግ እንደነበረበትም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በተደረገ ቀጥተኛ ውይይት ጋዜጣው በዘገበው መልኩ በተቋሙ ውስጥ ምንም አይነት እሳቤ የለም ያሉት አቶ ነብዩ፤ ይህንንም የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል፡፡ ከውጭ ግንኙነት ከዲፕሎማሲ ሥራዎች ጋር በተያያዘ መሰል የተሳሳተ መረጃ ሲኖሩ መታረም አለባቸው ብለዋል፡፡

በሀገር ጥቅም ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ዘገባዎችን ማዘጋጀት በሀገር መልካም ገጽታ ላይ የሚያሳድረው መጥፎ ጥላሸት መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህ የሀሰት ዘገባ ተገቢ አይደለም፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት በኩል ያለው ግንዛቤ ከዘገባው በተቃራኒ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለው የድርጅቱ አካውንት በአስተማማኝ ሁኔታ እየተጠበቀ መሆኑን የተቋሙት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ማስረዳታቸውንም አመልክተዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You