ባሌ ሮቤ፡- የኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አስተዳደሩና የኢኮኖሚ እድገቱ የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ በሚል በሁለት እንዲከፈልና ምሥራቅ ባሌ ጊኒር ላይ እንዲሆን በሚል ከኅብረተሰቡ የቀረበው ጥያቄ ቀና ምላሽ ያገኛል በሚል በጉጉት እየተጠበቀ መሆኑን የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አቶ ኢብራሂም ሐጂ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የዞኑ በሁለት መከፈል ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ለአስተዳደር ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ሲሆን፣ በኢኮኖሚው ሆነ በፀጥታው በኩል ለሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ሚናው የጎላ ይሆናል፡፡ ጥያቄው ቀደም ሲልም በኅብረተሰቡ ሲቀርብ የቆየና ክልሉም ለዚህ በጎ እይታ ያለው በመሆኑ ውሳኔው በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡
ሁለተኛ ዞን ይሆናል ተብሎ በሚታሰበው በኩል ቆላማ የሆኑ ወረዳዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በዚያ አካባቢ ደግሞ በአብዛኛው አርብቶ አደር የሚበዛባቸው ወረዳዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ትርፍ አምራች ወረዳዎች መሆናቸውን ተናግረው፣ በተለይ ጊነር ወረዳና ጎሎልቻ ወረዳ በጣም ሰፊ የኢንቨስትመንት ሥራ የሚካሄድበትና ከእርሻ ጋር ተያይዞ ትርፋማ የሆኑ ወረዳዎች የሚገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አርብቶ አደር ወረዳዎቹ ደግሞ ከዳዊ ሰረር ጀምሮ ቤልቱ ሰዊና ራይቱና መሰሎቹ ናቸው ያሉት፣ እነዚህ ወረዳዎች ከዞኑ ዋና ከተማ በርቀት ላይ ያሉ እንደመሆናቸው ለሚያጋጥማቸው ጉዳይ በቶሎ ምላሽ በማግኘቱ ላይ እንከን ሲፈጠርባቸው ይስተዋላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
«ይህ በመሆኑ ነው ዞኑ በሁለት ቢሆን የሚል የኅብረተሰብ ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረው» ያሉት አቶ ኢብራሂም፣ የክልሉ መንግሥትም ለወደፊት ለአስተዳደር በሚያመች መልኩ በሁለት ለመክፈል እየታሰበ ነው ሲል ምላሽ መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለፃ፤ የዞኑ በሁለት መከፈል ጠቀሜታው አንደኛ ለአስተ ዳደር ምቹ እንዲሆን ያደርጋል።በተለይም ደግሞ ኅብረተሰቡ በቅርብ ሆኖ አስፈላጊውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ያደርገዋል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጣም በርካታ የልማት ጥያቄዎች አሉና ጥያቄዎቹን በቅርበትና በፍጥነት ለመመለስ ያስችላል፡፡ ከፀጥታም ጋር ተያይዞ የተሻለ ሥራ ሊሰራም ይችላል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በቅርብ ያለው አስተዳደር በአካባቢው ያሉትን በቅርብ ርቀት ለመከታተልና ወዲያውኑ መፍትሄ ለመስጠት ምቹ ሁኔታን ይፈጥ ርለታል፡፡
«በተጨማሪም ከሱማሌ ክልል ጋር የሚያዋስኑ ወረዳዎች ስላሉ በአካባቢው ሁለቱንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚደርግ የንግድ እንቅስቃሴ አለ» ያሉት አቶ ኢብራሂም፣ ልውውጡም ስንዴ፣ ግመል፣ ጫት፣ ፍየልና በግ እንደሆነም ጠቅሰው፤ «በንግዱ በኩል ልውውጥ የሚደረግበት ነውና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብሎ መው ሰድ ይቻላል» ብለዋል፡፡
ዞኑ በሁለት ሲከፈል የትኛው ወረዳ ወደየትኛው ዞን ይካተታል የሚለው እምብዛም የሚያስቸግር አይደለም ያሉት አቶ ኢብራሂም፣ ይህ ግን በጥናት እንደሚመለስ አስታው ቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
አስቴር ኤልያስ