አዲስ አበባ፡- የጂኦተርማል ኢነርጂን ይበልጥ ለማልማትና የግል ዘርፉንና ባለሀብቱን ለማሳተፍ የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኤሌክትሪክ ኃይሉ የኮሚዩኒኬሽን ዳይ ሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የሕግ ማዕቀፉን መከለሱ ባለሀብቶች የሚጠበቅባቸውን ግዴታ አሟል ተው ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ግልፅ አሠራር ያስቀምጥላቸዋል።
በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ያልተካተቱ ነገሮችን እንዲካተቱ በማድረግ በተለይ የግልና የመንግሥት አጋርነት የሚባለው ፕሮጀክት በጂኦተርማል ዘርፉ እንዲሰማራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
«የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ ከመሆኑ አንፃር አሁን ባለው አቅም በመንግሥት ሊከናወን አይችልም» ያሉት አቶ ሞገስ፣ የሚሻሻለው የሕግ ማዕቀፍ የግል ባለሀብቱ መዋዕለ ንዋዩን ይዞ የሚያለማበት ዕድል እንደሚፈጥለትም ተናግረዋል፡፡
የጂኦተርማል ኃይል ከውሃ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ፣ ነገር ግን ዘላቂና ለሌሎች ችግሮች የማይጋለጥ በተፈጥሮ ሁኔታዎች ውስጥ የማይወድቅ ነው ያሉት አቶ ሞገስ፣ ከወንዞች ኃይል የምናመርትበት መንገድ ዝናብ በተዛባ ቁጥር የኃይል ስርጭታችን ይዛባል ብለዋል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ግድቦች ቀደም ሲል መያዝ ከሚችሉት በላይ እየያዙ ማስጠንቀቂያ እየተነገረ ውሃ የሚለቀቅበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ይህ ተፅዕኖ በጣም ጠንከር እያለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ የውሃ እጥረት የሚያጋጥምበት ጊዜ ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
«በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሥር ነው ያለነው፤ የውሃ ኃይል ማመንጫ ዝናብ ካልጣለ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት የማይሰጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ያሉት አቶ ሞገስ፣ የጂኦተርማሉ ኃይል ግን በትልቅ ኢንቨስትመንት የሚሠራ ቢሆንም አስተማማኝ የኃይል ማመንጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ማመንጨት ከጀመረ ለረጅም ዓመት ያለምንም ችግር የከርሰ ምድር እንፋሎት እስካለ ድረስ ሊቆይ እንደሚችልና በተፈጥሮ ሁኔታዎች ስጋት ውስጥ እንደማይወድቅ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ