በሕጻናትና ሴቶች ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለደቡብ ሱዳን ጥሩ ተሞክሮ ይሆናሉ

አዲስ አበባ:- በሕጻናትና በሴቶች ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለደቡብ ሱዳን ጥሩ ተሞክሮ እንደሚሆኑ የውጭ ግንኙነት እና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን የሥርዓተ ፆታ፣ የሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አያ ቤንጃሚን የተመራ ልዑክ ትናንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዮ ቋሚ ኮሚቴ ተወካዮች ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል።

በውይይቱ ላይ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በሕጻናትና በሴቶች ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለደቡብ ሱዳን ጥሩ ተሞክሮ ናቸው። በሴቶች ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሴቶች ተሳትፏቸው እየጨመረ እንዲመጣ አድርገዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለው ወዳጅነት እየጠነከረ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በከፍተኛ አመራሩና በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ጉብኝቶች እንደነበረ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን በርካታ የቴክኒክ ድጋፎችን ታደርጋለች ያሉት ፈቲህ (ዶ/ር)፤ ደቡብ ሱዳኖች በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እየተማሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል። ፀጥታና ደኅንነት ላይ በርካታ ድጋፎችና ውይይቶች እንዳሉም በማብራሪያቸው አንስተዋል።

በቀጣይ ሁለቱን ሀገራት የሚያጠናክረው የመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል። የሁለቱ ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና የንግድ ልውውጥ እየተጠናከረ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ዓባይ ግድብ ባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለራሷ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ላሉ ለአፍሪካ ሀገራት ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዑጋንዳ፣ ታንዛኒያና መሰል ሀገራት ኃይል አቅርቦትን ለማሟላት እየሠራች እንደምትገኝም ነው የጠቆሙት።

እንደ ዓባይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በቀጣናው ሠላም መስፈን እና መረጋጋት እንዲኖር በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ በመመሥረት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ውይይት ተደርጓል።

የፓርላማ ተመራጭ ሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ ወ/ሮ ኬሚያ ጁንዲ፤ ኮከሱ ሴቶችን በማብቃት በምክር ቤት የተሰጡ ተልዕኮዎችን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።

ሕግ ሲወጣ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ተሳታፊነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ እንዲሆን በማድረግ ሚናውን መወጣቱንም ነው የጠቆሙት። ክትትል እና ቁጥጥር ሲደረግ የሥርዓተ ፆታ ጉዳይ ባግባቡ እየተተገበረ ስለመሆኑ የሚታይበት አግባብ መኖሩን አመልክተዋል።

የሴቶችን ብቃት እና አቅም በማጠናከር በርካታ ለውጦች ተገኝተዋል፤ በፓርላማ ቁጥራቸውን እንዲሁም ብቃታቸውን የማሳደግ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። ቋሚ ኮሚቴዎችን በመምራት 50 በመቶ ውክልና እንዳላቸውም በማብራሪያቸው አመልክተዋል።

በምክር ቤት ብቻ ተወስኖ እንዲቆይ አንፈልግም፤ የሴቶች ተሳታፊነት በአመራር ሰጪነት እንዲያድግ እንፈልጋለንም ብለዋል። “በሁሉም መዋቅር ተገቢ ውክልና እንዲኖር እንፈልጋለን፤ ይህንን ተሞክሮም በጎረቤት ሀገራት እንዲተገበር ፍላጎት አለን። በተጨባጭ ለውጥ አምጥተው አሳይተዋል” ነው ያሉት።

ልምድ መውሰድ አቅምን እንደሚያጎለብትና በሴቶች ላይ የሚሠሩ ሥራዎችም ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ጠቃሚ ውይይት መደረጉን ያነሱት የደቡብ ሱዳን ፕሬስ ሴክሬታሪ ዳይሬክተር አስቴር ፊክሬ በበኩላቸው ሴቶች በፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ የተገበረችው ለደቡብ ሱዳን በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል። ሴቶች በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተሳታፊ እንዲሆኑ እና በአመራር ሰጪነት እንዲሳተፉ መደረጉ በመልካም የሚወሰድ ነው ብለዋል።

ደቡብ ሱዳን በግጭት ውስጥ የቆየች ሀገር መሆኗን በመጠቆምም፤ ተሞክሮውን በመቀመር በሚደረግ ምርጫ በመደራጀት ጥረት ለማድረግ እንደሚያግዝ፤ እውቀትን መሠረት ያደረገ ውይይት ለማካሄድ እንደሚጠቅም እንዲሁም የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማስፈን፣ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ለማቀድ እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።

ሴቶችን በማብቃት፣ በልማት ተሳትፏቸውን በማሳደግ እንዲሁም በአመራር ሰጪነት ላይ አቅማቸውን በመገንባት በኢትዮጵያ የተሠራው ሥራ ለደቡብ ሱዳን ተሞክሮ ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

ዘላለም ግዛው

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You